ኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የቅርስ ሃብቶች በስፋት ከሚገኝባቸው ቀዳሚ አገራት ተርታ ትመደባለች። ይሁን እንጂ እነዚህን ሃብቶች በሚፈለገው መጠን የማስተዋወቅ፣ የማልማትና ከሃብቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ አቅም ግን አሁንም ድረስ እንዳልጎለበተ ይታመናል። ይህን ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሠራ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልፅ ይሰማል።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ ያለፈው የክርስቶስ ልደት (ገና) በዓልን ምክንያት በማድረግ መላው ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲገቡና ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሃብቶችን እንዲጎበኙ፣ ሃገራቸውን እንዲያውቅና በተለያዩ አማራጮች ድጋፍ እንዲያበረክቱ በመንግሥት ጥሪ ተደርጎ ነበር። በዚያ መሠረት ገናን በላሊበላ፤ ጥምቀት በጎንደር በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል። ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንም ሃገራቸውን አውቀው ለቀሪው ዓለም እንዲያስተዋውቁ እድል የፈጠረ ነበር።
በዚህ በያዝነው ወር ደግሞ “ከኢድ እስከ ኢድ” በሚል መርሐ ግብር በውጪ ሃገራት የሚገኙ ዲያስፖራ የእስልምና እምነት ተከታዮች በተመሳሳይ የረመዳን ፆምና ፍቺን ተከትሎ ወደ ሃገራቸው እንዲገቡና የኢትዮጵያን የባህልና ቱሪዝም ሃብቶች እንዲጎበኙ፣ በታላቁ አፍጥር ሥነሥርዓት ላይ እንዲታደሙ፣ “መረዳዳት፣አንድነትና ኅብረትን” በሚያጠናክሩ መርሐ ግብሮች እንዲሳተፉ እየተደረገ ይገኛል። ከዚህ መርሐ ግብር መካከል በሐረሪ ክልል በልዩ ሁኔታ የሚከበረው የሹዋሊድ በዓል ይገኝበታል።
በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት “ከኢድ እስከ ኢድ” በሚል መርሐ ግብር ዝግጅት በተካሄደበት ወቅት የባህል ፌስቲቫል ተካሂዶ ነበር። የዝግጅት ክፍላችንም ይህን ታላቅ ሃገራዊ ጥሪ በማስመልከት የምስራቁ ክፍል ባህላዊ ሃብቶች በተለይ ደግሞ የሐረሪ ብሔረሰብ አልባሳት፣ ተወዳጅ ምግቦችና መጠጦችና ጌጣጌጦችን ልናስተዋውቃችሁ ወደናል። ይህን ባህላዊ ሃብትም የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብደሸ ገለፃ አድርገውልናል።
የሐረሪ ብሄረሰብ መገለጫዎች
