ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አፄ ቴዎድሮስ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመምህርነት ሰልጥነው በከፍተኛ ውጤት ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል፡፡ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ደቡብ ጎንደር ስማዳ በሚባል አካባቢ ተመድበው ለአንድ ዓመት በመምህርነት አገለገሉ፡፡ በመቀጠልም ንፋስ መውጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ትክል ድንጋይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተከታታይ ሁለት ዓመታት አስተምረዋል፡፡ ነፃ ትምህርት እድል አግኝተው ምስራቅ ጀርመን በመሄድ ለስድስት ወራት የቋንቋ ትምህርት ከወሰዱ በኋላ ሁለቱ ጀርመኖች ሲዋሃዱ ደግሞ በማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ፡፡ ለትምህርት በሄዱባት ሃገር መቅረትና የተሻለ የስራ እድል ማግኘት ቢችሉም በተማሩት ትምህርት ሃገራቸውን ለማገልገል ወስነው ተመለሱ፡፡
አማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ በዋግ ህምራ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር ፅህፈት ቤት ተመድበው ለአምስት ዓመታት ከሲቪል ሰርቪስ ኤክስፐርትነት እስከ ቡድን መሪ ድረስ ሰርተዋል፡፡ በመቀጠልም ሰሜን ሸዋ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ለሁለት ዓመት ፤ አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለሁለት ዓመታት ሰርተዋል፡፡ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ መቋቋሙን ተከትሎ በመምህርነት ተወዳድረው በማለፍ ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር የሲቪክ ትምህርት ክፍል ራሱን ችሎ እንዲቋቋም በማድረግና በስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊና የተማሪዎች ዲን በመሆንም ሰርተዋል፡፡
በኋላም የትምህርት እድል አገኙና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በፌደራሊዝም ጥናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰሩ፡፡ ከዚያ ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ለጥቂት ጊዜ ካገለገሉ በኋላ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የአካዳሚ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ተቋሙን ከስር መሰረቱ ከማደራጀት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ስርዓተ ትምህርት ቀረፃ እንዲሁም የመተዳደሪያ ደምብ ማዘጋጅት ድረስ የእንግዳችን ሚና የላቀ ነበር፡፡ የለውጡን መምጣት ተከትሎ በተቋሙ በተካሄደው የሪፎርም ስራ ላይም ተሳትፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የህገ-መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእንግዳችን ይለየሱስ ታዬ ጋር በፌደራሊዝም ስርዓትና በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለምልልስ አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለውይይታችን መነሻ ይሆነን ዘንድ እስቲ በቅድሚያ ስለፌደራሊዝም ሳይንስ ምንነትና አተገባበሩ ያብራሩልን?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡- ፌደራሊዝምን በቀላሉ ለማስረዳት የግልና ማህበራዊ ጉዳዮችን አጣጥሞ መሄድ የሚያስችል ሳይንስ ነው። የግልና የጋራ ጉዳይን አስተሳስሮ መሄድ የሚያስችል አስተሳሰብም ነው። በነገራችን ላይ ፌደራሊዝም አስተሳሰብ እንጂ የመንግሥት ስርዓት አይደለም። ፌደራሊዝም የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን የአስተዳደር ሳይንስ ነው። ቅርፁ የፌዴራል ፖለቲካል ስርዓት ነው የሚባለው። በእርግጥ ፌደራሊዝም እንደማንኛውም ፍልስፍና ወይም አስተሳሰብ የራሱ የሆነ እጥረት ይኖረዋል። አንፃራዊ በሆነ መልኩ ግን እንደ ኢትዮጵያ ብዝሃነት ባለበት ሃገር ውስጥ ሁሉንም የሚያስተናግድ ስርዓት ከፌደራሊዝም የተሻለ አለ ብዬ አላስብም። በተለይም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም ፖለቲካ ብዝሃነትን ማስተዳደር ነው። ትልቁ የመንግሥታት ራስ ምታትም ብዝሃነትን ማስተናገድ ነው። እንደሚታወቀው በሀገራችን ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ብዝሃነት ተጨፍልቆ ነው የኖረው። አሁን ላይ በዚያ መንገድ መቀጠል አይችልም። በአንድ በኩል ሉአላዊነት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማንነት ጥያቄ አለ። ሁለቱንም ነገር ማገድ አይቻልም። ሁለቱንም ሁኔታዎች አጣጥሞ መሄድ የሚችለው ይህ አስተሳሰብ ነው።
በፌደራሊዝም ውጤታማ ተብለው ከሚጠቀሱ ሃገራት መካከል ሲዊዘርላንድ ናት። ይህች ሃገር በቆዳ ስፋቷ አነስተኛ ብትሆንም በኢኮኖሚ ያደገችና በአውሮፓ ፖለቲካም የላቀ ሥፍራ ነው ያላት። በዚህች ሃገር ውስጥ ጀርመንኛ፤ ፈረንሳይኛ ፤ ጣሊያንኛ፤ ሮማቲሽ የተባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ይነገራል። እነዚህ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ህዝቦች ታዲያ በጋራ ሆነው ሲዊዝ የሚባል ሃገር መስርተዋል። የየራሳቸውን ማንነት ግን አላጠፉም። ያም ማለት ችግር አልነበረባቸው ማለት አይደለም፤ እርስበርስ የተዋጉበት አጋጣሚ አለ። የሲዊዝ ፍዴሬሽን ከመመስረቱ በፊት ኮንፌዴርሽን ነበረች። በካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች መካከል ግጭት ነበር። በኋላ ላይ ግን ተስማምተው እ.ኤ.አ 1948ዓ.ም የመሰረቱት ፌዴሬሽን እስካሁን ዘልቋል።
በተመሳሳይ ህንድም በፌደራሊዝም የምትመራ እና ከእኛ የበለጠ ብዝሃነት ያለባት ሃገር ናት። እነሱ ደግሞ ከቋንቋ ባለፈ የሚያገሉት ማህበረሰብ አላቸው። ህንድ ፌደራሊዝም መተግበር ከጀመረች ወዲህ ከሶስተኛ ዓለም ከሚባሉ ሃገራት ሁሉ በአንፃራዊነት የተሻለ ዲሞክራሲ ያለባት ሃገር እንደሆነች ነው የሚታመነው። የፌዴራል ስርዓታቸውም እ.ኤ.አ ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከአሁን አለ። ሲጀመር በመልካ ምድራዊ ፌደራሊዝም ነበር። ይሁንና ከሃገራቸው ነበራዊ ሁኔታ አንፃር ምቹ ባለመሆኑ እና በማህበረሰቡ ግፊት ዳግመኛ ጥያቄ ባሉባቸው አካባቢዎች ቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ዘረጉ።
በእኛም ሃገር በትክክል ከተገበርነው አንፃራዊ በሆነ መልኩ አብሮ ለመኖር የሚያስችል ስርዓት ነው። ያም ቢሆን ግን እንደአፈፃፀማችን ነው የሚወሰነው። በህግ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን አመለካከትን ከዚያ ጋር አስማምቶ መሄድ ይጠይቃል። ስርዓቱን በደንም ካልተገነዘብንና አስተሳሰቡን ውስጣችን ካላሰረጽን በትክክል መተግበር አይቻልም። ለምሳሌ አሀዳዊ አስተሳሰብ ይዘሽ የፌዴራል ስርዓት ልትተገብሪ አትቺይም። በእኛ ሃገር ብዙሃኑ አሀዳዊ አስተሳሰብ ነው ያለው። ከዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ቶሎ መፋታት ከባድ ነው፤ ጊዜ ይወስዳል ብዬ ነው የማስበው። ይሄ ግልፅ እና አሁንም የሚታይ ነው፤ ጥቂት የማይባለው ማህበረሰብ አዛዥ ታዛዥ ከሚለው አስተሳሰብ አልወጣም። አብሮ በእኩልነት መኖር፤ በጋራ ጉዳይ ላይ እኩል ውሳኔ መስጠት አይፈለግም፤ ከዚያ ይልቅ አንዱ የበላይ መሆን ነው የሚፈልገው። ይሄ ደግሞ በፌዴራል ስርዓት አይሰራም።
አዲስ ዘመን፡- ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት መከተሏ በራሱ ህዝቡን ተጠቃሚ አድርጎታል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡- በመሰረቱ እኔ ፌደራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት በአግባቡ ተተግብሯል ብዬ አላምንም። መጀመሪያ እዚያ ላይ ነው መግባባት ያለብን። አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ የፌዴራል ስርዓት በአስተሳሰብ ነው የሚመራው። አስተሳሰብ ደግሞ የሚሰርፀው በሂደት ነው። ህግ ረቆ ክልል ስለተመሰረተ ብቻ ስርዓቱ ተተገበረ ማለት አይቻልም። በእኔ እምነት ስርዓቱን እንዲያስተገብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ራሳቸው የፌዴራል አስተሳሰብ የላቸውም። ለዚህም እኮ ነው እዚህም እዚያም ከስርዓት ያፈነገጡ ችግሮች የምናየው። የማንንቀውና ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ግን ብዙ ቋንቋዎች እውቅና ማግኘታቸው ነው፤ ህዝቡ ቋንቋውን በአደባባይ እንዲጠቀምበት እድል ተፈጥሮለታል፤ ዜጎች የራሳቸው ክልል ኖሯቸው በራሳቸው ክልል የራሳቸውን ትምህርት ቤት፤ ሚዲያ መክፈት ችለዋል።
ራስን ማስተዳደር የሚለውን ነገር ከእነ ህፀፁም ቢሆን በተጨባጭ ያየነው ይህ ስርዓት ከተዘረጋ በኋላ ነው። አሁንም ችግሮች ቢኖሩም ብዙዎች ራስን የማስተዳደር መብት አግኝተዋል። አሁን ደግሞ ያሉትን ችግሮች መፈተሸንና በተሻለ መልኩ መተግበር ይገባል። ዞሮ ዞሮ ልምምዱ በራሱ መኖሩ እንደትልቅ ነገር የሚታይ ነው። በህገ-መንግስቱ መሰረት ስልጣን እኩል ለመከፋፋል ተሞክሯል። ክልሎች የሚጠበቀውን ያህል አልሄዱም እንጂ የተለያዩ ማዕከላት ተፈጥረዋል። የፌደራሊዝም አንዱ ቱሩፋቱ ይሄ ነው። ሁሉም ክልሎች የየራሳቸው ዋና ከተማ አላቸው። ከዚያ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ህዝቡም በገዛ ቋንቋው የመማር እድል አግኝቷል።
አዲስ ዘመን፡- በአፈፃፀም ረገድ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል የተወሰኑትን ቢጠቅሱልን?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡– ትልቁ ችግር ብዬ የምወስደው ህገ-መንግስቱ ከፀደቀና ክልሎች ከተመሰረቱ በኋላ ትክክለኛ የፌዴራል አስተሳሰብና አመለካከት እንዲኖር የተሰራው ስራ ደካማ መሆኑ ነው። ሁለተኛው ችግር ደግሞ ፌደራሊዝም ሁልጊዜ የሚከተለው ፍትሃዊና ሚዛናዊ መንገድን ነው። በተለይ እንደእኛ ብዝሃነት ባለበት ሃገር ላይ ሚዛን ካልጠበቀ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ለምሳሌ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የራስ አስተዳደር እንዳለው ሁሉ የጋራ አስተዳደር መኖሩ ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ መስራት ላይ ክፍተት አለ። ወደ አንዱ አዘንብለሽ የምትሰሪ ከሆነ የፌዴራል አስተዳደሩ ይሞታል፤ መለያየትም ሊመጣ ይችላል። በተለይ ስንከተል የኖርነው አውራ ፓርቲ ስርዓት ስለሆነ በፓርቲ ነው ሁሉ ነገር የሚያልቀው። ሁሉም ሃሳብ ከላይ ወደ ታች ነው የሚወርደው።
ክልሎች ሉዓላዊ ስልጣን ቢኖራቸውም፤ ግን በትክክል ተጠቅመውበታል ወይ? የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው። እዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ተደርጎ አለመሰራቱ በራሱ እንደአንድ ችግር ነው የማየው። ፍትሐዊ የስልጣን ክፍፍል ሲባል ስልጣንን መቀራመት ብቻ ሳይሆን ሃገራዊ እሴት ሁሉ የሁሉም መሆን አለበት። አጠቃላይ አስተሳሰቡ የጋራ ስነልቦና ላይ የተቀረፀ መሆን አለበት። አሁንም ሰው ማፈናቀል አለ፤ ይህ ችግር ደግሞ የፌዴራል ስርዓቱ ችግር ነው ወይ? የሚለው ነገር ግን ብዙ የሚያከራክረን ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የፌዴራል ስርዓቱ ባይኖር ኖሮ መፈናቀል አይኖርም ብዬ አላምንም። ይህም ከአስተሳሰብ ጋር የሚያያዝ ነው። የአንቺ መብት ከተከበረልሽ የጋራ የሆነውን መብት ማክበር አለብሽ። የአንዱ መብት ተከብሮ የሌላው ተረግጦ ፌደራሊዝም ስርዓት ሊተገበር አይችልም። ምክንያቱም የፌደራሊዝም ስርዓት መነሻው ሰብአዊነት ነው።
አንድ ግለሰብ እንደቁስ ብቻውን መቆም አይችልም። ምክንያቱም ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው። ከሰው ጋር አብሮ መኖር የግድ ያስፈልገዋል። በጋራ የሚኖርበትን አግባብ ማጣጣም አልተቻለም። የሰብአዊ መብት ያለመከበር፤ እኩል ተጠቃሚነት ያለመኖር ችግር ነው። ያ ማለት ግን እነዚህን ችግሮች የፈጠራቸው የፌደራል ስርዓቱ ነው እያልኩኝ አይደለም። ምንአልባት አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ትልቁ ችግር በአመለካከትና አስተሳሰብ ላይ አለመሰራቱ ነው። ሁሉም በገባው ልክ ሲፈፅመው ወደ ራስ
የማየትና ሃገራዊ ጉዳይን የመተው ነገር ነበር። ሚዛኑን ጠብቆ ካልሄደ የፌደራል ስርዓት አይቀጥልም። በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ መብቶች አይከበሩም፤ ከፌደራል ስርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቅዎችም በወቅቱ ምላሽ አይሰጣቸውም።
ለምሳሌ አሁን ላይ የግጭት ምንጭ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የማንነት ጥያቄ ነው። በተመሳሳይ የወሰን ጥያቄ ይነሳል፤ ግን በወቅቱ ባለመመለሱ የግጭት ምንጭ ሲሆን ይታያል። ይህ ራሱ የፌደራል ስርዓት ችግር ነው። ህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠ ነገር አለ፤ ግን መልስ አይሰጥም። ሌላው ይቅርና የክልልነት ጥያቄዎች እንኳን በቅርቡ ነው የተመለሱት። እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ማህበረሰቡን በማወያየት የፌደራል ስርዓቱን በደንብ በማስረዳት አላስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ለምን እንደማይሰጠው ህዝቡን በደንብ ማሳመን መቻል ይጠበቃል። እዚህ ላይ ብዙም ስላልተሰራ ነው አሁን ችግር ሲፈጠር የምናየው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት መልካዓ-ምድራዊ ፌደራሊዝም እንደሆነ ይናገራሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡- እኔ በዚህ ሃሳብ አልስማማም፤ አሁንም ቋንቋን መሰረት ባደረገው ፌደራሊዝም ቢሆንም መልክዓ-ምድር አለ፤ ሁሉም የሚኖረው በመልክዓ-ምድር ውስጥ ነው። ከሁሉ በላይ ብዝሃነታችንን የሚያስተናግደው ቋንቋ ላይ መሰረት ያደረገው ስርዓት ነው። ግን ደግሞ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል የሚኖረውን አማርኛ ተናጋሪ ‹‹ከአማራ ክልል የመጣ›› የሚለውን አስተሳሰብ አልቀበለውም። ህጉ የሚገልፀው አማርኛ ተናጋሪ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ብሎ ነው ። መባልም ያለበት ይህ ነው። 30 ዓመት እና ከዚያ በላይ የኖረውን ሰው በምን መልኩ ነው መጤ የሚል ስያሜ ሊሰጠው የሚችለው?። ህገ-መንግስቱ በግልፅ እንደሚያስቀምጠውም ክልሎች በቋንቋ ቢከለሉም የትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ በፈለገበት የሃገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሶ የመኖር፤ የመስራት መብት አለው። ከሌላ አካባቢ ስለመጣ ብቻ ልናገለውና እንደ ሁለተኛ ዜጋ ልንቆጥረው አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ አንዳንድ ክልሎች ስልጣን ገደብ ያልተበጀለት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግሥቱን ህልውና አደጋ ውስጥ እየጣለ ነው ብለው የሚሰጉ አሉ፤ ለእርሶ ይህ ስጋት ምንያህል ምክንያታዊ ነው? መፍትሔውስ?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡- እንደእኔ እምነት የስልጣን አጠቃቀምና ገደብ ላይ ችግር አይጠፋም፤ ለእኔ ግን ዋናው ቁምነገሩ ችግሩን እየተነጋገሩ መፍታት ላይ ነው። በክልሎችና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ጤናማ የሆነ የግንኙነት ስርዓት መኖር አለበት። ይህንን በሚመለከት በቅርቡ የክልል መንግሥታት ግንኙነት ስርዓትን ለመወሰን የሚያስችል ህግ በምክር ቤቱ ወጥቷል። ይህ የወጣበት ዋና ዓለማ ክልሎች ችግሮቻቸውን ቁጭ ብለው እንዲወያዩ ለማድረግ ነው። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ክልል በአንድ ሃገር ቀጣና ውስጥ ነው የሚኖሩት፤ ለአንድ ህዝብ ነው የሚሰሩት። ክልሎችም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ የየራሳቸው ስራ ቢኖራቸውም የጋራ ኃላፊነት ደግሞ አለባቸው።
ስለዚህ መፍትሔው ሊሆን የሚችለው ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው። ህገ-መንግሥቱ ስለመጣሱ ትርጉም የሚሰጥ አካል በመኖሩ ችግሩን ለዚያ አካል ማቅረብ ይገባል። ቁጭ ብለው ተነጋግረው የማይፈቱት ከሆነ ስልጣኔ ተወሰደብኝ የሚለው አካል ለህገ መንግሥት ተርጓሚው አካል ማቅረብ አለበት። እርግጥ ይህ አሰራር ብዙም አልተለመደም። እርምጃም ብዙም አይወሰድም። በህዝብ ብዛት፤ በቆዳ ስፋትና በአቅም የፈረጠመ ክልል ስለሆነ ብቻ ከህግ ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም። በተሰጠው ስልጣን ነው መንቀሳቀስ ያለበት። ሌላው የእኛ ሃገር ችግር መንግሥትና ፓርቲ መደበላለቅ ነው። ይህም ከዲሞክራሲ ባህላችን ካለማደጉ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ለዚህ እኮ ነው አስተሳሰባችን ላይ መስራት አለብን