አሸባሪው ሕወሓት ከትጥቅ ትግል እስከ መንግ ሥትነት በዘለቀው ጉዞው በሕዝብ ስም ምሎና ለምኖ ለሕዝብ ሳይሆን ለራሱ የኖረ፤ ለራሱም ሲል ሕዝብን አስይዞ የቆመረ፤ ለሕልውናው ሲል በሕዝብ ደም ላይ የተረማመደ ስብስብ ስለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ። የታሪክ ጉዞ ማህደሩም ሲገለጥ ይሄንኑ የሚያስረዳ ነው። ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ ገ/ሚካኤል፤ በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን ሕወሓት የፖለቲካ ድርጅት ቢሆንም ሕወሓትን የሚመሩ ወንጀለኛ ስብስቦች ፖለቲከኛ መሆን ተስኗቸው ከትናንት እስከዛሬ በትግራይ ሕዝብ ስም ሲያሴሩ፤ በሥልጣን ዘመናቸውም ሕዝቡን ሲጨቁኖ የኖሩ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንንም ሲበዘብዙ ዘመናቸውን ያሳለፉ፤ አሁን ደግሞ ከተጠያቂነት ለመደበቅ የትግራይን ሕዝብ አታልለው ወደ ትግራይ ሸሽተው የተቀመጡ ናቸው።
ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ በወቅቱ ቃለ ምልልሳቸው እንዳብራሩት፤ የሕወሓት ቡድን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በትግራይ ህዝብ ላይ ሲሰራ የነበረውን ሴራ ከድል ማግስት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሲፈጽም ቆይቷል። ግፉ ሞልቶ ሲተርፍ አገር የማፍረስና የማተራመስ ምኞቱ ጫፍ ሲወጣ የእኔ ያልሆነች አገር ምንም ትሁን በሚል እሳቤው በመከላከያው ላይ ጥቃት ፈጸመ። የትግራይ ሕዝብ ልጆችም በማያውቁትና ባላመኑበት ተግባር ውስጥ መስዋዕት እንዲሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል።
ቀድሞም መስዋዕት የሆኑን የምስኪኑ ሕዝብ ልጆች መሆናቸውን እና ይህ ወንጀለኛ ቡድን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ወደ ጦርነት ገብቶ የማያውቅ መሆኑን ያስረዱት ጄኔራሉ፤ በዚህ መልኩ የትግራይ ምድር ቀድሞ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት፣ ቀጥሎ በተከሰተው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ ወንጀለኛው ቡድን ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን ሲል በፈጸመው ጥቃት የግጭት አውድማ እንድትሆን ማድረጉን ገልጸው ነበር። የትግራይ ሕዝብም በእነዚህ የቡድኑ ወንጀለኞች የ80 እና 90 ዓመት ሽማግሌዎች ምክንያትም ለሶስተኛ ጊዜ ልጆቹን ለጥፋት እንዲያቀርብ እየተገደደ ለአያቶች መኖር የልጅ ልጆች መስዋዕት እየሆኑ እንደሚገኙም መናገራቸው ይታወሳል።
በዚህ መልኩ የሚገለጸውን የሕወሓት ሴራና እኩይ ጉዞ የሚናገሩት ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስም ሆኑ ሌሎች በርካቶች አሉ። ይህ እውነትም በእርሳቸው አንደበት ብቻም የሚገለጽ አይደለም። ይልቁንም ቀደምት የሕወሓት መስራቾችና ታጋዮች እንዲሁም ሕወሓትን በውስጥም በውጪም ሆነው በደንብ የሚያውቁት ሁሉ የሚሰጡት እማኝነት ነው። ቡድኑን በዚህ መልኩ የሚያውቁት ሰዎች እንደሚገልጹት፤ ሕወሓት ለሕልውናው ሲል የትግራይ ሕዝብን እንደ ማስያዣነት የሚጠቀም፤ ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲጋለጥ በማድረግም በስሙ የሚለምን፤ በስሙ የለመነውን ድጋፍም ሕዝብ እየተራበ ለቡድኑ ሃብት መፍጠሪያና መሳሪያ መሸመቺያ ያደረገ፤ አሁንም እያደረገ ያለ ስለመሆኑ ነው።
