ነጋዴ ሴቶች በንግዱ ዓለም ከወንዱ እኩል እንዳይንቀሳቀሱ ሰቅዟቸው የሚይዛቸው ብዙ ችግሮች አሉባቸው ።
የመንግስት የግዢ ስርዓት ለሴቶች ምቹ አለመሆኑ አንዱ ነው። ሌላው የአገራችን ኔትወርክ ሲስተምና ነባሩ አመለካከት ለሴቶች እንደ ወንዶች የተመቸ አለመሆን ነው። ሴቶች እንደ ወንዶች በመዝናኛ ቦታዎች እየተዝናኑ በንግድ ሥራቸው ዙሪያ ማውራትና በዋጋ መደራደር አይችሉም። ባህሉም አይፈቅድላቸዋል። አሉ ቢባል እንኳ ከአንድና ሁለት የማይበልጡና አብላጫውን የአገራችንን ሴቶች ቁጥር የማይወክሉ ናቸው። ቢያደርጉትም “እከሌን … አየሃት” የሚሉ ወንዶች መጠቋቆሚያ የሚሆኑበት ጊዜ ቀላል አይደለም።
አንዳንድ ሴቶች እንደሰጡን አስተያየት ጨረታዎችን ቢያሸንፉ እንኳን በሴትነታቸው ተጨማሪ ነገር ይጠየቃሉ። በዚህ ላይ ብዙ ጊዜ ጨረታው ውስጥ ለውስጥ ካለቀ በኋላ ለይስሙላ ያህል በመውጣቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል የለም። በተጨማሪም በጨረታ ሂደቱ ተሞልተው የሚያልፉት ወረቀቶች በመቶ የሚቆጠሩ ናቸው። ጎረቤታችን በሆነችው ኬንያ ግን ይሄን ዓይነቱን የነጋዴ ሴቶች ችግር ለመፍታት ራሱን የቻለ የግዥ ጨረታ ቅጾቹን መሙላት የሚችሉበት ጽሕፈት ቤት ተከፍቶላቸዋል፡፡ የኛ አገር ሴቶች በዚህ መንገድ የታገዙ ስላልሆኑና ቅጾቹን የመሙላት ዕውቀቱ ስለሌላቸው ገንዘብ ከፍለው በመቅጠር ነው ሲያስሞሏቸው የነበሩት። እንዲህም አድርገው ሁሉንም ጨረታ የሚያሸንፉት ወንዶች ናቸው።
የኬንያ ሴቶች ኃይለኞችና እልኸኞች ናቸው። እንደ እኛ አገር ነጋዴ ሴቶች በሁለትና በሦስት ሙከራ ከጨዋታው አይወጡም። በመሆኑም እኛ ከዜሮ ሳንወጣ እነሱ 30 በመቶ ተጠቃሚ ሆነዋል። ካዊ (CAWEE – ሴንትራል ፎር አክሴሲቢሊቲ ቱ ውሜንስ ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት) እነዚህን ጨምሮ በአጠቃላይ በመስኩ የሚገጥሙ የነጋዴ ሴቶችን ችግሮች ለመፍታት የተቋቋመው በፈረንጆቹ 2004 ነው። የካዊ መሥራጨና ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ንግስት ኃይሌ ባለፈው ሳምንት ከአጋር አካላት ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ ካዊ ከ80 በላይ ነጋዴ ሴቶችን በአባልነት ማቀፍና ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ከ20 አገራት በላይም ነጋዴ ሴቶችን ይዞ የገበያውን እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።
ሴቶቹ ምርቶቻቸውን በዚህ ዓይነቱ ጉብኝትና በስልጠና በመታገዝ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ አገራት እንዲልኩና መላክ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያጎለብቱ አስችሏል። ያኔ ወደ ሥራ ሲገቡ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ አገራት መላክ ቀርቶ እነሱ ራሳቸው ውጭ አገር ሄደው እንኳን የማያውቁ አባላት ነበሩት። ምርትን ወደ ውጪ የመላክ ዕውቀትም አልነበራቸውም። እነዚህ ሴቶች አሁን ላይ ምርቶቻቸውን አራትና በላይ ወደ ሚደርሱ አገራት መላክ ችለዋል። ለዚህ ደግሞ የኔክስት ፋሽን፣ የደሀብ ኮፊ፣ የሜሮን ሌዘር ፕሮዳክት ለአብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
እነዚህ ከአባላቱም ብዙዎቹ ነጋዴ ሴቶች ቀድሞ በተቋሙ አማካኝነት ወደ ውጪ አገራት ሄደዋል። የውጪውን ገበያ አይተው፣ ከገዢ ጋር የተገናኙበትና ከነጋዴ ጋር የተወያዩበትም አለ። በመሆኑም ናሙና በመስጠት፣ በመስማማት ምርታቸውን ወደ ውጪ አገራት መላክና በንግድ ሂደታቸው ወደ እድገት ማማ ለመሸጋገር በቅተዋል።
ብዙዎቹ የካዊ አባላት ወደ እዚህ ደረጃ ለመድረሳቸው ማሳያ ሲጠየቁ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ይናገራሉ። ከአንድ በላይ የንግድ ቅርንጫፎች መክፈታቸውንም ይጠቅሳሉ። እኛ እንዳረጋገጥነው ሜሮን የሌዘር ፕሮዳክት የካዌ አባል ከሆነች በኋላ ምርቷን ወደ ውጪ አገራት ከመላክ አልፋ አራት ኪሎ መሐል ያለውን መደብሯን ጨምሮ አራት የሌዘር ፕሮዳክት ቅርንጫፎችን መክፈት ችላለች። ሜሮን እዚህ ደረጃ መድረስ የቻለችው ከካዊ ጋር በተያያዘ ድጋፍ ነው። እንደ ካዊ መሥራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ንግስት ኃይሌ ሁሉም ነጋዴ ሴቶች እንዲህ ለውጥ ማምጣት የቻሉት የካዊ አባል ከሆኑ በኋላ በሚደረግላቸው ድጋፍ ነው። ለምሳሌ፣ ካዊ ከጃፓን መንግስት አግኝቶት በነበረው ድጋፍ ለሜሮን ከ30 በላይ የስፌት መሣርያዎችን እንደሰጣት ይናገራሉ። እንደዚሁም በሌዘር ፕሮዳክት መስኩ 12 ወጣት ሰራተኞችን እንዳሰለጠነላትም ይጠቅሳሉ። ለሜሮን ሌዘር ፕሮዳክት ለ12 ሰው የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በተለያዩ ስፍራዎች አራት ቅርንጫፎችን መክፈትና በአጠቃላይ አቅም መፍጠር ያስቻላትም ይሄው የካዊ ድጋፍ እንደሆነ ወይዘሮ ንግስት ያሰምሩበታል። ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትም ችግሩን በመፍታቱ ረገድ የራሷን አስተዋጾ እንድታደርግ አስችሏታል።
እንደ ዳይሬክተሯ ወደ ስድስት የሚጠጉ ዘርፎች ከ80 በላይ አባሎቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ይንቀሳቀሳሉ። አንዱ እርሻ ሲሆን ከአረንጓዴ ቡና ልማት ይጀምራል። ቡናውን በጥሬ፣ በመቁላትና በመፍጨት እሴት ጨምረው ወደ ውጪ ሀገር የሚልኩ አሉ። በዚሁ በእርሻ ዘርፍ አይብና የተለያዩ ወተትና የወተት ተዋፅኦ ምርቶችን የሚያመርቱና ወደ ውጪ የሚልኩም አባላት ይገኙበታል። በተለይ ባህር ዳር ያሉ አባላቶቻቸው በዚህ የሚጠቀሱ ናቸው። እንዲሁም በሁሉም በተለይም በኦሮሚያ ክልል በርካታ የማር ምርት በማምረትና ወደ ውጪ በመላክ የተሰማሩ አባላቶች አሏቸው። ቅመማ ቅመምና ከጤፍ የሚሰሩ የተለያዩ ምርቶችን እሴት በመጨመር ወደ ውጪ የሚልኩ አባላቶቻቸውም ቁጥራቸው በርካታ ነው።
ሌላው ዘርፍ ስፌትና ጨርቃ ጨርቅ ሲሆን በዚህም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አባላት አሏቸው። ቆዳ ሦስተኛው ዘርፍ ሲሆን አራተኛው የከበሩ ድንጋዮች ላይ አባላቶቻቸው እሴት ጨምረው ወደ ውጪ የሚልኩበት ነው። አምስተኛው የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሆነም ወይዘሮ ንግስት ገልፀውልናል። እነዚህ አባላቶቻቸው በቱሪዝምና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩና የየራሳቸው አማካሪ ያላቸው የሕግ ባለሙዎች ጭምር እንደሆኑም ነግረውናል።
ስድተኛው ‹‹ቴክኖ ስታይል›› የተሰኘና ምርት ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባ፣ በእንጨት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ዘርፍ ላይም አባላቶቻቸው እንዲሰሩ ያደርጋሉ። ሌሎች ዘርፎችን ጨምሮ አባላቶቹን የማሳተፍ ዕቅድ አለው። በነዚህ መስኮች ላይ ያተኮሩና ከኤ እስከ ዜድ ያሉ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን የሚሰጠውም ይሄው ካዊ ማእከል ነው።
በካዊ ማንም ምርቱን ወደ ውጪ መላክ ስለፈለገ አይልክም። አባላቶቹ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ለመላክ ዝግጅት እንዲያደርጉ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ እገዛዎችን ያደርጋል። ምርታቸውን ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችል ቢዝነስ ፕላን ያላቸው መሆኑንና ፕላኑን የት እንደሚያዘጋጁት እንዲሁም ምርታቸው የምርት ጥራት ደረጃ ያለውና የሌለው መሆኑን፣ ወጪያቸውን የተመለከቱ ግንዛቤዎችን ያስጨብጣል። ለአባላቶቻቸው ለሚሰጡት ስልጠና ድሮ ፈረንጆች እያመጡ ቢሰጡም አሁን አይሲቲን ጨምሮ ሀገር ውስጥ በመስኮቹ የሰለጠኑ አሰልጣኞች ስላሉ እነዚህን አቅሞች በመጠቀም የሚሰጡ እንደሆነ ነግረውናል። በአጠቃላይ ማእከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለውን አቅሙን አጎልብቷል።
አቅሙን ማጎልበት በመቻሉም እስከ አሁን በነበረው እንቅስቃሴ ወደ 20 ያህል የውጪ ሀገሮች ሄዶ አባላቶቹ በንግዱ መስክ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አስችሏል። ከነዚህ ሀገሮች መካከል መጨረሻ የሄደው ዴንማርክ ሲሆን ኖርዌይ፣ ሲውዲንና ፊንላንድንም ቀደም ብሎ ጎብኝቷል።
ከኮቪድ በኋላ እየተመረመሩ መሄድ ሲጀመር በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2021 መጨረሻ ኢንትራ-አፍሪካ ትሬድ የተሰኘና የአፍሪካ ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ ከአፍሪካ ዩኒዬን ጋር በሚያዘጋጁት ሳውዝ አፍሪካ፣ ደርባን ላይ በነበረ ዕድል አባላቶቻቸውን አሳትፈው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል አመቻችቷል። አሁን ላይ በዚህ ታላቅ የንግድ ዕድል የተሳተፉ አባላቶቻቸው የምርት ሳንፕሎቻቸውን ወደ ደርባን እየላኩ ይገኛሉ። በቀጣይ የፈረንጆቹ ወርም አባላቶቹን ወደ ኔዘርላንድስ ይዞ ለመሄድ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በጉዞው የሚሳተፉና ተጠቃሚ የሚሆኑት በግብርና እና በቆዳ መስኮች የተሰማሩ ናቸው። በእርሻ ከተሰማሩትና ኔዘርላንድስ ከሚሄዱት ተጓዥ ሴቶች መካከል የካዊ አባል በመሆናቸው የንግድ ድርጅታቸው ታዋቂነትን እያገኘ ያለው የ‹‹ደሀብ ኮፊ›› ባለቤት እንደሚገኙበት ማወቅ ችለናል። አውሮፓን ጨምሮ በብዙ አገራት የኢትዮጵያን ቡና ከመፈለግ አንፃር ‹‹ደሀብ ኮፊ›› በኔዘርላንድ የተሻለ ገበያ እንደሚገጥማት አያጠራጥርም። እነዚህ አባላቶቻቸው በኔዘርላንድ ምርታቸውን ከሚወስዱላቸው ጋር ይገናኙና ይደራደራሉ። በአጠቃላይም የቢዝነስ ውል ጨርሰው ይመጣሉ ተብሎ ይታሰባል። እንደ ወይዘሮ ንግስት አገላለፅ ይህ አሰራር አባላቶቻቸው ምርቶቻቸውን የሚልኩባቸው የውጪ አገራት እንዲበራከቱ ያደርጋል። አንዲት ሴት ምርቷን አራት አገራት ትልክ የነበረ ከሆነ ኔዘር ላንድ ሲጨመርላት አምስት አገራት እንድትልክ የሚያስችል ዕድል ይፈጠርላታል። ከኔዘርላንዱ ጉዞ ቀጥሎ ወደ ካናዳ ስለሚዘልቅ በተለይ በእርሻው ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ሴት ነጋዴዎች ምርታቸውን የሚልኩባቸውን የውጪ አገራት ቁጥር በእጅጉ ያሳድገዋል። በተጨማሪም ሴቶቹ ውጭ ሀገር ሄደው የማያውቁ ከሆኑ አገሩንና ገበያውን እንዲያዩ የማድረግ ዕድልን ይፈጥራል። “ምርቶቹ ምን ይመስላሉ፣ የኔ ምርት ከእነዚህ የሚለየው በምንድነው፣ እኔ እንዴት አድርጌ በዚህ አገር ላይ ምርቶቼን ለገበያ ማቅረብና ገበያ ማግኘት እችላለሁ?” ብለው አባላቱ እራሳቸውን እንዲመለከቱና ዝግጅት እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል።
