የዛሬው መንደርደሪያ ታሪካችን የአንድ ግለሰብ እውነተኛ ታሪክ ነው። ከጀርባው ተወግቶ ወደ ጎዳና የወጣ የሰባዎቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ምሩቅ። ሰዎች ፍትህን አጉድለው ከጀርባው የወጉት ሆኖ ራሱን በመቁጠር ከራሱ ጋር ብቻ ለመኖር ወስኖ ከተደላደለ ቤቱ በመውጣት ብዙ ኪሎሜትሮችን አቆራርጦ ዱከም መስመር ላይ የጎዳና ተወዳዳሪ ለመሆን የወሰነ አባት።
እውነት በአደባባይ ተክዳ እውነት ያለው ሰው ተሸናፊ ተብሎ ተቆጥሮ፤ አብረውት እንደሆኑ የገለጹ ግለሰቦች አይናቸውን በጨው አጥበው ሌላ ሰው ሆነው ሲያገኝ፤ እውነቴን አይክዱም ያላቸው ፈጽሞውኑ እንደማያውቁት ሲሆኑ፤ ለፈጣሪ ቃል ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ፈጽሞውኑ አላውቅህም ብለው እንደ ጴጥሮስ ሲክዱት፤ ብቻውን ይዞት ለቆመለት እውነት የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል ወደፊት በተራመደ ጊዜ ብቻውን መሆኑን የተረዳ ሰው ከጀርባ በመወጋት ውስጥ የተሞላው ልቡ የጎዳና ተዳዳሪ ኢንጂነር አደረገው። ስሜቱን ልቅም ባለእንግሊዝኛ ጽፎ ከሚኖርበት የመንገድ ዳር የላስቲክ ቤት ውስጥ በጥንቃቄ አስቀመጠ አንድ ቀን የእውነት ቀን ሲመጣ ሁሉንም እንደሚያወራው አምኖ የማያውቀውን አንድ ቀን እንዲሁ አሻግሮ የሚጠብቅ ግለሰብ። ያቺ ቀን ደርሳ «እንዴት ወደጎዳና ወጣህ? የሚሉኝ ሲመጡ አንብላቸዋለሁ» ብሎ እውነታውን የከተበበትን ወረቀት በጥንቃቄ ያስቀመጠ።
ከዕለታት አንድ ቀን ሰብሰብ ብለው ለሚስዮናዊ አገልግሎት ወደ ዱከም ቢሾፍቱ ያመሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከእዚህ ሰው የጎዳና ጎጆ ላይ ደረሱ። ተማሪዎችም ስለ እውነት አወሩ፤ «ዛሬ መንገድ ላይ ቢሆኑም ነገ ከእዚህ ይወጣሉ፤ የሚያስፈልገው ከፈጣሪ ጋር መታረቅ ነው» ብለው መልዕክታቸውን አደረሱ። የእኒህ አባት የመንገድ ዳር ምሁር ምላሽ የተደበቀውን ደብዳቤ አውጥቶ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ ማንበብ ነበር። ደብዳቤው ወጥቶም ተነበበ፤ ከተማሪዎቹም ጋር እየተላቀሱ ከጀርባቸው የመወጋታቸውን ታሪክ ተረኩ። ግለሰቡን ከጎዳና ላይ ለማንሳት ተማሪዎቹ ተንቀሳቀሱ። የግለሰቡን ገላ በማጠጥ፤ ንጹህ ልብስም በማልበስ አዲስ ምዕራፍ ወደፊት ይራመዱ ዘንድ ተማሪዎቹ አበረታቷቸው። እርሳቸውም ከጀርባ በመወጋት ወደ አደባባይ ያወጣቸውንና የጎዳና ተዳዳሪ ያደረጋቸውን ሽሽት ሊያቆሙ ወሰኑ። እውነትን ይዘው ሰዎችን በፍቅር ወደ እውነት ለመመለስ ምድር ከጀርባ ወጊዎች የሞሉባት በመሆኑ ለእነርሱ ቦታውን ለቆ መቀመጥ ውጤት አልባ ተሸናፊነት መሆኑን አምነው ተነሱ። ጉዞቸውም ከጀርባ ተወግቶ ሳለ እንዴት ሕይወትን በጤናማነት መምራት ይቻላል የሚለውን ለመመለስ ሆነ። ረጅሙን ታሪክ ለመንደርደሪያ ያህል እንዲህ ከተመለከትን ወደ ቀጣዩ እንለፍ።
ዛሬ በጎዳናዎቻችን ላይ ወድቀው ሃሩርና ብርዱ የሚፈራረቅባቸው መካከል ስንቶቹ ከጀርባቸው የተወጉ ስለመሆኑ ለማሰብ እንሞክር። እንደ ቤተሰብ በአጠቃላይ እንደ ማህበረሰብ ስንኖር እንዴት በመወጋጋት ውስጥ እንደምንኖር ምንያህል እንደሚያሳየን እናሰላስል። ወደ አደባባይ ያልወጡ በየጎዳናዋ የታፈኑ ድምጾች ምንያህል ሊሆኑ እንደሚችሉ እንዲሁ እናስብ።
