ከመኸር ወደ በጋ መስኖ፣ በመቀጠል በልግ እያለ የአገራችን የግብርና ሥራ በቅብብሎሽ እየተከናወነ አሁን ደግሞ ወደ ቀጣዩ 2014-2015 የምርት ዘመን የመኸር የግብርና ሥራ ላይ ተደርሷል።አርሶ አደሩ ሰኔ ግም ሲል የዘር ወቅት ስለሚሆን የግብርና ሥራውን ይበልጥ ማጠናከር ውስጥ ይገባል።
አገራዊ የግብርና ሥራው በስፋት የሚከናወነው በክረምት ወቅት በመሆኑም የመኸሩ እርሻ ስራ ከሌሎቹ ወቅቶች ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራበታል።በዚህ የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴው ለምርትና ምርታማነት ዕድገት ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ተባይ ማጥፊያ የመሳሰሉ የግብርና ግብአቶችም አብረው ተሟልተው መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
አርሶ አደሩም ሆነ የግብርና ሥራውን የሚያስፈጽመው የመንግሥት ተቋምና በተለያየ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉት ባለድርሻ አካላት በዚህ መልኩ ዝግጅት እያደረጉ የመሥራት ባህሉን ያዳበሩ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ መዘናጋት እንዳይኖር ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በዚህ ወቅት የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ፤ ያስገነዝባሉ።
እኛም ወቅቱን መሠረት አድርገን በመኸር የግብርና ሥራ ላይ ትኩረት ማድረጋችን ለዚህ ነው።በተለይ ደግሞ በዚህ የመኸር የግብርና ሥራ ወቅት በስፋት ጥቅም ላይ በሚውለው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ይገጥማል ተብሎ ከታሰበው የአቅርቦት ውስንነት ጋር በተያያዘ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ እየተጠየቀ መሆኑንን ተከትሎ የዛሬው የግብርና አምዳችን በዚህ ላይ እንዲያተኩር አድርገናል።
ፊቱንም ማዳበሪያ ሰው ሰራሽ የአቅርቦት ችግር ይስተዋልበታል።ወቅትን ጠብቆ አለማቅረብ፣ፍትሐዊነት የጎደለው ስርጭት መኖር፣ ለህገወጥ አቅርቦት የተጋለጠና በዋጋም የማይቀመስ እየሆነ መምጣት አርሶ አደሩ ደጋግሞ የሚያነሳው ጉዳይ ነበር።ለዚህም እንደ አንድ አማራጭ መፍትሄ የሚቀመጠው አርሶ አደሩ አገር በቀል የአፈር ማዳበሪያ/ የተፈጥሮ ማዳበሪያ/ እንዲጠቀም ነበር።አሁን ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ከቀደመው ከተቆራረጠ የማዳበሪያ ስርጭት ይለያል።
ለአቅርቦት እና ለዋጋ ንረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረው የማዳበሪያ ዋጋና የማጓጓዣ ወጪ ጭማሪ እንዲሁም በዩክሬንና በሩሲያ መካከል የተፈጠረው ጦርነት እንደ አንድ ምክንያት እየቀረቡ ናቸው፤ በእዚህ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ከገጠማት አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በውጭ ሀይሎች የገጠማት ጫናም ሌላው ፈተና መሆኑ ይታወቃል።ይህን ሁሉ ተከትሎ የሚፈለገውን ያህል ማዳበሪያ ማግኘት አይቻልም የሚል ስጋት አድሮም ነበር።
ይሁንና አገሪቱ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ደግሞ አገሪቱ ባደረገችው ርብርብ እንደ አገር ያስፈልጋል የተባለው የማዳበሪያ መጠን ተገዝቶ ወደብ ደርሷል።በዚህም በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የነበረው ስጋት ተወግዷል ማለት ይቻላል።