የሐረሪ ብሔረሰብ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች አሉት። ከባህላዊ ምግቦች መካከል ከማሽላና ከበቆሎ እንዲሁም ከስንዴ ዱቄት የሚዘጋጁ ኡኻት እና ጡፍጡፍ በመባል የሚታወቁ እንጀራዎች ይጠቀሳሉ። ማባያ ወጦችን በተመለከተ ሒልበት መረኽ በተለምዶ የአብሽ ወጥ እየተባለ የሚጠራው አብዛኛውን ጊዜ በሐረሪዎች ቤት የማይጠፋ ነው። ይህ የወጥ ዓይነት በኡኻት ተፈትፍቶ የሚበላ ሲሆን ለትልልቅ እንግዶች ፣በበዓላትና በሠርግ ጊዜ በቀዳሚነት ከሚቀርቡ የምግብ አይነቶች የሚጠቀስ ነው። ሌላው ‹‹አጥ መረኽ ››ከፍተኛ ክብር ለሚሰጣቸው እንግዶች የሚዘጋጅ የሒልበት መረኽ አይነት ወጥ ነው። አጥ መረኽ በአዘገጃጀቱ ከሒልበት መረኽ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ በግብዓት ደረጃ ቅልጥም ተሰባብሮ ከነመቅኔው ይጨመርበታል። የተመረጡ የሥጋ ክፍሎች እንደምላስ እና ሰንበር እንዲሁም ድንች ሳይላጥ የሚጨመር በመሆኑ ይለያል። ይህ የወጥ አይነት የተለየ ጣዕም ያለው ተወዳጅ የሐረሪዎች ምግብ ነው። አቅሌል መረኽ ከሥጋ የሚዘጋጅ ቀይ የጥብስ ወጥ ሲሆን በኡኻትና ጡፍጡፍ እንዲሁም ከሩዝ ጋር ይበላል። አቅሌል መረኽ የሐረሪዎች የዘወትር ምግብ ቢሆንም በሠርግ እና በበዓላት ወቅትም ይዘጋጃል። ዱባ መረኽ ከዱባ የሚዘጋጅ ወጥ ሲሆን በኡኻት የሚበላ ነው። ሳፍ መረኽ ከሥጋ የሚዘጋጅ ወጥ ሲሆን በኡኻት ይበላል። በበዓላት እና በሠርግ ወቅት እንዲሁም ለእንግዶች ይቀርባል። ከባብ መረኽ ከተፈጨ ሥጋና እንቁላል በወጥ መልክ የሚዘጋጅ ነው። በበዓላት እና በሠርግ ወቅት ለመስተንግዶ ከሚቀርቡ የሐረሪዎች ባህላዊ ምግብ መካከል ተጠቃሽ ነው።
ዙሑቅ :- የስንዴ ዱቄት ቢጫ ማቅለሚያ (ሲቆ) ተጨምሮበት ከተቦካ በኋላ በስሱ በምጣድ የሚጋገር የቂጣ አይነት ሲሆን በተቀመመ ወጥ ተለቅልቆ ይዘጋጃል።
ወቃሊም:- የተከተፈ ሥጋ በተለያዩ ቅመማ ቅመምና ማጣፈጫዎች ታሽቶ በደንብ ታጥቦና ተዘጋጅቶ በደረቀ የበሬ አንጀት ውስጥ አስገብቶ ከተቋጠረ በኋላ በጭስ እና በእሳት ወላፈን እንዲበስል ወይም እንዲደርቅ በማድረግ የሚዘጋጅ ነው። ይህ ባህላዊ ምግብ እንደ ቋንጣ ተሰቅሎ የሚቀመጥ እና ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል የምግብ አይነት ነው፤
ሑል መረኽ:- ከሀበሻ ጎመን የሚዘጋጅ ወጥ ሲሆን በኡኻት ወይም ጡፍጡፍ ይበላል።
ሚጣድ ጥብስ:- የተከተፈ ሥጋ በምጣድ በመጥበስ የሚዘጋጅ ነው።
ጣፋጭ ምግቦች (መሸባብር)
ሐረሪዎች ከተጠቀሱት ባህላዊ ምግቦች በተጨማሪ ከሰሊጥ ፣ ከስንዴ ዱቄት፣ ከሽምብራ ዱቄት፣ ከተለያዩ ማጣፈጫዎችና ቅመሞች እንዲሁም ከማር እና ከስኳር ጣፋጭ ብስኩቶችን ያዘጋጃሉ። እነዚህ ምግቦች ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉና በማንኛውም የሐረሪ ቤት የማይጠፉ ሲሆኑ፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ለመመገብ አመቺ ናቸው።በተለይም እንግዳ ሲመጣ አዲስ ምግብ ማዘጋጀት ሳያስፈልግ ለማስተናገጃነት ይቀርባሉ። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ጣፋጭ ብስኩቶች የሚከተሉት ናቸው።
ሙጠበቅ-ተፈትጎ የተቆላ ሰሊጥ በቀለጠ ማር ትኩሱን ተድቦልቡሎ የሚዘጋጅ ጣፋጭ ምግብ ነው።
ሰበዘይነባ :- ስንዴ ዱቄት ላይ ስኳር ፣ ጥቁር አዝሙድ ፣ ቅቤ ተቀላቅሎ ትንሽ ውኃ ተጨምሮበት ከታሸ በኋላ በትንሽ በትንሹ እየተቆነጠረ በስፌት (አፉፍቱ) ቅርጽ ወጥቶለት በዘይት ይጠበሳል። ጣፋጭ ብስኩት ነው።
ቡንቱር:- ስንዴ ዱቄት ላይ ትንሽ ስኳር ፣ ጥቁር አዝሙድ ፣ ቅቤ ተቀላቅሎ ትንሽ ውኃ ተጨምሮበት ከታሸ በኋላ በአነስተኛ የሎሚ መጠን እንደ ዳቦ ቆሎ እየተድበለበለ በዘይት ይጠበሳል። ከዚያም በማር ተለውሶ ይቀርባል። ቡንቱር በረመዷን የጾም ወር ከወንድ ቤተሰብ ለታጨች ልጃገረድ ቤተሰብ ጫት ሲላክ በምላሹ ከሴት ቤተሰብ ተዘጋጅቶ የሚላክ ነው። ቡንቱር ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል ጣፋጭ ብስኩት ነው።
ባጃያ:- ሽርክት የሽምብራ ዱቄት ለተወሰነ ሰዓት ውኃ ውስጥ ከተዘፈዘፈ በኋላ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት ፣ ባሃሮ ፣ ቃሪያ ፣ ከሞን ፣ ጨው ተጨምሮበት በትንንሹ እየተድቦለቦለ በዘይት ተጠብሶ የሚዘጋጅ ስኳርነት የሌለው ብስኩት ነው።
ኹረይባ :- ነጭ ዱቄት በዘይት፣ ሄል፣ ቀረፋ እና የተፈጨ ስኳር ከታሸ በኋላ በቅርጽ ማውጫ ተቆራርጦ በባትራ ይጠበሳል። ሙሉ በሙሉ የኩኪስ አይነት ባህሪ ያለው ጣፋጭ ብስኩት ነው።
ባህላዊ መጠጦች
ሐረሪዎች ከአኗኗራቸው፣ ከአመጋገባቸው፣ ከሥራ ባህል እና እምነታቸው ጋር የተያያዙ የተለያዩ ባህላዊ መጠጦች አሏቸው። እነዚህ መጠጦች በማንኛውም ሰዓት አሊያም በዓላት እና ሠርግን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ክንዋኔዎችና ሥነ-ሥርዓቶች የሚዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ። በአጠቃላይ መጠጦቹ ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸው የወተት፣ የማር፣ የፍራፍሬ፣ የቡና እና የመሳሰሉት ውጤቶች ናቸው። የሻይ እና የቡና ባህሪ ያላቸው ትኩስ መጠጦች አሊያም በቀዝቃዛ የሚጠጡ የለስላሳ አይነት መጠጦች ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ።
ትኩስ መጠጦች- ሐሸር ቃሕዋ፡- ከቡና ጀንፈል ላይ ውኃ፣ ሻይ ቅመም እና ትንሽ ጨው ተጨምሮበት ለሠርግ፣ ለበዓላት እና ለእንግዳ የሚዘጋጅ እንዲሁም ዘወትር የሚዘጋጅ ባህላዊ መጠጥ ነው።
