-ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ስምንት ሚሊዮን ብር ተመድቧል
አዲስ አበባ፡- ከህክምና ስህተት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ችግሮች የህክምና የሥነ ምግባር ህጎች ላይ ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ይፋ አደረገ።
ፕሮጀክቱ ትናንት ይፋ በሆነበት ወቅት የማህበሩ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ሰብሳቢና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር አዳሙ አዲሴ እንደገለፁት፤ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ በህክምና ባለሙያዎች ዙሪያ የህክምና ሥነ ምግባር እንዲበረታታ ማድረግ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝም ከህክምና ስህተት ጋር በተያያዘ በሚነሱ ችግሮችና የህክምና ህጎች ዙሪያ ለህክምና ባለሙያዎች፣ ለህግ አካላትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ሥልጠናዎችን በመስጠት ግንዛቤያቸው እንዲሰፋ ማድረግ ነው።
እንደ አስተባባሪው ገለፃ፤ ፕሮጀክቱ የተዘጋጀው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲሆን፤ ለአንድ ዓመት የሚቆይና በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አስር ሆስፒታሎች ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል። ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያም ከጤና ሚኒስቴር በኩል ስምንት ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፤ በቀጣይም በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚሰፋ ይሆናል።
ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት እንደፈጀ አስተባባሪው ያስታወሱ ሲሆን፤ ከዚህ ፕሮጀክት አፈፃፀም ልምድ በመውሰድ በቀጣይ በፕሮግራም መልክ እንዲቀጥል እንደሚደረግም ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
አስናቀ ፀጋዬ