የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ በአለም አቀፍ ደረጃ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የመድሃኒቶች ምርት እየቀነሰ መጥቷል። መድሃኒቶቹ ወደፊት የመመረታቸው እድልም መንምኗል። በኢትዮጵያም ከሌሎች በሽታዎች ባለተናነሰ መልኩ የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኗል።
በእንስሳት በኩል ያለው የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድም ከግዜ ወደ ግዜ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። በተለይ ደግሞ አግባባዊ ባልሆነ የእንስሳት መድሃኒት አጠቃቀም ምክንያት የችግሩ አሳሳቢነት ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል።
ዶክተር በላቸው ባጫ በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ውጤቶች መድሃኒትና መኖ ጥራት ምርመራ ማእከል የፊሲኮ ኬሚካል ላብራቶሪ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የፀረ- ተህዋሲያን መድሃኒት በጀርሞች መላመድ በእንስሳት በኩል የሚከሰትባቸው መንገዶች በርካቶች ቢሆኑም ዋናዎቹ በሳይንስ የተረጋገጡት ናቸው። እንስሳት በሽታ ሲይዛቸው ለማከም፣ በሽታ እንዳይዛቸው ለመከላከል፣ በአካባያቸው ካለው ሌላ እንስሳ ጋር ንኪኪ ኖሯቸው በሽታ እንዳይዛቸው አምራቹ፣ ገበሬው ወይም የእንስሳት ጤና ባለሙያው የእንስሳት ፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶችን በሚጠቀምበት ግዜ በሽታን የሚያመጡት የእንስሳት ተህዋሲያን መድሃኒቱን በግዜ መራዘም ሂደት ይለምዱታል። በዚህም ምክንያት የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች እንስሳትን ሳይፈውሱ ይቀራሉ፤ ወይም የመፈወስ እድላቸውን ያራዝማሉ።
የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በእንስሳት ውስጥ በጀርሞች መላመድ ሊከሰት የሚችለው በዋናነት መድሃኒቶቹን በአግባቡና በሚፈለገው መጠን ባለመጠቀም ሲሆን፤ በተለይ ደግሞ በሽታን ለመከላከል፣ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና በእንስሳት አረባብና አያያዝ ሂደት ውስጥ ያሉ ስህተቶችን ለመሸፈን መድሃኒቶችን መጠቀም እንስሳው በበሽታው በሚያዝበት ግዜ መድሃኒቱ እንዳይሰራና እንዳያድነው ያደርገዋል ወይም ደግሞ የመድሃኒት ሂደቱ እንዲራዘም ያደርገዋል።
እነዚህ ችግሮች በእንስሳው ላይ ብቻ ተወስነው አለመቀመጣቸው ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል። በተለይ ደግሞ ሰዎች ከእንስሳቱ በሚወስዱት ተዋፅኦዎች ለጤና እክል መጋለጣቸው የከፋና አስጊ ያደርገዋል።
እንደ ዶክተር በላቸው ገለፃ ካለው ችግር አንፃር እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል። በፊት የነበረው የእንስሳት መድሃኒት አያያዝ፣ አጠቃቀምና ከእንስሳት የሚገኙ የምርትና ምርታማነትን ጥራት ደረጃ መቆጣጠር አቅም ስራዎች ወደ አንድ ተቋም እንዲመጡ ተደርጓል። ከዚህ በፊት በተናጠል ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች በአንድ መስሪያ ቤት ጥላ ስር፣ በአንድ አካሄድ፣ በተደራጀ፣ በተቀላጠፈና ውጤት በሚያስገኝ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር የቀድሞ የእንስሳት መድሃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የአሁኑ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ይህንኑ ጥራት የሚቆጣጠር ላብራቶሪ ገንብቷል። በዚህም ደረጃውን የጠበቀ፣ የወቅቱን አለም አቀፍ የሳይንስ ደረጃ ባገናዘበ መልኩ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ያላቸውን መሳሪያዎችን በማስገባት፤ የአሰራር ሂደቶችን በመከተል የምርመራ ዘዴዎችን እየተጠቀመ፤ በተለይ ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን በሀገር ውስጥ እንዲመረመሩና ጥራታቸው እንዲረጋገጥ እያደረገ ይገኛል።
በየአመቱ ደግሞ የእንስሳት ቅሪት /Antimicrobial residues/ ዳሰሳዎች እንዲሰሩ በማድረግ፤ የመድሃኒቶች መላመድ በእንስሳቶች ውጤቶችና ምርቶች ላይ ምን እንደሚመስል ውጤቶችን ለባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላቶች፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለግብርና ሚኒስቴር የላይኛው መዋቅር በማቅረብ ርምጃ እንዲወሰድባቸው፣ አቅጣጫ እንዲሰጥባቸውና ትኩረት እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎችንም ይሰራል።
ዶክተር በላቸው እንደሚሉት የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መለመድ በእንስሳት በኩል ያለው ችግር ከግዜ ወደ ግዜ እየከፋ መጥቷል። እንደ ሀገር ችግሩ ቢኖርም እየተከሰተ ያለበትን መጠን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናት ማካሄድና መረጃዎችን መሰብሰብ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ችግሩን በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም ጉዳዩ በሚመለከተው አካል ብቻ መፍታት አይቻልም። ስለዚህ ሁሉንም ባካተተ መልኩ በተለይ ደግሞ የጤናና ግብርና ሚኒስቴርን፣ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንን ባቀናጀ መልኩ በአንድና ወጥ በሆነ የጤና አቀራረብ (አፕሮች) ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር አንስቶ ታች በገበሬና በአርብቶ አደሩ ደረጃ ያሉ የእንስሳት አመራረትና አያያዝ ደረጃዎችን በማሻሻል በማስተማር፣ ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ መልካም የአመራረት፣ ፅዳትና ንፅህና አጠባበቆችን እንዲያውቁ በማድረግም ጭምር ችግሩን መፍታት ይቻላል።
ከሁሉም በላይ ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል በእንስሳት አመራረት ላይ ቅድሚያ መሰራት አለበት። በተለይ ደግሞ ገበሬውና አርብቶ አደሩ እንስሳው ሲታመምበት ማሳከም ያለበት ቢሆንም የመጀመሪያ ስራው ግን እንስሳው እንዳይታመምበት መንከባከብ፣ ማስከተብና በአካባቢው ከሚገኝ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ጋር መስራት ይኖርበታል።
እንስሳቶች ከታመሙም አግባባዊ የሆነ የመድሃኒት አጠቃቀም መንገዶችን መከተል አለበት። በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎችም ገበሬው ወይም አርብቶ አደሩ በአግባቡና በትክክለኛው ሰአት ለታመመ እንስሳ መድሃኒት እንዲሰጥ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል። ገበሬው ወይም አርብቶ አደሩ መድሃኒቶችን ለእንስሳቱ ከተጠቀመ ደግሞ መድሃኒቱ ጥቅም ላይ ውሎ እስኪወጣ ድረስ ይህን ባገናዘበ መልኩ የመድሃኒት ምርቶችን ሰብስቦ ለሌላ ጥቅም የሚውሉበትን መንገድ መፈለግ ወይም ማስወገድ ያስፈልጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014