መንግሥት ኬንያውያን ዶክተሮችን ለስልጠና ወደ ኩባ የሚልክበትን አሰራር እንዲያቆም የኬንያ ዶክተሮች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተቃውሟቸውን አሰሙ። ተቃውሞው የተሰማው ሰሞኑን ሃሚሲ አሊ ጁማ የተባለ ለስልጠና ወደ ኩባ የተላከ አንድ ኬንያዊ ወጣት ዶክተር ሞት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነው።
ዶክተር አሊ ጁማ በኬንያ መንግሥት ስፖንሰር አድራጊነት ባለፈው ዓመት ለስፔሻላይዜሽን /ለልዩ ህክምና/ ወደ ኩባ ከተላኩ ሃምሳ ወጣት የኬኒያ ዶክተሮች መካከል አንዱ ነው። በኩባ ሃቫና በህብረተሰብ ጤና ህክምና የድህረ ምረቃ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየውና በሰላሳዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረው ዶክተር አሊ ጁማ ባለፈው እሁድ መነሻው በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት ባረፈበት ሆቴል ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል። ይህን ተከትሎም የኬንያ ዶክተሮች በመንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
በሁለቱ ትልልቅ ወኪሎቻቸው አማካኝነት ማለትም በኬንያ ህክምና ማህበርና በኬንያ የህክምና ባለሙያዎች፣ ፋርማሲስቶችና የጥርስ ሃኪሞች ማህበር አማካኝነት ተቃውሟቸውን እያሰሙ የሚገኙት ኬኒያውያን ዶክተሮች በባልደረባቸው ሞት በእጅጉ ማዘናቸውንና ኩባ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኬንያውያን ዶክተሮች ደህንነት እያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የኬኒያ ህክምና ማህበር የዶክተር አሊ ጁማን ሞት አስመልክቶ ከትናንትና ወዲያ ባወጣው መግለጫ “ገና ብዙ ሊሰራ የሚችለው ወጣቱን ዶክተር ያለ እድሜው ማጣታችን በእጅጉ የሚያሳዝን ነው” ብሏል። “ባልደረቦቻችን ለስልጠና ተልከው ኩባ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ የራሳችን የመንግሥት ተወካዮች ጨምሮ በዚያ የነበረው አቀባበል ጥሩ እንዳልነበረና የኑሯቸው ሁኔታም ምቹ አለመሆኑን የሚገልጹ በርካታ ቅሬታዎችን ስንቀበል ቆይተናል” ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጃኩዊን ኪቱሉ፣ መንግሥት የግድያውን ሁኔታ በአስቸኳያ እንዲያጣራና የኬንያውያን ዶክተሮችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ አሳስበዋል። ለዚህም የኬንያ መንግሥት ዶክተሮችን ወደ ኩባ እየላከ ለማሰልጠን ከሃቫና መንግሥት ጋር የፈጸመውን ስምምነት እንዲሰርዝና ኬንያውያን ዶክተሮችን ወደ ኩባ መላኩን እንዲያቆም ጠይቀዋል።
የኬንያ የህክምና ባለሙያዎች፣ ፋርማ ሲስቶችና የጥርስ ሃኪሞች ማህበር ባወጣው መግለጫ በበኩሉ፤ ሟቹ ዶክተር አሊ ጁማ በአንድ ወቅት “የኬንያ መንግሥት ወደ ኩባ ተልከው በሰው ሃገር ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ኬንያውያን ዶክተሮች የሚያስፈልገውን ወጭ በአግባቡ እየሸፈነላቸው አይደለም ከነጭራሹም ትቶታል” ማለቱን አስታውሷል። ስለሆነም የኬንያ መንግሥት ዶክተሮችን ለስልጠና ወደ ኩባ መላኩን እንዲያቆምና በሃገር ውስጥ ማሰልጠን እንደሚገባው ማህበሩ ገልጿል።
በኬንያ መንግሥት ለስልጠና ተልከው ኩባ ውስጥ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ዶክተሮች በዚያ እየገጠማቸው ያለውን ችግር አስመልክቶ ከሁለት ሳምንት በፊት ለኬንያ ፓርላማ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል። ኬንያውያን ዶክተሮች በኩባ እንዲሰለጥኑ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ኬንያ ያለባትን የስፔሻሊስት ዶክተር እጥረት ለማቃለል ኩባውያን ስፔሻሊስት ዶክተሮችም ወደ ኬኒያ መጥተው እንዲሰሩ በሃገራቱ መካከል ስምምነት አለ። በስምምነቱ መሰረት የኬንያ መንግሥት ባለፈው ዓመት አንድ መቶ ኩባውያን ዶክተሮች አስገብቶ የነበረ ቢሆንም ኩባውያኑ ዶክተሮች ከኬንያውኑ የበለጠ እንክብካቤና ክፍያ ያገኛሉ በሚል በተመሳሳይ ከኬኒያውያን ዶክተሮች ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ይበል ካሳ