ነጻ አእምሮ ሀገር ከምትገነባባቸው መሰረታዊ እሴቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ነጻ አእምሮ አቅምንና ሀይልን እውቀትን በበቂ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችል ጉልበት እንደሆነስ? ነጻ አእምሮ ከነጻ አስተሳሰብ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው:: ነጻ አእምሮ ለህዝብ ስልጣንና ሀላፊነት መስጠት ነው:: ሁሉም ሰው በሚሰራው ስራ ላይ ሀላፊነት እንዲሰማው መፍቀድ ጭምርም ነው:: ነጻ አእምሮ ለግለሰቦች ያልተገደበ ነጻነት መስጠት ማለት ነው:: የመማር፣ የመስራትና የመለወጥን ሀይል የሚያቀጣጥል እንዲህም ነው:: በዚህ እድገትና ስልጣኔ እንደ ውሀ በጠማን ጊዜ ላይ የግለሰቦች የአእምሮ ነጻነት ዋጋ አለው ብዬ አምናለው:: ለውጥ ከመማርና ከመስራት ባለፈ በነጻነት የሚፈጠር የእያንዳንዱ ዜጋ መልካም አስተሳሰብ ነው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት ያላገኙ በርካታ የለውጥና የመራመድ ሀሳቦች አሉ:: እነዚህ ሀሳቦች የሚወጡት ደግሞ አፋኝ ስርአት ተወግዶ ህዝባዊ ስርዐት ሲሰፍን ብቻ ነው:: ህዝብ ከመንግስት ጋር መንግስትም ከህዝብ ጋ እጅና ጓንት ሆነው ለአንድ አላማ መስራት ሲችሉ ነው:: ህዝብ ያልተረዳው መንግስት፣ መንግስት ያልተረዳው ህዝብ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም:: እዛም እዚም እድል ቢያገኙ የሚሰሩ እጆች ብዙ ናቸው:: የሚናገሩ አንደበቶች አሉ፣ ሀሳብ አፍላቂ ጭንቅላቶች አሉ፤ ነጻነት በመስጠት ወደ ህዝብና መንግስት እንዲደርሱ ማድረግ መልካም ነው:: እንዲህ አይነት ህዝብና መንግስት በጋራ የተጋመዱበት ስርዐት ያስፈልገናል::
ነጻ አእምሮ የማይደርስበት የማህበረሰብ ክፍል የለም:: የአሁኑ የአውሮፓና የኢሲያ ስልጣኔ ለግለሰቦቻቸው በሰጡት አእምሮአዊ ነጻነት የመጣ ነው:: እኛ ሀገር ሲሆን ግን ሁሉም ነገር ሌላ ነው:: አቅማችንን በበቂና ነጻ በሆነ መንገድ እንድንጠቀም የሚያስችል ፖለቲካዊ ስርዐት አልነበረም:: የመጣንው ሀሳባችንን መንግስት እየለከልን፣ ንግግርና ተግባራችንን በመንግስት አካል እየተመዘነና እየተለካ ከዚህ በላይ ታወራና ዋ እየተባልን ነው:: የፖለቲካ ስርታችን የሀገራችንን እድገት፣ የህዝባችንን ስልጣኔ ገድቦታል ባይ ነኝ:: የመስራትና የማሰብ፣ የመፍጠርና፣ የማድረግ ነጻነታችንንም አምክኖታል::
