እንሆ በኩረ እውነት..
ሀገር..ሀገር አለ..ይሄ ሀገረ ብርቁ፣
እኛም ሀገር አለን..የሚታይ በሩቁ።
ጥንታዊቷን አገሬን እንዲህ ነው የምገልጻት። ልክ አሁን ላይ ብዙዎቻችን ጓጉተንና ሽተን ልናያት እንደምንቋምጣት አሜሪካ፤ ጥንታዊቷም ኢትዮጵያ እንዲያ ነበረች። አፈሯንና፣ ታሪኳን፣ መልከዐ ምድሯንና መልካም ሕዝቧንም ናፍቀው ሊወዳጁን የሚሹ በርካቶች ነበሩ። ጥንት በእውነትና በፍትህ የቀደሙ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ሀሳብ የሚመክሩ፣ ስለአገራቸው ዘብ የቆሙ ብሩካን ነፍሶች ነበሩ። ከራሷ አልፋ አፍሪካን የፈጠረች፣ ከራሷ አልፋ ዓለምን የቀለመች ኢትዮጵያ የምትባል ፊተኛይት አገር ነበረችን። ይቺ አገር ዛሬ ምን ዓይነት ናት ላለ የምንመልሰው ብዙ መልስ አለን። አፍሪካን በጽናቷ አንድ ያደረገች፣ ጎረቤቶቿን በሰላሟ ያስታረቀች፣ ባህር ተሻግራ ቂመኞችን ያሸማገለች ኢትዮጵያ ዛሬ ምን ላይ ናት ላለን ብዙ መልሶች አለን።
አገር ከሰላም ውጪ ምንም መፈጠሪያ ስፍራ የለውም። አገር ለመፍጠር የሚሹ ሕዝቦች ሁሉ ከምንም በፊት ሰላም ሊያመጣ በሚችል ጉዳይ ላይ ሊግባቡ ይገባቸዋል። ሰላም መነሻውም መድረሻውም አገርና ሕዝብ ነው። በሰላም እጦት የሚከሰቱ ማናቸውም ችግሮች ሕዝብ ከመጉዳትና አገርን ከማውደም ባለፈ የሚፈጥሩት ጥቅም የለም። አሁን ላይ ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ሽብርና፣ ጦርነት፣ ለሰላም ቅድሚያ ካለመስጠት የመጣ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ሰላምን ስትዘምርና ለሰላም ስትተጋ የኖረች አገር ናት። ታሪክ እንደሚነግረን ከራሷ አልፋ ለብዙዎች የሰላም ተምሳሌት ሆና የኖረች አገር ናት። ዛሬ ላይ ያን ሰላም ማምጣት ለምን ከበደን ስል ራሴንም፣ መንግሥትንም፣ አንባቢዬንም እጠይቃለሁ። እርግጥ ነው በራስ ወዳድነት፣ በከሸፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲሁም ደግሞ ባልሆነና ባልተደረገ በውሸት ትርክት እየተመራን ለበርካታ ዘመናት ሰላም ስናጣ ኖረናል በጣም የሚገርመው ደግሞ እኚህ ነገሮች ዛሬም ድረስ የሰላማችን ጠንቅ ሆነው መኖራቸው ነው።
ከመከራችን ብዙ የተማርን ሕዝቦች ነን። በአሁኑ ሰዓት እንደ ሰላም፣ እንደ እርቅ የሚያስፈልገን ምንም ነገር የለም። ስለሆነም ተነጋግሮ መተማመንን የቀጣይ ፖለቲካችን፣ የቀጣይ ትውልዱ፣ የቀጣይ ሕይወታችን መርህ አድርገን በአዲስ ልብ አገራችንን ከስቃይ መታደግ ይኖርብናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ ሸር፣ በውሸት ድራማ ብዙ ነገሩን አጥቶ በድህነት ሲማቅቅ የኖረ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ቀን ያስፈልገዋል። ይህ ሕዝብ በመነጋገር ማሸነፍን ባህሉ አድርጎ እንዲኖር ፖለቲከኞቻችን በይቅርታ መተቃቀፍን መልመድ አለባቸው። አሁን ላይ አገር እያጠፋ፣ ትውልድ እያሰቃየ ያለው የፖለቲካው ምህዳር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትናንት እስከዛሬ አብሮ በመብላት፣ አብሮ በመጠጣት የኖረ ነው። አይደለም በፖለቲካ ሊጋጭ ቀርቶ፣ አይደለም በብሔርና በጎሳ ሊገፋፋ ቀርቶ፣ አይደለም በወንድሙ ላይ ሊጨክን ቀርቶ በተረት በሰማው ክፉ ወሬ እንባው የሚመጣ ለእንስሳ የሚራራ፣ ፈርሀ እግዚአብሔር ያለው ሕዝብ ነው። ፖለቲካው ግን አበላሸው፤ ንጹህ የባላገር ልቡን አሳደፈው።
የዝሆኖች ጥል መከራው ለሳሩ ነው፤ ዝሆኖች የሚራገጡት ሳሩ ላይ ቆመው ነው። ከትናንት እስከዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሹማምንቱን ጎድቶ አያውቅም የጎዳው የኢትዮጵያን ድሀ ሕዝብ ነው። በኑሮ ውድነቱ ብናየው እንኳን እያለቀሰና እየተራበ ያለው ድሀው ነው። እንደ አገር የሆነብንና እየሆነብን ያለው ሁሉ ከትናንት የተሻለ ዛሬን እንድናስብ ነውና በመነጋገር ሰላምን ማምጣት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ጊዜው ከመቼውም ጊዜ በላይ የምንነቃበት፣ የምንተባበርበት፣ በአንድ ሀሳብ አገር የምንገነባበት እንጂ የምንገፋፋበት አይደለም። እውነት እላችኋለሁ ብዙ ነገር የቀረብን ሕዝቦች ነን። ድህነቱ የማያሳስበው፣ ኋላ ቀርነቱ የማያስቆጨው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ይመስለኛል። ምክንያቱም በሰላም መንገድ ከድጥ ስንወጣ አንታይም፤ ሁሌም ከድጡ ወደ ማጡ የምንዳክር ነን። እስኪ ሮሮ ይብቃን፣ እስኪ ጦርነት ይብቃን፤ እስኪ በሰላምና በአንድነት ቀና እንበል። እስኪ ከፊታችን ያልደረስንበትን የሰላም መና እናስስ።
እኔ ሰላም ናፍቆኛል፤ በልጆቿ የተባበረ ክንድ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ስትታይ ናፍቆኛል። ለዚህ ሁሉ የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ። እናተስ? በሀሳባችን፣ በተግባራችን ለአገራችን በጎ ከሆንን አገራችንን ወደ ፊት የማናራምድበት ምንም ምክንያት የለም። ሁላችንም በብሔራዊ ምክክሩ ላይ በመሳተፍ፣ ለውጥ በማምጣት፣ የኢትዮጵያን የሰላም ጠንቆች ነቅሎ በመጣል ሂደት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ግዴታችንን መወጣት እንችላለን። እመኑኝ ካለ ሰላም ማሸነፍ አንችልም፤ የሚያሸንፉ ልቦች ሰላምን የሚያውቁ ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ የታሪክ፣ የባህል፣ የሥልጣኔ ቀደምት ናት። አገራችን ኢትዮጵያ የእውቀት፣ የጥበብና የግብረገብነት ሀብታም ናት። አገራችን ኢትዮጵያ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የብዙሀነት ፊተኛ ናት። ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ሰላም ርቆናል፤ ለምን? ዓለም የሌለው ብዙ ነገር ያለን ሕዝቦች ነን፤ ግን መተቃቀፍ አልቻልንም ለምን? ኋላ ቀርነት ያለበሰንን የራስ ወዳድነትና የአልሸነፍባይነትን ካባ አውልቀን በመጣል በምክንያታዊነትና ሰላምን መሠረት ባደረገ አመክንዮ ተነጋግረን መግባባት ይኖርብናል። ያለዛ እንደሁልጊዜአችን ከድጡ ወደማጡ ነን።
የዓለም ቀይ ዳማ መልክ በኢትዮጵያ አለላ ሰበዝ የተሰፋ ነው። የዓለም ስልጣኔ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ጥበብ ተደግፎ ነፍስ የዘራ ነው። ዓለም ማንን ትመስል ነበር ላለ ኢትዮጵያን የሚል መልስ ያገኛል። በዚህ ሁሉ የበረከት መትረፍረፍ ውስጥ በምንምነት መቆማችን ያሳዝነኛል። የአባቶቻችን እጆች ዓለምን ከሠሩና፣ የዓለምን አስደናቂ ቅርሶች ካነጹት ውስጥ ናቸው። አሁን ላይ እንደነዚያ ዓይነት እጆች ዓለም የላትም፤ እነዚያ እጆች ኢትዮጵያን የሠሩ፣ እኛን ያኮሩ ባለውለታ እጆች ናቸው። በዚህ ሁሉ የልዕልና ፊታውራሪ ውስጥ ግን ዛሬም ድረስ ተነጋግሮ መግባባት አልቻልንበትም። ዛሬም ድረስ ድሆች ነን። ሰው እንዴት በባህል፣ በታሪክ፣ በስልጣኔ ፊተኛ ሆኖ ድሀ ይሆናል? አገር እንዴት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሀብት ታድላ ድሀ ትባላለች? አብዛኞቻችን ኢትዮጵያ ለምን ድሀ አገር ሆነች ተብለን ብንጠየቅ የምንመልሳቸው በርካታ መልሶች ይኖራሉ። በጣም የሚገርመው ግን አንዳችንም የጥያቄውን መልስ እያወቅን አገራችንን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማውጣት ስንጥር አለመታየታችን ነው።
ከትናንት እስከዛሬ የኢትዮጵያን የድህነት ነቀርሳዎች እናውቃቸዋለን፤ ሆኖም አብረናቸው ተስማምተን ከመኖር ባለፈ ለነቀርሳዎቻችን መድፆኒት ስናበጅ ግን አይቼ አላውቅም። አንድ ሰው ከበሽታው ለመዳን መጀመሪያ የታመመው በሽታ ምን እንደሆነ ማወቅ አለበት። እኛም ለድህነት ያበቃንን፣ ለጦርነትና ለኋላቀርነት የዳረገንን በሽታችንን እያወቅን ለበሽታችን ተጨማሪ ህመም ከመሆን ባለፈ መፍትሄ ስናመጣ አልታየንም። አሁን ለበሽታችን መድኃኒት መፈለግ አለብን፤ ተነጋግረን በመግባባት ሰላም ማምጣት እንችላለን። በእርቅና በምክረ ሀሳብ በችግሮቻችን ላይ የበላይ መሆን ይቻለናል። በመገፋፋት ውስጥ ልዕልና የለም። በድህነት ውስጥ ክብርና ሞገስ የለም። ከትውልድ ወቀሳ እናመልጥ ዘንድ፣ የአገራችንን ይቅርታዋን እናገኝ ዘንድ በአዲስ አስተሳሰብ መቆም ይኖርብናል። እስከዛሬ ተጉዘንባቸው ካልጠቀሙን ልማዶችና አስተሳሰቦች መውጣት አለብን። ጊዜው የመቅደም ነው። በትናንት ጭንቅላት ዛሬን መኖር የማይቻልበት ዘመን ላይ ነን።