ቁጢ ቃሕዋ፡- ከቡና ቅጠል የሚዘጋጅ የሻይ አይነት ነው። እንደ ሐሸር ቀሕዋ ሁሉ ውኃ፣ የሻይ ቅመም እና ጨው ተጨምሮበት ይጠጣል። የመጠጫ እቃዎቹም ሆነ አቀራረቡ ከሐሸር ቀሕዋ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ዱስ ቃሕዋ፡- በማር ተብጥብጦ የሚዘጋጅ ሻይ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ለእንግዳ የሚቀርብ ነው።
ቀዝቃዛ መጠጦች- ብርዝ፡- ማር በውኃ በመበጥበጥ የሚዘጋጅ ባህላዊ መጠጥ ነው። ከተዘጋጀ በኋላ ከቆየ ስለሚፈላና የአልኮልነት ባህሪ ስለሚይዝ ማሩ እንደተበጠበጠ ወዲያውኑ ይጠጣል። ሌላው ሸርባት፡- የተጨመቀ ሎሚ ውኃ፣ ስኳር፣ ሄልና ሌሎች ቅመማ ቅመሞች ተጨምረውበት እንዲሁም ዕርድ ወይም ሌላ ማቅለሚያ ከተደረገበት በኋላ ይዘጋጃል። ይህ ባህላዊ መጠጥ ለመድኃኒትነት ሲወሰድ ወዲያውኑ እንደተዘጋጀ ይጠጣል። የሐረሪ ሴቶች የተለመደ መጠጥ ከሆኑት መካከል የሎሚ ጭማቂ ላይ ውኃና ስኳር ተጨምሮበት የሚዘጋጅ መጠጥ ነው። ዱስ ሚይ፡- ማር እና ስኳር በውኃ ተበጥብጦ ቅመማ ቅመም ተጨምሮበት የሚዘጋጅና ዘይት የሚመስል መልክ ያለውና በሠርግ ወቅት ከሴቷ ሙሽራ ቤት ወደ ወንዱ ሙሽራ ቤት የሚወሰድ ባህላዊ መጠጥ ነው። እነዚህ የተጠቀሱ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በአብዛኛው እንደተገለጸው በበዓላትና በተለያዩ ማኅበራዊ ክንዋኔዎችና ሥነ-ሥርዓቶች ወቅት የሚጠቀሙባቸው ቢሆንም እንደአስፈላጊነቱ ለዘወትር አገልግሎት ይውላሉ።
አልባሳትና ጌጣጌጥ
የሐረሪ ብሔረሰብ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ የወንዶችና የሴቶች ባህላዊ አልባሳት፣ የአጊያጌጥ ሥርዓት አለው። አለባበሱም ሆነ አጊያጌጡ ዕድሜንና የዕድሜ ሽግግርን መሠረት ያደረገ ነው። ወንዶች ልጆች እስከ ሰባት ዓመት የዕድሜ ክልል የሚለብሱት ቆሎ (ቀሚስ የመሰለ ልብስ) ነው። ከዚህ ዕድሜ በኋላ ‹‹የእስላም ወይም ገናፊ የሚባል ነጭ ሱሪ እና እንግሊዝ ቅድ የሚባሉ ሱሪዎችን ይለብሳሉ። እያደጉ ሲሄዱ ጉዱር ቀሚስ (ነጭ ጀለቢያ) ለብሰው ከላዩ ላይ ሰደርያ (ኮት) ይደርባሉ። በራሳቸውም ላይ ኢማመት ወይም ጥምጣም ይጠመጥማሉ። በባህሉ መሠረት እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሙሉ ሰው ሆነዋል ማለት ነው። ሌላው ከአልባሳት የሚጠቀሰው ጌይ ከሎይታ (የሐረሪ ኮፍያ) ነው። በብሔረሰቡ የሚታወቁ የተለያዩ የኮፍያ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፣ በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ጌይ ከሎይታ አንዱ ነው። ጌይ ከሎይታ የከተማ ኮፊያ ማለት ሲሆን በአሠራሩ ነጭ የሚበዛበት ሆኖ በማንኛውም ጊዜ የሚደረግ ነው።
ሌላኛው አሩዝ ከሎይታ የሚባለው ነው። አሩዝ ከሎይታ የሐረሪዎች ባህላዊ ኮፍያ በመባል ይታወቃል። ኮፍያው አብዛኛው መደብ ነጭ ሆኖ በተለያየ ቀለም ባለው ክር በዲዛይን የተጠለፈበት ነው። ይህ ኮፍያ የሙሽሮች ኮፍያ ተብሎ ይታወቃል። በሰርግ ጊዜ ሙሽሮችና ሙዜዎች ይደምቁበታል።
የሴቶች አልባሳትና አለባበስን በተመለከተ ከወንዶቹ አንጻር ስናየው በተለያየ ኅብረ ቀለማት ያሸበረቀና ማራኪ ነው ማለት ይቻላል። ከአለባበስ አንጻር ሴቶች በወጣትነት ዕድሜያቸው ጌይ ገናፊ የተባለ ባህላዊ ሱሪ ይለብሳሉ። ይህ ባህላዊ ሱሪ ከስር ጠባብ ሆኖ ከላይ ሰፋ ተደርጎ የሚዘጋጅ ነው። ሌላው ከጌይ ገናፊ በላይ የሚለበስ ቀሚስ አጥላስ ይባላል። ይህን ልብስ የሚለብሱት ሙሽሮች፣ በቅርብ ያገባች ‹ሐታም› የምትባል የሐረሪ ሴትና አልፎ አልፎ የብሔረሰቡ እናቶች ናቸው። በእድሜ የገፉ እናቶች ሺአሽቲ ሸለል የሚባለውን ባለ ጥቁር ቀለም ልብስም ይለብሳሉ።
ጠይ እራዝ፡- የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም ጥቁር ልብስ ማለት ነው። ነገር ግን ሁሉም ጥቁር ቀለም ያለው ልብስ በዚህ ስያሜ አይጠራም። የ“ጠይ ኢራዝ” የራሱ ዲዛይን ያለው ባህላዊ ልብስ ነው። ይህን ልብስ የሚለብሱት ያገቡ እና የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ እናቶች ናቸው። ጠይ እራዝ ከፊትና ከኋላ (በሁለት መልክ) ተገልብጦ ሊለበስ የሚችል በሁለት ዓይነት ቀለም የሚሰራ ቀሚስ ነው። ጠይ እራዝ ከአንዱ በኩል ጥቁር ሆኖ በሌላኛው ደግሞ ከላይ ቀይ ሆኖ ከታች ጥቁር የሆነና በጥልፍ ስራ ያጌጠና የተዋበ ነው። የሐረሪ ሴቶች ወደሰርግ ቦታ ሲሄዱ ከላይ ቀይ ከታች ጥቁር በሆነው በኩል ለብሰው ይሄዳሉ። ይህንን ቀሚስ እንደለበሱ በመንገድ ላይ እንደአጋጣሚ ለቅሶ ቢሰሙ ልብስ ለመቀየር ወደቤት አይመለሱም። ያንኑ የለበሱትን ልብስ በጥቁሩ በኩል ገልብጠው ለቅሶው ቦታ ይደርሳሉ።
ከጌጣጌጥ አኳያ የሐረሪ ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ የተለያዩ ጌጣጌጦች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ወቅሪ ሲሆን የሚሠራው ከብር ነው። ወቅሪ ከላዩ ላይ የተለያዩ ዲዛይኖች የሚደረግበት አሠራሩ እንደ ሀብል አንገት ላይ ተንጠልጣይ ጌጥ ነው። ጌጡ ደረት እላይ የሚቀመጥ በአንድ በኩል የሚከፈትና የሚዘጋ ክዳን እንዲኖረው ተደርጎ የተሠራ ስለሆነ ውስጡ ለተለያዩ መኳኳያዎች መሀረብንም ጭምር ለመያዝ ያገለግላል። ወቅሪን ልጃገረዶች ካህፋያ የሚባል ቁርዓን ሲያጠናቅቁ ያደርጉታል። በቅርቡ ያገባች ሴት (ሐታም) እስከምትወልድ ድረስ ታጌጥበታለች። ከዚህ በተጨማሪም ሠርግ ቤት ሲሄዱ ያጌጡበታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም