በኢትዮጵያ የነበሩ አሉታዊ ትርክቶችን በወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ በመለወጥ ወደፊት የማስቀጠል ጉዞ ተጀምሯል። ለዚህም ባለፉት አራት ዓመታት ውድቀቷን የሚመኙ አካላት እንደሚያስቡት የምትበታተን አገር እንዳልሆነች የሚያመላክት ወሳኝ ጥንስስ ተጥሏል። ይህንንም ማስቀጠል የሚችሉ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች መልካም ጅምሮች እየታዩ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ዜጎቿ ቁርጠኞች ሊሆኑ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባዘጋጀው ‹‹ስለኢትዮጵያ›› በተሰኘው መድረክ ላይ ተወስቷል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንደሚሉት፤ የትርክት ለውጥ ተጀምሯል ሲባል ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ የነበረው አሉታዊ ትርክት በመልካም ትርክት እየተለወጠ መምጣቱን የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው። የቀደመውን ክፉ ትርክት መለወጥ የሚያስችሉ መንገዶች ተጀምረዋል ሲባልም በዋናነት የትርክት ለውጡ ኢትዮጵያውያን ወንድማማቾችና እህትማማቾች ናቸው የሚል ነው። ይህም ኢትዮጵያውያኑ በባዕድነትና በመጤነት የሚተያዩ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህ የትርክት ለውጥ ኢትዮጵያን ለማስቀደም ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው።
አሉታዊ ትርክት ናቸው ከሚባሉት መካከል የጥላቻ፣ የቂም በቀል፣ የመከፋፈል ትርክት ሲሆን፣ እነዚህን በወንድማማችነት ትርክት ለመተካት የሚያስችል መልካም ጅማሮ መኖሩን ዶክተር ቢቂላ ያብራራሉ። በሌላ በኩል ዜጎች እርስ በእርስ እንዲጠራጠሩና እንደባይተዋር እንዲተያዩ የሚያደርገው ትርክት ተጠቃሽ ሲሆን፣ ሰው የትም ስፍራ ይወለድ ወይም ይኑር ወንድማማች ነውና አብሮ ይኖራል የሚለውን ትርክት የመትከል ጅማሮ ነው የተጀመረው ሲሉ ያስረዳሉ። ነገር ግን ይህን ማስቀጠል የሚችልና በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል ሊሆን የሚችል ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ በመጥቀስ፤ ይህም የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ትርክት ማለት እንደሆነ ያብራራሉ። ባለፉት አራት ዓመታት የአብሮነትና አብሮ የመቀጠል ትርክት፣ አንዱ ሌላውን እንደ ዓይኑ ብሌን የማየት ትርክት፣ እንደመጤ ያለመተያየት ትርክት የተተከለበት ጊዜ ነበር ያሉት ዶክተሩ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ከየትም ይምጣ ከየት ወንድምህ ነው የሚል ትርክት ለመሥራት ተሞክሯልም ይላሉ።
ተጀምሯል ከተባለው ትርክት ውስጥ ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮችም ተመዝግበዋል፤ ከእነዚህም አንዱ የተቋማት ግንባታ ሲሆን፣ ይህም መልካም የሚባል ጅማሮ ነው። ተቋማትን መገንባት ካልቻልን ኢትዮጵያን ማስቀጠል አንችልም የሚል ትልቅ ቁርጠኝነት በኢትዮጵያ ተጀምሯል። ለአብነት ያህል የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ፣ የጸጥታና ደህንነት በጥቅሉ ለመጪው ትውልድ የሚበጁ ተቋማትን መገንባት ተጀምሯል። የዴሞክራሲ፣ የደህንነት፣ እንዲሁም የፍትህ ተቋማት መልካም ጅምር ላይ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል፤ ይህን የአሁኑ ትውልድ በአግባቡ ከሠራና ለሚቀጥለው ትውልድ ማስረከብ ከቻለ ነፃ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ ተቋም በመኖሩ አገሪቱን ማስቀጠል ያስችላል።