የምልሽ። በአንድ ጊዜ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት መፍጠር አንችል ይሆናል፤ ግን በሂደት እያሻሻልን መምጣት መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፦ ይቅርታ ላቋርጦት፤ እርሶ በተለይ ሰላም ከማስፈን አኳያ አሁን ያለው ችግር በሂደት ዲሞክራሲው ሲሻሻል የሚመጣ ነው ብለን የምንተወው ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡- የፌዴራል መንግሥቱ ስልጣኑን ተጠቅሞ ሰላም ማስፈን ያልቻለው አቅም አጥቶ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ህገ- መንግሥት የሃገር ሰላም የማስጠበቅ ስልጣን በዋናነት የሰጠው ለፌዴራል መንግሥቱ ነው። የክልሎች ስልጣን ከገደብ አለፈ ተብሎ ከሁሉም ጋር ጦርነት አይገጠምም። እርግጥ እንዳልሽው ለምሳሌ ክልሎች የየራሳቸው ልዩ ሃይል ማቋቋማቸው በራሱ የፌዴራል መንግሥቱን ስልጣን እንደመጋፋት ሊታይ ይችላል። እሱም ቢሆን ግን የራሱ ፖሊሲና መነሻ አለው። ክልሎች ቢፈረጥሙም እንኳን የፌዴራል መንግሥቱም ስልጣኑን መጠቀም ይችላል። እስካሁን ለምን በአግባቡ ስልጣኑን አልተጠቀመም? የሚለው ነገር አብረን ልንጠይቅ እንችላለን። ለእኔ ግን ጉዳዩ ፖለቲካዊ ምክንያት እንዳለው ነው የሚሰማኝ። አሁንም ችግሩ የፖለቲካ ጉዳይ እንጂ የህግ ጉዳይ አይደለም።
ለምሳሌ በክልሎች ሰብአዊ መብት ከተጣሰ የፌዴራል መንግሥቱ እንዲገባ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ሆነው ማዘዝ እንደሚችሉ ህገ-መንግሥቱ ይደነግጋል። ስለዚህ የሚባለው ችግር ካለ አሁንም ለመነጋገር የሚያስችል የህግ አግባብ አለ። ሁለቱ ምክር ቤቶች ካመኑበት የክልሉ ፍቃድ ላይጠየቅ ይችላል። እስካሁን ይህ ሊሆን ያልቻለው ፖለቲካ ስለሆነ ነው። የፌዴራል ስርዓቱ ግን ያንን አልከለከለም። በሌላ በኩል ህገ-መንግሥታዊ ስርዓት ከተናደ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማዘዝ ይችላል።
በእኛ ሃገር ትልቅ ችግር የሆነው የፖለቲካ ውጥረቱ ነው። የፖለቲካ ውጥረቱ ደግሞ በስሜት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ ችግሮች እየገነኑ የሚሄዱበት ሁኔታ አለ። ከሁሉ በላይ ግን በአንድ ክልል ውስጥ ለሚፈጠር ችግር መፍታት ዋነኛ ኃላፊነት የክልሉ መንግሥት ነው ብዬ ነው የማምነው። የአማራ ክልል መንግሥት የኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር ሊፈታ አይችልም። ለዚህ ነው ሁሉም ቁጭ ብለው ይነጋገሩ የምንለው። ካለበለዚያ እርስ በርስ እልቂት ከመፍጠር ያለፈ ሚና ይኖረዋል ብዬ አላምንም። ሃገራችንን የምንወድ ከሆነ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ በማድረግ ነው። የራስን ዜጋ ገድሎ ዘራፍ ማለት አይመቸኝም። ከዚህ ባህል ካልወጣን ችግሩ አይፈታም፤ ምንአልባትም እንደሃገር ላንቀጥል እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ህገ-መንግሥቱ ራሱ የግጭት ምክንያት በመሆኑ ፈፅሞ መቀደድ አለበት ብለው የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንቀፅ 39ኝን ጨምሮ የተወሰኑ አንቀፆች መሻሻል አለባቸው የሚል አለ። እርሶ ከየትኛው ወገን ኖት?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡– እንዳልሽው አንዳንዶች መገንጠልን እንደመብት የሚወስዱ አሉ፤ ግን የዚህ አንቀፅ ዋነኛ አተያይ አስቀድሞ መብት ከተሰጠ መገንጠል አይታሰብም ከሚል ነው። አንዳንድ ፀሐፊዎች እንደሚሉት አብረሽ ለመኖር የተስማማሽው በጋራ ስለሆነ ካልተስማማሽ መለየት ህግና ስርዓት ተከትሎ ከሆነ ችግር የለውም ብለው ነው የሚያምኑት። በጦርነት ከሚሄድ በህግ ቢለያዩ የተሻለ እንደሆነ ነው የሚመክሩት። በሌላ በኩል ደግሞ የተመሰረተው የፌዴራል ስርዓት የሚወስነው እንደሆነ የሚናገሩም አሉ። ከእኛ ሃገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ስናመሳክረው እኛ የመሰረትነው ፌዴሬሽን በዘላቂነት አብሮ ህብረት ለመፍጠርና በጋራ ለመቀጠል ነው።
እንዲህ አይነት ቅሬታ ካለ በመጀመሪያ በውይይት ነው መፈታት ያለበት ብዬ ነው የማምነው። በመጀመሪያ አብረው ለመሆን ሲሞክሩ ያላቸውን ጥያቄ ሁሉ አቅርበው መስማማት አለባቸው። ከምንም በፊት አብሮ ለመኖር መተማመን ያስፈልጋል። እኔም የምደግፈው ይህንን ነው። በመሰረቱ እስከተማመኑ ድረስ አንቀፁ መካተቱ ትክክል አልነበረም የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። ልዩነት ያለው አካል ካለ ልዩነቱን አምጥቶ ውይይት ተደርጎበት ሊካተት ይችል ነበር። ህገመንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ ግን አብረን እንቀጥላለን የሚል እምነት ነው ማምጣት ያለበት። ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከሕወሓት በስተቀር ከዚህ ቀደም እንገነጠላለን ብለው የሚያስቡ ሁሉ ስርዓቱ ዲሞክራሲ ከሆነ አብሮ ለመቀጠል ነው ፍላጎታቸው። ያ ማለት ከስጋት ነፃ ነን ማለት አይደለም። ይህንን ስጋት ለመቅረፍ ደግሞ አስተሳሰብ ላይ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ግን በዚህ ስርዓት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት እየተሰበከ ትውልዱ የጋራ የሚለው እንዳይኖር በተደረገበት ሁኔታ አሁን ላይ የፈለገውን ያህል አስተሳሰብ ለመቀየር ቢሰራ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይታመናል?
ዶክተር ሃይለየሱስ፡– ልክ ነሽ፤ ከሃገር አንድነት ይልቅ የራስ አስተዳደር ብቻ እንዲጎለብት ነው የተሰራው። ትውልዱ የራሱን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ የጋራውን ፍላጎት ማሟላትና አብሮ የሚኖርበትን አስተሳሰብ እንዲኖረው አልተደረገም። ይህንን ችግር ደግሞ በክልሎች መዝሙር ላይ ጎልቶ እናየዋለን። በዚያ መዝሙር የሚተላለፈው መልዕክት ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ነው የሚሰብኩት። ይህም ደግሞ የህፃናትን አዕምሮ በመበረዝ ረገድ ቀላል አይደለም። ከአማራ ክልል መዝሙር ይሻላል እንጂ አብዛኞቹ የጋራ ነገር ወይም አንድነት የሚሰብኩ ሃሳቦች የለባቸውም። አብሮ ለመኖር የሚያስችሉ አይደሉም። አንድነት ላይ የሚሰራ ከሆነ አንድነት ላይ መሰራት አለበት። ሃገር ሃገር የሚሸት ነገር መካተት አለበት።
በነገራችን ላይ እኔ ህገ-መንግሥቱ ፍፁም ነው የሚል እምነት የለኝም። የሁሉም ሃገር ህገ-መንግሥት ችግር ሊኖርበት ይችላል፤ በሂደት ነው እየተስተካከለ የሚመጣው። ለምሳሌ የአሜሪካ ህገ-መንግሥት የተፃፈው በ1789 ነው። የተፃፈው ያኔ በነበረው እሳቤ መሰረት ነው። ያንን ህገ-መንግሥት የፃፉ ሰዎች ቤታቸው ባርያ ነበራቸው፤ ግን እስካሁን 30 ጊዜ ተሻሽሏል። ስለዚህ እኛ ሃገርም ማሰብ ያለብን ሁልጊዜ አዲስ ህገመንግሥት እየፃፍን መሄድ ሳይሆን እንደየጊዜውና ሁኔታው እያየን ማሻሻል ነው ያለብን። እስካሁን ሶስት ህገ-መንግሥት ጥለን አራተኛ ፅፈናል። ስለዚህ ህገ-መንግሥቱ የሚሻሻሉ አንቀፆች ይኖሩታል። ያ ግን የእኔ ሃሳብ ነው፤ ህዝቡ ግን መወያየት አለበት።
በመሰረቱ አሁን ያለው ህገ-መንግሥት ሲፀድቅ አልተሳተፍንም የሚሉ ሰዎችን አልቀበልም፤ ተሳትፈዋል፤ የተሳተፉት ግን በፓርቲ መስመር ነው። ተሳትፎውን የሚወስነው የዲሞክራሲው ሂደት ነው። የአማራ ክልልም ቢሆን ብአዴን ውስጥ በነበሩ ሰዎች አማካኝነት ተወክለዋል። በየቀበሌው ህዝቡን ማወያየታቸውን የሚገልፅ ቃለ ጉባኤ አለ። አሁንም ቢሆን የሕዝብ ተሳትፎ የሚወሰነው አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ነው። በተለይም የተመረጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ሊሂቃን ናቸው የሚሳተፉበት እንጂ ሁሉም ሰው ይሳተፍበታል ማለት አይደለም። ስለዚህ ተሳትፎን አንፃራዊ በሆነ መልኩ ብናየው ጥሩ ነው።
ህገ-መንግሥቱ አንዳንዶቹ እንደሚሉት ጨርሶ የማያስፈልግና ተቀዶ መጣል ያለበት አይደለም፤ እንዳውም አብዛኛው አንቀፅ ስለመብት ነው የሚያወራው። አንዳንድ ሰው እሱ ብቻ የሚፈልገውን ብቻ አንብቦ ሌላውን መቀበል አይፈልግም። ሌላው ደግሞ ጭራሽ እንዳይነካብኝ የሚል አለ። ያም ትክክል አይደለም። አሁን ካለው የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና እድገት አኳያ መሻሻል አለበት። ህገ-መንግሥቱን ሰበብ በማድረግ ህዝብ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ግለሰቦች እንደነበሩ አከራካሪ አይደለም። ግን ደግሞ ይሄ የህገ-መንግሥቱ ችግር ነው ብዬ አላምንም። ለምሳሌ አንድ ክልል የሚካለለው በህዝቡ ፍቃድ ላይ መሆኑ ቢታመንም ህዝቡ ግን ፍቃድ ተጠይቆ አያውቅም። ከህዝብ ፍቃድ ውጪ መካለሉ ህገ-መንግሥቱ ሳይሆን አመራሩ ነው ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው። ያኔ አብሮ በህዝብ ላይ በደል ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦች አሁንም ሰበብ የሚያደርጉት ህገ-መንግሥቱን ነው። በእኔ እምነት ግን እንዲህ አይነት ግለሰቦች ተጠያቂነት ከራስ ላይ ለማውረድ ነው። ከችግር መውጣት የምንሻ ከሆነ ተጠያቂነትንም አብረን መውሰድ አለብን።
ለምሳሌ እኔ አንቀፅ 39 በተለይ መገንጠል የምትለው ሃሳብ ብትወጣ ደስ ይለኛል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አንቀፅ 47 ማንኛውም ብሔረሰብ በማንኛውም ጊዜ የራሱን ክልል መመሰረት እንደሚችል መደንገጉ ተገቢነቱ አይታየኝም። ምክንያቱም ስለጠየቁ ብቻ 76 ክልል መመስረት አይቻልም። ምክንያቱም ያንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም የለንም። ስለዚህ ይህ አንቀጽ ቢሻሻል ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። በአጠቃላይ ግን ህገ-መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ ከመቀየር ይልቅ መሻሻሉ ላይ ብንስማማ ጥሩ ነው። ከሁሉ በላይ ግን የክልሎች ህገ-መንግሥት በመሰረታዊነት መሻሻል አለበት። ሊያሻሽሉ የሚገቡት የክልሎቹ ህዝቦች ናቸው። ያ ማለት ክልላቸው ውስጥ የሚኖረውንም ዜጋ መብት ባስጠበቀ መልኩ ሊሆን ነው የሚገባው። ለሌሎች ማህበረሰቦች እውቅና መስጠት አለባቸው፤ በፈለገው ቋንቋ ሊናገርና ሊስተናገድ ይገባል። እንደሃገር አብረን እንቀጥል ካልን የሚያዋጣን ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሃይለየሱስ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014