ኢትዮጵያ በቅርቡ የሰነድ መዋእለ ንዋዮች ገበያ / የአክሲዮን ገበያ/ ታቋቁማለች። ለእዚህም ገበያውን ማቋቋም የሚያስችል ስምምነት የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመነት ሆልዲንግ ኤፍኤስዲ አፍሪካ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር በቅርቡ ተፈራርመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት፤ ገበያው ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚው አዲስ ዘመንን የሚያበስር ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የሰነድ መዋእለ ነዋዮች ገበያ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥ ምረት የሚቋቋም ይሆናል።
በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ኢኮኖሚ ከፍተኛ መጠን ያለው ካፒታልና ለኢንቨስትመንት የሚውሉ ተጨማሪ የረጅም ጊዜ የገንዘብ ምንጮችን እንደሚፈልግ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ ገበያው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ማሰባሰቢያ መድረኮችን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ መነደፉንና ለውጤታማነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
ስምምነቱን ከተፈራረሙት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው ኢንቨስትመንት ሆልዲንጉ የመንግሥት ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፣ ተቋሙ መንግሥት ስትራቴጂክ ናቸው የሚላቸውን ዘርፎች የሚመራበት መሆኑን ይገልጸሉ። ከእነዚህ ዘርፎች መካከልም ኢንቨስትመንትን ማካሄድ፣ የመንግሥት ሀብትን ማስተዳደር፣ የኮሜርሻል ሀብት የሚባሉ የልማት ተቋማትን በአንድ ላይ በመሰብሰብ በሙያ የተደገፈ አመራር በማስፈን ተቋማቱ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የተቋቋመ መሆኑን ይገልጸሉ።
ገበያው በተለይ በኢትዮጵያ እየተደረገ ባለው የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ውስጥ በርካታ ዕድሎችን የሚከፍትና ለኢኮኖሚው እድገት የጎላ ሚና እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። ተቋማዊ ሥርዓት የሚበጅለትና ሕዝብ የሚተማመንበትም እንዲሆን ተደርጎ የሚቋቋም መሆኑንም ይጠቁማሉ፤ እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ካናዳን የመሳሰሉ አገራት የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ለኢኮኖሚያቸው አጋዥ ሞተር ሆኖ ያገለገላቸው ስለመሆኑም ያመለክታሉ።
የአክሲዮን ገበያው በዋናነት ከፍተኛ የካፒታል አቅም በመፍጠር ለግሉ ዘርፍ ምጣኔ ሃብት የገንዘብ ፍሰትን በማሻሻል፣ በቀላሉ ወደ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል ሃብትን በመፍጠር ባለሃብቱንና ሌሎች ባለድርሻዎችን እንዲሁም ሀገርን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ፣ የገንዘብ ጉድለት ወይንም እጥረት ላለባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች አገራዊ ሃብትን በማሰባሰብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለአገር ምጣኔ ሃብት እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ይታመናል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኀ ተስፋ ገበያውን አስመልክቶ ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የሰነድ መዋእለ ነዋዮች ገበያው ነጋዴዎች ገንዘባቸውን የሚያፈሱበትና ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ግለሰቦችን ጨምሮ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ይገልጻሉ። ለዕድገት ከፍተኛ መሠረት የሚሰጥም ሲሉ ነው ገበያውን የሚገልጹት።
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ ገበያው ሲደራጅ በመጀመሪያ ደረጃ ኩባንያዎች ያላቸው አቅም፣ አመራር፣ አሠራር፣ ትርፍና ወጪ በሙሉ በግልጽ ይቀመጣል። ይህን ሰነድ የተመለከተ ማንኛውም ነጋዴ በሚፈልገው መጠን ሼር መግዛት ይችላል። ሁለተኛው በሀገር ውስጥ ካለው በተጨማሪ በማንኛውም አገር ያለ አንድ ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሳይመጣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሳያወጣ ባለበት ሆኖ ሼር መግዛት ይችላል። በገዛበት ፍጥነትም ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ ያስገባል።
በሦስተኛ ደረጃ አዲስ ሥራ ለሚጀምሩ ወጣቶች ሰፊ እድል ይዞ ይመጣል ይላሉ። ስለዚህ የሰነድ መዋእለ ነዋዮች ገበያው ኩባንያዎች በከፍተኛ ደረጃ ካፒታል ሊያሰባስቡና ቁጥራቸውን ሊያበራክቱበት የሚያስችላቸው ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰው፣ ዓለም እየሠራበት ያለ መሆኑንም ይገልጻሉ።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ እንዲጀመር ከፍተኛ ግፊት ሲደረግና ብዙ ሲባልለት እንደነበረ ያስታውሳሉ። አሁን የመጣውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሲቻልም ዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ ዜጎች ሃብት ማፍራት ያስችላቸዋል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፤ ገበያውን በተለይ ባለሃብቶች በከፍተኛ መጠን ሊጠቀሙበት ይችላሉ፤ እያንዳንዱ ባለሃብት የአክሲዮን ገበያው በስፋት እንዲንቀሳቀስና እንዲሳለጥ በማድረግ የተሻለ ካፒታል አንዲያፈራ ያደርጋል። ግለሰቦችም በተመሳሳይ በሚገዙት አክሲዮን ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ይፈጥራል።
በአክሲዮን ገበያ ውስጥ እንደማንኛውም ምርት አቅራቢዎችና ፈላጊዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ አክሲዮን አቅራቢው ከአክሲዮን ገዢው ጋር ተገናኝቶ እንደማንኛውም ምርት የገበያ እንቅስቃሴ በማድረግ ግብይት የሚፈጸምበት የንግድ ዓይነት እንደሆነም ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፤ እስከ ዛሬ የአክሲዮን ገበያው በአገሪቱ ባለመኖሩ የአክሲዮን ዋጋ አይታወቅም ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግብይቱ በመፈቀዱ የአክሲዮን ዋጋ መታወቅ እንደሚችልና የትኛው አክሲዮን ከየትኛው የተሻለ ነው የሚለውን ጭምር የሚመልስ ሁኔታ ይኖራል። ኢትዮጵያ ውስጥ አክሲዮን እንጂ የአክሲዮን ገበያ አልነበረም። ለአብነትም አንድ ሰው ያለውን አክሲዮን ለመሸጥ ቢፈልግ አልያም አንድ አክሲዮን ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ማወቅ የሚያስችል መንገድ አልነበረም። ይህም ማለት አንድ ሰው በአንድ ባንክ ውስጥ አክሲዮን ቢኖረው ይህ አክሲዮን በዓለም ገበያ ምክንያት ምን ደረሰ የሚለውን ጥያቄ መመለስ አይቻልም። አክሲዮኑ በወቅቱ ገበያ ቢሸጥ ወይም ቢለወጥ ምን ያህል ያወጣል? ምን ትርፍ ይገኝበታል? የሚለውን ማወቅ የሚቻልበት ሁኔታ የለም።
እየተደራጀ ያለው የአክሲዮን ገበያ እንደማንኛውም ግብይት ሻጭና ገዢ የሚገናኝበት ይሆናል ያሉት ዶክተር ሞላ፣ እስካሁን ባለው ሂደት ግን አክሲዮን ከመግዛት ባለፈ ለሌላ ሲተላለፍ አልያም ሲሸጥ አልታየም ይላሉ። ለዚህ ዋናው ምክንያት የአክሲዮን ገበያ ባለመኖሩ ነው ያሉት ዶክተር ሞላ፤ በቀጣይ ግን የአክሲዮን ገበያ እንደሚኖርና ገበያው የዓለምን ሁኔታ ጭምር ያገናዘበ በመሆኑ የሚታወቅ ዋጋ ይኖራል። ዋጋው በየቀኑ፣ በየሰዓቱና በየደቂቃው የሚለዋወጥ እንደመሆኑም ይህን መሠረት በማድረግ ሻጭና ገዢ ተገናኝቶ ይገበያያል ሲሉ ያብራራሉ።
አሁን አገሪቷ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታስ የአክሲዮን ገበያውን ተግባራዊ ለማድረግ ያስኬዳል ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው ዶክተር ሞላ ምላሽ ሲሰጡ በመሠረታዊነት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ካለፈው ጊዜ በተሻለ የተሟሉ ስለመሆናቸው ነው የሚናገሩት። ለእዚህም ኢትዮ ቴሎኮምን በአብነት በማንሳት ቢያንስ ዝቅተኛውን መስፈርት ማሟላት እንደተቻለ ይጠቁማሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች መሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች ማሟላትና ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ። በአንድ ሀገር ስቶክ ማርኬትን ወይም የአክሲዮን ገበያን ለመክፈት ሲታሰብ መንግሥትም ይሁን ሌሎች አካላት አስፈላጊና መሠረታዊ መስፈርቶችን ማሟላት የግድ እንደሚላቸው አስታውቀው፣ የአክሲዮን ገበያውን በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።
የአክሲዮን ገበያ ግለሰቦችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው በጎ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ ሊወሰድ የሚገባው ጥንቃቄም እንዳለም ያስገንዝባሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የአክሲዮን ገበያ ወይም ስቶክ ማርኬት ወይም ካፒታል ገበያ ቅጽበታዊ የሆነና ከዓለም ገበያ ጋር መናበብ መቻልን የሚጠይቅ ነው። ለዚህም የተሻለ አደረጃጀት፣ መሠረት ልማትና ውጤታማ የሆነ መረጃ ያስፈልጋል። ስለዚህ ለገበያው ውጤታማነት እነዚህን መሠረታዊ መስፈርቶች ማሟላት የግድ ነው።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ጠንካራ ተቋም ከመገንባት ጀምሮ መሠረተ ልማቶችን ማሟላትና የአክሲዮን ገበያውን ሊመራ የሚችል የሰው ኃይል ማደራጀትም ያስፈልጋል። ገበያው አንዱጋ ገዝቶ ሌላው ጋ የመሸጥና የድለላ ዓይነት ሂደቶችንም የሚፈቅድ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋል። አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በተደራጀ መንገድ ካልተመራ ከታሰበለት ዓላማ ውጪ ሆኖ አገሪቷ ባልፈለገችው አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል። ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይሆናል። ጠንካራ ተቋም ተገንብቶ ሂደቱን ሊቆጣጠር የሚችል የሰው ኃይል ሊኖር ይገባል ባይም ናቸው።
ገበያው እንደ ማንኛውም ንግድ ጤናማ በሆነ መንገድ መመራት እንዳለበትም አስገንዝበው፣ ከሌሎች ንግዶች በበለጠ በተሻለ ጥንቃቄና ህግ መመራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። የሌሎች አገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ይህንኑ እንደሆነ ያመለክታሉ።
የአክሲዮን ገበያ ተግባራዊ በማድረግ አገራት በብዙ እየተጠቀሙበት መሆኑንና የገበያ እንቅስቃሴው እጅግ ፈጣንና በሰከንዶች ልዩነት የሚስተዋልበት እንደሆነም የሚናገሩት ዶክተር ሞላ፣ ሚሊዮን ብሮች በሰከንድ ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉም፣ በተመሳሳይ ደግሞ ሊያጡ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩን የበርካታ አገራት የአክሲዮን ገበያ ተሞክሮ ያሳያል ይላሉ። ለውጡ እጅግ ፈጣን እንደመሆኑ በቴክኖሎጂ እንዲሁም አጠቃላይ ለዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት መረጃዎችን በፍጥነት እየተቀባበሉ መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
‹‹የአክሲዮን ገበያ በአገሪቱ እስካሁን ተግባራዊ መሆን ያልቻለው አስፈላጊነቱ ሳይታወቅ ቀርቶ ሳይሆን ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው›› ያሉት ዶክተር ሞላ፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አክሲዮን ገበያውን መሸከም ይችላል አይችልም የሚል ጥያቄ እንደነበረም ያስታውሳሉ። ከዚህ አኳያ አሁን ባለው ሁኔታ ገበያው ተግባራዊ እንዲሆን የወሰነው አካል የሚያውቀው ነገር እንዳለ ሆኖ፤ የሚታዩ አስቻይ ሁኔታዎች አሉ ሲሉም ያብራራሉ። ለአብነትም ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን የደረሰበት የእድገት ደረጃ የተሻለ ሁኔታ እንዳለ የሚያመላክት እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ሌሎች ከሰው ኃይል ጋር ያለውን ክፍተት ማሟላት ከተቻለ ከቀደመው ጊዜ በበለጠ የአክሲዮን ገበያን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስም የሰነድ መዋእለ ነዋዮች ገበያውን ለማቋቋም በሀገሪቱ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ በመጥቀስ የዶክተር ሞላን ሀሳብ ያጠናክራሉ። ይህ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ካልተጀመረ መቼም አይጀመርም ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ከዛሬ 30 ዓመት አስቀድሞ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ይግቡ የሚለውን ሀሳብ ጨምሮ ውይይት ሲደረግ እንደነበረና አለም ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍና የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ሲያደርጉ እንደነበርና እንዳልተሞከረ አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ ገበያው መገባቱ ትክክለኛ መሆኑንና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ይልቅ ኢትዮጵያ ለገበያው ትልቅ መሠረት ያላት መሆኗንም በማስረዳት ነው ገበያው መቋቋሙን ትክክል መሆኑን ያብራሩት።
እንዲያውም ገበያው የዘገየ መሆኑን ነው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የሚናገሩት። በሀገሪቱ ምርት ሊወጣበት የሚችል ከመቶ ሺ ኪሎሜትር በላይ መንገዶች መሠራታቸው፣ በርካታ የኃይል ማመንጫዎችና ማሰራጫዎች መገንባታቸው፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲ በተለያየ ሙያ ሰልጥነው እየወጡ መሆናቸውና ሌሎችም በርካታ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ በማብራራት ነው አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያስረዱት።
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፤ የአክሲዮን ገበያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም በአግባቡና በጥንቃቄ መመራት ካልቻለ የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ ነውና ጠንካራ ተቋም ከመገንባት ጀምሮ ከቁጥጥርና ከግብዓት መሟላት ጋር ተያይዞ በጥንቃቄ መመራት አለበት፤ ያ ካልሆነ ግን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ የሚጎዳው ይሆንና ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል። በማለት እስከዛሬ በአገሪቱ ተግባራዊ ያልሆነው የአክሲዮን ገበያ ለውጤታማነቱ በአግባቡና በጥንቃቄ መመራት አለበት። ገበያውን በአግባቡ መቆጣጠርና መምራት እየተቻለ ሲሄድ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
‹‹በአክሲዮን ግብይት ውስጥ ዋናው ተዋናይ የንግዱ ማህበረሰብ ነው›› ያሉት ዶክተር ሞላ፤ አክሲዮን የሚሸጥና የሚገዛ እንደመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ በዚህ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄን ማድረግ፤ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ መመልከትና ልምዱን ተከትሎ መሥራት፣ ገበያው እንዴት እንደሚካሄድ መለማመድና ልምድ ማካበት እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ መንግሥት የሰነድ መዋእለ ንዋዮች ገበያውን መቆጣጠር የሚችልበት ጠንካራ ተቋም በመገንባት ገበያውን ተጠቅመው ጥፋት ሊሠሩ የሚችሉትን ሁሉ መቆጣጠር እንዳለበት ያስገንዝባሉ። ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ ውስጥ የሚመደቡ ሰዎችም ዕውቀት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2014