በአቅርቦት ላይ የተፈጠረውን ስጋት ተከትሎ የተፈጥሮ (ኮምፖስት) መጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አንድ አማራጭ መፍትሄ ሆኖ እንዲሰራበት ምክረ ሀሳብና ማሳሰቢያም ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።በምክረ ሀሳቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረው የማዳበሪያ ዋጋ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመፍታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ግንዛቤ ተይዞበታል።
እነዚህን ስጋቶች ተከትሎም የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ሂደት ከተጀመረ ቆይቷል።የአንዳንዶች ዝግጅት በተሞክሮ እየተጠቀሰ ይገኛል።ከተጠቀሱት መካከልም የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ይገኝበታል።ኮሌጁ በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ላይ ያለው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ጭምርም አርአያነቱን አጉልቶታል።
ኮሌጁ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዙሪያ ስላለው ተሞክሮ በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ዶክተር ገብረሥላሴ ዳንኤል፤ የትኩረታችን አቅጣጫ ስለሆነው የተፈጥሮ ማዳበሪያና ኮሌጁ በዚህ ዙሪያ ላይ ስላለው ተሞክሮ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ ኮሌጁ እያከናወነ ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ዋና ዓላማው በቀጥታ ለሚመለከታቸው አካላት ቴክኖሎጂውን በማስተዋወቅ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ነው። ስለተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀትና ጥቅሙን በተመለከተ በማሰልጠን ለአካባቢውና ለሌሎችም በሚጠቅም መልኩ ተሞክሮው እንዲሰፋ ማስቻል ነው።
ከተለያዩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ዘዴዎች አንዱ በሆነው ቨርን ኮምፖስት ላይ ነው ኮሌጁ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኘው።ቨርን ኮምፖስት የሚዘጋጀው የግብርና ምርቶች ተረፈ ምርት በሚመገቡ የትል አይነቶች ነው።በውስጡ ናይትሮጂን፣ ፎስፈረስ፣ ፖታሽ፣ ካልሽየም፣ ማግንዢየም፣አይረን፣ ማንጋዚን የሚባሉና ሌሎችንም ንጥረ ነገሮች የያዘ ግብአት ይገኛል።የያዛቸው ንጥረ ነገሮች ለእጽዋትና ለተለያዩ ሰብሎች ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆናቸው ተፈላጊና ተመራጭ ናቸው።
ይህ ኦርጋኒክ የተባለ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አፈርን በማከም የአፈር ለምነት እንዲጠበቅ ያደርጋል።የአፈር ጤንነት ሲጠበቅ ውሃ በቀላሉ መሬት ውስጥ ይሰርጋል።የሚፈለገውን የውሃ መጠን ለመያዝም ያግዛል።
ስለአጠቃቀሙም ዶክተር ገብረሥላሴ እንደገለጹት፣ ለአንድ ሄክታር ሁለት ቶን (20 ኩንታል)ቨርን ኮምፖስት ያስፈልጋል።ማዳበሪያውን በመጠቀም ከሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠን የሚወሰነው ግን በተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች ናቸው።አብዛኛው ንጥረ ነገር ከተሟላ ጥሩ የሚባል ምርት ይሰጣል።
ለማዳበሪያው ግብአት ስለሚውለው የትል ዝርያም እንደተናገሩት፤ በዓለም ደረጃ ተመራጭ የሆነውና ጥቅም ላይም እየዋለ ያለው ቀለሙ ቀይ የሆነ የትል አይነት ነው።ኮሌጁ ውስጥ ለሰርቶ ማሳያ እየተከናወነ ያለው በዚሁ ዝርያ ነው።በምርምር ተደርሶበት ለሰብል ልማት ምርታማነት ተመራጭ የሆነው ይህ የትል አይነት በሽያጭ እየቀረበ ነው ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው።ኮሌጁም በዚህ ዘዴ በመጠቀም ነው ለስልጠናው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሰርቶ ማሳያ ተግባር እያከናወነ የሚገኘው።