ይህ ብቻ አይደለም የሚሉት ዶክተር ቢቂላ፣ አካታች ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ለመገንባት የሚያስችል ሁሉንም ያቀፈ፣ ሁሉንም ኃይማኖት፣ ብሔርና ቋንቋ የያዘ፣ በየትኛውም ማዕዘን ያሉ ዜጎችን ያቀፈና ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መልካም እንቅስቃሴ ተጀምሯል ይላሉ። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፤ እርሷን እንገነባለን የሚለው ጅማሮ የተጀመረበት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ተፈጥሯል ሲሉም ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የዋጋ ሁኔታና የኑሮ ወድነት የሚፈታተነን ቢሆንም ኢኮኖሚውን ከውድቀት ለመታደግ የሚያስችሉ ጠንካራ ውሳኔዎች እየተወሰኑ ናቸው ማለት ይቻላል፤ ከለውጡ በፊት የአንድ ወር ደመወዝ መክፈል አቅቶት ሲንገዳገድ የነበረ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የተቻለበት፣ በውጭ ጫና ምክንያት መድኃኒት ማስመጣት እንዲሁም ብድሩን መክፈል የማይችል ኢኮኖሚ የነበረውን ሁኔታ እንዲያገግም ማድረግ የተቻለበት፣ አፋጣኝ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የተቀየሰበትና የአገር ኢኮኖሚ ከወድቀት መታደግ የተቻለበት ወቅት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።
ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓታቸው ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ምርጫ ማካሄድም ሆነ የአገር ህልውናና ሉዓላዊነት ማስከበር አይችሉም ተብሎ የተነገረ ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሉዓላዊነትን ማስከበር የተቻለበት ወቅት መሆኑ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አለመሆኑም እውን ነው። በተለይም አገር በተወረረበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በተለያየ ግንባር በመሆን አገሪቱን ከውደቀት ያዳኑበት ዓመት መሆኑን በሚገባ መናገር ይቻላል። ይህ ሊመጣ የቻለው የወንድማማችነት ትርክት ቦታውን እየያዘ በመምጣቱ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በተመሳሳይ የፕሮጀክቶቻችንን አፈጻጸም በምናስተውልበት ጊዜ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን አያልቁም፤ ትውልድም ኢኮኖሚም የሚበሉ ናቸው በተባለበት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ መካከል ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በብዙ አገሮች ዘመቻ የተካሄደበት ቢሆንም በፈተና ውስጥ ሆነንም ቢሆን ኃይል ማመንጨት እንደሚችልና የኢትዮጵያን ፍላጎት ማሳካት የሚችል ፕሮጀክት መሆኑን ያሳየንበት ወቅት መሆኑን መረዳት ይገባል ይላሉ።
ዛሬ ወንድማማችነት ያልነውን ትርክት የዛሬ ሃያና ሰላሳ ዓመት የሚወለደውም ልጅ ይህንኑ ወንድማማችነት የሚለውን ትርክት ሊያስተጋባ ይገባል። ወንድማማችነት ከዚህ በኋላ ወደኋላ የሚመለስ ነገር ሳይሆን ትውልድ እየተቀባበለ የሚያስቀጥለው መሆን አለበት። እንደ አገር የተቀመጠው ግብ የበለጸገች አገርን መገንባት ሲሆን፣ ይህ የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያ ነው ብለዋል።
የጥላቻ ትርክትን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ትርክት የመለወጡ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ረጋሳ ናቸው። ለውጡ ውስጥ እንደነበረና ለለውጡም አዎንታዊ ሚና እንደተጫወተ ሰው በአገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች መኖራቸው እሙን ነው። በዚህ ውስጥ ምንም እንኳ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ኢህአዴግ ማህበራዊው ነገር ላይ የተሻለ መስሎ ቢታይም ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ባለማስነካት በኩል አምባገነንነቱን ቁልጭ አድርጎ ሲያሳይ እንደነበር ዶክተሩ ይናገራሉ።
በኢኮኖሚው በኩል የአንድ ብሔር ገናናነት ሲንጸባረቅ ነበር ሲሉ የተናገሩት ዶክተር ዮሐንስ፣ እንደማሳያ በኢኮኖሚው በኩል ሌላው ብሔር የበይ ተመልካች ሆኖ መክረሙን ይጠቅሳሉ። ለአብነትም በኮንስትራክሸኑ ዘርፍ ብቻ ቢወሰድ እንኳ ከአንድ እስከ አስር ያለው ደረጃ የተያዘው በአንድ ብሔር መሆኑን ያመለክታሉ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ተጠቃሚ መሆን ያለብኝ እኔ ብቻ ነኝ የሚለውን ትርክት ነው። ይህ ደግሞ አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅነት ስሜት እንዲሰማው ከማድረጉም በላይ የበይ ተመልካች ላለመሆን አመጽ እንዲቀጣጠልና ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉንና የለውጡ መንግሥት መመስረቱን ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ እንዳያይ ሲሰበክ ቆይቷል። ለአብነት ያህል ደርግን ከእኛ ጋር ታግለው አልጣሉም በሚል ውሃ በማያቋጥር ምክንያት ብቻ ጥቂት የማይባሉ ክልሎች በአጋርነት ሲፈረጁ ቆይተዋል። ይህን ከፋፋይ ትርክት ለመጣል ትውልዱ ጥያቄ በማንሳት መሞገቱ ይታወቃል። ሲነገሩ የነበሩ አሉታዊ ትርክቶች ብዙውን ጊዜ ነጥሎ አንዱን የማጥቂያ መሣሪያ ሆነውም ከርመዋል።
እኔ ነኝ የበላይ ከሚለው ትርክት ውስጥ አንዱ ማሳያ በወቅቱ የነበረው መከላከያ የአገር አለኝታ መሆን ሲገባው መሣሪያ ታጣቂም ኢንቨስተርም የሆነበት ዘመን ነበር። ለዚህ ደግሞ ሲነገር የነበረው ትርክት እኔ ነኝ ደርግን የጣልኩት፤ እኔ ነኝ ለዚህች አገር ያለሁት የሚል ነው። ከዚህ የተነሳ በመከላከያ ውስጥ ብዝሃነትን ያስተናገደ ማንነት አልነበረም። አድራጊ ፈጣሪ አንደኛው ወገን ብቻ በመሆኑ በሌላው ዘንድ የባይተዋርነት ስሜት ተፈጥሮ ቆይቷል። ይህ ጥላቻና ቂምን አዝሎ ዜጋው ለሌላ ትግል እንዲሰናዳ ሲገፋፋውም ከርሟል።
ዜጋው፣ ኢኮኖሚውና ፖለቲካው አይመለከትህም፤ ለዚያ የሚሆን ችሎታ የለህም፤ አንተ ማድረግ ያለብህ ባህልህን ቋንቋህን መናገር ነው፤ ስለተባለ ብቻ ተገፍቶ መዝለቅ አልሆነለትም። ስለዚህም ሲደርስበት የነበረውን አሉታዊ ትርክት በመጣል ነፃነቱን ማወጅ በመፈለጉ ለውጡ ሊመጣ ችሏል ብለዋል።
የመናናቅ መንፈስ ነበር የሚሉት ዶክተር ዮሐንስ፣ አንዱ ሌላውን ይንቅ ነበር፤ ይህ ክፉ ትርክት ነው በማለት ይገልጻሉ። የእንትና ቋንቋ ከእንትና የተሻለ ነው ብሎ አሉታዊ ትርክትን ከማራመድ ይልቅ የእገሌንም የእገሌንም ቋንቋ ባውቅ እኔ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አልሆንም ወደሚለው አዎንታዊ ትርከት መምጣት ይጠበቅብናል ይላሉ። ቋንቋ አወቅን ማለት በየትኛውም ስፍራ ተገኝቶ መሥራትም መነገድም ይቻላል፤ በዚህ ውስጥ ደግሞ መጠቀምም ማትረፍም ይመጣል። ስለሆነም መናናቅን ወደመከባበር መለወጥ ይጠበቅብናል ሲሉ ያስረዳሉ። በእርግጥ በቋንቋ ማሳደግ በኩል አዎንታዊ ሚና ኖሮ ቢቆይም በተዘዋዋሪ ግን የእኔ አውቅልሃለሁ ትርክት በመኖሩ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ዘርፍ እኩል ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ነው የሚናገሩት።
እንደ ዶክተር ዮሐንስ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አካሄዶች መጥቀስ ይቻላል። ለአብነትም በለውጡ መንግሥት የተመለሱ ጥያቄዎች መኖራቸው አንዱ ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። ለዚህም እንደማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው አስረኛና አስራአንደኛ ክልሎች መመስረት መቻላቸው ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የእኔም ናት ወደሚለው መልካም የሆነ ትርክት የሚያመጣ ነው። በዚህም አብሮነት ይዳብራል፤ ይጎለብታልም።
በኢትዮጵያውያን መካከል ኢትዮጵያዊነት እንዲዳብር በለውጡ መንግሥት ከተሠሩ ሥራዎች ለማስታወስ ያህል ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት አንድ ዶላር ከአንድ ማኪያቶ ለተሰኘው ፕሮጀክት የተሰጠው በጎ ምላሽ ነው ሲሉ ተናግረው፤ በዚህም መከፋፈል ስለሌለበት አንድነት ገኖ እንዲወጣ ማስቻሉን አስረድተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ገበታ ለአገር መርሃግብር ቀደም ሲል ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ አዘንብሎ የነበረውን የቱሪስት መስህብ ወደሁሉም እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑ ነው የሚያስረዱት። ለፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያውያን በእኩል ስሜት ማዋጣት እንዲችሉ መደረጋቸውም የጋራ መንፈስ እንዲፈጠር ያስቻለ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ውስጥ የተገነቡ እንደ እንጦጦ፣ አንድነት እንዲሁም ወዳጅነት ዓይነት ፓርኮችን ስናስተውል ከስማቸው ጀምሮ የሚተርኩት ኅብረትንና አብሮነትን ነው። ፓርኮቹ የሕዝብ ናቸው። በጥቅሉ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው እነእገሌ እንጂ እኛ አልተጠቀምንም የሚለው አስተሳሰብ በተግባር ተቀይሮ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸውና ይህ ይጎልብት የሚል አተያይ ነው ያለኝ ብለዋል።
ሌላው ደግሞ መደመር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በራሱ መልካም የሆነ ትርክትን ያዘለ በመሆኑ ለዜጎች ኃይልን የሚጨምር ነው። እንዲያውም መደመር የሚለው ሃሳብ ላለፉት ጊዜያት ተነጣጥሎና ተገፋፍቶ የነበረውን ማኅበረሰብ በወንድማማችነት መንፈስ በመደመር ጉልበት ማግኘት የሚያስችል መንገድ ነው ብለዋል።
ዶክተር ቢቂላ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አሁን የተደረሰበት አዎንታዊ ትርክት እንዳይንሸራተት ከማድረጊያ መንገዶች አንዱ ከሁሉም ቀድሞ መሠራት ያለበትና ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለ ልዩነት መረባረብ ያለበት የወንድማማችነትንና የእህትማማችነትን ትርክትን ማጽናት ላይ ነው። ወንድማማችነትና እህትማማችነት ጸንቷል ማለት የሚቻለው ደግሞ ከሰሜን የመጣው ደቡብ ላይ እንዲሁም ከምዕራቡ የመጣው ምሥራቅ ላይ መኖርና መሥራት ሲችል ነው። የትርክት ለውጡ የትም ተወለድ የትም እደግ ኢትዮጵያዊ እስከሆንክ ድረስ ወንድሜ ነህ የሚለውን ትርክት መርህ ማስያዝ ነው። በዚህ መልኩ ወንድም ወንድሙን እንደ ዓይኑ ብሌን መጠበቅ ካልቻለ አገርን ማስቀጠል አንችልም። በብዝሃነት አንዱ ሌላውን አቅም እንዲሆን ማስቻል ነው። እያንዳንዱ ዜጋ የወንድማማችነትንና የእህትማማችነትን ትርክት የሚያቀነቅን ከሆነ በየቦታው በጽንፈኝነት ምክንያት እየተፈጠረ ያለው የመገፋፋትና የመፈናቀል ፈተና በሙሉ ይቆማል። የጥላቻና የቂም በቀል ትርክ የሚቀጥል ከሆነ ግን አገርን ማስቀጠል ቀርቶ ባለችበት ማቆየት አይሞከርም።
የተዘራውን የጥላቻ ትርክት በመንቀል ብዝሃነትን ያስተናገደ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት መትከል ይጠበቅብናል የሚለው ትልቁ ሥራ ነው የሚሉት ዶክተር ቢቂላ፣ በተመሳሳይ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ከፍተኛ ሥራ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል። ይህ ደግሞ እንደ ዜጋ የሁሉም ኢትዮጵያ ድርሻ ነው የሚለው ላይ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ የግድ መሆኑንም አስምረውበታል።
ጽንፈኝነትና አክራሪነት ፈተና ነው፤ የእኔ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ ማንነት ብቻ ይኖር፤ የሌሎቻችሁ በሙሉ ይጥፉ ማለት የዜጎችን ደህንነት ፈተና ውስጥ የሚያስገባ ስለሆነ መጋፈጥ ይጠበቅብናል። ምክንያቱም ወንድማማችነትና አንድነት በጠፋ ጊዜ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስ ይሞክራሉ፤ ስለዚህ ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን የማይሸከም ማኅበረሰብ መፍጠር ትልቁ የቤት ሥራ ነው። ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን መጸየፍና ማጋለጥ ደግሞ የዜጎች ድርሻ ነው ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም