እንደ መግቢያ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅፅ 15 ላይ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በዛሬው ዕትማችን አንዱን ይዘን ቀርበናል። የሰነድ መለያ ቁጥር 79189 መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ.ም አምስት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት ለበርካታ ጊዜ ክርክር ሲደረግበት የነበረው ጉዳይ የመጨረሻውን እልባት ለማግኘት ተቃርቧል። ዳኞች የመጨረሻ ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት ሁሉን ነገር በአንክሮ ተመልክተዋል።
ባለጉዳዮች
አመልካች፡- የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ባለስልጣን – ነገረ ፈጅ ወይዘሮ ሕይወት ደምሰው የቀረቡ ሲሆን፤ ተጠሪዎች፡- ጂ.ኤም.ቲ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠበቃ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በችሎቱ ፊት ቀርበዋል። ዳኞችም ለረጅም ጊዜ ሲመረምሩ በነበረው ጉዳይ ፍርድ ተሰጥቷል።
የክርክሩ ሂደትና ፍርድ
በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር በተጀመረበት ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ እና አመልካች እንደቅደም ተከተላቸው ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ የነበሩ ሲሆን፤ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የነበሩት ደግሞ የሰበር ክርክሩ አካል ያልሆኑት እንደቅደም ተከተላቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የማረሻ፣ የወገልና የቢላዋ ስ/አ/ህብረት ስራ ማህበር ናቸው። በ06/07/02 ተሻሽሎ የቀረበው ክስ ይዘትም ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ስር ከሚገኘው የፍትህ አስተዳደር መምሪያ የ3ኛ ተከሳሽ ንብረት የነበረ ድርጅት በጨረታ ገዝቶ መረከቡን፣ ይሁን እንጂ ከ3ኛ ተከሳሽ የሚፈለግ የካፒታል ዕድገት ግብር ካለ እንዲገለፅ ከአንደኛ ተከሳሽ ለተፃፈለት ደብዳቤ ሁለተኛ ተከሳሽ በወቅቱ ምላሽ አልሰጠም።
1ኛ ተከሳሽም የ2ኛ ተከሳሽን መልስ ሳይጠብቅ እና ግብሩን ሳይቀንስ ተራፊውን ገንዘብ በሙሉ ለ3ኛ ተከሳሽ በመመለሱ እና የ3ኛ ተከሳሽ ካርታ ሳይቀርብ ከሳሽ በንብረቱ እንዲበደር ለባንክ ማረጋገጫ በመስጠቱ 3ኛ ተከሳሽ ከግብር ነፃ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃና ካርታ ሳያቀርብ ሙሉ ገንዘብ በመቀበሉ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በአንድነትና በመመሳጠር በፈጸሙት ተግባር ከሳሽ ስሙን አዛውሮ በንብረቱ ለመጠቀምና ብድሩን ለመክፈል አለመቻሉን የሚገልጽ ሆኖ በከሳሽ ላይ የታሰበውን የብድር ወለድ ብር 1ሚሊዮን785ሺ539ብር ከ20 ሳንቲም ተከሳሾቹ ለከሳሽ እንዲከፍሉ እንዲወሰን ዳኝነት የተጠየቀበት መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ክስ የቀረበበትን የወለድ ገንዘብ ለመክፈል ተከሳሾቹ የሕግም ሆነ የውል ግዴታ የለባቸውም በማለት ክሱን ውድቅ በማድረግ መዝገቡን ዘግቷል ይላል ከችሎቱ የተገኘው መረጃ።
ወደ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ይግባኙ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በፍርድ ባለመብት አሰፋ አርጋው እና የፍ/ባለዕዳ በነበረው 3ኛ መልስ ሰጪ መካከል በነበረው አፈፃፀም ይግባኝ ባይ የ3ኛ መልስ ሰጪ ንብረት የነበረውን ድርጅት በ22/03/99 ዓ/ም በብር 6,700,000 በጨረታ ገዝቶ ገንዘቡን አጠቃሎ ገቢ በማድረግ ድርጅቱን እንደተረከበ ድርጅቱን ለመግዛት ይ/ባይ ከወጋገን ባንክ ጎፋ ቅርንጫፍ ብር 4,265,100 ሲበደር የስም ዝውውሩ ወደ ይግባኝ ባይፈፀም ካርታውን በቀጥታ ለባንኩ እንዲልክ ለ2ኛ መልስ ሰጪ በደብዳቤ የሚያሳውቅ መሆኑን በመግለፅ የፍትህ አስተዳደር መምሪያ ለባንኩ ማረጋገጫ እንደሰጠ፣ ከ3ኛ ተከሳሽ የሚፈለግ የካፒታል ዕድገት ግብር እንዲገለጽለት 1ኛ መልስ ሰጪ ለ2ኛ መልስ ሰጪ ደብዳቤ የፃፈው በ09/09/99 ዓ.ም ሆኖ 2ኛ መልስ ሰጪ ብር 803,997.33 የካፒታል ዕድገት ተቀንሶ እንዲሰጠው በመጠየቅ ምላሽ የሰጠው ከዘጠኝ ወራት በኋላ በ06/06/2000 ዓ.ም እንደሆነ፣ በዚህ ጊዜ መሀል 3ኛ መ/ሰጪ የተራፊውን ገንዘብ በሙሉ እንደወሰደ፣ በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 37 መሰረት የካፒታል ዕድገት ግብር የመክፈል ግዴታ የሻጭ በመሆኑ ግብሩ እንደሚፈለግብኝ አላውቅም ነበር በማለት 3ኛ መልስ ሰጪ ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም የሚል ተከራክረዋል።
1ኛ. መልስ ሰጪ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ አይገባውም ወይም ግብሩ ሊኖር እንደሚችል መገመት የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም ባይባልም ግድፈቱ ሚዛን የሚደፋ እንዳልሆነ በፍርድ ቤቶች የሚፈፀም ስህተት በይግባኝ ከሚታረም በስተቀር ለሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት አለባቸው የሚባል ከሆነ በሀገሪቱ ምስቅልቅል የሚፈጠር እንደሆነ፣ 2ኛ. ከዘጠኝ ወር በኋላ ግብሩ ገቢ እንዲደረግለት ጠይቆ ገንዘቡ ለ3ኛ መልስ ሰጪ መለቀቁ ሊገለጽለት ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ቤት እና ለፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደብዳቤ መፃፉ የራሱን ስህተት ግምት ውስጥ እንዳያስገባ ስህተቱን ሌሎች መልስ ሰጪዎች እንደፈፀሙት በማድረግ መሯሯጡ ተገቢነት አልነበረውም።
ይህንን በዝርዝር ከገለፀ በኋላ ይግባኝ ባይ ድርጅቱን የተረከበው በመሆኑ መ/ሰጪዎች የባንክ ብድር ወለድ ይክፈሉኝ በማለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው ይሁን እንጂ ከክርክሩ መረዳት እንደተቻለው ይግባኝ ባይ ግዴታውን ሙሉ በሙሉ ተወጥቶ እያለ ስሙ እስካሁን ያልተዛወረለት በመሆኑ 2ኛ መልስ ሰጪ የድርጅቱን ባለቤት ስም ወደ ይግባኝ ባይ ያዘውር የካፒታል ዕድገት ግብሩን ብር 803ሺ997 ብር ከ33 ገንዘቡን ከወሰደበት ቀን ጀምሮ ከሚታሰብ ወለድ ጋር 3ኛ መልስ ሰጪ ለ2ኛ መልስ ሰጪ ገቢ ያደርግ 2ኛ መልስ ሰጪም ተከታትሎ ገቢ ያስደርግ ይግባኝ ባይ ለዳኝነት የከፈለውን ገንዘብ 2ኛ እና 3ኛ መልስ ሰጪዎች በታሪፉ መሰረት ግማሽ ይከፈሉት፣ ቀሪውን ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበው የጠቅላይ ፍር ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ሲሆን፤ በ24/08/04 ዓ.ም አዘጋጅቶ ያቀረበው አቤቱታ ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ተጠሪ ያቀረበው ክስ በጨረታ አሸንፎ የተረከበውን ድርጅት በአመልካችና በሌሎች የስር ተከሳሾች ጥፋት ወደስሙ ማዛወር ባለመቻሉ ከባንክ ለወሰደው ብድር ለብር 1,785,539.20 የወለድ ክፍያ የተዳረገ በመሆኑ ወለዱ ሊተካልኝ ይገባል የሚል ሆኖ አመልካች ስም እንዲያዛውር የካፒታል ዕድገት ግብር ከነወለዱ ከስር 3ኛ መልስ ሰጪ ተከታትሎ ገቢ እንዲያደርግ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ከክሱ ጋር የሚጣጣም መሆን አለመሆኑን ለመመርመር ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የፅሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን ተመርምሯል። በዚህም መሰረት ተጠሪ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ06/07/02 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ አሻሽሎ ባቀረበው ክስም ሆነ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ባቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ የጠየቀው ዳኝነት የወለድ ክፍያ መሆኑን እና በይግባኝ ሰሚውፍርድ ቤት የተሰጠው ዳኝነት ደግሞ የስም ዝውውር እንዲፈፀም መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል።
ይሁን እንጂ ተጠሪ በከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር ዳኝነት ለጠየቀበት የወለድ ክፍያ ዋንኛ መንስኤ የሆነው በስር ተከሳሾች (መልስ ሰጪዎች) ድርጊት ሳቢያ የስም ዝውውሩ ሊፈፀም አለመቻል መሆኑን በግልጽ ሲከራከርበት የነበረ በመሆኑ የድርጅቱ የስም ዝውውር ጉዳይ የስር ፍርድ ቤቶች ዳኝነት ከጠየቁበት ጉዳይ ውጪ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም በዚህ ረገድ በአመልካች የቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው አይደለም። በሌላ በኩል ግን የስም ዝውውሩን እና የካፒታል እድገት ግብሩን ክፍያ መፈፀም ቅደም ተከተል አስመልክቶ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ከገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንፃር ተገቢ መሆን አለመሆኑ መጤን የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህም መሰረት ማናቸውም በዚህ አንቀጽ ግብር የተጣለበትን የካፒታል ንብረት ዝውውር የመቀበል ወይም የመመዝገብ ወይም በማናቸውም መንገድ ማጽደቅ ስልጣን የተሰጠው ሰው ግብሩ መከፈሉን ሳያረጋግጥ ዝውውሩን እንደማይቀበል እንደማይመዘግብ እና እንደማያፀድቅ በአዋጅ በአንቀጽ 37(7) ስር በግልጽና በአስገዳጅነት ተደንግጐ ይገኛል። የዚህ ዓይነቱ ግልጽ የሕግ ክልከላ ባለበት ሁኔታ ደግሞ የስም ዝውውሩ ከግብር ክፍያው አስቀድሞ ሊፈጸም የሚችልበት አግባብ ስለማይኖር በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው የአፈፃፀም ቅደም ተከተል ከአዋጁ ድንጋጌ አንፃር መስተካከል የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል።
አመልካች ከስር 3ኛ መልስ ሰጪ የካፒታል እድገት ግብሩን ተከትሎ ገቢ እስኪያስደርግ ድረስ የስም ዝውውሩ መዘግየት ጉዳት ያስከትልብኛል የሚል አቋም ኖሮት ተጠሪው ግብሩን ከፍሎ የስም ዝውውሩን የሚያስፈፅም ሆኖ ከተገኘም የከፈለውን የካፒታል ዕድገት ግብር ከስር 3ኛ መልስ ሰጪ የማስተካት መብት እንዲኖረው መደረጉን ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
ውሳኔ…
1.የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመመለያ ቁጥር 69181 በ30/06/04 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍርድ ቤትበ ስነስርዓት ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሏል።
2. አመልካች ካፒታል እድገት ግብሩን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በውሳኔው መሰረት ከስር 3ኛ መልስ ሰጪ ተከታትሎ ገቢ ካስደረገ በኋላ የስም ዝውውሩን ያስፈጽም በማለት ወስነናል።
3. ተጠሪ የጉዳዩ መዘግየት ሊያስከትልበት የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ያስችለው ዘንድ ግብሩን እራሱ ከፍሎ ከስር 3ኛ መልስ ሰጪ ለማስተካት የሚፈልግ ከሆነ የካፒታል እድገት ግብሩን ብር 803,997.33 (ስምንት መቶ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት ከ33/100) ከፍሎ የስም ዝውውሩን እንዲያስፈፅም እና የስር 3ኛ መልስ ሰጪም ይግባኝ ሰሚው ችሎት በወሰነው መሰረት ይህንን ገንዘብ ከነወለዱ ለተጠሪ እንዲተካ ወስነናል ሲል ዳኞች ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።።
4. የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
5. በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተሰጠው የወጪና ኪሳራ ውሳኔ አልተነካም።
6. የአፈፃፀም እግዱ ተነስቷል።
7. ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል ሲል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻውን ውሳኔ በማሳለፍ መዝገቡ ዝግ ሆኗል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014