የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ የተፈጠረ ውዝግብን የሚዳስስ ነው። በደል ተፈጽሞብኛል ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ያሉት ግለሰብ አትሌት ሙሉየ እያዩ ይባላሉ። አቤቱታ አቅራቢው ለዝግጅት ክፍላችን ቅሬታቸውን እንዲያመለክቱ የዳረጋቸው ፍሬ ነገር ከፈጠራ ባለንብረት ጋር የተያያዘ ነው።
አቶ ሰለሞን ገለታው የተባሉ ግለሰብ የአእምሮ ፈጠራዬ የሆነውን እና በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ተመዝግቦ እውቅና ተሰጥቶት ስሰራበት የቆየሁበትን የፈጠራ ስራ የራሳቸው ፈጠራ በማስመሰል ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ፈቃድ በማውጣት የፈጠራ ስራየን ከህግ አግባብ ውጭ እየተጠቀመበት ይገኛል ሲሉ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ ዝግጅት ክፍሉ የደረሰበትን ሙሉ የምርመራ ውጤቱን እነሆ ብሏል። መልካም ንባብ።
አትሌት ሙሉየ እያዩ ማን ናቸው ?
ከአቤቱታ አቅራቢው አትሌት ሙሉየ እያዩ ይባላሉ። በሩጫው ዘርፍ አሰልጣኝ እና አትሌት ናቸው። ከዚህም ባሻገር የብዙ ፈጠራዎች ባለቤት መሆናቸውን ከሰነዶች ተመለክተናል። ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለ ሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መስራች እና ስራ አስኪያጅ ናቸው። ድርጅቱ 306 አይነት የተለያዩ የስራ ዘርፎችን ይሰራል። የተለያዩ አለም አቀፍ የሽልማት ፕሮግራሞችንም ያዘጋጃል። ድርጅቱ በስፋት ሽልማት በማዘጋጀት ለተለያዩ አካላት ሽልማት ካበረከተባቸው ዘርፎች መካከል ስፖርት ፎር ክላይሜት ቼንጅ (Sport for Claimate Change) አንዱ ነው።
እንደ አትሌት ሙሉየ ገለጻ፤ ስፖርት ፎር ክላይሜት ቼንጅ (Sport for Claimate Change) ተብሎ የሚጠራው ዘርፍ በጣም ሰፊ አንድምታ አለው። ስፖርትን ከአየር ንብረት ጋር በማያያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ ሽልማት ያዘጋጀው ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለ ሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው።
ለአለም የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉም አለም አገራት እጅ አለበት። ይህም በአለም ላይ የሚገኙ ስፖርተኞችን ስርዓተ ትንፈሳ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጎዳ እየተስተዋለ ነው። ይሁን እንጂ አንድም አገር ሆነ ድርጅት ለአለም የአየር ንብረት መዛባት የራሴ ድርሻ አለበት ብሎ ሃላፊነቱን የሚወስድ ለአልነበረም። በዚህ ምክንያት ችግሩን በሚችሉት ደረጃ ለመቅረፍ ለረጅም ጊዜ በግላቸው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ጉዳዩን የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች የህግ ከለላ ያስፈልገዋል ብለው በማመን ወደ ኢትዮጵያ አእምሯዊ ጥበቃ ባለስልጣን በመውስድ እንዳስመዘገቡት ይናገራሉ። የኢትዮጵያ አእምሯዊ ጥበቃ ባለስልጣንም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ምዝገባ ሰርተፍኬት አንደሰጣቸው ሰነዶች ያሳያሉ። ያገኙት ፈቃድም የአለም የአየር ንብረት ለውጥ በስፖርቱ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እያሳዳረ እንደሚገኝ በአለም አቀፍ ደረጃ የአለምን ህዝብ በማነሳሳት ግንዛቤን ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
ስፖርት እንቅስቃሴ ነው። ክላይሜት ቼንጅ ደግሞ የስርዓተ ትንፈሳ ሊያፋልስ የሚችል ነገር ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ከዚህ ቀደም 115 ሃገራት ሯጮች በኤንባሲዎቻቸው በኩል በመጥራት እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የሁሉምን ክልሎች ሯጮች በማሳተፍ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድሮችን በማድረግ ለአሸናፊዎች ሽልማቶችን አበርክቷል። በዚህም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ የስፖርቱን ዘርፍ ምን ያህል ተጽዕኖ እያደረበት እንዳለ ለማስገንዘብ መቻሉን ይገልጻሉ።
አቤቱታ አቅራቢው ከውድድር ባለፈም የስፖርት ፎር ክላይሜት ቼንጅ ጽንሰ ሃሳብን በተለያዩ አለማት እየተዘዋወረ ማስተማሩን ይናገራሉ። ለአብነት ያህል በብራዚል፣ በእንግሊዝ፣ ቻይና፣ ቤልጄም እና መስል አገራት ላይ በአካል መጎብኘት የአየር ንብረት ለውጥ በስፖርቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ ማስገንዘብ ችለዋል።
ሌላው ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ስር አለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል በዛሬው ዝግጅታችን የምንመለከተው እና ለውዝግቡ መነሻ የሆነው አለም አቀፍ የአድዋ ሽልማት ተጠቃሽ ነው። አለም አቀፍ አድዋ ሽልማት በዋናነት የሚያተኩረው ከአገራችን ህልውና ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መስዋእትነትን ለከፈሉ እና አገራችንን በአለም አቀፍ አደባባይ ስሟ በመልካም ነገር እንዲጠራ አስተዋጾ ለአበረከቱ ሰዎች ነው።
አለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት የተሰኘው የፈጠራ ውጤት በአገራችን በአይነቱ የመጀመሪያ ነው። ይህን ፕሮግራም በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ራሱን ችሎ ተመዝግቦ ስራ ከመጀመሩ በፊት ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) በተሰኘ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን በተመዘገበ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ኤጀንሲ ስር ተመዝግቦ ከአደዋ ጋር ተያይዞ ሽልማት ለሚገባቸው ግለሰቦች ሽልማቶች ሰጥቷል።
አለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት የሚዘጋጀው በአለም ዙሪያ ስለፍቅር፣ ለሰላም እና ለአንድነት ሲባል እውቀታቸውን፣ ሃብታቸውን እና ስልጣናቸውን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለህዝባቸው እና ለአገራቸው እንዲሁም ለአለም ያበረከቱት አከላትን እውቅና ለመስጠት እና ሌሎች ሰዎችም ይህን መልካም ተሞክሮ ተመልክተው ለአገራችን ብሎም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በጎ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማድረግ ታስቦ ነው።
የውዝግቡ መነሻ የሆነው አለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት
የአለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት ለመሸለም የፈጠራ ባለመብትነታቸው እንዲረጋገጥ እና የኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣንን ለበርካታ አመታት መጠየቃቸውን አቤቱታ አቅራቢው ይናጋራሉ። ይሁን አንጂ አለም አቀፍ የአድዋ ሽልማት ፕሮግራምን ለብቻው ነጥሎ መስራት እንደማይቻል እና አደዋ በራሱ የተለየ እና የህዝብ ንብረት የሆነን ነገር ለግለሰብ አይሰጥም ተባለ። በአገሪቱ ያሉ የማህበራዊ ማቋቋሚያ ህጎች አሳሪ ስለነበሩ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ለግለሰቦች መስጠትን ስለሚከለክል ፈቃድ አንሰጥም መባላቸውን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። ይህን ተከትሎ ፈቃድ ማግኘት ካልቻልኩ የአለም አቀፍ የአደዋ ሽልማትን ለማከናወን ምንድን ባደርግ ይሻላል? ሲሉ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንን እንደጠየቁ ይናገራሉ። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣንም ይህንን ሽልማት ማካሄድ ወይም ማከናወን በሚያስችል ተቋም ስር እንዲገቡ እና በዚያ ተቋም ስርም ሽልማት ፈቃዱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁሟቸዋል።
ይህን በእንዲህ እንዳለ ስለጉዳዩ የፍትህ ሚኒስቴርን ለመጠየቅ እንደሄዱ እና በፍትህ ሚኒስቴርም ምንም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል እንዳላገኙ አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። ለውጡን ተከትሎ አሳሪ የነበሩ ህግጋት ተነስተው ማህበራት ማደራጃ ወደ ሲቪክ ማህበረሰብ መጡ። በዚህም የአለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት ፕሮግራምን በኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) በተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ስር አስገብተነው እንደ አንድ የስራ ዘርፍ በማድረግ በ2011 ዓ.ም መመስረቱን ይናገራሉ።
ይህን ተከለትሎ አለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት ፕሮግራምን ከመጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ስራውን አስጀመረ። ከመጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁንም ድርጅቱ ትልልቅ ስራዎችን እየሰራ መቆየቱን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። በተለይም 125ኛው የአድዋ ድል በዓል ሲከበር የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ በአለም ዙሪያ ስለፍቅር፣ ለሰላም እና ለአንድነት ሲባል እውቀታቸውን፣ ሃብታቸውን እና ስልጣናቸውን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለህዝባቸው እና ለአገራቸው እንዲሁም ለአለም ያበረከቱት አካላትን ማወዳደራቸውን እና ለመጀመሪያ ጊዜም የአለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት የተሰጠውም ለእቴጌ ጣይቱ እና ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ መሆኑነን ይናገራሉ። ምክንያቱም ለአድዋ ድል ፋና ወጊ የነበሩት እቴጌ ጣይቱን እና ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ስለመሆናቸው አቤቱታ አቅራቢው ያብራራሉ።
እቴጌ ጣይቱን እና ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ በህይወት የሉም። በህይወት ባይኖሩም ለእነሱ ሸልመናል። አጼ ምኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ በህይወት ስለሌሉ ባለፉት ዘመናት በጀግንነት ለአገራቸው ዋጋ በመክፈል ገድል የሰሩ አባት አርበኞች እና እነሱን ይወክላሉ ብለው ለአሰቧቸው የጎንደር አባት አርበኞች ሽልማቱን ማበርከታቸውን ያስረዳሉ። ሽልማቱም ስነ ሥርዓት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተደረገ እንደነበር ጠቁመዋል።
መጋቢት 15 ቀን በ2012 ዓ.ም ድርጅቱ በይፋ አለም አቀፍ የአደዋ ድል ሽልማት ፕሮግራም እንጀመረ እና ከዚህ ጀምሮ ድርጅታቸው አለም አቀፍ የአደዋ ድል ሽልማት ፕሮግራም እንደሚያስቀጥለው በጋዜጣዊ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ማሳወቃቸውን ይናገራሉ። በ2013 ዓ.ም የኮቪድ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገራችን ብሎም አለማችን በበርካታ ውስብብስብ ችግሮች ውስጥ እየተፈተኑ ቢሆንም እንኳን ድርጅቱ የሽልማት ስራውን እንዳላቋረጠ አቤቱታ አቅራቢው ተናግረዋል።
በኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) በተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሽልማት ከሰጠን ከሁለት ወር በኋላ አቶ ሰለሞን ገለታው የተባሉ ሌላ ግለሰብ አደዋ አዋርድ በዩቲውብ ብለው ሽልማት ሰጡ። የምዝገባ ስሙም አደዋ ሽልማት በዩቲውብ ብሎ ነው የተመዘገበው። ሙሉ አሰራሩን ግን ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) ከተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይነት ያለው ነው።
አቶ ሰለሞን ገለታው በኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለውን አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት አሰራር በሙሉ ማግኘት የቻሉበት በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነኝህ ምክንያቶች አንዱ በመጋቢት ወር በ2011 ዓ.ም ከሽልማቱ ጋር ተያይዞ የጋዜጣዊ መግለጫ እንደሰጡ እና በዚያ ጋዜጣዊ መግለጫም አቶ ሰለሞን ገለታው መገኘታቸው ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም 125ኛው የአደዋ ድል በዓል ሲከበር የነበረው ሙሉ ሂደት ደግሞ በመገናኛ ብዙሃን ተላልፎ ስለነበር መረጃውን ከመገናኛ ብዙሃን አግኝቷል። ከመገናኛ ብዙሃን ባለፈ ስለ ሽልማቱ በማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ በስፋት ሃሳቡ ተንሸራሽሯል። አቶ ሰለሞንም ሃሳቡን ከዚህ በመውሰድ አደዋ አዋርድ በዩቲዩብ ብሎ እንደመሰረተ እርግጠኛ መሆናቸውን ይናጋራሉ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢው ገላጻ፤ ከ2013 ዓ.ም በፊት ባሉ ጊዜያት የአለም አቀፍ አደዋ ሽልማትን ብቻውን ከኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) ከተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ውጪ ይሰጠን ብለው ጠይቀው ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ጥበቃ ባለስልጣን ፈቃድ አልሰጥም በማለት ከልክሎ ነበር። ለዚህም እንደምክንያ የተጠቀሰው አድዋ የህዝብ ነው የሚል ነበር።
ነገር ግን አቤቱታ አቅራቢው ስንት አመት ጠይቀው ያልተፈቀደላቸውን የስራ የአቤቱታ አቅራቢውን የስራ ፈጠራን ለሰረቀው ሰው የአደዋ አዋርድ ሽልማትን መስጠት እንደሚቻል እና ፈጠራውም የአቶ ሰለሞን ገለታው አድርጎ በመቁጠር ፈቃድ እንደተሰጠው አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። ይህን ተከትሎ እንዴት የአእምሮ ባለንብረትነት ጥበቃ ባለስልጣን የአንድ ድርጅት ሆኖ ሳለ፤ ከዚህ ቀደም ሽልማቱ ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) በተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ስር እየተሰራበት እያለ ለሌላ ሰው እንዴት ፈቃዱ ለሌላ ሰው ይጣል ? ሲሉ የኢትዮጵያን አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣንን መጠየቃቸውን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያን አእምሯዊ ንበረት ጥበቃ ባለስልጣንን ለዘመናት ምክንያት እየፈጠረ ሽልማቱን ረሱን ችሎ እንዳይሄድ ሲከለክል እንዳልነበር ሁሉ ለአቶ ሰለሞን ፈቃድ ከሰጠ በኋላ አንተም ለመሸለም ፈቃድ መውሰድ ትችላለህ ብሎ እንደመለሰላቸው እና ባለስልጣን መስሪያቤቱ እርሳቸውን የአለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት መሸለም አንዲችሉ ፈቃድ አንደሰጣቸው ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ባልስጣን መስሪያ ቤቱ አቶ ሰለሞን ያመጣውን ፈጠራ የመዘገብነው የሽልማት ዋንጫውን ምስል እንጂ ሽልማት እንዲሰጥ አይደለም። ሽልማት እየሰጠ ከሆነ ለዚህ ስራው ቢከሰስም ቢታሰርም ራሱ ኃላፊነቱን የሚወስድ ይሆናል የሚል ምልሽ እንደሰጧቸው ይናገራሉ።
ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት በቁጥር ባ/ቱ/ስ/መ/9594116-1/2013 በቀን 07/01/2013 እንደተመለከተው ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በውስጡ ከያዛቸው 306 በላይ የመፍትኄ ኃሳብ ስራዎች መካከል ለሰዎች ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ ሲባል ኃብታውቸውን፣ እውቀታቸውን እና ስልጣናቸውን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለህዝባቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለዓለም ማህበረሰብ እና ለማንኛውም ችግር በመፍትሄነት ጥሩ ስራ ለሰሩ ሰዎች የሚሸልሙበት አለም አቀፍ የአደዋ ሽልማት ፕሮግራም በጎንደር ከተማ በ2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ስለጠየቁ፤ የጠየቁት ጥያቄ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የከተማ አስተዳደሩ ትብብር ይደረግላቸው የሚል ነው ።
ይህን ተከትሎ የጎንደር ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት በቁጥር የጎ/ከ/አስ/ከ/2219/ሥ/220 በቀን 19/04 /2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ እንዳመላከተው ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት) ኦ.ተ.ሃ (Intrnational Claimate Change and Sport ኦ.ተ.ሃ) የተባለው አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በየካቲት 23/2013 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሽልማት ማካሄድ እንደሚችሉ ያስረዳል። እዚህ ላይ ከሰነዶች እንደምንረዳው አቤቱታ አቅራቢው አለም አቀፍ የአደዋ ሽልማትን ይሰጡ እንደነበር ነው።
መመሪያዎች ምን ይላሉ?
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 91(3) ላይ መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ኪነ ጥበብን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል። በዚሁ መሠረት መንግሥትም የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር ይረዳው ዘንድ አዋጅ ቁጥር 410/1996 በማውጣት ሥራ ላይ አውሎ በመተግበር ላይ ይገኛል። የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ሁል ጊዜ እያደጉ እና እየተለዋወጡ የሚሄዱ በመሆናቸው በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ላይ የተወሰነ ማሻሻያና ጭማሪ በማስፈለጉ ይህ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 872/2007 ማሻሻያ አድርጎ በሥራ ላይ አውሏል። ይህም መሆኑ ከአለም እና ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ለመራመድ ያስችላል።
ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የቅጅና ተዛማጅ መብት ጽንሰ ሀሳብ እንደሚከተለው ያብራራል። የቅጅ መብት ማለት የኪነ-ጥበብ፣ ዕደ-ጥበብ፣ የሥነ-ጽሑፍና የሳይንስ መስክ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤቶች በፈጠራ ሥራዎቻቸው ላይ የሚኖራቸው የአእምሯዊ ንብረት መብት ነው። ይህ መብት የኢኮኖሚና የሞራል መብቶችን የሚያካትት ነው። የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዓላማ የፈጠራ ባለሞያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለማከናወን ያፈሰሱትን እውቀት፣ ጊዜና ኃብት እንዲያካክሱና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ሆነው ለተጨማሪ የፈጠራ ሥራ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው። በመሆኑም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች መጠበቅ ቀጣይ የፈጠራ ሥራን ለማበረታታትና ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ አቅም ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።
በጥቅሉ ኮፒራይት የፈጠራ ባለመብቶችን የሞራል መብት በማስጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ በማድረግ ቀጣይነት ያለው የፈጠራ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል እና በህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲያመጡ ማድረግ ነው።
በአሁኑ ሰዓት የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በተመለከተ ጥበቃ የሚያደርግላቸው በ1996 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/1996 እና ይህንን አዋጅ ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 872/2007 ናቸው። አዋጅ ቁጥር 872/2007 በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ውስጥ የተካተቱ የተወሰኑ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ ያደረገ እና አዲስ መብቶችን ያካተተ ነው። በመሆኑም አዲሱ አዋጅ ነባሩን አዋጅ ቁጥር 410/1996 ሙሉ ለሙሉ የሻረ አይደለም።
በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 2(8) ላይ “የቅጅ መብት ማለት ከአንድ ሥራ የሚመነጭ የኢኮኖሚ መብት ሲሆን አግባብነት ባለው ጊዜ የሞራል መብቶችን ይጨምራል” በማለት ትርጉም ይሰጠዋል። ከትርጉሙ እንደምንረዳው የቅጅ መብት የሥራው አመንጪ የሆነው ሰው ከሥራው የሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ እና የሞራል መብት ነው። እነኚህ የሥራው አመንጪ መብቶች በአንቀጽ 7 እና 8 ላይ ተገልፆ ይገኛሉ። የሥራው አመንጪ የራሱን አእምሮ ውጤት የሆነውን የፈጠራ ሥራ ማለት የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ፣ ዕደ-ጥበብ እና የሳይንሳዊ መስኮች በተለይም መጽሐፍ፣ ቡክሌት፣ በመጽሔት ወይም በጋዜጣ ላይ የሚገኝ መጣጥፍ፣ የኮምፒዩተር ፕሮግራም፣ ንግግር፣ ሌክቸር፣ የሀይማኖት ስብከት፣ ድራማ፣ ድራማዊ ሙዚቃ ሥራ፣ የመድረክ ውዝዋዜ፣ የኦዲዮ ቪዥዋል ሥራ፣ የኪነ ህንፃ ሥራ፣ የስዕል የቅብ፣ የቅርፃ ቅርጽ ሥራ፣ የፎቶ ግራፍ ሥራ፣ ስዕላዊ መግለጫ፣ ካርታ ፕላን እና የመሳሰሉት ሥራዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ እና የሞራል መብትን ያገኛል።
በአዋጁ አንቀጽ 2 (14) ላይ “ተዛማጅ መብት ማለት ከዋኝ፣ የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲውሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በሥራው ላይ ያለው መብት ነው” በማለት ትርጉም ሰጥቶታል። የተዛማጅ መብቶች ባለቤት በሥራው ላይ የሁለተኛ ደረጃ መብት ነው ያላቸው። በሥራው ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መብት ያለው የሥራው አመንጪው ነው።
የፈጠራ ባለቤትነት መብትን ለማስጠበቅ አዋጁ የራሱ የሆ የተፈጻሚነት ወሰን፣ ጥበቃ ለማግኘት የሚስፈልጉ መመዘኛዎች እና የብቸኝነት ተፈፃሚነት ወሰን አስቀምጧል። በዚህ መሰረት ጥበቃ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መመዘኛዎች] አንደኛው የሥነ-ጽሑፍ፣ ኪነ-ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ መስክ ፈጠራ የሆነ ሥራ የሥራው አንጪው የአዕምሮ ውጤት እስከሆነ ድረስ የሥራው ዓላማና ጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ወጥ (ኦርጅናል) ከሆነ እና የተቀረጸ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ሥራው በመውጣቱ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንዲያገኝ በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 6(1) ላይ ተገልፆል። በመሆኑም የሥራው አመንጪ ለሥራው ጥበቃ ለማግኘት ሥራው 1ኛ ወጥ (ኦርጅናል) መሆን ያለበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሥራው ግዙፋዊነት ያገኘ መሆን እንዳለበት እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ ህግን ተላልፎ በተገኙ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች ላይ ምን አይነት እርምጃ ሊያስወስድ እንደሚችል በግልጽ ተመላክቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአእምሯዊ ንብረት ትሪቡናል/ የዳኝነት ሥልጣን የማን ነው የሚለውም በግልጽ ተቀምጧል። በዚህ መሰረት፡- በነባሩ አዋጅ ቁጥር 410/1996 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውንም በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ የሚነሱ ፍትሐብሔራዊ ክርክሮችን የሚዳኘው መደበኛው ፍርድ ቤት እደሆነ በአንቀጽ 33 እና 34 ተደንግጎል።
በቅጂና ተዛማጅ መብቶች በባህሪያቸው ለየት ያለ የተወሰነ እውቀትን በጉዳዩ ዙሪያ የሚጠይቁ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የማስረጃዎቻቸው በባህሪያቸው ውስብስብ በመሆናቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት ላይ ከመደበኛ ሥራቸው ላይ ጫና የሚያሳድሩ እና የጉዳዩ መጎተትን የሚያስከትሉ በመሆናቸው እና በተግባርም ይኸው እያጋጠመ ያለ ችግር ነው። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሲባል በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 872/2007 ውስጥ መፍትሄ ማሰቀመጥ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በዚሁ መሠረትም በተሻሻለው አዋጅ ውስጥ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች የሚነሱ ከውል ውጭ ስለሚደርስ ሃላፊነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በስተቀር የፍትሐብሔር ክርክሮችን የመዳኘት ስልጣን የሚኖረው በአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በሚያቋቁመው የአእምሯዊ ትሪቡናል እንደሚሆን ደንግጎል።
ነገር ግን ይህ ትሪቡናል እስኪቋቋም ድረስ ክርክሩን የመዳኘት ስልጣኑ የመደበኛው ፍርድ ቤት ሆኖ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል። ይህ ትሪቡናል ከተቋቋመ በኋላ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተት አለ የሚል ተከራካሪ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት በ60 ቀናት ውስጥ ይግባኙን ማቅረብ እንደሚችልም ተገልፆል።
በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ስለተፈጠው ነገር ማብራሪያ እንዲሰጡን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን በደብዳቤ የጠየቅን ቢሆንም ከችግሩ ከብደት አንጻር ጉዳዩን በጥልቀት ማብራራት ስለሚጠይቅ ስለጉዳዩ በበቂ ደረጃ በማጣራት ትክክለኛውን መረጃ ባገኙ ጊዜ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደሚገልጹ ባለስልጣን መስሪያቤቱ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ አቶ ሰለሞን ገለታውንም ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ስለዚህ ከዚህ ጋር በበተያያዘ ሃሳብ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል ቢመጣ የምናስተናገድ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014