ህገወጥ ግብይት በሀገራችን እየተንሰራፋ ነው።ህገወጥ ግብይቱ በተለያዩ መንገዶች እየተፈጸመ ሲሆን፣ በዚህም ህዝቡም መንግስትም ክፉኛ ተማረዋል።እኔ ከህገ ወጥ ግብይቱ ኮንትሮባንዱ ላይ ነው ትኩረቴ።
የኮንትሮባንድ ነገር ሲነሳ በማናችንም ህሊና ውስጥ የሚታወሰው በህገወጥ መንገድ ከውጭ ሀገሮች ወደ ሀገራችን የሚገቡ ምርቶች ጉዳይ ነው።ብዙዎቻችን የምንመለከተውም የሸቀጦቹን ዋጋ መቀነስ፣ አንዳንዴም ጥራትን ነው።ኮንትሮባንድ ሲባል የሚታሰቡን እነዚህ ናቸው።
በዚህ ህገወጥ ንግድ አዳዲስ አልባሳት፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ የቤት ውስጥና ሌሎች መገልገያ እቃዎች፣ ወዘተ በስፋት ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ። የሚገርመው ደግሞ ያገለገሉ አልባሳት፣ ጫማዎች/ ቶርሽን የሚባለው ስኒከር ጫማ/ጭምር በኮንትሮባንድ ወደ ሀገራችን ገብተው ሲቸበቸቡ ይታያሉ፤ እነዚህ ጫማዎች በአብዛኛው ይሸጡ የነበረው ከጠረፍ አካባቢዎች ብዙም ባልራቁ አካባቢዎች ነበር።አሁን አሁን በክልል ዋና ዋና ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባም ጭምር እንደሚቸበቸቡ ይገለጻል፡፡
በኮንትሮባንድ ንግዱ እየተደረገ ያለውን ቁጥጥር ተከትሎ አሁን አሁን ለውጦች እንዳሉ ይነገራል።ቀደም ሲል ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል በሚባልበት ወቅት ጭምር ንግዱ በጣም የጦፈ እንደ ነበር ይታወቃል።የመንግስት ባለስልጣናት በተለይ የትህነግ ሰዎችና ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ብዙ ተጠቅመውበታል።ኮንትሮባንድ ንግድን እንዲቆጣጠሩ የተቀመጡ አካላት ጭምር በዚህ እጃቸው ተጨማልቆም ነበር ይባላል፡፡
በዚያን ዘመን የኮንትሮባንድ ሸቀጦች በቁጥቁጥ ሳይሆን ይመጡ የነበረው በከባድ መኪኖች ጭምር ነበር ሲባል አስታውሳለሁ።ይህ ሁሉ ይደረግ የነበረው ተጓዥ ግለሰቦችና ነጋዴዎች ይዘዋቸዋል የተባሉ ሸቀጦች እየተወረሱ ባለበት ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ ነው፣ እየተወሰደ ነው በሚባልበት ወቅትም ነው።
የኮንትሮባንድ ንግዱ እንደ ፊቱ የተንሰራፋ ባይሆንም አሁንም በስፋት እየተፈጸመ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ለእዚህ ደግሞ በየጊዜው ተያዙ የሚባሉት የኮንትሮባንድ ሸቀጦች ይጠቀሳሉ።በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች እየተቸበቸቡ ያሉት ልባሽ ጨርቆች፣ የተዘጋጁ አዳዲስ ልብሶች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ሽቶዎች ጥሩ ማሳያ ናቸው።
የኮንትሮባንድ ንግዱ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚደረግ ብቻ አልሆነም፤ ከሀገር ውስጥ ወደ ጎረቤትና ሌሎች ሀገሮች የሚደረግበት ሁኔታ እየሰፋ መጥቷል።ወርቅ ፣ የግብርና ምርቶች፣ የቁም እንስሳት፣ ወዘተ በስፋት በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት ሀገሮች እየተላኩ ናቸው። የውጭ ምንዛሬ ማሸሺያ አንዱ መንገድም ይሄው የኮንትሮባንድ ንግድ ሆኗል።
ከሀገር ቤት ወደ ጎረቤት ሀገሮች የሚደረገው የኮንትሮባንድ ንግድ በእነዚህ ብቻ አልተወሰነም።እንዲወጡ እየተደረጉ ያሉት ምርቶች አይነትና መጠን እየጨመረ መጥቷል።በውጭ ምንዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ምርቶች ሳይቀሩ በኮንትሮባንድ ወደ ሶማሊያ፣ ኬንያ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን እየተላኩ ናቸው። ይህ ሁኔታ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው በጣም እየተስፋፋ መሆኑን ያስገነዝባል። ሀገሪቱ ዜጎችን ከኑሮ ውድነት ለመታደግ በሚል ውድ በሆነው የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር እያስገባቻቸው ያሉት የምግብ ዘይትና ነዳጅ የዚህ ሰለባ ሆነዋል።
ነዳጅ ለኮንትሮባንድ ንግድ እንዲጋለጥ ያደረገው አንዱ ምክንያት በጎረቤት ሀገሮች ነዳጅ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ነው ይባላል።ኮንትሮባንዲስቶች በድጎማ የገባውን ነዳጅ ወደ እነዚህ ጎረቤት ሀገሮች ለማሻገር በስፋት እየተሰማሩ እንደሚገኙ እየተጠቆመ ነው።
ይህ አንድ የሚገርም ነገር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ደግሞ የነዳጅ ማደያዎች በጠረፍ አካባቢዎች መስፋፋት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ እየተጠቆመ ይገኛል።በቅርቡ በዚሁ አምድ የጠቀስኩት በጠረፍ አካባቢዎች የማደያዎች መበራከት ምናልባትም ከዚሁ ህገወጥ ግብይት ጋር ሳይያያዝ አይቀርም እየተባለ ነው።ከፍተኛ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ካለበት የሀገሪቱ ከተማ ይልቅ ያን ያህል የትራፊክ እንቅስቃሴ በሌለበት የጠረፍ ከተማ በርካታ የነዳጅ ማደያዎች መገንባታቸውን በነዳጅ ላይ የሚሰሩ አካላት ጤነኛ ኢንቨስትመንት እንዳልሆነ እያመለከቱ ናቸው።
ይህ ወደ ጎረቤት ሀገሮች የሚደረግ የኮንትሮባንድ ንግድ በኢትዮጵያ የቁም እንስሳት የውጪ ንግድ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው።ኮንትሮባንዲስቶች የቁም እንስሳትን ወደ ጎረቤት ሀገሮች በኮንትሮባንድ እንዲወጡ ሲያደርጉ ኖረዋል፤ እያረጉም ናቸው።አሁን ይህን ችግር አሳሳቢ የሚያደርገው የቁም እንስሳቱን ወደ ውጪ የሚልኩ አካላት በቀጥታ ወደ መዳረሻ ሀገሮች ከመላክ ይልቅ ወደ ጎረቤት ሀገሮች እየላኩ ያለበት ሁኔታ ነው።ላኪዎቹ ጎረቤት ሀገር የሚልኩት ለኳረንቲን ሊሆን ይችላል።
በኳረንቲን በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት በሀገር ውስጥ የኳረንቲኖች ግንባታ ተጀምሮ እንደነበርም አስታውሳለሁ። ግንባታው አልቆ ስራ ጀምሯል ስለተባለ ኳረንቲን የተባለ ነገር ግን እስከ አሁን አልሰማሁም። ይህ ትልቅ ክፍተት ነው።በኳረንቲን እጦት የቁም እንስሳት ንግዱ ለኮንትሮባንድ ንግድ ሊጋለጥ አይችልም ተብሎ አይታሰብም፡፡
ይህን ጉዳይ እንዳነሳ ያደረገኝ በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቁም እንስሳት ንግድን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ነው፤ የቁም እንስሳት የወጪ ንግዱ በኢትዮጵያውያን ብቻ እንዲፈጸም በሚል አሰራር ቢቀየስም ነገሮች እንደታሰበው እየፈጸሙ እንዳልሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከዚህም ንግዱ የውጭ ላኪዎች እጅ ከሚገባ በኢትዮጵያውያን ቢሰራ በሚል የተሰጠውን እድል እየተጠቀሙ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያውያኑ ለቁም እንስሳቱ አስፈላጊውን ምርመራ አስደርገው ወደ መዳረሻ ሀገሮች በቀጥታ ይልካሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከብቶቹን በጎረቤት ሀገሮች ለሚገኙ የውጭ የቁም ከብት ላኪዎች በማሻገር ላይ መጠመዳቸውን ነው።ይሄ ደግሞ ከኮንትሮባንድ ንግድ ምንም አይለይም፡፡