ሁላችንም ችግር ፈጣሪ ከመሆን ወጥተን መፍትሄ ፈጣሪ ወደ መሆን መጥተን የአገራችን የጋራ የትንሳኤ ችቦ ማብራት ይኖርብናል። ከእኛ ውጪ የእኛን ተስፋና ብርሀን የሚያበስር አካል የለም። እኛው ለእኛ በቂ..ከበቂም በላይ ነን። አገራችን ቤታችን እስከሆነች ድረስ በእያንዳንዳችን አስተሳሰብ ውስጥ ናት። አንዱ መልካም እያሰበ ሌላው መጥፎ በማሰብ የምትቆም አገር የለችንም። የናፈቅነውን ስልጣኔ፣ የናፈቅነውን ብልጽግና እናይ ዘንድ ሁላችንም በአንድ ልብ ለጋራ ጥቅም መሰለፍ ይኖርብናል። ከሁሉም በፊት ግን በመሀከላችን የተዘራውን፣ ተዘርቶም የበቀለውን የጥላቻና የመገፋፋት ነቀርሳ መነቀል አለበት። እኚህ ነቀርሳዎቻችን እስካልተወገዱ ድረስ የምንገነባው አገርና ትውልድ አይኖረንም። ተባብረን ወደ ኋላ ላስቀሩን የድህነት ነቀርሳዎቻችን መፍትሄ ካልሰጠን ገና ከዚህም የባሰ ይጠብቀናል።
አሁን ላይ ሁላችንም ልንረዳው የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ዘመኑ የሀሳብ ልዕልና የሚያይልበት ዘመን መሆኑ ነው። አሁን በተሻለ ሀሳብ የተሻለ ነገር የሚከወንበት ጊዜ ላይ ነን። ምርጥ ሀሳቦች የሚፈልቁበት፣ ለአገር የሚጨነቁ ትውልዶች የሚፈጠሩበት እጅግ ስልጡን ዘመን ላይ ነን። ቅሬታዎቻችንን በሀሳብ የበላይነት እየፈታን ለጋራ ጥቅም በጋራ የምንቆምበት የመጨረሻው ድንቅ ጊዜ ላይ ነን። ከዚህ ውጪ አገር ለመገንባት አማራጭ የለንም። ከሰላም ውጪ ሁሉንም አማራጮች ሞክረናል ግን አልተሳካልንም። ተነጋግሮ ከመግባባት ውጪ ሁሉንም ዓይነት ነገር ሞክረናል ግን እንደ አገርም እንደ ግለሰብም አላተረፍንም። አሁን በመመካከር ሰላምን፣ በሰላም አንድነትን፣ በአንድነት አገር የምንፈጥርበት ጊዜ ላይ ነን። ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ፣ ለሕዝቡና ለትውልዱ የሚጨነቅ ሁሉ ሊያደርገው የሚችለው ነገር በብሔራዊ ምክክሩ ላይ መሳተፍና ብሔራዊ ምክክሩ ፍሬ እንዲያፈራ መንገድ መጥረግ ነው።
ለምንድነው በሀሳብ ማሸነፍ ያቃተን? ለምንድነው በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ሰላም ማምጣት የተሳነን? መልሱን ልንገራችሁ..? መልሱ የአእምሮ ስልጣኔ ማጣት ነው። በየትኛውም መመዘኛ መዝኑት አንድ አገር ወይም ደግሞ አንድ ግለሰብ አወቀ፣ ሰለጠነ የሚባለው በዙሪያው ካሉት ጋር ተነጋግሮ መግባባት ሲችል ነው። ሰው ተነጋግሮ መግባባት ካልቻለ ገና ንቃተ ህሊና ላይ አልደረሰም ማለት ነው። የእኛንም የዘመናት የፖለቲካ ሽኩቻ፣ የሰላም እጦት፣ የመገፋፋት አባዜ በዚህ ልክ ነው የማየው። ሰላም ለማምጣት በአካል ሳይሆን በአእምሮ መበልጸግ አለብን..። ሰላም የሚመጣው በሰላም መንገድ እንጂ በጦርነት አይደለም። እናም እላለሁ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ የሆናችሁ ፖለቲከኞቻችን ከአካል ስልጣኔ ወጥታችሁ አእምሯዊ እሳቤን እንድታዳብሩና ወደሰላም እንድትመጡ አደራ እላለሁ።
ከእኛ አገር ውጪ ሌላው አገር በሀሳብ የሚዋጋ ነው። እኛ አገር ብቻ ነው በጦር መሣሪያ የምንዋጋው። ስናውቅ፣ በአእምሮ ስንሰለጥን በሀሳብ ነው የምንዋጋው። የሀሳብ ውጊያ ሞትና ጉስቁልና የለውም። ከሁሉ የተሻለ፣ ለአገርና ለትውልድ የሚጠቅም፣ ብዙሀነትን የተላበሰ፣ አንድ ሁነኛ የጋራ ሀሳብ የሚፈጥር ነው። እኛ አገር ሁሉም ሌላ ነው..። ከጦርነት በፊት ለሃሳብ፣ ለእርቅ፣ ለስምምነት የሚሆን ምንም አቅም የለንም። ብዙ ነገራችንን ካጣን ከጦርነት በኋላ ለንግግር የምንቀመጥ ነን። ይሄ አይገርምም ትላላችሁ? እንደ ዜጋ በአገሬ የፖለቲካ ሥርዓት ያላዘንኩበት ጊዜ የለም። ከሰው በፊት ተፈጥረን ከሰው ኋላ መቅረታችን ያናድደኛል። በቀን ሦስቴ መብላት አለመቻላችን ያሳስበኛል። ሁሌም መቼ ይሆን ወደ ተሻለ አስተሳሰብ ወደ ተሻለ አመለካከት የምንሻገረው ስል ራሴን እጠይቃለሁ። ሰላም የሚያመጣ ሀሳብ ያስፈልገናል። በነውጥ ሀሳብ ብዙ ከስረናል። በጥላቻ ሀሳብ ብዙ ነገር አጥተናል። ዛሬ ላይ በሁሉ ነገራቸው የምንቀናባቸው አገርና ሕዝቦች የልዩነት ነቀርሳቸውን ገድለው በሀሳብ የበላይነት የበለጸጉ ናቸው።
ምርጥ አገር የብዙ ምርጥ ሀሳቦች ውጤት ናት። ምርጥ ማህበረሰብም ከብዙ ምርጥ ሀሳቦች መካከል የሚገኝ ነው። ምርጥ ሀሳቦች ደግሞ ሁሌም መፈጠሪያቸው ሰላም ውስጥ ነው። ስለዚህ ምርጥ አገርና ምርጥ ትውልድ ለመፍጠር ምርጥ ሀሳቦች የሚፈጠሩበትን አስተማማኝ ሰላም መገንባት ይኖርብናል። ስልጣኔ እንዲያው ዝም ብሎ የሚገኝ ነገር አይደለም። የበለጸገ ሀሳብ ይፈልጋል። ልዩነቱን በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፈታ ስልጡን ማህበረሰብ ይሻል። በሚያግባባው እንጂ በሚለያየው ጉዳይ ላይ ጊዜ የማያጠፋ ትውልድ ይፈልጋል። ከቻልን የክፋት፣ የእኔነት አመለካከታችንን እንግደል። ከቻልን ወደ ኋላ የሚጎትተንን እርባና ቢስ ሀሳባችንን እናጽዳ። የአንተ መውደቅ የአንተ ብቻ አይደለም። የኔም ነው። የአንተ ኋላ መቅረት የአንተ ጉዳይ ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን። አገር የእኔና የአንተ አስተሳሰብ፣ ውህደት፣ ባህልና አብሮነት ውጤት ናት። የአንተ ኋላ መቅረት የማህበረሰቡ ኋላ መቅረት ነው። የአንተ ፊት መቅደምም እንደዚያው የማህበረሰቡ ከፍታ የማህበረሰቡ ስልጣኔ ነው። ለአገራችን የሚሆን መልካም ሀሳብ ሊኖረን ይገባል። ተያይዞ ለመቆም እንጂ ተያይዞ ለመውደቅ መሽቀዳደም የለብንም። በተባበረ ክንድ የኢትዮጵያን የኋላ ቀርነት ምንጮች እናድርቅ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም