አዲስአበባ፡- የኦሮሚያ የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ለምርት ዘመኑ የግብአት አቅርቦት እና የአርሶአደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ። ዝግጅቱ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የግብአት አቅርቦት የተደራሽነት ችግርን ይቀርፋል ተብሏል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በክልሉ ባለፈው የምርት ዘመን ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ ፣ፀረ-አረምና የተለያዩ መድኃኒቶችና ሌሎች የግብርና ግብአቶች በተሟላ ሁኔታ ለክልሉ አርሶአደሮች አልቀረቡም። ቢሮው ችግሩ በሁሉም አካባቢዎች በእኩል ስርጭት አለመከናወኑን በጥናት ለይቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ዳባ ገለፃ በጥናት የተለዩ ክፍተቶችን በመለየት ችግሩ እንዳይደገም ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት ተደርጓል። ዝግጅቱ በተለይ ዝናብ ሲዘንብ ተደራሽነቱ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት አስቀድሞ እንደሚሰራጭ አስታውቀዋል።
የአርሶአደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማሳ ደግ አንጻርም ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ትኩረት መሰጠቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣በተለይም ከመስኖ ልማት ጋር የተያያዙ ፕሮክጀክቶችን ለመተግበር አቅጣጫ ተቀምጧል። አርሶአደሩ የእርሻ ሥራውን በኮምባይነርና በትራክተር እን ዲያከናውንም ቀድመው በተጀመሩበት አካባቢ ያለውን ተሞክሮ በማስፋት የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በሚገኙ ሰፋፊ ቦታዎች ይከናወኑ የነበሩ የበቆሎ ዘር የማዳቀል ተግባር በአካባቢው በተከሰተው የጸጥታ ችግር የተዳቀለ የበቆሎ ዘር ከማሳ ላይ ሳይለቀም የቀረና በተወሰነ ደረጃም የተበላሸ መኖሩ አስታውሰው፣ ችግሩ በባለሙያ ከታየ በኋላም ሌሎች አማራጮች እንደሚወሰዱ አመልክተዋል። ተግዳሮት የሆነውን በቆሎን የሚያጠቃውን ‹‹የአሜሪካ መጤ ትልም›› 70 በመቶ በህብረተሰብ ተሳትፎ፤ ቀሪውን ደግሞ በመድኃኒት በመከላከል የተጠናከራ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አርሶአደሩን የመደገፍ ሥራ መጠናከር እንዳ ለበት የጠቆሙት አቶ ዳባ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መሆኑን አመልክተዋል። በ2010 የምርት ዘመን 51 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን፣ በ2011 የምርት ዘመን ደግሞ አጠቃላይ ውጤቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ይፋ የሚያደርገው ቢሆንም በክልሉ መረጃ መሰረት ግን 171 ኩንታል መገኘቱን ገልጸዋል። ውጤቱ አበረታች ቢሆንም የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ የግብርና ሥራውን በማዘመን ላይ መሰራት እንዳለበት አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ለምለም መንግሥቱ