በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን የ1960ዓ.ም ህትመቶችን ቃኝተናል፤ በቅርቡ የድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በአገራችን መከበሩ ይታወሳል፡፡ ይህ ሚያዝያ 27 የሚከበረው የድል በዓል በንጉሡም ዘመን ለየት ባለ ሥነሥርዓት ይከበር እንደነበር የሚያመለክት ዘገባ ይዘን ቀርበናል የልማትና ዓለም አቀፍ ዜናም ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡
በመሶብና በእንሥራ በእንጦጦ ጋራ ላይ ግብዣ ተደረገ
አዲስ አበባ፤(ኢ.ዜ.አ.) በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አለቃ መርሐ ጥበብ በየዓመቱ የሚከበረውን የድል ቀን መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ፤ ሚያዝያ ፳፯ ዓ/ም/ በእንጦጦ ተራራ ላይ ከፍያለ ግብዣ አድርገዋል፡፡ አለቃ መርሐ ጥበብ ያደረጉት ግብዣ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ከመሆኑም በላይ የጥንቱን ሥነ ሥርዓት ይዞ ጠላ በጋን ጠጅ በእንሥራ ተሹሞ ተጋባዦችን ደስ አሰኝቶ ነበር፡፡
አለቃ መርሐ ጥበብ አስቀድመው የቦታው ባለርስት ከሆኑት ከአቶ ታደሰ ዋኬኔ ጋር ተነጋግረው ስለነበረ አቶ ታደሰም ጣሪያውና ግድግዳው በለመለመ የባሕር ዛፍ ቅጠል የተሸለመ ትልቅ ዳስ ሠርተው ለተጋባዡ ማረፊያ አዘጋጅተዋል፡፡
አለቃ መርሐ ጥበብ ባደረጉት የእንጦጦ ተራራ የጫካ ግብዣ ላይ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤት ባልደረቦችና የወታደርና የሲቪል ሠራተኞች ተገኝተዋል በግብዣውም ላይ ከ፩፻፶ የሚበልጡ መኳንንትና ወይዛዝርት ተካፋይ ከመሆናቸውም በላይ፤ ከእነዚህ ከአሥራ አራቱ ጠቅላይ ግዛቶች የተውጣጡ በመሆናቸው ግብዣው የወንድማማችነት መንፈስ የተሞላበት ነበር፡፡
አለቃ መርሐ ጥበብ ይህንን በዓል በትውልድ አገራቸው በመንዝ ውስጥ ከብዙ ዓመታት ጀምረው ሲያከብሩት ከመቆየታቸውም በላይ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከሆኑ ጀምረው ከብዙ ወንድሞቻቸው ጋር በየዓመቱ ያከብሩታል፡፡ እርሳቸውም ስለበዓሉ ሲናገሩ ‹‹ይህ በዓል የመላው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ቢሆንም፤ የእንጦጦ ተራራ ደግሞ ድልና ድል አድራጊው ወደ መናገሻ ከተማ የገቡበት በር ስለሆነ ይህንን በዓል በዚህ ተራራ ላይ በወንድማማችነት መንፈስ ስናከብረው ከፍ ባለ አንክሮ ነው በማለት ለተጋባዦች ባደረጉት ንግግር ገልጠዋል፡፡
(ሚያዝያ 30 ቀን 1960 አም)
አቶ ገመዳ ፶፭ ሺህ ካ.ሜ. ቦታ ለገሡ
ነቀምቴ ፤(ኢ.ዜ.አ.) በወለጋ ጠቅላይ ግዛት የሆሮ ጉድሩ ወረዳ ገዥ አቶ ገመዳ ጐጀር ለትምህርት ቤት ማሠሪያ እንዲሆን ፶፭ ሺህ ፫፻፲፪ ሜትር ካሬ ቦታ ከግል ርስታቸው ሰጡ፡፡
አቶ ገመዳ ጐጀር ከአሁን በፊት በዚሁ ወረዳ ለሚገኘው ትምህርት ቤት ሰባት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍል፤ ፭ ክፍል የመምህራን መኖሪያ ቤትና ፲ ሺህ የባህር ዛፍ ተክል የሚገኝበትን ፵፬ሺህ ፮፻፹፰ ሜትር ካሬ ቦታ ካርታ ለትምህርት ሚኒስቴር ማስረከባቸውን የአውራጃው ትምህርት ቤቶች ሥራ አስኪጅ አቶ አማኑኤል አያና ገለጡ
(ግንቦት 6 ቀን 19 60 አም)
ሌላ ጉድጓድ ካልተገኘ ከ፴፪ ዓመት በኋላ ዓለም የዘይት ችግር ይገጥመዋል
ከለንደን፤(ሮይተር) በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከሚገኙት የነዳጅ ጉድጓዶች ሌላ የነዳጅ ምንጭ ካልተገኘ በሠላሳ ሁለት ዓመታት ውስጥ ዓለም የነዳጅ እጥረት እንደሚያጋጥመው በለንደን ውስጥ የተደረገው ግምት ትናንት ገለጠ፡፡
ይህንንም ለመረዳት የተቻለው የብሪቲሽ ነዳጅ ኩባንያ ባወጣው ስታትስቲክስ መሠረት ሲሆን፤ በጥቅም ላይ የሚውለው ነዳጅና ተቀማጩም ጭምር ተጠንቶ ነው:: በጥናቱም መሠረት፤ በዓለም ላይ በየቀኑ ለመጠቀሚያ የሚውለው ነዳጅ ፴፮ ሚሊዮን በርሜል ሲሆን በዓመት ሲገመት ደግሞ አሥራ ሦስት ሚሊዮን በርሜል መሆኑ ነው፡፡
እስካሁን ድረስ ተቀማጭ መሆኑ የታወቀውና ይወጣል ተብሎ የተገመተው ፬፻፲፯ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ነው በዚህም መሠረት በዓመት በሚያስፈልገው አሥራ ሦስት ሚሊዮን በርሜል በየዓመቱ ከታደለ፤ ተቀማጭ ነዳጅ በ፴፪ ዓመቶች ውስጥ ያልቃል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙት የነዳጅ ኩሬዎች፤ በዓመት ፪፻፹፬ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የሚገኝባቸው ሲሆን ይኸውም ከዓለም ነዳጅ ፶፱ እጅ መሆኑ ነው ከአፍሪካ የሚገኘው ፵፪ሺህ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ፤ ከመቶ አስር እጅ ሲሆን ይህም ነዳጅ በብዛት ከሚገኝበት ከአሜሪካ ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡
(ግንቦት 6 ቀን 19 60 ዓ.ም )
የቆቃን ሐይድሮ ኤሌክትሪክ ሹም ኤሌክትሪክ ገደላቸው
አዲስ አበባ ፤(ኢ-ዜ-አ-) በየረርና ከረዩ አውራጃ የሚገኘው የሐይድሮ ኤሌክትሪክ ጣቢያ ሹም ግንቦት ፳፩ ቀን ረቡዕ ከቀኑ ፮ ሰዓት ሲሆን በሥራቸው ላይ እንዳሉ የኤሌክትሪክ አደጋ ደርሶባቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ይኸው አደጋ እንደደረሰ፤ ናዝሬት ከተማ ወደሚገኘው የኃይለማርያም ማሞ መታሰቢያ ሆስፒታል ተወስደው በተደረገላቸው ምርመራ ኤሌክትሪክ አፈናጥሮ በጣላቸው ጊዜ ራሳቸው በኃይል ተመትቶ ስለነበረ የመዳን ተስፋ እንዳልነበራቸው ታውቋል፡፡
የአቶ አሻግሬ ገብረ ጎዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር ትናንት የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር አቶ ሰይፉ ማኅተመሥላሴ፤የመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት ናዝሬት ከተማ በሚገኘው በመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን መፈጸሙን የሐረርና ከረዩ አውራጃ ግዛት ወኪላችን ባስተላለፈው ዜና ገለጠ፡፡
(ግንቦት 22 ቀን 19 60 አም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014