ገበሬው በአጭር ታጥቆ ለግብርና ሥራ እራሱን ዝግጁ የሚያደርግበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው። ለነገሩ ገበሬው አመቱን ሙሉ ከግብርና ወደ ግብርና ሥራ ከተሸጋገረ ሰነባብቷል። ይህን ባህል በማዳበር ብዙ ሥራ የሚቀር ቢሆንም፤ ገበሬው የመኸር ወቅትን ብቻ ጠብቆ የግብርና ሥራ ያከናውንባቸው የነበሩ ጊዜያቶች ማለፋቸው እየተነገረ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባርም እያየን ነው። ከመኸሩ የግብርና ሥራ ጀምሮ በበጋ የቆላ መስኖና በበልግ የሰብል ግብርና ሥራና በጓሮ አትክልት ልማት ጭምር በግብርና ሥራው ላይ ነው የቆየው። አሁን ደግሞ ዋናው የግብርና ሥራ በሚከናወንበት የክረምት ወቅት ላይ በመሆኑ የመኸሩ ዝግጅት የበለጠ ነው የሚሆነው። የገበሬው ባጭር ታጥቆ ሞፈርና ቀንበሩን ማዘጋጀት ወይንም በዘመናዊው የእርሻ መሣሪያ ዘዴ ትራክተር ለመጠቀም መሰናዳት ብቻውን በቂ አይደለም። ለእርሻ ሥራው የሚያስፈልጉ ግብአቶችም አብረው መሟላት ይኖርባቸዋል። በተለይም በዚህኛው የመኸር የግብርና ወቅት በዓለም ላይ ዋጋው እየናረና በአገር ውስጥም ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያቶች የማዳበሪያ አቅርቦት ቀደም ባሉት አመታት እንደነበረው እንደማይሆን ይጠበቃል። አርሶአደሩ እየተበረታታ ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲጠቀም ነው። በዚህ ረገድ ሁሉም በየአካባቢው ዝጅግት ማድረግ እንደሚጠበቅበትም መረጃዎች ቀድመው መሰራጨታቸው ይታወሳል። እኛም ለዛሬ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀትና በአጠቃላይ በመኸር የግብርና ሥራ ዙሪያ የጅማ ዞንን እንቅስቃሴ ከዞኑ ቡና ልማት፣ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ እንድሪያስ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፤ በ2014-2015 ዓ.ም የምርት ዘመን ላይ የምንገኝ ቢሆንም ያለፈው የምርት ዘመን ለዚህኛው ተሞክሮ የሚገኝበት በመሆኑ የነበረውን ሂደት ያስታውሱንና በወቅታዊው ላይ ትኩረት እናድርግ።
አቶ ኤልያስ፤ በቆላ የበጋ መስኖ የለማው ሰብል ተሰብስቦ ወደ ቀጣዩ የግብርና ሥራ ሽግግር የምናደርግበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ዝግጅትም እየተደረገ ነው። በቆላ የበጋ መስኖ ልማት የተለያየ የሰብል ልማት የተከናወነ ሲሆን፣ በአብዛኛውም የተከናወነው ግን የስንዴ ልማት ነው። ምርቱም ከማሳ ላይ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል። በዞኑ የበልግ እርሻ ተብሎ የሚያዝ ዕቅድ የለም። የተለመደም አይደለም። ይሁን እንጂ በዞኑ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሰፋ ያለ መሬት የሚሸፈን ሲሆን፣ ወደ 550ሺ ሄክታር መሬት ይገመታል። በአካባቢው በተለመደው የእርሻ ሥራ ዋናው የመኸር የግብርና ሥራ ከሚከናወንበት የክረምት ወቅት ቀድሞ ነው ሥራ የሚጀመረው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የመኸሩ የግብርና ሥራ ተጀምሯል። የአገዳ ሰብል ልማት ሥራ በማሳ ላይ ሰፊ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ቀድሞ ነው የሚጀመረው በአሁኑ ጊዜም ዘር መዝራት የጀመሩና ዝግጅት ላይ የሚገኙ አሉ። በተያዘው የመኸር የግብርና ሥራ ወደ 552ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል በመሸፈን ለማምረት ነው የታቀደው። ባለፈው የምርት ዘመን 550ሺ ሄክታር መሬት ነው በተለያየ ዘር በመሸፈን የግብርና ሥራው ተከናውኗል። በዘንድሮው መኸር እስካሁን ባለው ክንውን ወደ 70 በመቶ የሚሆን ሥራ ተሰርቷል። በ2014-2015 ምርት ዘመን ከ19ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
ዕቅዱን ለማሳካት፣ ግብአቶችን ቀድሞ ማቅረብ፣ አርሶአደሩም የሚፈልገውን እገዛ እንዲያገኝ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን መስጠት የሚጠበቁ ተግባራት በመሆናቸው በጽህፈት ቤቱ በኩል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርተዋል። ከግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ዓለምአቀፍና አገርአቀፍ በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ መፍትሄ በመፈለግ ምርትና ምርታማነቱን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሯል። ከሚደረጉት ጥረቶች አንዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ጥቅም ላይ እንዲውል ሲሆን፣ አርሶ አደሩ ቀድሞ ዝግጅት እንዲያደርግ የንቅናቄ ሥራ ተሰርቷል።
