ባለፈው ሃሙስ የወቅታዊ አምድ ዝግጅታችን ወቅታዊ የአገራችን ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ይዘን መቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው የወቅታዊ አምዳችንም በተለይ የኑሮ ውድነት፣ የሠላም ማጣት እና ከሕወሓት ጋር ባለው ግጭት ዙሪያ የምክር ቤት አባላት ምን እየሠሩ ነው በሚለው እና በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከአቶ ክርስቲያን ታደለ ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የኑሮ ውድነት እና የሠላም ማጣት ችግሮች የጎሉ እንደሆነ በየጊዜው የምናየው ነው፤ ይህንን ችግር ለማቃለል የምክር ቤቱ ድርሻ ምን ያህል ነው፤ ኃላፊነቱንስ ምን ያህል እየተወጣ ነው?
አቶ ክርስቲያን፡- የኢትዮጵያን የወቅቱን የኑሮ ውድነት የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ቢያብራሩት የተሻለ ነበር። ነገር ግን እንደአንድ እንደራሴ ልንገረው የምችለው እኛንም የምክር ቤት አባላት ሁሉ እያሰቃየ ያለ ጉዳይ ነው። መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው የተለዩ ዕቃዎች ሳይቀሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋቸው እየጋሸበ ማግኘት እስከማይቻልበት እንደቅንጦት እስከመቆጠር እየደረሱ ነው። ይህንን ችግር ለማቃለልና ለመቅረፍ መንግስት የአጭር ጊዜ የመካከለኛ ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን ማቀድ አለበት ብለን እናምናለን።
ባለፈው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ይህንኑ አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ለመስጠት ምክር ቤት ተገኝቶ ነበር። በዛ ወቅት የተነሱ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ። በዛ ወቅት የተነሳው በኢትዮጵያ ውስጥ የፖሊሲ እና የቁጥጥር ሥራዎች አለመቀላጠፍ የፈጠሩት ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ ዓለም ላይ ያለው ሁኔታም ታሳቢ መደረግ አለበት። በተለይ የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ላይ ቀላል አይደለም። መሠረታዊ የሚባለውን የዓለምን የዘይት ፍላጎት 70 በመቶ የሚሆነውን የሚያቀርቡት ዩክሬን እና ሩሲያ ናቸው። ግማሽ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎትንም የሚሸፍኑት እነዚሁ አገራት ነበሩ። ኢትዮጵያ ደግሞ በዋናነት የዘይት ፍላጎቷን የምታስመጣው ከውጪ ነው። አገር ውስጥ ያሉ የዘይት ፋብሪካዎችም የሚያጣሩትን የዘይት ድፍድፍ የሚያመጡት ከእነዚሁ አገራት ነው። ስለዚህ ዘይት በጣም እንዲወደድ ሆኗል። ይህ በዓለም ላይ የተከሰተ ነው። የዘይት ምርታቸውን ወደ ውጪ የሚልኩ እነ ቱርክን የመሳሰሉ አገራትም ወደ ውጪ ከመላክ ታቅበዋል። የፍጆታ ገደብ እስከማስቀመጥ የደረሱም አሉ። የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን የባህር ትራንስፖርት ሥርዓቱም ተቃውሷል። ስለዚህ በተቀላጠፈ መልኩ የማጓጓዝ ችግርም ያጋጥማል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የፀጥታ መደፍረስ ባጋጠመ ጊዜ የትም አገር እንደሚያጋጥመው ከግጭት የማትረፍ እና ሃብት የማጋበስ ሁኔታዎች አሉ። እናም ምርቶችን የማከማቸት አዝማሚያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምርቶችን ለማስገባት ችግር እንደሚፈጥር ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።
ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ እና ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን ለማስገባት የሚያስችሉ የውጪ ምንዛሬዎችን አለማግኘት በራሱ ትልቅ ችግር ነው። በዚህ ምክንያት ክፉኛ እየተፈተንን መሆኑን ሁሉም ማወቅ አለበት። ኢትዮጵያ የልጅ ሃብታም ናት። በዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ ዘርፍ ልምድ እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው ጉምቱ የሆኑ ኢኮኖሚስቶች ከዚህ ቀውስ ለመውጣት የሚያግዝ አማራጭ ካላቸው ለምክር ቤቱ ሊሆን ይችላል ወይም ለአስፈፃሚው በማቅረብ ህዝባችንን እያሰቃየ ላለው የኢኮኖሚ ህመም ፍቱን ሊሆኑ የሚችሉ የመፍትሔ አማራጮችን እንዲያቀርቡ ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያውያን በተለይ ዳያስፖራው ከምንጊዜውም በላይ ከምንዛሬ እጥረት አንፃር አገር እየተፈተነች መሆኑን በመረዳት ህጋዊ በሆነ መንገድ የውጭ ምንዛሪ በመላክ ቢያንስ ለማስታገስ መተባበር ይኖርበታል። ምክር ቤቱም የተለያየ የፓርላማ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት እና ውጪ ጉዳይም ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በማድረግ መንግስትም የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ የውጪ ኢንቨስትመንት ሊስቡ እና ሊያሻሽሉ የሚችሉ የገበያ አማራጮችን ምናልባት የውጪ ምንዛሪ ክምችትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት አለበት የሚል እምነት አለኝ።
የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ የኑሮ ውድነት ላይ ቀጥተኛ የሆነ አስተዋፅኦ አለው። አብዛኛዎቹ የምንጠቀምባቸው የፍጆታ ዕቃዎች በውጪ ምንዛሬዎች የሚመጡ በመሆናቸው እዛ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። በእርግጥ እኔ ኢኮኖሚስት አይደለሁም። ነገር ግን በተለይ አስፈፃሚው አካል በዘርፉ ላይ ያሉ ኢኮኖሚስቶች የሚሰጡትን ምክረሃሳብ በወጉ ማድመጥ ይጠበቃል። በዚህ ወቅት ለአገራችን ሁሉም እኩል ያስፈልጋል። ጠቃሚ የሚሆኑ ሃሳቦችን ሙግት እና ክርክር አድርገንባቸው መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው መወሰድ ይኖርበታል። ሕዝባችን በየትኛውም አማራጭ ምርታማነቱን ማሳደግ አለበት። ገበሬው የተገኘውን መሬት ቆፍሮ ቢያንስ የዕለት ፍጆታውን መሸፈን የሚያስችል ምግብ ማምረት ያስፈልጋል። የከተማው ነዋሪ ንግዱ ላይ በደንብ መበርታት ይኖርበታል። መንግስት ደግሞ ነጋዴውን እና አምራቹን ሊደግፉ የሚችሉ አበረታች እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- ሰላምን በሚመለከትስ ምክር ቤቱ ሚናውን የሚወጣው እንዴት ነው ?
አቶ ክርስቲያን፡- ሰላም በሕይወት ለመኖር ወሳኝ ነው። የኑሮ ውድነቱ ለመባባስ አንደኛው ምክንያት የሠላም እጦት ነው። ሠላም በሌለበት ልማት ሊኖር አይችልም። የውጪም ሆነ የአገር ውስጥ አልሚዎች የፀጥታ መደፍረስ ባለበት አካባቢ አምነው ገንዘባቸውን ሊያፈሱ እና ኢንቨስት ሊያደርጉ አይችሉም። ሰላም ሲኖር ኢንቨስትመንት ይኖራል። ኢንቨስትመንት ሲኖር የሥራ ዕድል ይፈጠራል፤ የቢዝነስ እንቅስቃሴ እና ሌሎችም ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። በተለይ የውጭ ኢንቨስተር ሲኖር ደግሞ የውጭ ክምችትን ለማሳደግ አንደኛው አማራጭ ነው። እንደዜጋ ማመን ያለብን ነገር፤ የሕዝባችንን ደህንነት እና አንድነትን ማስጠበቅ በሁለተኛነት ልናስቀምጠው የሚገባ አይደለም። ቀይ መሥመር መሆን መቻል አለበት። ምክር ቤቱ ምንም እንኳ ከተለያየ አካባቢ እና ፓርቲ ተመርጦ የመጣ ቢሆንም የሁሉም ኢትዮጵያውያን ወኪል ነው። የመላው የ120 ሚሊየን ህዝብ ደህንነት ጉዳይ ይገደናል። የኢትዮጵያ አንድነቷ እና ቀጣይነቷ ሊጨንቀን ይገባል። በዚህ ረገድ የምክር ቤቱ እንደራሴዎች በግለሰብ ደረጃም ሠላም ከቤት ስለሚጀምር ከመራጭ ማህበረሰብ ጋር በመውረድ እያንዳንዱ መራጭ ለሠላም በጎ አስተዋፅኦን እንዲያበረክት መቀስቀስ ያስፈልጋል።
ምክር ቤቱ አንዱ ኃላፊነቱ ህግን ማውጣት ነው። ሰላምን፣ ደህንነትን እና ፀጥታን የሚረጋግጡ ሕጎችን ሲያወጣ አስፈፃሚው በወጉ መወጣቱን የመከታተል እና የመደገፍ እና የመቆጣጠር ሥራዎችን እንሠራለን። ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የተወሰኑ የመገናኛ ብዙሃኖች እና የመሣሠሉት ቀጥታ ተጠሪ ናቸው። በዚህ ሒደት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች ከሌላው ማህረሰብ በተለየ ሕዝቡ ይመለከታቸዋል፤ ይሠማቸዋል።አርአያ አድርጎ ይወስዳቸዋል። ስለዚህ ሠላምን በሚያረጋግጡ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትልቅ ምክር ቤት ነው። ጥያቄዎች ካሉ በዚህ ምክር ቤት ማናቸውም ጥያቄዎችን ማቅረብ ይቻላል። የሚቀርቡ ጥያቄን ሕዝብ በቀጥታ ይመለከታል። በማናቸውም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ክርክር ሙግት ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን በዋናነት ሁሉም ሕዝብ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት። ኢትዮጵያ ስትኖር ብዙ ነገር አለ። ቀልድ ይመስላል። በርካታ አገራት ሲፈራርሱ ታይቷል። ሶሪያ ትልቅ አገር ነበረች። የመን ትልቅ የታሪክ አገር ነበረች። ሊቢያም አደግን ከሚሉ አገሮች በተሻለ መልኩ ዜጎች ተንደላቀው የሚኖሩባት አገር ነበረች። ዛሬ ለዜጎቿ ሲኦል ሆናለች። እንኳን ለመፋቀር እና ለመመካከር ለመጣላትም ለመኮራረፍም አገር ያስፈልጋል። ይህንን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። በሁሉም ነገር ላይ መስማማት ላይኖር ይችላል። በሁሉም ነገር ላይ መስማማት አይጠበቅም። የግድ እንደአገር ለመቀጠል እና በልዩነት ውስጥም ቢሆን በሰላም ወጥቶ ለመግባት አስቻይ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ዋነኛው ሠላም ነው።
ሠላም ላይ ልዩነት መኖር የለበትም። የተሻለ አማራጭ ፖሊሲ አቅርቦ ነገ በምርጫ ተወዳድሮ ሥልጣን ለመረከብም ሠላም ግዴታ ነው። እኛ እንደእንደራሴዎች በምክር ቤት የሚወጡ ህጎች ለዜጎች ሠላም፣ ደህንነት፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲን የሚያረጋግጡ ስለመሆናቸው እናረጋግጣለን። ይሔ ማለት ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ ይሆናሉ ማለት አይደለም። ሕዝቡ ይህንን ተረድቶ እኛንም ጭምር መሞገት አለበት። እኛንም የለም የእኛ ፍላጎት እንደዚህ ስለሆነ የምንፈልገው ይህንን ፍላጎታችንን እንድታስፈፅሙልን ነው ብሎ እኛን መጠየቅ መሞገት መቻል አለበት። እያንዳንዱ ሰው ሠላምን የሚረብሹ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ያሉት ለህግ እንዲቀርቡ ማስቻል አለበት። አስፈፃሚው አካል ሕግን ማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ዝቅተኛ ግዴታው መሆኑን መረዳት አለበት። አንድም ግለሰብ ቢሆን ሊገፋ እና ሊሳደድ አይገባም። እውነት ለመናገር የምናያቸው አዝማሚያዎች ደስ አይሉም። ያሉት ሁኔታዎች ተከባብሮ አንቱ ለመባባል አስቻይ አይደሉም። አገር እየነደደ እና ዜጎች በብሔር እና በሃይማኖት እየተገፋፉ መቀጠል የለባቸውም። ሁላችንም መስከን ይኖርብናል። ነገ በታሪክ ፊት ስለሚኖረን ገፅታ በደንብ ማሰብ አለብን። እኛ ኢትዮጵያውያን ለታሪካችን የምንጨነቅ ነን። ከሞታችን ይልቅ አሟሟታችን የሚያስጨንቀን ለዚህ ነው። ነገ በታሪክ ፊት የኛ ተወላጆች እኛ እንወክለዋለን የምንለው ማህበረሰብ የሚያፍሩብን መሆን የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ምክር ቤቶች በአብዛኛው ሥራዎችን የሚሠሩት በቋሚ ኮሚቴ ነው። እርሶ የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ክርስቲያን፡- ጥረቶችን እያደረግን ነው። ዓመታዊ ዕቅድ አለ። ዕቅዳችንን ተከትለን እንሠራለን። እኛ ተልዕኳችን ዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት ኦዲት አድርጎ የከፋ የኦዲት ግኝት አለባቸው ያለባቸውን ተቋማት ለይቶ ይልክልናል። ኦዲት ተደራጊ መስሪያቤቶች ብዙ በመሆናቸው ምናልባት ከህዝብ ፍላጎት እና ከሚያንቀሳቅሱት የገንዘብ መጠን አንፃር ምናልባት ለአገር ልማት ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ አንፃር፣ ከሚያንቀሳቅሱት የሰው ሃይል አንፃር እየመዘንን ኦዲት ጉድለቱ አንፃር የከፋ የሚባሉት ላይ ይፋዊ የህዝብ መድረክ እንጠራለን። እስከአሁን በርካታ ተቋማትን አይተናል። በዚህ ዓመትም 26 ተቋማትን ለማየት ዕቅድ ይዘናል። በዕቅዳችን መሠረት እየሔድን ነው። ይፋ መድረክ መያዙ አንድ ነገር ነው። ኦዲት ናሙና ነው። በዚህ ተቋማትም ራሳቸውን እንደመስታወት እንዲያዩበት እንፈልጋለን። ያንን ሊጠሉት አይገባም። መቼም አንድ ሰው አይኑ ላይ ጉድፍ እያለ መስታወት ቢያይ መስታወቱን መጥላት ሳይሆን ጉዱፉን ማንሳት አለበት። የኦዲተርም ሆነ የኛ ሥራ ተቋማት ያለባቸውን ጉድፍ እንዲያነሱ ማድረግ ነው። በህዝብ ዘንድ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ነው። በዚህ ሂደት የአሰራር ክፍተቶች ካሉ እንዲስተካከሉ እና የሕግ ክፍተትም ካለ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ጉድለቱን የፈጠረውን አካል ማስተካከል ነው።
የአደረጃጀት እና የአሠራር ችግር ካለም አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ አደረጃጀታቸው ላይ ችግር ካለም አጢነው ከልሰው ለወደፊቱ መሰል ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ማድረግ ነው። እንዝላልነትም ካለ ተጠያቂነት እንዲኖር ነው። ቀጥታ ይወገር ይገደል ማለት ሳይሆን፤ በየደረጃው ተጠያቂነት እንዲዳብር እየሠራን ነው። እስከአሁን ባየናቸው ተቋማት እንዲያስተካክሉ ብለናቸው እነርሱም ማስተካከያዎችን ልከውልን በእርግጥ እያስተካከሉ ነው ወይ የሚለውን በወረቀት ብቻ ሳይሆን በአካልም ሔደን እያረጋገጥን ነው። መሻሻል ያለባቸውም አሉ። ቀጣይነት ያለው ክትትል የምናደርግባቸው አሉ። በተጨማሪ ተጠያቂነት የሠፈነባቸው ተቋማትም አሉ። በክስ ደረጃ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት የደረሱ አሉ። በተመሳሳይ ደረጃ በገንዘብ ቅጣት በማስጠንቀቂያ የታለፉም አሉ። አሁን ስላላለቀ እና ይፋ ለማድረግ ስለሚከብድ እንጂ አሁንም ክስ የሚመሠረትባቸው ተቋማት አሉ። የእኛ መሠረታዊ ፍላጎት ግለሰብ አመራሮችን መቅጣት ማስቀጣት አይደለም። የኛ መሠረታዊ ፍላጎት ስህተትን እየነቀሱ እያወጡ ተቋማትን ማኮሰስ አይደለም። አመራሩን ማንቋሸሽ አይደለም። የኛ ፍላጎት በሒደት መሠል ችግሮች እንዳይደገሙ ራሳቸውን አድሰው ክህዝብ እና ከአገራዊ ፍላጎት አንፃር ብቁ ተቋማት ብቁ አመራር እንዲሆኑ ድጋፍ መስጠት ነው። ድጋፋችን ደግሞ ቁጥጥር ነው። ሥራቸውን ሲሠሩ በህግ ተቋማቱ ከተቋቋሙበት ዓላማ አንፃር መሥራታቸውን ማረጋገጥ ነው። ይህንን እየሠራን ነው ብለን እናምናለን። ሌብትን የሚጠየፉ አመራሮች፣ የመንግስት ሠራተኞች እና ተቋማትን እንፈልጋለን። ምናልባት የከፋ የኦዲት ግኝት ያለባቸው ሹመኞች ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በሃላፊነት ደረጃ የሚቀመጡበት ሁኔታ መኖር የለበትም ብለን እናምናለን። ወደ ፊት የክዋኔም ሆነ ሌላ ኦዲታቸው እንደመወዳደሪያ ዶክመንት ተወስዶ በህግ ጭምር እንዲገደብ ጥረት እናደርጋለን። ምክር ቤቱ ይህንን ሲሰራ ነበር። ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን የምክር ቤቱን ሥራ በበጎ ይቀበሉታል።
አዲስ ዘመን፡- በምክር ቤቱ ከህግ ውጪ የሚፀድቁ ህጎችን በሚመለከት የመገናኛ ብዙሃን ቦርድን በሚመለከት ሃሳብ አቅርበው ነበር። እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በህግ መጠየቅ የሚቻልበት መንገድ የለም?
አቶ ክርስቲያን፡- አለ። ምክር ቤቱ የሚመራበት የአባላት የአሰራር ደንብ አለ። በደንቡ ላይ በየትኛው ደረጃ በምክር ቤቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ድጋሚ አይታዩም። ነገር ግን በልዩ ሁኔታ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት የሥነምግባር ደንብ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ የተቀመጠ አለ። ግልፅ የሆነ የህግ ሥህተት ካለ በዛው ደንብ በአንቀፅ 49 ንዑስ 3 ላይ የተቀመጠ እና በልዩ ሁኔታ በአማካሪ ታይቶ የተወሰነው ውሳኔ የሕግ ስህተት ስላለበት ማሻሻል ይቻላል የሚል ግልፅ አሠራር አለ። ስለዚህ በባለፈውም የኢትዮጵያ ብሮድካስት የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ አመራሮች ሹመት ሲፈፀም በአዋጅ የተቀመጠው 1238/2013 ያስቀመጣቸው አሠራሮች እና ሥነስርዓቶች አልተከበሩም። በወቅቱ በምክር ቤቱ እኔም ዕድሉን አግኝቼ ስለነበረ ይህ ነገር የስነስርዓት እና የህግ ጥሰት ስለመሆኑ ጠቅሼ ነበር። እኔ የምወስደው በበጎ ነው። አዋጁ ላይ ግንዛቤ ባለመኖሩ ነው። ድምፅ ተሰጥቶ ፀድቋል። ነገር ግን አሠራሩም የሚፈቅድ በመሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ በቀጣይ በሚኖረን የምክር ቤት ስብሰባ ይህን ጉዳይ አንስተነው ይታያል የሚል ተስፋ አለኝ።
እኔ ምክር ቤት የገባሁት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክዬ ነው። እዚህ የፓርቲያችን የፓርላማ ቡድን አለ። በፓርቲ ተጠሪያችን በኩል እንዲያዝ ተደርጓል። ምክንያቱም መነጋገሪያ ሆኗል። የሚዲያው የዜጎች እና የፖለቲከኞች መነጋገሪያ ሆኗል። ነገር ግን ይህ ወደ ፊትም ሊፈጠር ይችላል። ዋናው ነገር ጉዳዩ ከታወቀ በኋላ ትክክለኛውን ህጋዊውን መንገድ ሥርዓት ማስያዝ ከእኛ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። ይህንን ማድረጋችን ለምክር ቤቱ ሞገስ እና ክብር ቢሰጠው እንጂ ምክር ቤቱን የሚያኮስስ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ከሕወሓት