‹‹በምንሰራው የጥራት ናሙና ላይ የሚቀርበው  ቅሬታ ከአንድ ፐርሰንት በታች ነው››  – አቶ በኃይሉ ንጉሴ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገበያና ግብይት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ

የገበያ ትርጉም በተለምዶ ሰዎች ምርታቸውን በመሸጥ የሌላቸውን ምርት የሚሸምቱበት መንገድ ነው:: የተለምዷዊ ግብይት ስርዓት በዘመናዊ መንገድ ግብይት ሲከናወን ለህዝብም ሆነ ለሀገር ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው:: መንግስት ተለምዷዊ የሆነውን የግብይት ስርዓት በዘመናዊ መንገድ መምራት ያስችለው ዘንድ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በአዋጅ ቁጥር 550/1999 በድጋሜ በ1050/2009 አሻሽሎ አቋቁሟል::

ተቋሙ በውድድር ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ የሆነ የግብይት ስርዓት የመዘርጋት፤በሀገር ደረጃ የሚመረቱ የግብርና ውጤቶችን በተደራጀና ስርዓት፤ምርቶችን ተረክቦ፤ ደረጃ አውጥቶ፣ ከዝኖ፣ ሽጦ ገንዘቡን ለባለቤቱ የማስረከብ ኃላፊነት የተሰጠው፤በዚህም ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ ነው።

የዝግጅት ክፍላችን ተቋሙ የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት አኳያ የት ጋር ነው ? እስካሁን ባለው የስራ አፈጻጸም ለሀገርስ ምን ጥቅም አስገኘ? ግብይት ስርዓቱን ተወዳዳሪ በማድረግ ረገድ፤ የግብይት ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?፤ በተለይ በቡና ምርት እና በጥራጥሬ ምርቶች ግብይት ውስጥ ያለውን ችግር በምን መልኩ እየተፈታ ነው? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የምርት ገበያ የገበያና ግብይት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በኃይሉ ንጉሴ አነጋግሮ፤ ምላሻቸውን እንደሚከተለው አቅርቦታል::

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በአዋጅ የተቀመጡለትን ኃላፊነቶችን ከመፈጸም አንጻር ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ በኃይሉ፡- በአዋጁ ተቆጥረው የተሰጡንን ስራዎች እያከናወነውን ነው:: ገበያውን ከእጅ በእጅ ግብይት ወደ ቴክኖሎጂ የታገዘ ግብይት የማሸጋገር ስራንም በሙከራ ደረጃ ፓይለት አድርገናል:: እሱን ለማሳደግ ጠንክረን መስራት አለብን ብለን በ2017 ዓ.ም እቅዳችን ላይ ይዘነዋል:: ይህንን የወደፊት ግብይትን ማጥናት፣ አዋጭነቱን ማጥናት እንዲሁም ተግባራዊነቱን ማጥናት አለብን የሚለውን በእቅዳችን ላይ ይዘን እየሰራን ነው:: ተጠሪነታችን ለንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ለፓርላማ እና ንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ነው:: በየጊዜው ሪፖርቶችን እየላክን ይገመገማል፤ ግብረመልሶችን እናገኛለን:: ከሞላ ጎደል መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ተቋሙ በተልዕኮ የተሰጠውን እየፈጸመ ነው::

በአዋጁ ላይ በግልጽ የተሰጠን በውድድር ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ የሆነ የግብይት ስርዓት መዘርጋት ነው:: ገበያው ሲጀመር የቀን ማስተጋባት ወይም ማስነገር የግብይት ስርዓት የሚባል ነበር:: ብዙ ገዥዎችና ብዙ ሻጮች መድረክ ላይ ተገናኝተው ዋጋቸውን፤ የምርታቸውን አይነት፤ ምርት የሚገኝበትን ቦታ እየጠቀሱ ድርድር የሚያደርጉበት፤ በአካል ተገናኝተው የሚገበያዩበት የግብይት ስርዓት ነበር:: ምርት ገበያው ያንን የግብይት ስርዓት ለስምንት ዓመታት አካባቢ ሲጠቀምበት ቆይቶ አሁን ወደ ኢሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት ማሸጋገር ችሏል:: ይህ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓት ድሮ ሰዎች በአካል ተገናኝተው የሚያደርጉትን ግብይት ከኮምፒውተር ላይ ቁጭ ብለው ግብይት የሚያደርጉበትን የግብይት ስርዓት መዘርጋት ችለናል:: ዲጂታላዜሽን እንደ ሀገር ስትራቴጂ ሆኖ እየሰራንበት ያለ ስራ በመሆኑ የኦንላይን የግብይት ስርዓት ለምቶ በሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛል::

አዲስ ዘመን፡- ግብይቱን ከማዘመን አንጻር የተመዘገቡ ስኬቶች ምንድን ናቸው?

አቶ በኃይሉ፡– ከስኬቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው ዘመናዊ ግብይትን በራሱ ማንበር ወይ መፍጠር እና ማዝለቅ እንዱ ነው:: በሌሎች ሀገራት ሲታይ ምርት የሚከዝን፤ ጥራት የሚያወጣ፤ ገበያ፤ ተገበያዩም ክፍያ የሚፈጽምበት የተለያዩ ተቋማዊ አደረጃጀቶች አሏቸው:: በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እነዚህ ተቋማት በሌሉበት የተፈጠረ ተቋም ነው:: ምርቶችን ተረክቦ፤ ደረጃ አውጥቶ፣ ከዝኖ፣ሽጦ ገንዘቡን ለባለቤቱ ማስረከብ፤ይህንን ችግሮች ሳይከሰቱ ማሳካት እንደ ስኬት የሚወሰድ ነው:: ከአዲስ አበባ በአንድ መጋዘን ተነስተን ዛሬ ላይ በሀገሪቱ 25 ቦታዎች ላይ አገልግሎት የምንሰጥባቸው መጋዘኖችና ቢሮዎች ተዘጋጅተዋል:: ሁለት ቦታዎች ላይ ደግሞ ሌሎች የግብይት አማራጭ ለሚያስፈልጋቸው ምርቶች የምድር ሚዛን አገልግሎት የምሰጥባቸው መጋዘኖች ተደራጅተዋል::

ከግብይትም አንጻር ሲታይ ግብይት አዲስ አበባ ላይ በዋና ቢሮ የተጀመረ ነበር:: አሁን ላይ ግን በስድስት ቦታዎች ላይ ልክ እዚህ አዲስ አበባ እንዳለው ሆኖ ግብይት የሚካሄድበት ስርዓት መፍጠር ተችሏል:: ከምናገበያያቸው ምርቶች አንጻር እንደ ስኬት ሊቆጠር የሚችለው ብዝሃ ምርቶችን ወደ ግብይ ስርዓት ማምጣታችን ነው:: እነዚህ ምርቶች ደግሞ ለውጭ ገበያ የሚውሉ ናቸው:: እንደ ሀገር የግብይት ስርዓት መፍጠር የገበያ መሰረተ ልማት የሚባለው ከ‹‹ሀረድዌሩ›› ባለፈ ‹‹ሶፍትዌሩ›› የሰው ኃይል ላይ ዘመናዊ ገበያ ያስፈልጋል የሚለውን አመለካከት መቅረጽ አስፈላጊ ነው::

እስካሁን የምናገበያየው የግብርና ምርቶችን ሲሆን አሁን ላይ የኢንዱስትሪ ምርቶች ለማገበያየት ውይይቶች እየተደረጉ ነው:: ምርት ገበያ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ መረጃዎች ተደራጅተው ተቀምጠዋል:: ይህ መሆኑ ለምርምር፣ ለፖሊሲ ጥናት ይሁን ትልቅ አቅም አለ:: ገበያው በራሱ የቆመ አይደለም:: የተፈጠረው ስነምህዳር ነው:: ይህም ምርት ክምችትን ከምርት ግብይቱ፤ ምርት ክምችቱን ከፋይናንስ ስርዓቱ እና ከታከስ ስርዓቱ ጋር እንዲገናኝ ተደርጓል:: በእኛ ግብይት ስርዓት ውስጥ መጥቶ የሚገበያዩ ምርቶች ታክስ ይሰበስብባቸዋል::

እስካሁን ባደረግናቸው ግብይቶች ወደ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ታክስ ለሚመለከተው አካል ማስገባት ችለናል:: አቅምን ለማሳደግ ደግሞ የምርት ገበያ አካዳሚ ገንብተናል:: አካዳሚው ለምናገበያያቸው ምርቶች በኢንዱስትሪ ላይ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለመድፈን በተለያዩ መስኮች ስልጠናዎችን እንሰጣለን:: የቡና ቅምሻ ስልጠና፤ የጥራጥሬና ቅባት፤ የምርት ጥራት ምደባ፤ የኤሌክትሮ ግብይት ስልጠና እንሰጣለን:: አካዳሚው ለሌሎች ሀገራትም ጭምር ስልጠና እየሰጠ ነው:: ግብጽ፤ ኬንያ፤ አንጎላ፤ ሞዛምቢክና መሰል የአፍሪካ ሀገራት እስከ 10 ሺ ዶላር ከፍለው ስልጠና ወስደዋል:: ቆዳና ሌጦ ላይ ጥናቶች ተሰርተዋል:: አቅም ከመገንባት አንጻር ከ8 ሺ በላይ ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ስራ አስገብቷል:: ገበያዎች ላይ ብዙ ወጣቶች ስራ ላይ ናቸው::

አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በቡና ምርቱ ምን ያህል ቶን ግብይት ተፈጸመ?

አቶ በኃይሉ፡– በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 20 ሺ ሜትሪክ ቶን የሚሆን የቡና ግብይት ተፈጽሟል:: ከተደረገው ግብይት ከፍተኛው የሀገር ውስጥ ግብይት ነው:: የሀገር ውጭ የቡና ግብይት ላይ በገጠመን ችግር ምክንያት አቁመን ነበር:: ችግሩን ለመፍታት ከግብርና ሚኒስቴር እና ከንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን አቅጣጫ ተቀምጧል:: በሚቀጥሉት ቀናት የኤክስፖርት ቡና ግብይት በሰፊው ይደረጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን::

አዲስ ዘመን፡- የሀገር ውጭ የቡና ግብይቱ እንዲቆም የተደረገበት ምክንያት ምን ነበር?

አቶ በኃይሉ፡– የቡና ግብይት የሚገበያይበት አውድ ከሌሎቹ የተለየ ነው። የተለየ የሚያደርገው የቡናና ሻይ ባለስልጣን የሚያስቀምጠው የቡና ዋጋ ገደብ አለ:: የቡና ዋጋ ገደብ ለምን መጣ? ከተባለ በግብይት ስርዓት ውስጥ ያለው አንድ ችግር ምርቶች በሀገር ውስጥ የሚገዙበት ወይም የሚሸጡበት ዋጋ እና ወደ ውጪ የሚሸጥበት ዋጋ የተናበበ አልነበረም:: የዚህ መሰረታዊ ችግር የእኛ የውጭ ምንዛሬ ወይንም ‹‹ፎርኤክስ›› ለገበያ የተለቀቀው ትክክለኛ ‹‹ቫሊው›› የተደረገ አልነበረም:: በዚህ ምክንያት በተለይ ላኪዎች ቡናን ወይም ሌሎች ምርቶችን ሀገር ውስጥ በከፍተኛ ዋጋ ይገዙና ከሀገር ውጭ ሲሄዱ የሚሸጡት በዝቅተኛ ዋጋ ነው:: ያንን ኪሳራ ለማጣራት ወደ ውጭ በሚልካቸው ምርቶች ላይ ዋጋ እየጨመሩ ትርፋቸውን ሲያጣሩ ነበር::

ላለፉት ዓመታት ስንቸገርበት የነበረው አንዱ ነገር ምርቶች የሚገበያዩት በትክክለኛ ዋጋቸው አልነበረም:: ስለዚህ ከዛ ጋር ተያይዞ ቡና እና ሻይም ምርቶች በከፍተኛ ዋጋ ነው የሚሸጡት ስለሚባል የቡና ዋጋ ይሰጠን ነበር:: የቡና ዋጋ ከዚህ ውጪ ካልሆነ እንዳታገበያዩ በሚል ባለስልጣኑ ዋጋ ተምኖ ይሰጠን ነበር:: ሌላው የነበረው ችግር የሚተመነው የቡና ዋጋ ትክክለኛ ዋጋው አልነበረም::

ምክንያቱም ሰዎች ወደ እዚህ ገበያ እየመጡ አልነበረም:: ሌሎች አማራጭ የግብይት ስርዓቶች ስለነበሩ እዛ ሄደው ግብይት ያደርጋሉ:: በቅርቡ በተደረጉ ንግግሮች የግብርና እና የንግድና ቀጠናዊ ሚኒስትሮች አቅጣጫ አስቀምጠውልናል:: ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ጋር ተነጋግረን ለገበያው የቀረበ የቡና ዋጋ ደረጃ ተቀምጦ ግብይቶች የሚጀመሩበት አግባብ በዚህ ሳምንት ተግባራዊ ይሆናል:: ስለዚህ ያለው ችግር ከሞላ ጎደል ተቀርፏል ማለት እንችላለን::

አዲስ ዘመን፡- በተያዘው በጀት ሩብ ዓመት ላይ የውጭ ሀገር የምርት ገበያ አለመኖሩ ምን ክፍተት ፈጠረ?