የግብርና ሥራ በአንድ የሰብል ልማት ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም። ሁለገብ ነው መሆን ያለበት በመሆኑም በጅማ ዞን ሁለገብ የግብርና ሥራ ነው በመከናወን ላይ የሚገኘው።ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን የቡና፣ የአትክልት፣ የእንስሳት ልማቶች ይከናወናሉ። በጅማ ዞን ከሰብል ልማት ቀጥሎ በዋና ልማት የሚያዘው የቡና ልማት ነው። 80 በመቶ የሚሆነው የአካባቢው ማህበረሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡና ጋር የተቆራኘ ነው። የኑሮ መሰረቱ ነው ማለት ይቻላል። ልክ ለመኸር የሰብል ልማት የሚደረግ ዝግጅት ለቡና ልማትም በተመሳሳይ ዝግጅት ይደረጋል። ለቡና ችግኝ መትከያ የሚሆን ጉድጓድ ይቆፈራል። በዚህ ወቅት ማንኛውም የግብርና ሥራ በኩታገጠም (ክላስተር) ስለሚከናወን ቡናን ጨምሮ በክላስተር ነው የግብርና ሥራው የሚከናወነው። በዚህ መሠረት ወደ490ሺ በሚሆን ማሳ ላይ የቡና ልማት በማካሄድ ምርታማነቱን የመጨመር ሥራ ይሰራል። አትክልትና ፍራፍሬ ልማቱም ጎን ለጎን የሚከናወን በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በአሁኑ ጊዜም የአቮካዶና የሙዝ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ በማከፋፈል ልማቱን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ነው። ልማቱ የወጭ ንግድንም ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በትኩረት ነው የሚከናወነው። አምና ወደ 40 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ለአውሮፓ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል።በዘንድሮ የምርት ዘመን በስፋት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። ንብ ማነብ ከእንስሳት ልማት አንዱ ነው። አካባቢው ለንብ ማነብ ምቹና የሀብቱ መገኛ ነው።በዚህ ረገድም የማር ልማቱን ለማዘመን ብዛት ያለው የንብ ቀፎ ለአልሚው በማሰራጨት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ እስካሁንም ከ28ሺ በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎ ተሰራጭቷል።በነበረው ተሞክሮ የንብ ቀፎ ስርጭቱ ከ20 በታች ነበር። የንብ ቀፎ ስርጭት ቁጥሩ ከፍ እያለ መምጣት የልማቱ እድገት አንዱ ማሳያና ለዘርፉም እየተሰጠ ያለውን ትኩረት ያመላክታል። ይሄ ትልቅ ስኬት ነው።
አዲስ ዘመን፤ በ2014-2015 የምርት ዘመን ከ19 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ሲታቀድ መነሻው ምንድ ነው?
አቶ ኤልያስ፤ ያለፈውን የምርት ዘመን ነው መነሻ ያደረግነው። በ2014-2015 የምርት ዘመን 18 ነጥብ 7 ሚሊየን የሚጠጋ ምርት ነው የሰበሰብነው። ከ2013-2014 የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው። ይህ በአጠቃላይ በዞኑ ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል።ለእድገቱ መመዝገብ ደግሞ በየምርት ዘመኑ የሚሰሩ ሥራዎች ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ነው። ለውጡ የግብርና ግብአትን ቀድሞና በመጠንና አስፈላጊውን አሟልቶ በማቅረብ እንዲሁም በክትትልና ድጋፍ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ይገለጻል። አርሶአደሩ ለዘመናዊ የአመራረት ዘዴ የሰጠው ትኩረትና በመተግበረም ያሳየው ተነሳሽነት ለእድገቱ ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል። በተለይም በዘመናዊው የአመራረት ዘዴ አርሶአደሩ በትራክክተር በማረስና ምርት መሰብሰብ ደረጃ መድረሱ ትልቅ ለውጥ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ባለፈው አመት የምርት ዘመን ብቻ በአማካይ 10ነጥብ3 በመቶ ምርታማነትን መጨመር ተችሏል።ይሄ በኩንታል ወደ አንድ አራት ነጥብ አራት ሚሊየን ሲሆን፣ በአንድ አመት የተመዘገበ ውጤት ነው። የተጀመሩት ሥራዎች ከተጠናከሩና አዳዲስ አሰራሮችንም መጨመር ከተቻለ የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልና ትልቅ አቅምም መኖሩን ያሳያል። አሁንም መሥራቱ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ግንዛቤ ተይዟል። ዘንድሮም ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ ለመጨመር ነው የታቀደው።
አዲስ ዘመን፤ የዘንድሮው ከባለፈው የምርትዘመን ከፍ ብሎ ሲታቀድ ለግብርና ሥራው የተመቻቹ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነው?