እንደ ዶክተር ገብረሥላሴ ማብራሪያ፤ ቨርን ኮምፖስት ከከብት እዳሪና ከተለያየ ተረፈ ምርት ግብአት ከሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ይለያል፤ ትሉ በራሱ ሂደቱን ጨርሶ ነው የሚፈለገው ውጤት ላይ የሚደርሰው።ጥቁርና እይታን የሚስብ የአፈር ሽታ ያለው ሆኖ ነው የሚወጣው።ውጤቱን ለማየት የሚወስደው ጊዜም ከ8 እስከ 12 ቀናት ናቸው።
የሚዘጋጅበት ዘዴም ኮንክሪት በተባለ ግብአት በተዘጋጀ ጉድጓድ ውስጥና የፕላስቲክ ውጤት ከሆነ መጠኑ ከፍ ባለ ሳጥን ውስጥ ግብአቶቹን በማጠራቀም ነው።ከፕላስቲክ ውጤት የሚዘጋጀው ሳጥን ግን ይመረጣል።አዘገጃጀቱም ሂደት አለው።አሲድነትና ቅባትነት ያላቸው ግብአቶች ለቨርን ኮምፖስት ማዘጋጃነት ወይም ግብአትነት እንዲውሉ አይመከርም።
አርሶ አደሩ ሂደቱን በስልጠና የሚያገኘው ቢሆንም፣ ትሉን በግዥ ነው የሚያገኘው።ለማዘጋጃ ጥቅም ላይ የሚውለው የፕላስቲክ ዕቃም ሆነ በጉድጓዱ ውስጥ ኮንክሪት ስለሚያስፈልግ ወጪ ይጠይቃል።ተሞክሮው ከሰፋ በኋላ አስፈላጊ በሆኑ የግብአት አቅርቦቶች አለመሟላት አርሶ አደሩ ከመጠቀም ወደኋላ እንዳይል ይህን አስቀድሞ ማሰብ ይገባል።በዚህ ረገድ ኮሌጁ ሊያደርግ የሚችለው እገዛ ይኖር እንደሆንም ዶክተር ገብረሥላሴ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አሁን ላይ ትኩረቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ማዘጋጀት ስለሚቻልበት ዘዴ ነው።ወደፊት ግን በምክክር የሚከናወኑ ስራዎች ይኖራሉ ብለዋል።
በኮሌጁ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የቨርን ኮምፖስት አዘገጃጀት ዘዴ ተሞክሮን የማስፋት እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ዶክተር ገብረሥላሴ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ በሲዳማ ክልል ዶሬ ባፈኖ በተባለ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተሞክሮውን እንዲያገኙ ተደርጓል።ጥቂት ቢሆኑም ፍላጎት ያሳዩ አርሶ አደሮችን ማግኘት ተችሏል።ሙከራው ገና ጅምር በመሆኑ ሰፊ ሥራ አልተከናወነም።ወደፊት ግን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው።
በሰጡት ምክረ ሀሳብ ቨርን ኮምፖስት ሽታ ከሚያመጡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀቶች የተሻለ በመሆኑ የአካባቢ ብክለት አያስከትልም። ትሉን በማባዛት ተጠቃሚ መሆን ስለሚቻል የሥራ ዕድል ይፈጥራል። አርሶ አደሩ ወደ ቨርን ኮምፖስት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ቢያዘነብል በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ።
በአጠቃላይ ከኬሚካል ነጻ የሆነ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ቢውል የአፈር ጤንነት ስለሚጠበቅ ምርቱም ለሰው ልጅ ተስማሚ እንደሚሆንና የአፈር መሸርሸርንም በመቀነስ እንደሚረዳ እንዲሁም የተስተካከለ ሥነ ምህዳር እንደሚኖር በምክረ ሀሳባቸው ገልጸዋል።
ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ለግብርና ሥራ ምቹ የሆነና ለሰው ልጆች ጤንነትም መጠበቅ በሚያግዙ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ለመሳተፍ ሚናው የጎላ እንደሆነ ይታወቃል።የአፈር ለምነት ጥበቃ ሥራው የሚሰራው የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን በመትከል በመሆኑ ችግኞችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ነው ሚናውን የሚወጣው።ይህንንም ተግባር የሚፈጽመው በሚሰጠው የአካባቢ ማህበረሰብ አገልግሎት ነው።
ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የአካባቢ ማህበረሰብን ማዕከል በማድረግ እያከናወነ የሚገኘው ይህ በአፈርና ጥበቃ ሥራ እንዲሁም የሠርቶ ማሳያ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጃ ስራው ወደ ተጠቃሚው ተደራሽ እንዲሆን የባለድርሻ አካላትም ተሳትፎ የጎላ ሚና አለው።በተለይም ግብርናውን የሚመራው አካል ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
በዚህ ላይ የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የግብርና ግብአትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር በላይነህ ባራሞ እንዳስረዱት፤ ኮሌጁን ጨምሮ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሆን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በተለያየ መንገድ የሚዘጋጅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረት እየተደረገ ነው።
ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ እያከናወነ ያለውን የቨርን ኮምፖስት ተሞክሮ በቢሮ ደረጃ መልካም ሥራ እንደሆነና ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ተገምግሟል።ተሞክሮው እንዲሰፋፋም በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ውይይት እየተደረገበት ይገኛል ይላሉ።
እንደ ዶክተር በላይነህ ገለጻ፤ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዙሪያ ቢሮው በትኩረት እየሰራ ነው፤ ክልሉ በቡና ልማት ይታወቃል።ተረፈ ምርት (የቡና ገለፈት) ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ግብአት እንዲውል ጥረት እየተደረገ ነው።በተጨማሪም ከከብት እዳሪና ከተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎችም እንዲዘጋጅ እየተደረገ ነው።ከቤትና ከተለያየ ቦታ የሚወገድ ደረቅ ቆሻሻም ጥቅም ላይ እንዲውል በተለይም ቆሻሻ የሚጣልበት በተለምዶ ቆሼ አካባቢም ሥራ እንዲሰራ ጥረት እየተደረገ ነው።
ከየአካባቢው ከሚወገድ ቆሻሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው ለገበያ በማቅረብ ሙከራ ላይ የሚገኙም አሉ።ግብአቱ በተለይም በሀዋሳና በዙሪያዋ ለከተማ ግብርና ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው።በገጠርም በአነስተኛ ማሳዎች ላይ በተመሳሳይ በማከናወን ለመጠቀም እየተሞከረ ነው።ሙከራው የሚበረታታ በመሆኑ አጠናክሮ በመቀጠል ወደፊት ለሰፋፊ እርሻ ሥራ የሚውለበትን መንገድ መፍጠር ስለሚገባ ቢሮውም በዚህ ደረጃ መስራቱን ቀጥሏል።የበቆሎ ልማት የሚካሄድባቸው ከሀዋሳ እስከ ዲላ ያሉት ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ሰፋ ያለ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ይጠይቃሉ።
ከወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ እንዲሁም በሲዳማ ግብርና ቢሮ የተገኙ መረጃዎች አንደሚያመለክቱት ቨርን ኮምፓስት ማዳበሪያን አዘጋጅቶ ለግብርና ስራው ማዋል በብዙ መልኩ ፋይዳ አለው።ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ አፈርን በማከም በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ እንደ አገር ሊገጥም የሚችለውን ሰው የሰራሽ ማዳበሪያ ችግርና እየጨመረ ያለው የማዳበሪያ ዋጋ ሲታሰብ የዚህ ማዳበሪያ ጠቀሜታ አጠያያቂ አይደለም።ይህን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሌሎች ክልሎችም አዘጋጅተው እንዲጠቀሙበት ተሞክሮውን ለማስፋት በትኩረት መስራት ይኖርበታል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014