ኢትዮጵያውያኑ የቁም እንስሳትን ወደ ውጪ ለመላክ አንዱ ወሳኝ መሰረተ ልማት የሆነውን ኳረንቲን ገንብተው ወይም መንግስት እንዲገነባ ጠይቀው ቢሰሩና ከብቶቹን በቀጥታ ወደ መዳረሻቸው ሀገሮች ቢልኩ ሀገርም እነሱም በእጅጉ መጠቀም ይችሉ ነበር።
ኢትዮጵያ የቁም እንስሳቱን ምርመራና የመሳሰሉትን ራሷ ጨርሳ እስካልላከች ድረስ የቁም እንስሳት የወጪ ንግዱ ጤነኛ መንገድን ሊከተል አይችልም።የቁም እንስሳትን ወደ ጎረቤት ሀገሮች እየላኩ በማስመርመር ለውጭ ገበያ ማቅረብ/ ላኪዎቹ ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም እንኳ/ ሀገርን አይጠቅምም። መንግስት ይህን ሁኔታ ሊመለከተው ይገባል። ኳረንቲኖች ከሌሉ እንዲኖሩ ማድረግ፤ ከሌሉም በውጭ ኳረንቲኖች ለመጠቀም የሚያስችል ስርአት መዘርጋትና መቆጣጠርና መከታተል ይኖርበታል፡፡
ሌላም አንድ ጉዳይ ላንሳ።ከጥቂት አመታት በፊት ቢሾፍቱ ላይ አንድ የአህያ ቆዳ የሚፈልግ የቻይና ኩባንያ ቄራ ከፍቶ ነበር።ቄራው ብዙም ሳይቆይ ከኢትዮጵያውያን ባህል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያን መተቸታቸውን ተከትሎ ሳይሆን አይቀርም እንዲዘጋ ተደረገ። ኩባንያው ግን ከኢትዮጵያ ብዙም ሳይርቅ ኬንያ ውስጥ ለሞያሌ ቅርብ በሚባል አካባቢ ቄራውን ከፍቶ ነበር ይባላል።በእዚያ ስፍራ ቄራውን የከፈተውም የኢትዮጵያን አህዮች በቅርበት ለማግኘት አስቦና አቅዶ መሆኑ ሲገለጽ ነበር።
እንደተባለውም የኢትዮጵያ አህዮች ወደ ተባለው ቄራ ተጫኑ። ይህ መሆኑ ካልቀረ ተብሎ ይሁን ወይም በሌላ ሰበብ ቄራው ከኬንያ ተነቅሎ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደገና እንደተከፈተ ሰምቻለሁ። ኬንያ እያለ ቄራው የሚያስፈልገውን አህያ ያገኝ የነበረው ከኢትዮጵያ ነበር ይባላል።ይህ መቼም በህጋዊ መንገድ አይደለም ሲፈጸም የነበረው፤ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎች አልተፈጸመም ተብሎም አይታሰብም።
ከአጠቃላይ የኮንትሮባንድ ንግዱ በመነሳት ከነዳጅ ፣ ከቁም እንስሳትና ከቄራው አኳያ ያነሳኋቸው መረጃዎች ኮንትሮባንዲስቶች የኮንትሮባንድ ንግዱን ለማጧጧፍ ብዙ ርቀት እየሄዱ መሆናቸውን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በተለይ ከሀገር ቤት ወደ ጎረቤት ሀገሮች የሚደረጉ የኮንትሮባንድ ንግዶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በጽሁፉ ተመልክቷል፤ ይህ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እስከ አሁንም ካሉት የተለየና የአሁኑ ይባስ የሚያሰኝ እንደመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ ሊቀመጥለት ይገባል እላለሁ።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014