የአሁኗ ኢትዮጵያ ሀሳባቸውና ተግባራቸው በተገደበባቸው ዜጎች የተፈጠረች ናት:: የአሁኗ ኢትዮጵያ ብዙ መስራት እየቻሉ እንዳይሰሩ በተገደቡ አእምሮና ልብ የተበጀች ናት እላለው:: ብዙ ነገራችን በመንግስት ተሰፍሮ የተሰጠን ህዝቦች ነን:: የሀገራችን ትላንትናዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ሀገርና ህዝብን መሰረት ከማድረግ ይልቅ ጥቂት ቡድኖችን ታሳቢ ተደርጎ የተቀነቀነ ነበር:: ዛሬ ላይ ያ የፖለቲካ ድፍርስ እሳቤ ጉድ አፍልቶብን እንዳንነጋገር፣ እንዳንተማመን በሩን ከርችሞብናል:: እንደ ሀገር፣ እንደ ፖለቲካ ያልገቡን ብዙ ነገሮች አሉ:: ከዚህ በላይ ትናገርና ዋ ተብሎ ገደብ በተበጀለት ማህበረሰብ ውስጥ የሚመጣ ለውጥ የለም::
መንግስት ሀሳቡንም፣ ንግግሩንም በወሰነለት ትውልድ ውስጥ የምናሰፋው የፖለቲካም ሆነ የርዮተ አለም ምህዳር አይኖርም:: ትላንትናዎቻችን የጠበቡት እኮ በጠበበ የፖለቲካ እሳቤ ነው:: ዛሬ ላይም በብዙ ነገር ጠበንና አንሰን የቆምነው በነዛ እኩይ ጥበቶች ነውና መስፋት አለብን:: መንግሰት ለሚመራው ማህበረሰብ ነጻነትን ሰጥቶ አዲስ ማህበረሰብ ጸንሶ መውለድ አለበት:: ዲሞክራሲያዊ መብት ሰጥቶ ከመጥበብ የራቀ ሃሳቡ የሰፋ ትውልድ ወልዶ ማሳደግ አለበት:: የጀመርነው ሀገራዊ ምክክር ፍሬ የሚያፈራው በሀሳብ ስንሰፋ ነው:: በመተማመን ስንልቅ ነው:: ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ በሆነ ባልተገደበ መንገድ ስሜታቸውን መግለጽ ሲችሉ ነው:: በዚህ አውድ ውስጥ እስካልቆምንና አዲስ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እሳቤዎችን ወደ ህዝቡ እስካላወረድን ድረስ ከመጥበብ አንድንም::
ለውጥ ማሰብ ነው፤ ለውጥ የብዙ አስተሳሰቦች ፍጭት ነው:: የተለያዩ ሀሳቦች እንዲወጡ፣ እንዲፈጠሩ የግለሰቦች የነጻነት መብት ወሳኝነት አለው:: መማራችሁ መስራታችሁ መነሳት መውደቃችው አላማው ነጻነት ነው:: ብዙዎቻችን ለምን እንደምንማር ለምን እንደምንሰራ ይሄን ሁሉ ውጣ ውረድ ለምን በበጎ እንደተቀበልን ስንጠየቅ የምንመልሰው መልስ አለን፤ እሱም የተሻለ ነገን ለመፍጠር የሚል ነው:: ህይወት ያለነጻነት ምንም ናት:: ሀገር ያለህዝቦች ነጻ አስተሳሰብ ምንም ናት:: በህይወት ውስጥ ሁሉ ቢኖረን ሁሉን ብንታደል ነጻነት ከሌለን ግን የህይወት ትርጉሙ፣ የመኖር ዋጋው ይጠፋናል:: በአለም ዙሪያ ያሉ በስነልቦና አስተምህሮ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ከርዕሶቻቸው አብዛኞቹ የአእምሮ ነጻነት የሚሉ ናቸው:: የአአምሮ ነጻነት የሌሎች ነጻነቶች መፈጠሪያ ስፍራ ነው:: የአእምሮ ነጻነት ሳይኖረን የምናሳካው ትልቅ ግብ የለም:: የአእምሮ ነጻነት ሳይኖረን የምንፈጥረው ብሩህ ነገ የለም:: ሁሉም ነገራችን ባለን የመስራት፣ የማሰብ፣ የመለወጥ ነጻነት ውስጥ የተደበቀ ነው::
ሀገር ለመፍጠር፣ ተነጋግሮ ለመግባባት መጀመሪያ አስሮ ከያዘን ፖለቲካዊና ማህበራዊ እስራት ነጻ መውጣት ይኖርብናል:: ሀገር ለማቆም ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን ስራ ላይ መዋል አለባቸው:: እንዲህ ስናደርግ ተነጋግሮ ለመግባባት ቅርብ እንሆናለን:: እንዲህ ስናደርግ የፖለቲካ መጥበብ፣ የማህበራዊ ነውር አይጎበኘንም:: ነጻነት ህይወትን ውብ ከምናደርግባቸው ትሩፋቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው:: ቅድም እንዳልኳችሁ በህይወታችሁ የቱንም ያክል ስኬታማና እድለኛ ብንሆን ለነጻ ፍቃዳችን የሚሆን አእምሮአዊ ነጻነት ከሌለን ትርፋችን እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም:: ብዙዎች መኖርን እንደ ትልቅ ነገር ይቆጥሩታል..አዎ እውነት ነው መኖር ትልቅ ነገር ነው ግን ካለነጻነት መኖር ብቻውን ጣዕም አልባ ነው:: ሀገር ከፍ ለማለት በነጻነት ውስጥ የሚንሸራሸር ሀሳብ ትሻለች:: በነጻነት ውስጥ ታስቦ የሚከወን ተግባር ትፈለጋለች:: የከሰርንባቸውን እነዛን የጥበትና የጭቆና ዘመኖች እንደመሸጋገሪያ ድልድይ ተጠቅመን በነጻነት መንፈስ በሀገራዊ ምክክር ፍሬ የምናፈራበት ወቅት ላይ ነን:: እውቀት መር በሆነና ምክንያታዊነትን በተደገፈ ነጻ መድረክ ያጠፋን እየወቀስን፣ ጥሩ የሰራን እያሞገስንና እያወደስን ለሀገራችን ጥሩውን የምንሰራበት ሰሞን ላይ ነን::
ነጻነት የትም ቦታ ዋጋዋ ከፍ ያለ ነው:: ዛሬ ላይ በታሪክ፣ በባህል በሁሉ ነገራችን ከአለም ቀድመን የምንኖረው እኮ አባቶቻችን በሰጡን ነጻነት ነው:: ለብዙ የአፍሪካና የአለም ሀገራት ምሳሌ ሆነን በኩራት የምንጠቀሰው እኮ መስዋዕትነት በተከፈለበት ሰውነት ነው:: በአባይ ድርድር ላይ ግብጽና ሱዳን ለአሸማጋይነት አውሮፓና አሜሪካንን ደጅ ሲጠኑ ነጻነትን የምናውቀው እኛ ግን ‹የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን› ስንል አቋም ይዘን አሁንም ድረስ አለን:: ይሄ ማለት እኮ ነጻነትን በሚያውቁና ነጻነትን በማያውቁ ሁለት ሀገራት መካከል የተፈጠረ የአስተሳሰብ ልዩነት እንደሆነ ማሰብ አይከብድም:: የነጻነት መፈጠሪያ ምድር ሆነን ነጻነት ማጣታችን ያስገርማል:: ያለፈው የፖለቲካ ሸማኔ ደውሮና አድርቶ ሀገር የሰራው ለራስ ብቻ በሚመች የሽመና ጥበብ የዜጎችን የመናገርና የማድረግ ነጻነት ገድቦ ነበር:: ነጻነት በሌለው፣ ኢትዮጵያን በማይመስል የኔነት ድርና ማግ ተሸምና ግን ደግሞ ያልተቋጨች ሀገር ላይ ደረስን:: በነጻነት አውድ ሀገራችንን ቋጭተንና አሳምረን በአንድነት እንለብሳት ዘንድ የአንድነት ኢትዮጵያዊ ሀሳብ ግድ ይለናል:: በቃ ይሄን ነው የምላችሁ..ሌላ ምንም የለኝም::
የነጻነትን ዋጋ እናውቀዋለን..በነጻነት ውስጥ ሀገር መፍጠር ብርቃችን አይደለም:: ግን ታሪክ ከማውራት ወጥተን ታሪክ ወደ መስራት ከፍ ማለት አለብን:: ታሪክ ለመስራት ደግሞ የመናገር፣ የመስራት፣ የማድረግ ሌሎችም ያልተገደቡ ብዙ ነጻነቶች ያስገፈልጉናል:: መቼም የትም ይሁን ነጻነታችሁን ለሌሎች አሳልፋችሁ አትስጡ:: ሀይላችሁ፣ ጥበባችሁ ያለው እሱ ውስጥ ነው:: ነጋችሁ፣ ለውጣችሁ ያለው እሱ ውስጥ ነው:: በትምህርት ቤት መምህራኖቻችሁ አሉታዊ ተጽዕኖን የሚያደርሱባችሁ ከሆነ በትምህርታችሁ ውጤታማ መሆን አትችሉም:: በስራ ቦታ አለቆቻችሁ የአእምሮ ነጻነት ካልሰጧችሁ ለራሳችሁም ሆነ ለምትሰሩበት ድርጅት አመርቂ ስራን መስራት አይቻላችሁም:: በትዳርሽ ውስጥ የባልሽ ተጽዕኖ ካለ ለልጆችሽ ጥሩ እናት ለባልሽም ጥሩ ሚስት መሆን አትችይም:: በትዳርህ ውስጥ የሚስትህ ተጽእኖ ካለ ለሚስትህ ጥሩ ባል ለልጆችህ ጥሩ አባት መሆን አይቻልህም:: በህይወት ውስጥ ለሚፈጠሩ ማናቸውም ሰውኛ ችግሮች አመክኒዮ ባላቸው የጋራ ሀሳቦች ለመፍታት መሞከር እንጂ በአንድ ሰው የበላይነት እንዲፈቱ ማድረግ ነጻነትን ለሌሎች አሳልፎ እንደመስጠት ነው የሚቆጠረው::
ታላቅ ለመሆን ታላቅ ነጻነት ያስፈልገናል:: በአሁኑ ሰዐት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ታላቅ ለመሆን እርምጃ ላይ ትገኛለች:: እርምጃዋ ሳይደነቃቀፍ ወደ ፊት እንዲቀጥል ሀገራዊ የእርቅ ምክክር አስፈልጋል:: በሁሉም ረገድ አንድነትና ህብረት ያለው ህዝብ ግድ ብሏል:: ልዩነታችንን ወደ ጎን ብለን በሚያግባቡን ሀሳቦች ላይ እንድናተኩር የሚያደርግ የእርቅና የተግባቦት መድረክ ተዘጋጅቷል:: እኚህ ሁሉ ብርሀናዊ እርምጃዎች ከዛሬ ርቀው ነገን እንዲረግጡ በነጻነት ተጀምሮ በነጻነት የሚጠናቀቅ ውይይት፣ አመራር፣ እርቅ፣ ድርድር ያስፈልገናል::
በትላንት ፖለቲካ፣ በትላንት ቁርሾ የዛሬን አዲስ ምዕራፍ እንዳንገልጽ እርቅ ያስፈልገናል:: የሀሳብ እርቅ፣ የአንድነት እርቅ:: የወንድማማችነት እርቅ:: ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እርቅ:: በሰነቅንው ሀገርን የማሻገር መንፈስ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች እያለፍን በአንድ ልብ አንድ ሀገር የምንገነባበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም:: እመኑኝ ታላቅነታችሁ ያለው በታላቅ ነጻነታችሁ ውስጥ ነው:: እስካሁን ካለ ሙሉ ነጻነት ስንጎድል ኖረናል:: ተምረን እውቀታችንን በበቂ ሁኔታ እንዳንጠቀም የፖለቲካ ሳንካ ተፈጥሮብን ያውቃል:: መናገር እየቻልን፣ ትላላቅ ጠቃሚ ሃሳቦችን ይዘን ነገር ግን እንዳንናገር ሆነን የኖርንባቸው ጊዜአቶች ነበሩ:: እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በሚል አጉል ማህበረሰባዊ አመለካከት ተጠፍንገን ኖረን እናውቃለን:: አሁን ግን በነጻ መድረክ፣ በነጻ ሀሳብ ነጻዋን ኢትዮጵያ አምጠን መውለድ አለብን::
ከእንግዲህ በራሳችሁ ላይ የራሳችሁን የነጻነት አብዮት ፍጠሩ:: ካለነጻነት የምትኖሩት ህይወት የምትመሩት ቢዝነስ፣ እውቀት ትዳራችሁ ዋጋ የለውም:: ታላቁ እናተ ያለው በታላቁ ነጻነታችሁ ውስጥ ነው:: እስካሁን ድረስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተደረጉ አለመግባባቶች ሁሉ መነሻቸውም መድረሻቸውም ነጻነት ነው:: እስካሁን ድረስ የተፈጠሩ ጦርነቶች፣ ውይቶች ሁሉ ነጻነትን በመሻት የሆኑ ናቸው:: ከዚህ በኋላም የሚመጡ ማናቸውም ልዩነቶች በነጻነት ሰበብ የሚፈጠሩ ናቸው:: ነጻነት ዋጋ ባይኖረው ኖሩ ይሄን ያክል ዋጋ ባልተከፈለበት ነበር:: ከሁሉም ምርጡ ነጻነት ግን በመነጋገር የሚፈጠረው ነው:: በመነጋገር ውስጥ መስማማት አለ በጦርነት ውስጥ ግን መስማማት ሳይሆን የአንድ ወገን የበላይነት ነው የሚንጸባረቀው:: በጥልና ክርክር የመጣ ነጻነት ዋስትና የለውም:: በጦርና በአፈሙዝ የመጣ ነጻነት እድሜ የለውም:: እውነተኛ ነጻነት በመነጋገር የሚገኝ የብስለት ውጤት ነው:: እናተም ብትሆኑ ነጻነታችሁን ከጥልና ክርክር ውጪ በሆነ መንገድ ለማግኘት ሞክሩ:: ለታላቅ ክብር ሰው ሆነናል..በማሰብ እንድንኖር ተፈጥረናል ከሁሉ ትልቁ እውነታችን ይሄ ነው::
ካለማሰብ የምንኖረው ህይወት ከጉዳት ባለፈ ይዞልን የሚመጣው አንዳች በረከት የለም:: በእያንዳንዳችን ህይወት ላይ ጥቁር አሻራን ትተው ያለፉ መጥፎ አጋጣዎች ሁሉ አንድ ወቅት ላይ ባለማሰብ የሆኑ ናቸው:: ማሰብ በህይወት የመኖራችን አንዱና ዋነኛው ማረጋገጫ ነው:: በነገራችን ላይ ብዙ ፈላስፎች ማሰብን ከመኖር ጋር ያገናኙታል:: የሰው ልጅ ኖረ የሚባለው ማሰብ ሲጀምር ሲሆን ሞተ የሚባለው ደግሞ ማሰብ ሲያቅም ነው ይላሉ:: በህይወት እየኖረ መልካም ነገር የማያስብ ሰው እንደሞተ ነው የሚቆጠረው ማለት ነው:: ይሄ ማለት በህይወት እያለ ለራስም ሆነ ለሌሎች ጥሩ ነገር የማያስብ ሰው በህይወት ቢኖርም እንደሞተ ነው የሚቆጠረው ማለት ነው:: ከእንግዲህ ባለው ህይወታችሁ ጥሩ ነገር በማሰብ መኖር እንድትጀምሩ አደራ እላችኋለው:: ትልቁ ሞት የሚመጣው በህይወት ውስጥ ቀን በቀን በምንሞታቸው ትንንሽ ሞቶች በኋላ ነው:: ያ ማለት በተስፋ መቁረጥ፣ ባለማሰብ፣ ለራስ ክብርና ዋጋ ባለመስጠት በነዚህ ሁሉ ከሞትን በኋላ ነው ለትልቁ ሞት እጅ የምንሰጠው ማለት ነው:: በማሰብ ሞታችሁን እንድትገሉት አደራ እላችኋለው:: ማሰብ በህይወት የመኖራችን ቀዳሚው ማሳያ ነው:: ማሰብ ሰውነትን ከእንስሳነት የሚለየው አንዱና ትልቁ መስፈርት ነው:: ማሰብ ስንል የሚጠቅመንንም የማይጠቅመንንም ማሰብ ማለት አይደለም:: ማሰብ ማለት መምረጥ ነው:: ወደ ፊት ሊያስኬደን የሚችልን እጅግ ዋጋ የለውን ነገር መርጦ ማሰብ ማለት ነው:: ሀገርና ወገን የሚጠቀሙበትን መልካም ሀሳብ ማፍለቅ ማለት ነው::
ነጻነት የህይወት ጌጥ ናት፤ የነፍስ ሁሉ አሸክታብ:: የክረምት ጣይ….የበጋ ጥላ…የሰው ልጅ ሁሉ ጥያቄ እንዲህም:: ካለ እሷ መድመቅ አትችልም..ካለእሷ ሁሌም ደብዛዛ ነን:: መኖራችሁ፣ መፈጠራችሁ፣ ህይወትና ለህይወት የሚያስፈልጋችሁ ነገሮች ሁሉ በእሷ ውስጥ ነው ያለው:: ሁሉም ነጻነት ደግሞ መልካም አይደለም:: ህይወት አስተውለን በተራመድንው ልክ የምትሰምር ናት:: ነጻነት አለን ብለን እንደፈለግን የምንሆንና ያልተገባ ነገር የምናደርግ ከሆነ አጥፊያችን ነው የሚሆነው:: አሁን ላይ ሀብትና ዝናቸውን ተጠቅመው ሀገርና ህዝብ እያገለገሉ ያሉ እንዳሉ ሁሉ ለሀገርና ህዝብ ነቀርሳ ሆነው የሚኖሩም አሉ:: ህዝብ በሰጣቸው ስልጣን ሀገር ከመጥቀም ባለፈ ባገኙት እድል ተጠቅመው መጥፎ ስራን የሚሰሩም ሞልተዋል::
ከትላንት እስከዛሬ ባገኙት ነጻነት ሳያተርፉ የከሰሩ ብዙ አሉ:: ብዙዎች በርተው ጠፍተዋል:: ብዙዎች ደምቀው ደብዝዘዋል:: ሀላፊነትን በአግባቡ መጠቀም ህይወትን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር አንድ ነው:: ነጻነት አለን ብለን ህይወታችንን፣ ትዳራችንን፣ ስራችንን መበደል የለብንም:: ነጻነት ትርፍ የሚኖረው ለበጎ ነገር ስንጠቀመው ብቻ ነው:: ብዙዎች ገንዘብና ነጻነት አለን በሚል አጉል አመለካከት ራሳቸውን ለሱስና ለአላስፈላጊ ነገር ሰለባ አድርገው ከስረው የሚኖሩ ናቸው:: አዳምና ሄዋን እንኳን የገነትን በለስ የበሉት በተሰጣቸው ገደብ የለሽ ነጻነት ነው:: ወደዚህ አለም ስንመጣ በሚገሉንና በሚያኖሩን ሁለት ገደብ የለሽ ነጻነቶች ታጅበን ነው:: በጎውን እንምረጥ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014