ሆኖም አብዛኞቹ ነጋዴ ሴቶች አሁንም የውጪው ገበያ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ይሄ ብቻ በቂ አይደለም። የውጪው ገበያ ቀርቶ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ሴቶች የአገር ውስጥንም ገበያ አግኝተው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። ለምሳሌ፦ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ዪኒፎርም የመስፋት ዕድል እንኳን አጥተዋል። ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ንግስት እንደሚሉት በቀን ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንጀራ የሚጠቀም ዩኒቨርሲቲ ጨረታን ማሸነፍ የቻሉትም ነጋዴ ወንዶች ናቸው። የሚገርመው ወንዶቹ የእንጀራውን ጨረታ ሲያሸንፉ ሥራውን መልሰው በሽርፍራፊ ሳንቲም ለሴቶቹ ነው የሰጧቸው። ‹‹በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ›› እንደሚባለው ትልቁን ገንዘብ ግን ኪሳቸው ይከታሉ። ካዊ በዚህ በጣም ይቆጫል። አሰራሩ ትክክል ነው ብሎም አይወስደው። መንግስት ይሄን ችግር ሳያውቀው ቀርቶ አይመስላቸውም። ሆኖም ስላልተጮኸለትና ሴቶቹም ስላላወሩት አልተሰማም።
እኛም እንደታዘብነው ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ንግስትም እንደነገሩን በዚህ ሁኔታ የተበሳጩ ሴቶች አንዳንድ ዘርፎች ተለይተው ለሴቶች መከለል አለባቸው እያሉ ነው። ነጋዴ ሴቶቹ በአባልነት ባቀፏቸው በካዊ በኩል ከ15 ቀን በፊት በነበረ ዘመቻም ይሄንና መሰል የእሮሮ ድምፃቸውን አሰምተዋል። ከእነዚህና ዘንድሮ መንግስት ለግዢ ከመደበው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ነጋዴ ሴቶች አንድ ሚሊዮኑን ብር እንኳን መጠቀም ካለመቻላቸው ጋር ተዳምሮ ካዊ ነጋዴ ሴቶች ድምፃቸውን እንዲያሰሙም ነው የዕለቱን መርሐ ግብር በራዲሰን ብሉ ሆቴል ያዘጋጀውና በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን መግለጫም የሰጠው። ‹‹ቢቸግረን ከሴቶች ይልቅ ይበልጥ ታዋቂ ወንዶችን አጋር አድርገናል። ዘመቻችን ውስጥ በማስገባትና በአምባሳደርነት በመሾም ለነጋዴ ሴቶቻችን ድምፅ ይሆኑናል ብለን እናስባለን›› ብለውናልም ዳይሬክተሯ። እነዚህ የካዊ የወንድ አጋሮች ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ሴክረተሪውና ዳይሬክተር፣ ከኦክስፋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር፣ ከእናት ባንክ ፕሬዚዳንቱ፣ ከሶሻል ኢንተርፕራይዝ ፕሬዚዳንቱ አቶ ክብረት ናቸው፡፡ እንዳስተዋልነውም እነዚህ ወገኖች በዕለቱ ለሴት ነጋዴዎች ድምጻቸውን ለማሰማት ፈቃደኛ ሆነው በመድረኩ ተገኝተዋል። በሰጡት መግለጫም የመቆርቆር ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ ዳይሬክተሯ ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት የአገራችን የግዢና የንግድ ስርዓት ለሴቶች እንዲመች ማድረግ፣ የተወሰኑ የንግድ ዘርፎች ለሴቶች መከለል፣ የግዢ ጨረታዎች ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የፀዱ እንዲሆኑ ማድረግን እንደ መፍትሄ ይጠቀሳሉ። ሰላም
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014