ለዚህ ብሂላቸው እንደ ማሳያ የሚያነሱት የ77ቱን ድርቅ ተከትሎ የሆነውን እውነት ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው። ሕወሓት በነጻ አውጪ ስም ተልዕኮ ተሸክሞ ጫካ በገባበት ወቅት በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ ክፍል ከፍ ያለ የድርቅ አደጋ ይከሰታል። በዚህ ጊዜ ሕወሓት ድርቁን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የትግራይ ሕዝብ ከማዕከላዊ መንግሥት እርዳታ እንዳይደርሰው በማድረግ ወደ ሱዳን እንዲሰደዱ ያስገድዳል። ሕዝቡን በሱዳን አስፍሮ በረሃብ የተጎሳቆለ መልካቸውን ለዓለም እንዲታይ በማድረግ ሰብዓዊ ርዳታ ይለምናል።
የምታገልለት ሕዝብ በረሃብ እያለቀ ነው ሲል ለምኖም፤ በርካታ ድጋፍ ያሰባስባል። ድጋፉን በዓይነትም በገንዘብም ካገኘ በኋላ ግን አምስት በመቶ እንኳን የሚሆን ለሕዝቡ ሳያደርስ ዓይነቱን በገንዘብ ለውጦ ወደ ካዝናው አስገባ። ያ ገንዘብ ዛሬ ላይ በድርጅቱ ሥር የሚተዳደሩ ግዙፍ የሃብት ማመንጫ ድርጅቶችን ያቋቋሙበት፤ ድርጅቶቹም ለሕወሓት ሰዎች እንጂ ለሕዝብ ጠብ የሚል ነገር ሳያደርጉ የኖሩ ናቸው። ይህ የሚያሳየው ሕወሓት የራሱን ፍላጎት ለማሳካት ሲል ሕዝቡን ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ዳርጎ መጠቀሚያ ማድረጉን፤ ለችግር በዳረገው ሕዝብ ስም ለምኖና በሕዝቡ ስም የተገኘን ድጋፍ ከሕዝብ ጉሮሮ ነጥቆ ለራሱ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት ማዋሉን ነው።
ይህ ሕዝብን አስይዞ የመቆመር ተግባሩ በ27 ዓመታት የፌዴራል መንግሥቱን የስልጣን ማማ ከተቆጣጠረ በኋላም የዘለቀ ነው። በእነዚህ ዓመታት አያሌ ብድርና እርዳታዎች ከውጭ መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ተቋማት ደርሰዋል፤ አያሌ የሰብዓዊ ርዳታዎችን በየዘመናቱ ለሕዝብ እንዲደርሱ በሚል ተሰጥተውታል። ይሁን እንጂ ብድርና ርዳታዎቹ ለሚፈለገው ልማት፤ ሰብዓዊ ድጋፎቹን ድጋፉን ለሚሻው ሕዝብ በሚፈለገው መልኩ የደረሱበት አግባብ ላይ አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል ነገር የለም።
ለምሳሌ፣ በ27 ዓመታት ውስጥ ከውጭ የተገኙ ብድርና ድጋፎች የሕወሓት ቡድን ዘርፎ ወደ ውጭ ካወጣውና በውጪ ባንኮች ከሸሸገው ሃብት የተመጣጠነ ነው። ይህ ደግሞ ሃብቱ በብድርና ርዳታ ስም ይግባ እንጂ ለአገር ውስጥ ልማት ማሳለጫነት ከመዋል ይልቅ የቡድኑ ቀንደኛ አካላት ሃብቱን በቀኝ እጃቸው ተቀብለው በግራ እጃቸው እዛው በውጪዎቹ አገራት ባሉ ባንኮች እያከማቿቸው መቆየታቸውን የሚያሳይ ነው። እናም ብድርና ርዳታዎቹ ለአገር ሳይሆን ለግለሰብና ቡድን ሃብት ማካበቻነት የዋሉ፤ በአንጻሩ በስሙ ብድርና ድጋፍ የተገኘበት ሕዝብ እና መከረኛዋ አገር የልማቱ ሳይሆን የእዳው ባለቤት ሆነው መቅረታቸው መሰማቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
በተመሳሳይ፣ አንድም ሕወሓት ሁን ብሎ ከተረ ጂነት እንዳይላቀቅ የሚፈልገውን አካባቢና ሕዝብ በማበጀቱ፤ ሁለተኛም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የሚከሰቱ አደጋዎችን ተከትሎ በሚፈጠሩ ድርቅና ረሃቦች ምክንያት የሽብር ቡድኑ እንደ ወቅቱ መንግሥት አገርን ወክሎ ግብረ ሰናይ አካላት ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ ሲያቀርብ ኖሯል። ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ግጭትና ሌሎች ክስተቶችን ተከትሎም በየዘመናቱ በርካቶች የሰው እጅን የሚጠብቁበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ስለነበርም እነዚህ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሰው ልጆችን ለመርዳት ሲሉ ድጋፍ ሲያደርጉም ነበር።
ይሁን እንጂ እነዚህ የሰብዓዊ ድጋፎች በሚፈለገው ልክ ድጋፍ ፈላጊው ሕዝብጋ ሳይደርሱ የቡድኑን ፍላጎት መሰረት አድርገው ሲፈጸሙ ኖረዋል። ለምሳሌ፣ አስር ዓመት እየጠበቀ (በኋላም በየአምስትም፣ በየሁለትም ዓመታት) ሲከሰት የነበረው ድርቅ በርካቶችን ለከፋ ጉዳት ዳርጎ ነበር። ለአብነት በ2007 እና 2008 ዓ.ም አካባቢ የተፈጠረው ድርቅ በርካታ ሚሊዮኖችን ለአስቸኳይ ሰብዓዊ ርዳታ ዳርጎ ነበር። በዚህ ወቅት በርከት ያሉ ድጋፎች ከውጪም ከውስጥም ተሰባስበው እንደነበር ይታወቃል። ይህ ወቅት ደግሞ ሕወሓት/ኢህአዴግ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የጫጉላ ሽርሽሩ ላይ የነበረበት ወቅት ነበር። እናም በስማቸው የተለመነባቸው ሚሊዮኖች በረሃብ ሲንገበገቡ፤ በስማቸው የለመኑ ጥቂቶች ግን በተለያዩ ድርጅታዊ የጫጉላ ሽርሽር ውድ ድግሶች ላይ ውስኪ ይራጩ፤ ጮማ ይቆርጡ፤ ዳንኪራ ይረግጡ ነበር።
ዛሬም በሕወሓት መንደር እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ትናንት በደደቢት በረሃ ሸምቆ የ1977ቱን ድርቅ እንደ በለስ ቆጥሮ በትግራይ ሕዝብ ድጋፍ ለምኖ በርካታ ድጋፍ ያሰባሰበው፤ ነገር ግን በስሙ የለመነበት ሕዝብ በርሃብ ሲንገበገብና ሲረግፍ ቡድኑ የሃብት አቅሙን ሲያሳድግና የጦር መሳሪያ ሲሸምት የነበረበትን እውነት፤ ዛሬም የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ሰብዓዊ ችግር እንዲጋለጥ ዙሪያውን በጦር አጥሮ በመያዝ በስሙ የሚገባውን ድጋፍ ለራሱ እያዋለው መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።
ቀደም ሲል በተጠቀሰው ቃለ ምልልስ ላይ ሌተናል ጄኔራል ዮሐንስ የጠቀሱት እውነትም ይሄንኑ የሚያስረዳ ነው። ጄኔራሉ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት እንዳሉት፤ የሕወሓት ወንጀለኛ ቡድን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በትግራይ ህዝብ ላይ ሲሰራ የነበረውን ሴራ ከድል ማግስት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሲፈጽም ቆይቷል። ለውጡን ተከትሎም የበዛ ወንጀሉ እረፍት ስለነሳው ሸሽቶ ሕዝቡን በማታለል መቀሌ ገብቷል። መቀሌ ከገባ በኋላ ግን ሁለት ዓመት ሙሉ ለሕዝቡ የልማት ሥራ ከማከናወን ይልቅ ከ18 ዓመት በታች የሆናቸው ህጻናትን በመመልመል ልዩ ኃይል በማሰልጠን ህልውናውን የሚያቆይበትን መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል።
አሸባሪው ሕወሓት የትግራይ ሕዝብን ማስያዣ አድርጎ መለመንና ሃብት በማሰባሰብ የግል ፍላጎቱን የማሳካት ጉዞው በጫካ ሳለ አንድ ብሎ ያደገበት፤ በሥልጣን ዘመኑ ለ27 ዓመታት የዘለቀ፤ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ከተገፋ በኋላም ዛሬም ድረስ ይዞት የዘለቀው ሃቅ ነው። ቀደም ብለን ከጠቋቆምነው በትግል ዘመኑ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፈጸመው ግፍ እና በ27 ዓመታት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው ደባ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የትግራይ ሕዝብ ላይ በተለየ መልኩ 27 ዓመቱን ሙሉ ሲሰራ ኖሯል።
እነዚህ 27 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ኢኮኖሚው እንዳይጠነክር፤ ይባስ ብሎም የተመረጡ አካባቢዎች ምንም ሳይኖራቸው የሴፍቲኔት ተደጓሚ ሆነው የእሱው እጅ ጠባቂ እንዲሆኑ ነው የተፈረደባቸው። በዚህም በክልሉ የሕወሓት እንደራሴዎች (የአመራሮቹ ቤተሰቦችና የጥቅም ተጋሪነት) በስተቀር ሰፊው ሕዝብ ይሄ ነው የሚባል ተጠቃሚነት ሳይኖረው፤ ይልቁንም ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚልቀው የትግራይ ሕዝብ የሴፍቲኔት ጥገኛ ሆኖ ኖሯል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ለሕገ ወጥ ስደት በመዳረጋቸው፤ በርካቶች በየበረሃው አሸዋ በልቷቸው፤ በርካቶችም በየውቂያኖሱ ሰጥመው ቀርተዋል።
ይህ የሽብር ቡድኑ ሕዝብን እንደ ማስያዣ በመያዝ በሕዝብ ስም የመነገድ እኩይ ተግባር ውጤቱ እጅግ የከፋ እና ሰብዓዊ ስሜትን የሚፈታተን አሳዛኝ ነው። ሆኖም ይህ ለሕወሓት ቡድን ምንም አይደል። ምክንያቱም ሕልውናው የሚቆየው የትግራይ ሕዝብ ላይ የሚገለጥ ሰብዓዊ ቀውስ እና እሱን ተከትሎ የሚመጣ የቡድኑን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነገር ነው። ምክንያቱም፣ አሸባሪው ሕወሓት ለጥፋት ተፈጥሮ በጥፋት እድሜውን የገፋ ዛሬም ከነጥፋቱ እየኖረ ያለ ቡድን ነው፤ በዚህ ሁሉ ጉዞው ደግሞ ሰብዓዊ ቀውስ እያባባሰ የሰብዓዊ ርዳታዎችን እንደ ፍላጎት ማስፈጸሚያ አድርጎ ሲጠቀም የኖረ፤ ዛሬም በዚሁ ባሕሪው እየተገለጸ ያለ ነው።
ይህ ቡድን ከማዕከላዊው መንግሥት በሕዝብ ትግል ተገፍቶ ከወጣ በኋላ ወደ መቐለ ሄዶ በመመሸግ በትግራይ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው ግፍ ዳግም የትግል ወቅት ሴራውን የሚያስታውስ ነው። ምክንያቱም ቡድኑ ወደ መቐለ ከመሸገ በኋላ ሕዝቡን ከለላ ለማድረግ የተጠቀመበት “ትግራይን በቅርብ ሆነን ለማልማት መጣን” ከሚለው መሸንገያ፤ “ትግራይ ዙሪያዋን ጠላት ከብቧታል” እስከሚለው የጠላትነት ስዕል መፍጠሪያ የሃሰት ዲስኩሩ የሚያረጋግጠው ይሄንኑ ነው። የትግራይ ሕዝብ በሴፍቲኔት ተሸብቦ እንዳይናገር 27 ዓመታት መኖሩ ሳያንሰው፤ ላለፉት አራት ዓመታት አንዴ በጦርነት ስጋት ውስጥ፤ ሌላ ጊዜ በጦርነት ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል። አርሶ እንዳይበላ ሰላሙን ነስቶ፤ ድጋፍ እንዳያገኝ ዙሪያውን በጦር አጥሮ ተቆጣጥሮታል።