አንባቢ ሆይ እውነትን ፊትለፊት ተነጋግሮ ነገሮችን ወደ ትክክለኛው መስመር ማምጣት የመቻል አቅም በሌለበት ሁኔታ አጋጣሚው ያመቻቸው ሰዎች ያሉት ነገር እውነት ይመስልና ንጹሃን ሰለባ ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለምና በአንተ ደርሶ ከሆነ በርታ። መተማመንን ሰርስሮ ጥሎ እየኖርን እንዳልኖርን የሚያደርግ ነውና። ከእሴቶች መካከል ታላቁን እሴት የሚመታ ታላቅ ህመም።
መተማመን – ታላቁ እሴት
አንድ ሰው ብቻውን ሊሠራ የሚችለው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ምላሹ ምንም የሚል ነው። በዚህ ዘመን አንድ ሰው ብቻውን ሊሠራ የሚችለው ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር በአብሮነት የሚሠራ ነውና። ሰዎች አብረው ሆነው ያላቸውን ነገር አብረው አድርገው የሚሠሩት ነገር ብዙ ነው ሳይሆን ሁሉም ነገር እንደእዚያው።
ነጋዴው ገንዘቡን አውጥቶ የከፈተው ምግብቤት በደንበኞች የተወደደ ይሆን ዘንድ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት አካላት ብዙ ናቸው። የአንዱ ሰው በቦታው እንደሚገባው አለመሆን ደንበኛው ጋር የመድረስ ፍጥነቱ ከፍተኛ ነው። ማብሰያ ክፍል የሚፈጠረው ችግር፣ በመስተንግዶ አካባቢ የሚፈጠረው ማናቸውም ለደንበኛው የማይመቸው ነገር፣ ሂሳብ ሥራ ጋር የሚፈጠረው እንዲሁ መዛነፍ ወዘተ ድምር ውጤቱ ምግብቤቱ እስከመዘጋት ሊያደርሰው የሚያስችል ውድቀት ውስጥ ሊጨምረው ይችላል። እኒህ የተለያዩ አካላት መካከል ያለው እሴት፣ ያላቸው በሥራው ላይ ያላቸው ግልጸኝነት፣ ወዘተ ተዳምሮ ውጤታማ ያደርጋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች ተቋማትም ሆነ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶች ውስጥ ይሠራል። እሴት ደግሞ ነገሮችን አስተሳስሮ የሚይዝ ሆኖ ይገኛል። በሁሉም አካላት መካከል የሚኖረው መተማመን ደግሞ ታላቁ እሴት ሆኖ የሚጠቀስ ይሆናል።
የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ እንደሚባለው አለመተማመን ሲሆን አላስፈላጊ የሆኑ ስብሰባዎችን ያበዛል፣ የሥራ ሰዓትን ያሳጥራል፣ ለአንድ አላማ የተሰለፉ ሰዎች መካከል መከፋፈልን ይፈጥራል ወዘተ። በመተማመን ውስጥ ግን ነገሮች ቅርጽ ይዘው ወደ ውጤት መፍሰስ ባለባቸው ልክ ሊፈስሱ ይችላሉ።
መተማመን ታላቁ እሴት በመሆኑ በጥንቃቄ ሊያዝ እና አንዴ ከተሰበረ በቀላሉ መጠገን የማይታሰብ መሆኑን መረዳት ላይ መድረስን ይጠይቃል። ከጀርባ መወጋትን ከባድ የሚያደርገው የመተማመንን አጥር አልፎ የሚመጣ በመሆኑ ነው። የመተማመንን አጥር አልፎ የሚመጣ ስለሆነ መከዳት ከባድ ይሆናል፤ አገላለጹም ከጀርባ መጎዳት።
መጠርጠር እስከምን ድረስ