አቶ በኃይሉ፡– እንደገበያ የምናገበያያቸው ምርቶች ቀንሰዋል:: ነገር ግን ያለን አቋም አማራጭ የግብይት ስርዓቶች መኖር አለባቸው የሚል ነው:: ሰዎች በአንድ የገበያ አማራጭ ብቻ መገደብ የለባቸውም:: ይህ ገበያ ሲቋቋም ሁሉም ምርቶች በአስገዳጅነት የሚገቡበት የግብይት ስርዓት ነበር:: ነገር ግን ከጊዜ ወደጊዜ የተገበያዮች ፍላጎት ታክሎበት መንግስት አማራጭ የግብይት ስርዓቶችን ዘርግቷል:: እኛ ደግሞ እነዛን የግብይት ስርዓቶች እንዲዘረጉ የራሳችንን አበርክቶ አድርገናል:: ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮምን በጣም ያበረታው የሳፋሪኮም ወደ ውድድር መምጣቱ ነው::

ስለዚህ የምናስበው የውድድር መንፈሱ ይፈጠራል፤ ከአማራጭ የግብይት ስርዓቶች ጋር ተወዳድረን ለማሸነፍ ጠንክረን እንሰራለን:: በአጋጣሚ አሁን ላይ የተፈታው እና ትክክል ያልነበረው በባለስልጣን መስሪያ ቤት እየተተመነ የሚላከው እና የሚሰራበትም መንገድ ትክክል ስላልነበር የተፈታበት መንገድ አለ:: ምርት ገበያውም ተወዳድሮ በአገልግሎት አሰጣጡ ተመራጭ ሆኖ፣ ደንበኞችን ስቦ ለደንበኞች የተቀላጠፈ ወጪ ቆጣቢ የሆነ የግብይት አገልግሎት በመስጠት ማሸነፍ አለበት ብለን ስለምናስብ ባለፉት ዓመታት የነበሩበት ነገሮች ከዚህ በኋላ ለምንሰራው ስራ ትምህርት ሰጪ ናቸው:: ወደ ኦንላይን ለመውጣት ያሰብነው ከእነዚህ ትምህርት በመነሳት ነው::

ከማገበያየት አንጻር ከፍተኛ የሆኑ ምርቶች በሌሎች አማራጭ የግብይት ስርዓቶች እየተገበያዩ ነው:: ነገር ግን እንደሀገር እስከመጨረሻው ዓላማችን አንድ ነው:: በማንኛውም መንገድ ብንሄድ እነዚህ ምርቶች ተወዳዳሪ ሆነው በጥራት ተመርተው ዓለም ገበያ ውስጥ ገብተው አሸንፈው ለሀገር የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እስካመጡ ድረስ በተፈጠረው ስነ-ምህዳር ውስጥ እኛ የምንጫወተው ሚና አለ:: ለአብነት ብንጠቅስ እኛ ጋር ባይገበያዩም እነዚህ ምርቶች ሲመጡ የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት ልንሰጥ እንችላለን፣ የምድር የምርት ምዘና አገልግሎት ልንሰጥ እንችላለን፣ ምርቶቹን ማስቀመጥ ለሚፈልጉ ደግሞ የመጋዘን አገልግሎት እንሰጣለን:: ስለዚህ በዚህ ውስጥም ሚና አለን:: ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ስናገበያየው ከነበረው መጠን አንጻር ሲታይ ቅናሽ አሳይቷል:: ይህ እንደ አንድ ክፍተት የሚታይ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ተጥሎ የነበረው የቡና መገበያያ ተመን ሙሉ በሙሉ ተነስቷል? ከዚህ በኋላስ ትክክለኛ ተመን እንዲወጣ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?

አቶ በኃይሉ፡– አሁን ተመኑ በትክክለኛው መንገድ እንዲተመን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አቅጣጫ ተቀምጧል:: ይህ ተመን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተግራዊ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን:: ተመኑ የሚሰራው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ነው:: ለምሳሌ በዓለም ላይ ዛሬ ቡና የሚገዛበት ዋጋ ይታወቃል:: ሂሳቡን የሚሰራው ኔትዎርክ ላይ ነው:: ኢትዮጵያ ላይ ቡና በስንት አካባቢ መሸጥ አለበት? ብሎ ተቀናሽ የሚሆኑ ወጪዎችን ቀንሶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የሚኖረውን ተመን ይዞ ነው:: ስለዚህ የምናስበው ተመኑ ማንም ተመነው ማንም በቀመር የሚሰራ ስለሆነ ትክክለኛ ተመን ይሆናል ብለን ነው::

እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ‹‹ሪፎርሙ›› ከታች እስካለው ገበሬ ድረስ መውረድ አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል:: ስለዚህ ይህንን ለማሳካት የተያዘ ስለሆነ በቅርበት ከቡና እና ሻይ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመስራት ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጧል::

አዲስ ዘመን፡- የኒውዮርክ ገበያን በመመልከት ዋጋ እንደምታወጡ ይታወቃል፤ የኒውዮርክ ገበያ ብዙ ጊዜ በካፒታሊስት ባለሀብቶች የሚመራ ነው:: ከዚህ አንጻር ጥቅም እና ጉዳቱን እንዴት ይገልጹታል? የኒውዮርክን ገበያ መሰረት ከማድረግ ውጭስ ሌሎች አማራጮች አሉ?

አቶ በኃይሉ፡– ኒዮርክ ላይ የሚደረገው ገበያ ዋጋ አመላካች ነው:: ይህም ማለት ኒዮርክ ላይ የሚደረገው የቡና ገበያ አንዱ ‹‹ፊውቸርስ›› የሚባል ገበያ ነው:: ‹‹ፊውቸርስ›› ኮንትራት ማለት፤ እኛ የምናገበያየው እጅ በእጅ ነው:: ምርት፤ ገንዘብ ስለሚኖር እንቀያየራለን:: ኒዮርክ ላይ ግን ኮንትራት ይኖራል፤ ያን ኮንትራት መልሶ መሸጥ ይቻላል:: ምርትን የማስረከብ ግዴታ አይጣልም::

የኒዮርክ ገበያ ግብይት ዛሬ ተፈጽሞ የሚደርሰው ከሁለት ወይም ከሶስት ወር በኋላ ነው:: አመላካች ነው ያልኩበት ምክንያትም አሁን ጥቅምት ላይ ነው ያለነው፤ ታህሳስ ወይም ጥር ላይ የዓለም የቡና ዋጋ ወዴት ሊሄድ ይችላል? የሚለውን ትክክለኛውን ሳይሆን አመላካች የሆነውን ዋጋ ይሰጠናል::

በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ትልቁ ጥቅም የሚሆነው እኛ የምናመርታቸው ምርቶች በጣም በርካታ የሆነ ‹‹ስፔሻሊቲ›› ቡናዎችን ስለሆነ የሚተመኑት በኒዮርክ ገበያ አይደለም:: የሚወጣው ከገዢ ሀገር ነጋዴ ጋር እርስ በእርስ በሚደረግ ተመንና ድርድር ነው:: ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ቡና በጣም ተወዳዳሪ ከማድረግ አንጻር ከኒዮርክ በጣም ከፍ ባለ ዋጋ መሸጥ ያስችላል:: ጥራታቸው ዝቅ ያሉ ከኒዮርክ ዋጋ ዝቅ ባለ ዋጋ ግብይት የሚደረግበት አውድ አለ:: ለሌሎች ምርቶች እንዲሁ አመላካች ገበያዎች አሉ:: ሰሊጥ ህንድ፤ ቻይና ይገዛሉ:: በሀገራቱ አካባቢ ያለው ዋጋ ለእኛ ምልክት ይሆነናል:: ነገር ግን የኢትዮጵያ ሰሊጥ በትክክል ስንት ይገባዋል? ቢባል ሰሊጥ ከሌሎች ሀገራት ሰሊጥ ጋር ጥራቱ እኩል አይደለም:: የራሳችን የሆነ የመወዳደሪያ ዕድል ስላለን ላኪዎቻችን የሚደራደሩት ያንን ይዘው ነው::

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ከብዙ አምራች ሀገራት በተሻለ ተወዳጅ ቢሆን ከአመራረት አሰባሰብ ሂደቱ ጋር በተገናኘ በሚፈጠሩ የጥራት ችግሮች የሚሸጥበት ዋጋ ዝቅተኛ ነው:: ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በቅንጅት ከመስራት አኳያ ምን ታስቧል?

አቶ በኃይሉ፡– ይህንን ጥያቄ በተመለከተ ከእኔ በተሻለ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ቢመልስው ይሻላል:: ምክንያቱም የቡና እና ሻይ ከማስመረት ከሀገር ውጭ እስከመሸጥ ያለውን አጠቃላይ የግብይት ሰንሰለት የሚቆጣጠረው እሱ ነው:: ነገር ግን እኔ ከጥራት አንጻር በተለይ የምርቶችን ጥራት ከማሳደግ አንጻር አንድ የምናደርገው ነገር ለምርቶች ደረጃ እንሰጣለን::

ለምሳሌ የቦንጋ ምርት ሲመጣ የምርት ጥራት ደረጃ እናወጣለን:: ደረጃ የምንሰጠው ቦንጋ አካባቢ ያመረቱ ወረዳዎች ያገኙት የምርት ጥራት ደረጃ ምን እንደሚመስል ግብረመልስ በመስጠት ነው:: የምርት ጥራት ደረጃ እየተሻሻለ ነው ወይም ዝቅ እያለ ነው የሚል ግምገማ ይደረጋል::

አዲስዘመን፡- ምርት ገበያን በእጅጉ ይፈትኑታል የሚባሉት የጥራት ደረጃ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋል ሙስና ነው ይባላል፤ ችግሩን ለመከላከል ምን እየሰራችሁ ነው?

አቶ በኃይሉ፡– እንግዲህ ጥራት አስቸጋሪ ነገር ነው:: እንደፍልስፍና የምናስበው ብዙ ሰው ላመረተው ምርት ትክክለኛ የሆነ የጥራት ደረጃ ይዞ ትክክለኛ የሆነ ዋጋ ለማግኘት ይሰራል ብለን ነው:: ነገር ግን ግብይት ስርዓቶች ውስጥ ሌሎች ነገሮች ውስጥ እንዳለው ሁሉ አንዳንድ ሰው ደግሞ በራሱ በትክክለኛው መንገድ ያላገኘውን ለመጠቀም የሚፈልግ ይኖራል:: ይህ ተግባር ደግሞ የእኛን ሲስተም ይፈትናል:: በጥራት ደረጃ አሰጣጥ ውስጥ የሚኖሩ ችግሮች ይኖራሉ:: ነገር ግን አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ አሰራር ስርዓት መዘርጋት ነው::

የአሰራር ስርዓቱ አንድ የምርት ገበያ ላይ አንድ ሰው ምርቱን ይዞ ሲመጣ ተመዝግቦ ከምርቱ ናሙና ይወሰዳል:: ናሙናው ሲወሰድ ናሙናውን የሚወስዱት አካላት ወደላቦራቶሪ ሲልኩ የማን እንደሆነ አይታወቅም:: ልክ ደም ስንሰጥ በኮድ ተወስዶ ላቦራቶሪ ቴክኒሻኑ እንደሚመረምረው ኮድ ያደረግና ላቦራቶሪ ውስጥ ይገባል:: ላቦራቶሪ ውስጥ የሚሰራው አንድ ሰው አይደለም:: ፓናል ተደራጅቶ የሚከታተል ልምድ ያለው እና አባላት ያሉት ነው:: በዚህ ጥረት ትክክለኛውን የጥራት ደረጃ ለማምጣት ጥረት ይደረጋል:: አምራች ወይም ላኪ የጥራት ደረጃው ከተሰጠው በኋላ አቤቱታ ያቀርባል:: ይህ ትክክለኛ አይደለም የሚልበትን አግባብ ግብረ መልስ የሚሰጥ ቡድን አደራጅተናል::

አንድ አምራች ቅርንጫፍ ላይ ምርትህ ደረጃ ሶስት ነው ሲባል፤ ምርቴ ደረጃ ሁለት ነው የሚል ከሆነ ደረጃ ሁለት መሆኑንና አለመሆኑን ድጋሚ ይፈተሻል:: ካልተፈታ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተልኮ ይመረምራል:: ከዚያ ባሻገር ከሆነ ሌሎች ገለልተኛ ተቋማት መርምረው የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል:: ከምንሰራው ናሙና የሚቀርበው ቅሬታ ከአንድ ፐርሰንት በታች ቢሆንም አንድም ቅሬታ ቢሆን በትክክል መሰራት አለበት::

ከሙስና ጋር ተያይዞ እንዲህ አይነት ነገሮች በተጨባጭ መረጃዎች በእራሳችን ‹‹ኢንተለጀንስ›› እና በሰዎች ጥቆማ ካገኘን እርምጃ እንወስዳለን:: እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ምንም ትግስት አናደርግም:: ይህንን ለመስራት የክልል ቢሮዎችን ያካተተ የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚቴ አለ:: የአገልግሎት መስጫዎችን የተቀመጡ ሲሆን በዋና መስሪያ ቤት ደረጃ ቅሬታ የሚቀበሉ አሉ:: እንደዚህ አይነት ጥቆማዎችን እየወሰድን በተቻለ መጠን የእርምት እርምጃዎችን እንወስዳለን፤ ችግሩም እንዳይንሰራፋ ስራዎችን እየሰራን ነው:: ከዚህ ቀደም በጣም ብዙ እርምጃዎችን ወስደናል:: ብዙ ማሻሻያዎችንም አድርገናል:: በቅርቡም ከዋና መስሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ቅርንጫፎች ድረስ ትልቅ ማሻሻያ አድርገናል:: በርካታ ሰራተኞችንም ቀይረናል::

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከማዘመን አኳያ ምን እየሰራ ነው?

አቶ በኃይሉ፡– የምንሰጠው አገልግሎት የግብይት አገልግሎት ነው:: በዚህ አገልግሎት ላይ በቃል ከማስተጋባት ወደ ኤሌክትሮኒክ እንዲሄድ አድርገናል:: አሁንም ከኤሌክትሮኒክ ወደ ኦንላይን እንዲያድግ ተደርጓል:: ከተደራሽነት አንፃር አዲስ አበባ ስንሰራ የነበረውን ስራ ወደ ስድስት የክልል የገበያ ማዕከላት አሳድገናል:: ከግብይት ሞዴል አኳያ የነበረን አንድ ሞዴል ነበር:: አሁን ወደ ሶስት ሞዴል ማሻሻል ችለናል:: ሌሎችም የሚመጡ ምርቶች ሲኖሩም እንደ ባህሪያቸው እየታየ ሌሎች ሞዴሎችን እንፈጥራለን::

በመጋዘን አገልግሎት ላይ የሚዛን አገልግሎታችንን ዘመናዊ ለማድረግ ዲጂታል ሚዛኖችን የመግጠም ስራ ተሰርቷል:: የእኛ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች በሌሉበት ቦታዎች የሚዛን አገልግሎት ለመስጠት የሳተላይት ቅርንጫፎችን የማደራጀት፤ የምርት የጥራት ደረጃዎችን ለማሻሻል በተለይ በላብራቶሪ ውስጥ የሚሰሩ የሰው ኃይል እና መሳሪያዎችን በማደራጀት የመረጃ ቅብብሎሹንም ለማዘመን በርካታ ስራዎችን እየሰራን ነው::

ከማገበያየት ጀምሮ ማከማቸት፤ የምርት ደረጃ ሰርተፍኬት መስጠት እና ምርቶችን የማከም አገልግሎት ከግዜ ወደ ግዜ እየተሻሻሉ የመጡ አገልግሎቶች ናቸው:: ከትላንት ዛሬ የተሻለ ነው:: ከዛሬም ነገ የተሻለ ይሆናል:: በተለይ የዲጃታላይዜሽን ስራው ትልቅ አቅም ይሰጠናል:: ወደ ኦንላይን ስንሄድ፤ ወደ ቴሌ ክላውድ ሲስተም ስንገባ መጋዘኖቻችን አካባቢ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ስንተክል ከዛሬ የተሻለ አገልግሎት እንሰጣለን::

አዲስ ዘመን፡- ሲሚንቶ፤ ስኳር እና የኢንዱስትሪ ጨው ግብይት በምርት ገበያው እንዲካሄድ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ እንዳለ በሚዲያ ተነግሮ ነበር:: ጥናቱ ምን ደረጃ ላይ ነው? ወደ ትግበራ የሚገባው መቼ ነው?

አቶ በኃይሉ፡- በዚህ ቀን ማለት አንችልም፤ ምክንያቱም ቀኑ በእኛ የሚወሰን አይደለም:: እነዚህ ጉዳዮች ረጅም ግዜ ይወስዳሉ:: አንዳንዶቹ ጥናቶች ተጠንተው ለረጅም ግዜ ይቀመጡና የሆነ ግዜ ላይ ይነሳሉ:: ለምሳሌ ስሚንቶ ላይ ሰፊ የአዋጭነት ጥናት አጥንተናል:: የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማየት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ንግግር አድርገናል:: እንደ ምርት ገበያ ማቅረብ የምንችለው ‹‹ፕሮፖዛል››ነው:: ማዕድን ሚኒስቴርም ጥናቱን አይቶ ገምግሞታል:: ነገር ግን ያለው ችግር አንድ ምርት ወደ ምርት ገበያ እንዲገባ በበቂ ሁኔታ መመረት መቻል አለበት:: ስለዚህ ስሚንቶ ላይ ያለው አንዱ ፈተና በበቂ አለመመረቱ ነው::

አሁን ተስፋ የምናደርገው አዲስ የተገነቡ የስሚንቶ ፋብሪካዎች አሉ:: የሀገራችንን የስሚንቶ ምርትን በ50 በመቶ ሊጨምር የሚችል ፋብሪካ አሁን በቅርቡ ተመርቋል:: ይህ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ገበያው ላይ በበቂ ሲሚንቶ እንዲኖር ያስችላል:: ከሀገራችን አልፈንም ለኤክስፖርት ልናቀርብ እንችላለን:: ያንጊዜ የተደራጀ ገበያ ያስፈልጋል:: አሁን ላይ ግን እጥረቱ ስላለ ግብይት የሚፈጸመው ፋብሪካው በር ላይ ነው:: በተመሳሳይም የስኳር ምርታማነታችን ላይ እየተሰራበት ነው:: ምርቶቹ ገበያ ላይ በበቂ ሲኖሩ የተደራጀ፤ ዘመናዊ፤ ፍትሃዊ እና ተወዳዳሪ ገበያ ስለሚያፈልግ ጥናቱን አጥንተን ይዘናል::

አዲስ ዘመን፡- የጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎቹ ምን ያህል ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ እና አስተማማኝ ናቸው?

አቶ በኃይሉ፡– የጥራት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎቻችን ዘመናዊ የሚባሉ ናቸው:: ለምዘና ስራ የሚውሉ መሳሪዎች እና የምርት ጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎቻችን በየዓመቱ በኢትዮጵያ ስነልክ ኢንስቲትዩት ፍተሻ ይደረግባቸዋል:: የስነልክ ኢንስቲትዩት ልኬት ያላደረገባቸው የሚዛን መሳሪዎች፤ የምርት ልኬት መሳሪያዎች እና የምርት ጥራት መሳሪያዎች ስራ ላይ አይውሉም:: እንደ ምርት ገበያ በየዓመቱ በዝግጅት ምዕራፍ ከምንሰራቸው ስራዎች አንዱ ያንን መሳሪያዎች ቆጥሮ ለቅሞ ለስነልክ ኢንስቲትዩት የፍተሻ እና የማረጋገጫ ስራ ይሰራልን ብሎ ማቅረብ ነው:: መሳሪዎቹ ተፈትሸው ልክ ናቸው ሲባሉ ብቻ ወደ ስራ እናስገባለን::

አዲስ ዘመን፡- የምትፈልጓቸውን አይነት የጥራት ልኬት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በበቂ ገበያው ላይ የማግኘት ሂደት ምን ይመስላል?

አቶ በኃይሉ፡- ምርት ገበያው ለራሱ ሲቀጥር አሰልጥኖ እና ፈትኖ ስለሚቀጥር ብዙ ችግር የለም:: ብዙ የተማረ የሰው ኃይል ስላለ የራሳችንን አቅም እያሳደግን እና እያሰለጠንን እንሄዳለን:: የምርት ገበያ አካዳሚ አንዱ እና ዋነኛው ጠቀሜታው በቡና እና በቅባት እህሎች ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል መፈጠር ነው:: ምርቶቻችን በጥራት እንዲመረቱ እና በጥራት ከሀገር እንዲወጡ ከተፈለገ ሰዎች ላይ መሰራት አለበት:: እውቀት እና ክህሎት ያለው ባለሙያም ያስፈልጋል::

አካዳሚው የሚያደርገውም ተምረው እውቀት ይዘው ቀጥታ ኢንዱስትሪው ላይ የሚሰሩ ሰዎችን ከማፍራት አኳያ በቡና ቅምሻ እና በጥራጥሬና በቅባት እህሎች ስልጠና እየሰጠ ነው:: እኛ ስልጠናዎችን እንሰጣለን ለራሳችን ሰዎችን ስንፈልግ አወዳድረን እንቀጥራለን:: ኢንዱስትሪዎችም በተመሳሳይ ሰልጣኞችን ይቀጥራሉ:: ስለዚህ ኢንዱስትሪዎች ላይ ያለውንም ክፍተት እንሞላለን::

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ያቀደው እቅድ ምንድን ነው?

አቶ በኃይሉ፡– የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ዘመናዊ በሆነ የግብይት ስርዓት ውስጥ እንዲገበያዩ እናልማለን:: ኢትዮጵያ በቅርቡ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ትሆናለች:: በአፍሪካ ደረጃ የነጻ ገበያ ስራዎች ተጀምረዋል:: እንደምርት ገበያ የአፍሪካ የምርት ገበያ አባል ነን:: በዛም የምንሰራቸው ስራዎች አሉ:: ራዕያችን በአፍሪካ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የሆነ የግብይት ማዕከል መሆን ነው:: የንግድ ዘርፉ ተዋንያን ፍትሃዊ እና ተወዳዳሪ የሆነ የገበያ ስርዓት ውስጥ እንዲሳተፉ እና በዘመናዊ የገበያ ስርዓት ውስጥ የሚመነጩ መረጃዎችን ለታክስ ስርዓታችን አስተሳስረን በመጠቀም የበለጸገ ሀገር እንዲኖረን ያስችለናል::

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

አቶ በኃይሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

መክሊት ወንዶሰን እና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

 

Recommended For You