ይህ በህዝብ ላይ የሚፈጽመው እኩይ ተግባር ሕዝቡን ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እየዳረገው ይገኛል። ይሄን ደግሞ ቡድኑ የሚፈልገው የፖለቲካ ጉዳዩን ማሳኪያ ሁነኛ መሳሪያው ነው። የትግራይ ሕዝብ በጦርነት ስጋት ውስጥ ነው ብሎ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት፤ የትግራይ ሕዝብ ለከፋ የሰብዓዊ ችግር ተጋልጧል፤ ተርቧል፣ ሕክምና አጥቷል እያለ ዓለምአቀፍ ትኩረትን በመሳብ የቡድኑን ሕልውና ማቆያ የሚሆኑ አያሌ ድጋፎችን ማሰባሰቢያ መንገዱ ነው። ከጥቅምት 24 በኋላ በቡድኑ እና በክልሉ ህዝብ መካከል እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ለፖለቲካ ትፍር ሲባል ጦርነት ከፍቶ ተወጋሁ፤ እርዳታ እንዳይገባ ከልክሎ ሕዝብ ተራበ ማለት።
ለምሳሌ፣ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት መንግ ሥት መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ባስወጣ ማግስት በርካታ መጠባበቂያ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ነዳጅና ሌላም አስፈላጊ ነገሮችን ለሕዝቡ ጥቅም ሲል አስቀምጦ ነው። ቡድኑ ግን እነዚህን ለሕዝብ ሳይሆን ለራሱ አደረገ፤ አልሚ ምግቦችን ሳይቀር ለተዋጊ ኃይሎቹ ሲያከፋፍል፤ አመራሮቹን በውስኪ ሲያራጭና በየምሽቱ ሲያስጨፍር፤ የትግራይ ሕዝብ የረሃብን አስከፊ ገጽታ ዳግም እንዲያስተናግድ ፈርዶበት ነበር። ዛሬም የፌዴራሉ መንግሥት በብዙ ውጣ ውረድ ወደ ክልሉ ድጋፍ እንዲገባ እያደረገ ቢሆንም፤ ቡድኑ ድጋፎቹን ወደ ህዝብ ከማድረስ ይልቅ ለራሱና ለተከታዮቹ እያከማቸና እያከፋፈለ ስለመሆኑ ይነገራል።
ባስ ብሎም በሕዝብ ስም የሚሄድን ድጋፍ አከማ ችቶ ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ ስለመሆኑ በርካታ ምንጮች ይጠቁማሉ። በዚህም ሕዝብን በማስያዣነት ተጠቅሞ በመለመንም፤ በሕዝብ ስም የሚደርሱ የሰብዓዊ ድጋፎችንም ለራሱ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት በመጠቀምም የሚታወቀው ይህ ቡድን፤ ዛሬም የምግብ ድጋፎችን ሳይቀር ለተዋጊ መመልመያነት እየተጠቀመ ይገኛል። በዚህ እኩይ ሴራም የትግራይ ሕዝብ ለከፋ ችግር መጋለጡ፤ ለአስከፊ ስቃይ መታጨቱ ብዙዎችን እያሳሰበ ያለ እውነት ነው።
ይህን እውነት ደግሞ ለብዙዎች የሚጎመዝዝ ሃቅ ቢሆንም፤ ዛሬም የትግራይን ሕዝብ ከዚህ የችግር ወጥመድ ማውጣት፤ ስቃዩን መቀነስ የቻለ ኃይል የለም። ይልቁንም ከቡድኑ ጎን ቆሞ ችግሩን ለማባባስ የሚጣጣር፤ የመንግሥትን ጥረት ከመደገፍና ሕዝቡን ከማገዝ ይልቅ የሕወሓትን ሕልውና ለማስጠበቅ የሚተጋ በዝቶ ይታያል። ይህ ግን ሊሆን የማይገባው፤ የሕዝቡ ጩኸትና ጭንቀት ተደምጦ ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ እንደመሆኑ፤ በሕወሓት መንደር የሚታየው ሕዝብን እንደ ማስያዣ፣ ሰብዓዊ ርዳታን ለፍላጎት ማስፈጸሚያ የመጠቀም ጨዋታ በቃ ሊባል ይገባል።
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2014