በመከዳት ጊዜ ነገሮችን ውስብስብ የሚያደርገው አስቀድሞ መከዳት ቢኖር ብሎ ካለማሰብ እንደሆነ አጥኚዎች ይናገራሉ። በአገራዊ አባባላችን «ያልጠረጠረ ተመነጠረ» እንደሚባለው። ሰዎች በመሆናችን ግን ፊትለፊት ከሚታየው ነገር ጀርባ ያለውን ለማየት መሞከር አስቸጋሪ ነገር መሆኑን እንረዳለን። ሰዎችን በጥርጣሬ ውስጥ እየተመለከቱ ይህን ያለው ከምን ተነስቶ ነው ማለት እንቅስቃሴን የሚያስርም ሆኖ ልናገኘው ደግሞም ልናስብም እንችላለን።
ይህ ማለት ግን ለጥርጣሬ ቦታ መስጠት አለመቻል ትክክል ነው ማለት አይደለም። ያለ እምነት አብሮ መሥራት ወይንም መኖር እንደማይቻለው አንድነገር ከመሆኑ በፊት እንዲህ ቢሆንስ ብሎ ሳያስቡ መኖር ደግሞ በክፉ ቀን አደጋውን ከፍተኛ ያደርገዋል። የጀርባ መጎዳት ክብደቱ ባልጠረጠሩት ሰው በመወጋት እንጂ በሚጠረጥሩት በመወጋት አይደለም። የሚጠብቁት ሰው ያንን ቢያደርግ ላያስገርም ይችላል። የምንጠብቀው ስለሆነ እንደ አመጣጡ ልናስተናግደው ይገባል።
መጠርጠር መስመሩን አጥቶ ሁሉንም ነገር ወደ መጠርጠር ውስጥ ከገባ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ መሆኑ የማይቀር በመሆኑ መፍትሔ ያስፈልገዋል። መፍትሔው በተለያየ አቅጣጫ ጉዞ ማድረግ ወይንም እምነትን የመገንባት ሥራን መሥራት ሊሆን ይችላል። እንደ እርግብ የዋህ መሆን ጥቅም እንዳለው ሁሉ የእባብ ብልህነትም ቦታ ሊሰጠው የተገባ ነው።
የመንደርደሪያ ታሪካችን ላይ የጠቀስናቸው የምህንድስና ባለሙያው ግለሰብ በሕይወት ጉዟቸው ውስጥ አንድ ቀን ወደ ጎዳና እወጣለሁ ብለው አስበው ሊሆን የመቻላቸው ዕድል አነስተኛ ነው። ሰዎች በዚያ ደረጃ ሊጎዱኝ ይችላሉ ብለው ጠብቀውም አያውቁ፤ ምክንያቱም ጠብቀው ቢሆን ኖሮ ወደ ጎዳና ለመውጣት ውሳኔ አያሳልፉም ደግሞም ብዙ ኪሎሜትሮችን አቆራርጠው የሚያውቃቸው ሰው በማይኖርበት ቦታ ላይ ተደብቀው ለመኖር የፌስታል ጎጆ አይቀይሱም።
ከጀርባ መወጋት በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም መሆኑን ከተረዳን ሊያጋጥም ቢችል የሚለው ግንዛቤ አስፈላጊ ነው። በእምነት እና በጥርጣሬ መካከል ያለውን የእውቀት ሚዛን ፈልጎ ማግኘት ደግሞ ብልህ ያደርጋል። ጀርባወጊዎች ቢመጡ፤ ከማዕዳችን ባስቀመጥነው ሰው ብንከዳ፤ ኩላሊታችንን ያጋራነው ሰው የማያውቀን መሆኑን ቢነግረን፤ ያለንን ሁሉ ሰውተንለት የእኛ ያልነው ሰው ጀርባችንን የሚወጋ ሆኖ ቢገኝ ወዘተ እንዲህ ሊሆን ይችላል ብሎ አስቀድሞ የሚያስብና በሚዛን ውስጥ የሚኖር ሰው ጉዳቱ ለከፋ የሚሰጥ አይሆንም።
ሰዎች ዓላማቸውን እንዲተዉ፣ ሰብዓዊ ስሜታቸውን ከውስጣቸው ተሟጦ እንዲወጣ፣ ለመልካም ተጽእኖ ከመሥራት ይልቅ ዝምብሎ ነዋሪ ሊያደርጋቸው የሚችሉ፣ ትልቅ ነገርን ከሰዎች ጋር ሆኜ ሠርቼ ዳር አደርሳለሁ የሚል እምነት እንዳይኖራቸው የሚያደርገው ወዘተ በአብዛኛው በትናንት ውስጥ ያለ የእርስበእርስ መስተጋብር ውጤት ነው።
በሆነስጊዜ
ከጀርባ መወጋት በሆነ ጊዜ፤ የስሜት መዘበራረቅ ሲገጥመን፤ ሁሉንም ተጠራጣሪ ሆነን ስንገኝ ለምንወስደው እርምጃ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ምናልባት በአሁን ሰዓት በጀርባ መገፋት ስሜት ውስጥ ያላችሁ አንባብያን ይህንን ልብ እንድትሉት ይገባል። ከጀርባ መጎዳት በሚሆን ጊዜ ትልቅን ምስል የሚያደበዝዝና በበዛ ስሜታዊነት ውስጥ የሚያስገባ ነው። ስሜታዊ ውሳኔዎቹ ወደ በቀል የሚወስዱ፣ ራስን መጉዳትን እንድናስብ የሚያደርጉ፣ ከራስ ጋር ብቻ ንግግር የሚያደርግ ሰው ማድረግን ወዘተ ያስከትላል።
ዛሬ ላይ በመከዳት ወይንም በጀርባ መወጋት ስሜት ውስጥ ያልሆነ ሰው ነገን ታሳቢ አድርጎ በእኔ ሕይወት ቢሆን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ስለሆነም በሆነ ጊዜ ሊደረጉ የሚገባቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል የመጀመሪያው እውነታውን መቀበል ነው። እውነታውን በመቀበል ውስጥ የሚኖር ከራስ ጋር የሚኖር ፍትጊያ ብዙ አቅምን ሊጨርስ ይችላል። ያ እንዳይሆን ፈጥኖ የሆነውን ነገር ተቀብሎ፤ የአገሬ ሰው «ጉድ አንድ ሰሞን ነው» እንደሚለው ሕይወት ልትቀጥል እንደምትችል ማሰብ አለበት። ሕይወት በሌላ አቅጣጫ የሚቀጥል መሆኑን በማመን ከመከዳት ስሜት በላይ መራመድን ይጠይቃል። ይሁድ ክርስቶስን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ይሁዳ በጸጸት ራሱን ቢያጠፋም ተላልፎ የተሰጠው ከሞት ተነስቶ ክርስትና እምነት ሆኖ በዘመናት መካከል መዝለቅ ችሏል። በጦር ግንባር፣ በቤተእምነት፣ በፖለቲካ፣ በትዳር፣ በማህበራዊ ሕይወት ወዘተ ከጀርባ መወጋት የሚስተዋል ነው።
ከመቀበል ቀጥሎ ከጀርባ ከወጋን ሰው ጋር እንዴት ባለሁኔታ ጋር ቀጣይ ሕይወትን መኖር እንደሚገባ መደንገግ አስፈላጊ ነው። ብዙ ጊዜ ከጀርባ የሚወጋ ሰው በቅርባችን ያለ ሰው ይሆንና ቀጥሎ ያለውን ነገር ከማስተካከል አንጻር ነገሮች አስቸጋሪ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ። ቢሆንም ቅሉ ቁጭ ብሎ ጉዳዩ ላይ አውርቶ ቀጣይ ህመምን ሊቀነስ ከተቻለም ሊያጠፋ በሚችል አግባብ በሌሎች ምክርም በመታገዝ ቀጥሎ ያለውን ነገር መመልከት ያስፈልጋል። ቀጣዩን አቅጣጫ መተለም አስቸጋሪ ቢሆንም ከእዚያ በመቀጠል ሊከተል የሚገባው ከጀርባ የወጋንን ሰው መነሻ አድርገን ሌሎች ሰዎችን ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ እንዳንመለከት ውስጣችን ለማከም ጊዜ መስጠት ነው። ችግሩን ተቀብለን፣ የችግሩ ምንጭ ከሆነው አካል ጋር በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለብን ካሰመርን በኋላ የገጠመን ነገር ተጽእኖው በቀጣይ ሕይወታችን ላይ ጥላውን እንዳያጠላ ማድረግ ነው። የመጨረሻው ነጥብ ከጀርባ ለመጎዳታችን የእኛን አስተዋጽኦ በመመርመር በቀጣይ ሕይወታችን የእኛ ጥፋት ያልነውን ማስተካከል ያለብንን ጥፋት ያልነውን ነገር ማስተካከል ነው። የራስን ጥፋት መርምሮ እውቅና እንደመስጠት አስቸጋሪ ነገር የለም። እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንደንጹህ የመመልከት ዝንባሌ ስላለ ሂደቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ራስን እያስተካከሉ ለመሄድ ግን ጥቅሙ የትየለሌ ነው። ብልህ ሰው ብቻ ሊያደርገው የሚችለው ተግባር። ቀጥሎ ብልህ ማን ነው? ብለን በመጠየቅና ትርጉም በመስጠት ወደ ማጠናቀቂያው እንምጣ።
ብልህ ማን ነው?
ብልህነት የሚታወቀው በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ በማድረግ ከአስቸጋሪ ነገሩ ለመውጣት በብልሃት የተሞላን አካሄድ በመሄድ ውስጥ ነው። የአገራችን ፖለቲካ ብልሃት የጎደለው መሆኑን የምንረዳው ሁሉም ታጋይ ከጀርባው የተወጋ የመሆኑ ትርክትን ይዞ የሚታገል፤ ብሶትና በቅልን ቅኝት ያደረገ በመሆኑ ነው። ብልህ ሰው ግን ከትናንት ችግር ለነገ የሚሆን ቤትን ይሠራል እንጂ ከትናንት ችግር በመሸሽ ለነገ ሌላ ችግር ዛሬ አይፈጥረም። ተመሳሳይ ችግር በሃይማኖት ቤቶች ትርክት ውስጥ እናገኛለን። የሃይማኖት እንቅስቃሴዎች የሚያምኑበትን እውነት ከማስተማር ባለፈ መወጋትን ታሳቢ ያደረገ ትርክት ላይ ተከታዮቻቸው ሲሰማሩ እናስተውላለን።
ብልህ ሰው ግን የእርግብን የዋህነት የእባብን ብልጠት ታሳቢ አደርጎ ለነገ ሕይወቱ የተሻለውን መንገድ የሚቀይስ ነው። በመከዳት ወይንም ጀርባን በመወጋት ስሜት ውስጥ ላለው ሰው በብልህነት ወደ መፍትሄ መሄድ እንጂ ሌላ አማራጭ የሌለ መሆኑን የሚረዳ።
ሌላው የብልህ ሰው መገለጫ ቀመር ዕድሜውን እየቆጠረ የሚሄድ ነው። ሕይወት አጭር ነች፤ ብልህ ለዘላለም መኖር እንደማይችል ያውቃል። ሁሉንም ከማግበስበስ በቁጥብነት፤ እኔ እኔ ከማለት በሌላው ጫማ ውስጥም ሆኖ ማሰብ፤ ከራስ አማራጭ በተሻለ ሌላማ አማራጭ ይኖር ይሆን ብሎ ማሰብ ወዘተ ይገባል። ብልህ ሰው ዕድሜውን ቆጥሮ የብርታት ዘመኑን በብልሃት የሚጠቀም ነው።
አንተ ወጣት ዕድሜህን በአግባቡ ለመጠቀም ምንም ዓይነት ምክንያትን ላለመቀለብ ውሳኔን አሳልፍ። ከጀርባ መወጋት ቢሆን ሌላ ተጽእኖ በኃይል የተሞላውን ዕድሜ ወደ ፍሬያማነት ጎዳና ከመውሰድ እንዳይከለክልህ ጥረትን ልታደርግ ይገባል።
ብልህ ሰው ኃላፊነትን እና ተጠያቂነትን የሚወስድ ነው። ሰዎች ሌላ ሰውን የሚጎዱት ተጠያቂነታቸውን ለማሸሽ ሲያስቡ ነው። እራስን ተጠያቂ ላለማድረግ ሌላ የመስዋእት በግ ፍለጋ ስንሄድ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የመገፋት፣ የመከዳት እና ከጀርባ የመወጋትን ስሜት ላይ እንደርሳለን።
አንባቢ ሆይ እንደማህበረሰብ እብደት በሚመስል ወቅት ላይ እንገኛለን። ኑሮው፣ ማህበራዊ ሚዲያው፣ ፖለቲካው፣ ወንጀሉ፣ ሽፍታው፣ ፍቺው፣ ወዘተ ተደማምሮ ሁሉም እብደት እየመሰለ አለ። እንዲህ ባለወቅት ደግሞ የበለጠ መከዳዳት፤ የበለጠ የጀርባ መወጋጋት አጋጣሚ ይኖራል። ከጀርባችሁ ለተወጋችሁ፤ ከጀርባ ወጊ በመሆን በህሊናችሁ ለምትወቀሱ፤ ምናልባት ዛሬ ሁሉም ሰላም የሆነላችሁና ነገ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ሊገጥማችሁ ለሚችል ስለሁላችሁ እኒህ የቁምነገር ቃላት ሰፈሩ። አንባቢው ለእራሱ ሲል ያንብብ፤ ጨው ለራሱ ሲል ይጣፍጥ እንደሚል። አሜን።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014