አቶ ኤልያስ፤ ተግዳሮች እንደሚኖሩ ታሳቢ ተደርጓል። አርሶአደሩ የሚፈልጋቸው የምርጥ ዘር ዝርያ አቅርቦት ከሌለ የሚፈለገው ውጤት ላይገኝ ይችላል። ለአብነትም የበቆሎ ምርጥዘር ዝርያ ይጠቀሳል። ሊሙ፣ ሾኔ፣ ፓዮኔር የበቆሎ ዝርያዎች ይፈለጋሉ። በምርት ዘመኑ በተለያየ ዘር ለመሸፈን በዕቅድ ከተያዘው ከ552ሺ ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ 180ሺ ሄክታር የሚሆነው በበቆሎ ዘር ነው የሚሸፈነው። አርሶአደሩ የሚፈልገው የምርጥ ዘር አይነት መቅረቡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ነው። ነገር ግን የመሟላቱ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ስለሆነ በሌላ ዝርያ በመተካት ልማቱን ማከናወን ደግሞ ግድ ነው። ክፍተቶች ቢኖሩም የአካባቢውን ስነምህዳር መሰረት ያደረገ የሥራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ከሚከናወነው በተጨማሪ መገናኛብዙሃንን በመጠቀም ከአርሶአደሩ ጋር ለአንድ ሰአት ያህል የቀጥታ ውይይት ይካሄዳል።ውይይቱ በተለያየ ርስጉዳይ ሲሆን፣አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ የምርጥዘርና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በመሆኑ በትኩረት ምክክር ይደረግበታል።በዚህ ውይይትም አርሶአደሩ የተለያዩ ጥያቄዎች ቢኖሩት የመጠየቅና መልስ የማግኘት መብት አለው። እንዲህ ያለው የውይይት መድረክ መመቻቸቱ አርሶአደሩ ቀጥታ ከባለሙያ ጋር ካለው ግንኙነት በተጨማሪ በባለሙያው ያልተመለሱለት ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ዕድል ያገኛል።
አዲስ ዘመን፤ አርሶአደሩ የሚፈልጋቸው የበቆሎ ዘር አይነት አቅርቦት አለመኖር መነሻ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ኤልያስ፤ ምንጩን ወይንም የተፈጠረውን ክፍተት በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን።አንዱ በእኛ በኩል የሚፈታ ነው። ሌላው በሌላ አካል የሚፈታ ነው። ለአብነትም በአርሶአደሩ በኩል በጣም ተፈላጊ የሆኑት የፓዮኔር ዝርያ በዞኑ አቅም የሚፈቱ አይደሉም።በክልሉ አስተዳደር ወይንም በፌዴራል ደረጃ የሚፈቱ ናቸው። ጥያቄው በተለያዩ መድረኮች ቀርቧል። ከሚመለከታቸው የዘርፉ የበላይ አመራሮች ጋርም ውይይት ተካሂዷል። እስካሁን ያለማቋረጥ ጥያቄው እየቀረበና እየተነጋገርንበት ቢሆንም ችግሩ እየጨመረ እንጂ መፍትሄ እያገኘ አይደለም። መፍትሄ ለማስቀመጥ ጥረቶች ቢኖሩም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል። አርሶአደሩ ዝርያውን በደንብ የሚያውቀው በመሆኑ በቀላሉ እንዲተወው ማድረግ ያዳግታል። እኛ ሳይንስን መሰረት በማድረግ ሌላ የዝርያ አይነት እንዲጠቀም ነው የምንነግረው እርሱ ደግሞ የትኛው ዝርያ ከየትኛው እንደሚሻል በተግባር ነው የሚያየው።ዝርያውን አባዝተው የሚያቀርቡት ኩባንያዎች ናቸው። ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል ብዬ የማስበው መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ኩባንያዎቹ ዘርፉን አባዝተው የሚያሰራጩበትን መንገድ እንዲያመቻች ነው።
አዲስ ዘመን፤ በዝርያ አቅርቦቱ ላይ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት በሚኖራችሁ ወቅት የምታገኙት ምላሽ ምንድነው?
አቶ ኤልያስ፤ ሁለት ምላሽ ነው የምናገኘው። አንዱ በአካባቢ ላይ በሚገኝ ዝርያ አይነት መጠቀም ወይንም እንዲተካ ማድረግ ነው። ሌላው በረጅም ጊዜ ደግሞ የዝርያ ብዜቱን በመጨመር ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚል ነው። እንደ ሙያ ሲወሰድ በአካባቢ የዝርያ አይነት መተካት የሚለው ትክክል ነው። በተመሳሳይ ሥነምህዳር ውስጥ ሊሆኑ የሚችሉ ዝርያዎች አሉ። ያንን እየተኩ መሄድ ይቻላል። እዚህ ላይ ያለው ተግዳት አርሶአደሩ የትኛው ከየትኛው ዝርያ በምርታማነት እንደሚበልጥ በተግባር የሚያውቀው በመሆኑ ማሳመኑ ላይ ነው። ለጊዜው ሊጠቀም ይችላል። የሚተገብረው ግን በፍላጎት ደስተኛ ሆኖ አይደለም። ጉዳዩ ከአገር አቅም በላይ መሆኑም ይታወቃል። የእናት ዝርያ የሚባለው ከውጭ እንደሚገባና በአገር ውስጥ ተባዝቶ የሚቀርብ መሆኑ ይታወቃል። ፓዮንየር የተባለው የበቆሎ ዝርያ ተባዝቶ ይቀርብ የነበረው በምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች ነው። በነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው የፀጥታ ችግር ዘር በማባዛቱና በስርጭቱ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል። እንደአገርም በጦርነት ውስጥ መቆየታችንና የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትና በነዚህ ተጽዕኖዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠም የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተደማምሮ ችግሩን የከፋ አድርጎታል።
አዲስ ዘመን፣ በግዥ ከውጭ ይገባ የነበረውን ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገው የተፈጥሮ ማዳበሪያን የማዘጋጀት እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ኤልያስ፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ አይደለም።በመሆኑም ልምዱ አለ። አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ በመንግሥት ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ተሞክሮ የማሳደግ ሥራ ነው የሚሰራው። በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲዘጋጅ ቀደም ብሎ አቅጣጫ በመቀመጡ ዝግጅቱ ቀድሞ ነው የተጀመረው። ኮምፖስት ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚወስድ ቀድሞ ነው ዝግጅት መደረግ ያለበት። በአሁኑ ጊዜም በዞኑ በተለያየ መንገድ እየተዘጋጀ ነው። አንዱ መሬት ውስጥ ተቀብሮ እስከ 20 እና 25 ቀናት እያገላበጡ የሚከናወነው ነው። ሌላው በትል የሚከናወነው በርሚ ኮምፖስት የሚባለው ነው። ተመራጭ ኮምፖስት ነው። የትሉ ዝርያ ከእስራኤልና ከህንድ ነው የሚመጣው። በዞኑ ውስጥ ወደ 135 ሺ አርሶአደሮች እየሰሩ ይገኛሉ። ወደ 120ሺ ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከትል ተዘጋጅቷል። በዞኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጃዎች በመገንባት ላይ ናቸው። አንዱ ግንባታ በዞኑ ጌራ ወረዳ ላይ ሲሆን፣በወር እስከ 180 ኩንታል በርሚ ኮምፖስት የሚያዘጋጅ ነው። ማእከሎቹ ኮምፖስት ማዘጋጃ ብቻ ሳይሆኑ አርሶአደሩም ክህሎት የሚያገኙባቸው ናቸው። የትላትል ዘርም በማዕከሎቹ እንዲገኝ ይሰራል። ባዮሲለር የሚባል የኮምፖስት አዘገጃጀት ዘዴም እየተከናወነ ነው።ባዮጋዝ ኃይል አመንጭቶ ከውስጡ የሚወጣው ተረፈምርት ለማዳበሪያ ጥቅም ይውላል።ወደ አራት ነጥብ አራት ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረት ነው ታቅዶ እየተሰራ ያለው። እስካሁን በግማሽ ተከናውኗል።
አዲስ ዘመን ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
አቶ ኤልያስ፤ እኔም አመሰግናለሁ
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም