ጎርፍና ንፋስ የቀላቀለው ሳይኮሎን 2.6 ሚሊየን የሚሆኑ የሞዛንቢክ፣ ዙምባብዌ ና ማላዊ ዜጎችን ለከፍተኛ ቀውስ እንደዳረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ፡፡ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ከስድስት ቀን በፊት በሰዓት 187 ኪሎ ሜትር እየጋለበ በድንገት ያጥለቀለቃቸውን የሳይክሎን ተጠቂዎችን ለማትረፍ አሁን ድረስ የነፍስ ማዳን ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
እርዳታ አድራጊዎቹ እንደሚገልጹት ከጥቃቱ የተረፉት አብዛኛዎቹ የገጠራማ አካባቢ ሰዎች በዛፍ ላይ እና የቤቶች ጣራ ላይ በመውጣት እራሳቸውን ለማዳን ሞክረዋል ይላሉ፡፡ የሞዛንቢኩ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኒውሲ እስከ አሁን ቁጥራቸው አንድ ሺህ የሚጠጋ የሀገሪቱ ዜጎች የሳይክሎን ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸውም አሳውቀዋል፡፡
የቤይራ ከተማ የቀይ መስቀል አስተባባሪ ጃሚ ሌሱር ክስተቱ ያስከተለው ጉዳት በቅርብ ጊዜ በሞዛንቢክ ታሪክ ታይቶ እንደማይታወቅ የገለጹ ሲሆን በአካባቢው የሚገኙት ትልልቅ ወንዞች ችግሩን እንዳባባሱት አስረድተዋል፡፡ ጎርፉ የስድስት ሜትር ጥልቀት የነበረው ሲሆን መኖሪያ ቤቶችን፣ ዛፎችንና የኤሌክትሪክ ፖሎችንም ያጥለቀለቀ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የሞዛንቢክ መንግሥት ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡ የሀገሪቱ ዜጎች በሳይኮሎን ተጽዕኖ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ቢገልጽም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፉ ምግብ ፕሮግራም ግን በሞዛንቢክ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን፣ በማላዊ ዘጠኝ መቶ ሃያ ሺህ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳውቋል፡፡ ይህ ድንገተኛ ቀውስ በሰዓታት ውስጥ የአካባቢውን ነዋሪዎች የሰው እጅ እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡
የፑንጊ እና ቡዚ ወንዞች ከልክ በላይ ሞልተው ብዙ ማይልስ የሸፈነ ውቅያኖስ መፍጠራቸው ተጠቂዎችንም ሆነ የእርዳታ ሰራተኞችን ወደ ፈለጉበት እንዳይላወሱ አድርጓቸዋል፡፡ እድለኛ የሆኑት በሄሊኮፕተር እገዛ እየተደረገላቸው ሲሆን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀምም የነፍስ ማዳንና የእርዳታ ስራዎች እንደሚሰሩ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣኖች ተናግረዋል፡፡
የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ፋሀሚድ ሚለር ከቤይራ ከተማ ባስተላለፈችው ዘገባ በከተማ ውስጥ በዳርቻው ተተክለው የነበሩ ታላላቅ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ወድቀዋል፡፡ ምንም አይነት የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ሰዎች የድረሱልን ጥሪ ለማስተላለፍ እንኳን አልተቻላቸውም። በዚህም የትኞቹ አካባቢዎች አፋጣኝ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንኳን ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
በከተማዋ ውስጥ የሚገኘው ሆስፒታልም ጉዳት ስለደረሰበት አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡ በሶፋላ ክፍለ ሀገር የወደብ ከተማ በሆነችው ቤይራ በሰዓት 178 ኪሎ ሜትር የሚጋልበው ዝናብ የቀላቀለው ንፋስ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኛ የሆኑት ክርስቲያን ሊነድ ሜር ማንኛውም ለሰው ልጅ የሚያስፈልግ እርዳታ ሁሉ ቢያስፈልገንም በሚፈለገው መጠን ማግኘት ግን አልቻልንም፡፡
የአካባቢው ባልስልጣናት እንደሚናገሩት በሄሊኮፕተር ተዘዋውረን ለመቃኘት ስንሞክር ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ ነው። አብዛኛዎቹ ሰዎች እቤታቸው ጣራ ላይ ሰፍረው የእርዳታ ምልክት ያሳዩን ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሶስት እስከ አራት ቀናት በዚህ አይነት ሁኔታ ያሳለፉ በመሆናቸው ምግብም ሆነ ንጹህ ውኃ አላገኙም፡፡ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ያነጋገራት አንዲት እናት ሁኔታውን እንዲህ ታስረዳለች፡፡
‹‹ከተማችን በድንገተኛው የሳይክሎን አደጋ ስትመታ እኔና ቤተሰቦቼ የልጄን የልደት በዓል ለማክበር ቤት ውስጥ ነበርን፡፡ ዓይናችን እያየ ጎርፉ አስፋልቱን አጥለቀለቀው፤ ከዛም ቤቶችን መዋጥ ጀመረ፤ ክስተቱ አንዳች የጦርነት ወረራ እንደተፈጸመ አይነት የሚዘገንን ነበር፤ ህጻናት ያለቅሳሉ፣ ሰዎች ይጮሃሉ አሁን በቤይራ ቤት አልባ፣ ቤተሰብ አልባ የሆኑ ሰዎችን ታገኛለህ፡፡ ምግብ የለም፤ መኝታም የለም፤ እኔ እራሴ ከዛን ቀን ጀምሮ አልተኛሁም ›› ትላለች፡፡
ከዚህ በፊት በቀጣናው ከተከሰቱት መሰል አደጋዎች እንደ አሁኑ የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ የአካባቢው ባለስልጣናት ይናገራሉ፡፡ የሞዛንቢክ ፕሬዚዳንት ፈሊፔ ኒዩሲ ከ1 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ዜጎች በሳይክሎን መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡ አስከ አሁን የጉዳቱ መጠን በውል ያልታወቀ እንደሆነና የሟቾችና የስደተኞቹ ቁጥርም እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል እየተገመተ ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ኢያሱ መሰለ