ከሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጨ ያለ አንድ አስተማሪ የችሎት ገጠመኝ አለ። ከተለመደው ልምድ ውጭ ፍርድ የሰጠ ዳኛ ያሳየው ሰብዓዊነትን በሚያወድሱ አስተያየቶች የተሞላ ጽሁፍ። ከሳሽ ተሰርቄያለሁ ሌባውም ይህነው ብሎ ለሚጠብቀው ፍትህ ዳኛው ተከሳሽን ከክሱ ነጻ አድርገው ከሳሽ ላይ ፍርድ ማሳለፋቸውን የሚያትት ትረካ። ታሪኩ በተጨባጭ የተከናወነ ትክክለኛ ታሪክ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማግኘት ባይቻልም ስለሰብዓዊነት ያለው አስተማሪነቱ ከፍተኛ ስለሆነ እንደ መንደርደሪያ እንጠቀምበት።
ከሳሽ ያቀረበው ክስ ፍሬ ነገሩ ታዳጊው ልጅ ዳቦ ከከሳሽ የንግድ ሱቁ እንደሰረቀ የሚያስረዳ ነው። ዳኛው እንደተለመደው እጅ ከፍንጅ የተያዘ ሌባ ላይ ከሚሰጠው ፍርድ መለስ ብሎ ልጁ ለምን ሊሰርቅ እንደቻለ ተከሳሹን በመጠየቁ ሂደት ውስጥ ትኩረትን ሳቢ ውሳኔ ላይ የደረሰው። ተከሳሽ ለምን እንደሰረቀ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ እርቦት እንደሆነ ነው። ቤተሰቦቹ ስለምን አልመገቡትም ብሎ ዳኛው ባስከተለው ጥያቄ ሌላ ገጽ ተገለጠ፤ የተከሳሽ እናት በህመም ምክንያት አልጋ ላይ መሆናቸውን የሚያስረዳ። በስተመጨረሻ ተከሳሽ ስርቆት የፈጸመው የራሱንም የእናቱንም ሕይወት ለማትረፍ እንደሆነ ችሎቱ ተረዳ። የዳኛው ፍርድ የነበረው ሌባውን ተከሳሽ ጥፋተኛ ማለት ሳይሆን የችሎቱን ታዳሚዎች፣ ራሱን ዳኛውንና ከሳሽን ጥፋተኛ ማድረግ ነበር። “እኛ እያለን እንዴት አንድ ታዳጊ ዳቦ መስረቅ ውስጥ ይገባል?” የሚል ጥያቄን በፍርድ አሰጣጡ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት ዳኛው ይሞክራል። ከሳሽ ከተከሳሽ ሊከፈለው የሚገባ ነገር እንዳይጠብቅ ሆኖ በተቃራኒው ከሳሽ ለተከሳሽ መክፈል ያለበት ተነገረው፤ ችሎቱ ውስጥ የተሰበሰቡ እንዲሁ ለተከሳሽ መክፈል ያለባቸው ተነገራቸው፤ ዳኛውም አብነት ሆኖ የራሱን መዋጮ አስቀደመ መዝገቡም ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ ታዘዘ። “እኛ እያለን እንዴት አንድ ታዳጊ ዳቦ መስረቅ ውስጥ ይገባል?” የሚለው ጥያቄን መልስ ይሰጡ ዘንድ በዳኛው ዙሪያ የተሰበሰቡ በተለያየ መጠሪያ የሚጠሩ አካላት ተጋበዙ። ሰዎች ዳቦ ወደ መስረቅ ከሄዱ ችግሩ የእነርሱ ሳይሆን የሁላችን ነው የሚል መልእክትም ተላለፈ።
ይህ ታሪክ በተጨባጭ የሆነ ታሪክ በመሆን ዙሪያ ላይ እርግጠኝነት ባይኖረንም አስተማሪነቱ ብዙ ስለሆነ እያሰላሰልነው እንዝለቅ። ራሳችንን በዳኛው ቦታ፣ በከሳሽ ቦታ፣ በተከሳሽ ቦታ፣ በችሎት ታዳሚያን ቦታ አድርገን የሚሰጠንን ትርጉም አውጥተን አውርደን እንየው።
በአገራችን ችሎቶች ድንገት እግር ጥሎን የምንመለከታቸው ጥቃቅን የሚመስሉ መዝገቦችን ባህሪ ስንመለከት ከታዳጊው ልጅ ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን አያሌ መዝገቦች ማግኘት እንችላለን። ከተለመደው አልፎ በመሄድ ውስጥ በቀላሉ በቅኖች ሊፈቱ የሚችሉ መዝገቦች።
በዛሬው ቆይታችን በማህበረሰባችን ውስጥ ተከሳሽ አድርገን ስለምናቀርባቸው በማህበረሰብ ጤንነታችን ውስጥ ችግር ስለሆኑብን ጉዳዮች እንዲሁም የቅኝት ፍተሻ እናደርጋለን። “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፤ ሲይዙት ያደናግር”እንደተባለው በሰዎች እጅ ነገሮች የሚሆኑበትን ነገር ተመልክተን በብዙ ከሳሽ ሆነን ነገር ግን ራሳችንን በአግባቡ መመልከት ስንችል የሚኖረንን አተያይ እንፈትሻለን። ማህበረሰባዊ ለውጥን ከእሴት፣ እውቀት እና ተግባር ውስጥ ማግኘት እንችል ዘንድ የሚቀሰቅስ መልእክት። እዚህም እዚያም የበዙትን የክስ መዝገቦችን ቀጥሎ እንመልከት፤
የክስ መዝገቦች በየመልካቸው
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጥናታቸውን የሚያደርጉ ባለሙያዎች እያረጋገጡ የመጡት አንዱ እውነት ማህበራዊ ሚዲያ ግነትን የሚፈልጉ፤ ትኩረት ሳቢ የሆኑ፤ ከተለመደው ወጣ ያሉ ነገሮችን ይዞ መቅረብን የሚገፋፋ መድረክ መሆኑን ነው። በአጭሩ ከሌላው ተለይቶ የመታየት በሽታ ሰለባ የሚያደርግ። ይህም ጭንቀት የመፍጠር አቅሙን እና ጭንቀትን የማጋራትና የማስፋት አሉታዊ ጎኑን ያሳያል። አንድ ሰው እንዴት ባለ ሁኔታ ቢያቀርብ ለየት ያለ ነገር ሊያቀርብ እንደሚችል እንዲያስብ የሚያነሳሳና ድፍረትን መጠቀምን የሚሰብክ ልንለውም እንችላለን። በዚሁም ምክንያት ግለሰቦች በብዙ ጉዳዮች ላይ ድፍረት በተሞላው መንገድ አቋማቸውን ሲያራምዱ ይስተዋላል። በአካላዊ ግንኙነት ደፍረው የማይሉትን ነገር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ግን የሚሉበት እድል ያለ መሆኑን የሚያመላክት ነው። የክስ መዝገቦች በየመልካቸው የሚታየውም እዚያው ማህበራዊ ሚዲያዎች ገጽ ላይ ነው።
እግር ኳስ ተጫዋቹ፣ አርቲስቱ፣ የአገር መሪው፣ የአካባቢ አስተዳዳሪው፣ የማህበረሰብ አንቂው፣ የአገር ሽማግሌው ወዘተ ሁሉም የቀረበበት የክስ መዝገበው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በግልጽ ተሰጥቶ ይታያል። ክስ ያልቀረበበት አካልን ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ በየቀኑ የክስ መዝገብ በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቲውተር እና በሌሎችም መድረኮች ላይ ሲዘንብ እናገኛለን። ሁሉም ከሳሽ፤ ሁሉም ተከሳሽ ሆኖ የሚታይባቸው መድረኮች ብንላቸው እንችላለን። ለአንድ ጉዳይ ወደ አንድ ተቋም ባለጉዳይ ሆኖ የገባ ሰው ከእርሱ ጉዳይ በመነሳት ተቋሙ ላይ የቁጣ ዝናብ አዝንቦ ሊያልፍ ይችላል። ሁሉም ነገር ላይ በድምዳሜ ‘ይህ የሆነው፤ ይህን ለማድረግ ነው ወዘተ’ በማለት ደምድሞ አደባባይ ላይ ክስ ማስቀመጥ የማይቸግርበት ዘመን። እንዲህም ማድረግ እንደ ጀብዱ የሚቆጠርበት ጊዜ። ምናልባትም ወደፊት መደበኛው ፍርድ ቤት እየቀረ ሰው ሁሉ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ክስ አቅርቦ እዚያው ተከታዮቹ በአስተያየት መስጫ ሳጥን ውስጥ ድምጽ ሰጥተው ብይኑን አሳልፈው ይህን ወስነናል የሚሉበት ዘመን ይመጣም ይሆናል ብለን እንድናስብ የሚያደርግ።
እንዲህ ባለሁኔታ የክስ መዝገቦች በየመልካቸው ገበያ በወጡበት ዘመን ውስጥ ነገሮችን በጥንቃቄ የሚመረምሩ፤ ነገሮችን በችኮላ ከማየት ይልቅ እርጋታን የሚመርጡ፤ ብልሃትን ልብስ አድርገው ለብሰው የሚንቀሳቀሱ ሰራተኛ የሆኑ ሰዎች አንሰው ይታያሉ። መከሩ ብዙ ነው፤ ሰራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው እንድንል የሚያደርገን የዘመን ገጽ። እሴት፣ እውቀት እና ተግባር ተገናኝተው ከአንድ ተከሳሽ ታሪክ ውስጥ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ፍርድን የመፈለግ አቅምን የሚፈትን ጊዜ።
መከሩ ብዙ፤ ሰራተኞች ጥቂቶች
ለውጥ የሰዎች የተጋድሎ ውጤት ነው። በየዘረፉ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ሲነገር እንሰማለን። በተለይ በአገራችን በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱ ጥያቄ ውስጥ በገባበት ሁኔታ ውስጥ ጥራት ያለው አምራች ሃይል ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የክስ መዝገብ በአደባባይ ተሰጥቶ በምናይበት በዚህ ዘመን ውስጥ ሰዎች ወደ ኃላፊነት በተለይም ወደ ህዝብ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከመምጣት እንዲሸሹ እየሆኑ ደግሞ የለውጥ አብነት የሚሆኑ ሰራተኞችን ቁጥር ያመነመነው ይመስላል። በተወሰነ ደረጃ የኢትዮጵያ ችግር አንዱ መንስኤ ይህ ሊሆን እንደሚችል ብናስብ የተሳሳትን አንሆንም።
የፈረሰው ነገር ብዙ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ለስራው የሚገኙ ሰራተኞች ጥቂት በሆኑበት ሁኔታ የከሳሽና ተከሳሽ መድረክ የራሱን ሌላ መልክ ይይዛል። ይህ ሲሆን ለመንደርደሪያ ታሪካችን የተጠቀምንበት የሌብነት መነሻ የሆነውን ጉዳይ ተረድቶ መፍትሔ መስጠት ሩቅ የተሰቀለ ሊሆንም ይችላል። እንደ አገር አንድ ሰው ስለሚበላው ምግብ ብሎ ወደ ስርቆት ከገባ ተጠያቂነቱ የሁላችንም ነው ብሎ ለማሰብ ከሚያጋፋው ሁሉ ወጣ ብሎ በሚዛን ማሰብ የሚችሉ የለውጥ አብነቶችን የሚፈልግ ስለሆነ።
የዘመኑ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የተሰወሩ እውቀቶች መገለጥ እንዲሁም ከታሪክ ወይንም ከትላንት የሚወሰደው ትምህርት መብዛት ባለበት ሁኔታ ወደ አስደማሚ እድገት የሰው ልጅ መግባት ይኖርበት ነበር። በተጨባጭ ግን የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ተከብቦ ግናግን የጋርዮሽ ኑሮን ይኖር እንደነበረው አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እየኖረ ይገኛል። የሰው ልጅ በብሔሩ ሆነ በኃይማኖቱ አግላይ ወይንም የሚገለል ሲሆን ወይንም አግላይ ሲሆን አንዳች የጎደለ ነገር ስለመኖሩና ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አተያይ ላይ አለመገኘቱን ያሳየናል። ለዚህ የሚቀርበው ምክንያት በዘመኑ ውስጥ ያለው እድገት ማነስ ሳይሆን ያለው ሰዎች ቁጥር ማነስ ወይንም ጎልተው መታየት አለመቻላቸው ነው።
ለውጥን የሚፈልጉ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፤ ነገር ግን ሰዎቹ በበቂ ሁኔታ የሉም። ስለሆነም የከሳሽና ተከሳሽ ባህላዊው መዝገብ ባለበት መንገድ ይቀጥላል። ሌባው ስለምን ብሎ ሌባ ሆነ? ሴተኛ አዳሪዋ ስለምን ብላ ሴተኛ አዳሪ ሆነች? ወዘተ ብሎ ጠይቆ ወደ ችግሩ ምንጭ ለዘላቂ ለውጥ ከመሄድ የሚመልስ ሆኖም እንረዳዋለን። የተከሳሽና ከሳሽ ቀመሩን መፈተሽ አለብን ብለን ስንነሳ ሊሰራ የሚገባውን ብዙ ስራ እናያለን። በእሴት ያደጉ ሰዎችን፤ በሌላኛው ጫማ ውስጥ ሆነው ነገሮችን የሚመለከቱ፤ ኃላፊነትን ከእኔ ተጠያቂነቱ ትርጉም ሰጥተው የሚኖሩ፤ የሥራ ውጤትን በመልኩ በመለካት ከዛሬ ነገ የተሻለ ማድረግን ግብ የሚያደርጉ ወዘተ መኖራቸው ለለውጡ ዋና ሃይል ናቸው።
አንባቢው እራሱን ይጠይቅ ሊሰሩ የሚገባቸው ብዙ ስራዎች እንዳሉበት ትውልድ አንድን ቀዳዳ ለመድፈን እየሰራ በመሆኑ የከሳሽና ተከሳሽ መዝገብን እየቀነሰ ያለ ወይንስ በተቃራኒው መዝገብ እያበዛ? ለጥያቄው የሰጠውን ምላሽ ለጊዜው ያዝ አድርጎ ሁሉ ከሳሽ፤ ሁሉ ዳኛ በሆነበት ወቅት ውስጥ ስለመሰረታዊ ለውጥ እናስብ።
መሰረታዊ ለውጥ
መዳረሻችን በመነሻችን ውስጥ ያነበብነው ታሪክ ውስጥ እሴት፣ እውቀትና የተግባር እርምጃ የፈጠሩትን አዎንታዊ ተጽእኖን ማሳየት ነው። የዳኛው ልብ ከደረቅ ህጎች ባሻገር። መዝገብ በአደባባይ በተሰጣበት ሁሉ ከሳሽ ሁሉ ዳኛ በሆነበት ዘመን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው አንድ የአዎንታዊ ለውጥ እርምጃ። እርምጃው ወደ ውጤት የሚያደርስ ይሆን ዘንድ ወደ ብሩህ ብርሃን የመመልከት። አስደናቂዋ ሴት ሔለን ኬለር “ወደ ፀሐይ ጮራው ተመልከት፤ ያንጊዜ ጥላውን አታይም” እንዳላቸው ሊታይ ወደሚገባው አቅጣጫ ማየትን በማስቀደም የተከሰተ ቢሆንም ሊታይ ያልተገባውን ያለማየት ማሳያ። የለውጥ መንገድ አተያይ።
በለውጥ መንገድ ውስጥ ሲሆን በለውጥ ውስጥ በመገኘት ውጤትን የራስ ለማድረግ ሲታሰብ የሚኖረው ፈተና ቀላል አይሆንም። ሁሉ ከሳሽ ሁሉ ዳኛ ሆኖ ሲመጣ ዳኛው የህግ ስርዓቱን አካሄድ አበላሽቶ እንዲህና እንዲያ ወስኗል ተብሎም ሊጠቀስ ይችላል። የከሳሽን መብት ረግጧል ወዘተ የሚሉ ድምጾች መሰማታቸውም እንዲሁ ሊሰማ ይችላል። የአስተሳሰብ ለውጥ በሌለበት ቦታ ሁሉም ነገር አነጋጋሪ ሆኖ በጎራ መሰለፍን የሚገባዝ በመሆኑ።
ስለ መሰረታዊ ችግሮች መፈታት ስናስብ መሰረታዊ አስተሳሰብ ለውጥ የግድ እንደሆነ ደጋግሞ በማስመር ማለፉ አስፈላጊ ነው። ለመሰረታዊ ለውጥ ከተለመደው ወጣ ብሎ ለመሄድ እይታን ሊታይ በተገባው ላይ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ፀሐይ ላይ። በእርግጥ ወደ ብርሃን ጉዳይን ይዞ መውጣት ቀላል አይደለም። ሁሉ ወደ ብርሃን ቢወጣ ሰው ሁሉ እውነትን ወደ መነጋገር ቢመጣ፤ ሰው ሁሉ ሊያየው የሚገባው ላይ ትኩረት ቢያደርግ የጨለማው ስራ በስፋት በተገለጠ እና የለውጥ መንገዶች አንድ ምእራፍ ብቻም ሳይሆን በእጥፉ ወደ ውጤት ባደረሱን ነበር።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምንዝርና የተያዘች ሴት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ቀረበች። በሙሴ ህግ መሰረት ተወግራ ትገደል ዘንድ ህግ የሚደነግጋበት። የእርሷን ጉዳይ እንዴት እንደሚያየ የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ድንጋይ በእጃቸው አድርገው መውገር ከመጀመራቸው በፊት እርሱንም በፈተና ጠልፈው ለመጣል ወደ እርሱ ይዘዋት ቀረቡ። እርሱም ፈረዳ ፍርዱም ምንም ኃጢአት የሌለበት ሰው እርሱ የመጀመሪያውን ወጋሪ ይሁን የሚል ሆነ። ሁሉም ራሱን ሲመለከት ከጀርባው የተሸከመው ትዝ እያለው ድንጋዩ እያስቀመጠ ወደኋላ ተመለሰ። ከተለመደው ወጣ ብሎ ፍትሕ በመስጠት ውስጥ የተላለፈ ብይን። እሴት፣ እውቀት እና ተግባር ተገናኝተው የሚፈጥሩት የአስተሳሰብ ለውጥ ማሳያ።
እሴት፤ እውቀት፤ ተግባር
የመነሻ ታሪካችን ዳኛን በእሴት፣ እውቀት እና ተግባር ውስጥ ተመልክተን ወደ መውጫችን እንድረስ። በዳኛው ውስጥ ያለው የእሴት ሕይወት ተጠርጣሪውን በተለየ መንገድ እንዲያይ የተጠርጣሪውን እውነት ለማየት ብዙ እርቀትን መራመድ እንዲችል ያደረገው ነበር። በእሴት የተገነባ ግለሰብ፣ ቤተሰብ እንዲሁም ማህበረሰብ በቀላሉ ለፈተናዎች እጅ የማይሰጥ ነው። ለፈተናዎች እጅ አለመስጠት ብቻም ሳይሆን በሌሎች ጫማ ሆኖ ነገሮችን ተመልክቶ በሚጠቀም መንገድ ውስጥ መራመድ የሚችል።
እውቀት ሌላው ዳኛውን መመልከቻ ነጥብ ነው። በህግ ትምህርት ቤት ውስጥ ያለፈ ሰው ሊኖረው የሚገባውን እውቀት ይዞ በቦታው ላይ የተሰየመ መሆኑን ስናይ የምናገኘው። እውቀቱ ከእሴት ጋር ተዳምሮ ለሰጠው ውሳኔ አስተዋጽኦ ማድረጉም ግልጽ ነው። እውቀትን ለማህበረሰብ ጥቅም በሚውልበት ሁኔታ ላይ መጠቀም ለሚወድ አስተዋጽኦ ጉልህ ነው። እውቀት ምን ያደርጋል የሚያስፈልገው እሴት ያለው ሕይወት ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ገጥመውን ይሆናል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ እውቀትና ገንዘብ ተብሎ ተከራክረንም እናውቅ እንደነበረው። እውቀት ለማህበረሰብ ለውጥ ያለውን ጥቅም ወደ ጎን አድርገን ልናይ የምንችልበት ምንም አይነት እድል የለም። እውቀትና እሴት ሁለቱም አስፈላጊዎች ናቸው ነገር ግን በተግባር መሬት ላይ የሚውሉ ካልሆኑ ጥቅም የሌላቸው።
የተግባር ሕይወት ለእያንዳንዳችን በሚበዛበት ጊዜ የመልካም ተጽእኖ መዳረሻችን እየጨመረ ይሄዳል። የተግባር ሰው እውቀቱን እና እሴቱን ደምሮ በሌላው ጫማ ላይ ሆኖ ስለ ሰው አስቦ ሰው ሆኖ ሲገኝ ያ ትልቅ ነገር ነው። የለውጥ መንገድ። ከተለመደው መንገድ ወጣ ብሎ አስቦ ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ መንገድ። “ለውጥ የምቾት ቀጠና መጨረሻ ላይ የሚጀምር ነው” እንደሚባለው አባባል ግለሰቦች እሴትን፤ እውቀትን እና ተግባርን አወዳጅተው ሲኖሩ የምችቶ ቀጣናቸውን ለቀው መኖር ይጀምራሉ። ያኔ ለተከሳሽ ፍርድ ይሰጣል። ከሳሽ ተደስቶ የሚቀበለው ፍርድ፤ በጋራ የማሸነፍ፤ ነገ ሌባ እንዳይኖር የሚያደርግ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014