ጋር ባለው ግጭት ላይ በምክር ቤቱ ምን መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ክርስቲያን፡- በዚህ ጉዳይ ላይ አፈ ጉባኤው ቢጠየቁ መልካም ነበር። ነገር ግን እንደአንድ የምክር ቤት አባል እንደግለሰብ አስተያየቴን ስሰጥ የምክር ቤቱ አቋም ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በመሠረቱ ሰላም ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። የትኛውም አካል በኢትዮጵያ ላይ በጎ አበርክቶ ሊኖረው ይችላል። አሁንም ድረስ ሕወሓት ባዘጋጃቸው ደንቦች እየተመራን ነው። በአካል ጫካ ቢሆንም በአሠራር እና በስሪት ቤተ መንግስት ያለ ቡድን ነው። የምንመራበትን የአባላት ደንብ ሕገመንግስቱም ሁሉም በሕወሓት የተዘጋጀ ነው። ግለሰቦቹ በአካል ባይኖሩም ሥርዓት እና ሥሪቱ የሕወሓት ነው። ይሔ አንድ ራሱን የቻለ ክርክር የሚፈልግ ነው። ነገር ግን እኔ መናገር የምፈልገው በመርህ ነው። ሕወሓት በዚህ ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ነው። በሌላ በኩል አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ይታወቃል። ሕወሓት እንደ ድርጅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ገሃነም ድረስ እገባለሁ ብሎ የተነሳ ነው። ዛሬም ድረስ የአፋር እና የአማራን ግዛቶችን ተቆጣጥሮ የሚገኝ አካል ነው። ዛሬም ድረስ አፈንግጦ ከኢትዮጵያ ጋር ውጊያ እየፈፀመ ነው። ለሰላም በጎ እርምጃ እየወሰደ አይደለም። ያከማቸውን ሃብት በመጠቀም ከኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም በተቃርኖ የቆመ አካል ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ላይ የመጣ ነው።
የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከተው ኢትዮጵያውያንን ነው የሚል እምነት አለኝ። ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር እንዴት ትውጣ በሚል ማሳተፍ መርዝ ቀማሚን ባለመድሃኒት የማድረግ ስህተት ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ግን ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው። የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያ እዚህ እንድትደርስ ጉልህ አበርክቶ ያለው ሕዝብ ነው። ይህንን እንዲቀጥል። ኢትዮጵያን ወደ ፊት በማሻገር ሒደት ውስጥ የሚሳተፍበት ፕላት ፎርም መዘጋጀት እንዳለበት አምናለሁ። ፕላት ፎርሙ እንዴት መደረግ አለበት በሚለው ላይ ምክክር ያስፈልጋል። ቀጣይ ንግግር ያስፈልጋል። በየትኛውም ሁኔታ ደግሞ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን። በትግራይም ሆነ በአፋር እና በአማራ ክልል በየትኛውም አካባቢ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን። ሁሉም ባለድርሻ አካል መወያየት መመካከር አለበት። ምናልባት ኢትዮጵያን ሰላም ለማድረግ የሚወሰነው ውሳኔ የሚጎመዝዝ ቢሆን እንኳ ሕዝብን ወደፊት የሚያሻግር እስከሆነ ድረስ መቀበል አለብን። በተለይ የፖለቲካ ሃይሎች በእነርሱ እምነት ኢትዮጵያን ሰላም ሊያደርግ የሚችል ዕቅድ ቢያቀርቡ ልንነጋገርበት የምንችልበት ዕድል አለ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
አቶ ክርስቲያን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም