ባለፈው ሐሙስ የአርበኞች ቀንን አክብረናል። ይህ የአርበኞች ቀን በጀግኖች አባቶቻችን ተጋድሎ ዳግም የተገኘ ድል ነው። በዓድዋ ጦርነት ሽንፈት የተከናነበው ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ዝግጅት አድርጎ ዳግም ወረራ ፈጽሟል። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በለመዱት የጀግንነት ስልትና ወኔ ባደረጉት ተጋድሎ ሉዓላዊነታቸውን አስከብረዋል። በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ይህን ኢትዮጵያውያን ፋሽስት ጣልያንን ድል ያደረጉበትን የድል ቀን እናስታውሳለን።
የተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› የባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጽሐፎችን እና የተለያዩ ድረ ገጾችን በምንጭነት ተጠቅመናል።
ኢትዮጵያ ከ81 ዓመታት በፊት በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ሰንደቅ ዓላማዋ ከታጠፈ፣ ሉዓላዊነቷ ከተደፈረ 5 ዓመታት በኋላ በጠላቷ ፋሽስት ጣልያን ላይ ድል የተቀዳጀችው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በአርበኞች ብርታትና መስዋዕትነት የፋሽስት ጣሊያንን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ መንግሥት ሲሰቅሉ ነው፡፡
የሚያዝያ 27 የንጉሰ ነገስቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ሌላው ታሪካዊነቱ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 በዚያው ቀን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን መሆኑ ነው፡፡ ጣሊያን ከዓድዋ ሽንፈቷ 40 ዓመታት በኋላ በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በወታደራዊ ኃይል ይበልጥ ተደርጅታ ኢትዮጵያን ከሦስት አቅጣጫዎች ወረረች፡፡ ከዓድዋው ዘመቻ ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያም የጣሊያንን ጦር በፅናት ተዋጋች፡፡
የወቅቱ ሃያላን አገሮች እንግሊዝና ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ በግዢ እንዳታገኝ ለጣሊያን ተደርበው ስላሴሩባት ኢትዮጵያ ብቻዋን ጦርነቱን በመጋፈጧ ድል ማግኘት አልቻለችም፡፡ የየግንባሮቹ የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች ብዙዎቹ ሞተው ሠራዊቱም በመርዝ ጋዝና በአውሮፕላን ቦምብ ተደብድቦ ያለቀው አልቆ የቀረው ቀርቶ ጣልያን ጊዜያዊ ድል አግኝታ ዋና ዋና ከተሞችን ብትቆጣጠርም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በገጠሩ ክፍል እምቢ ለነፃነቴ ፣ እምቢ ለአገሬ ብለው የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ።
ንጉሰ ነገስቱም ስደት ሄደው በጊዜው ለነበረው የመንግሥታቱ ማህበር(ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አቤቱታ አቀረቡ። የሚሰማቸው ግን አላገኙም። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን ከቀን ወደ ቀን ድል እየተቀዳጁ የጣሊያን ወታደሮችን መፈናፈኛ፤ መግቢያ መውጫ አሳጧቸው። ከጣሊያን ወታደሮች ይማርኳቸው በነበሩ መሣሪያዎች ራሳቸውን እያደራጁ አብዛኛውን የገጠር ክፍል ተቆጣጠሩት።
በዚህ መሃል እንግዲህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ነበረው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ ጣሊያን የናዚ ጀርመን አጋር ሆነች። ያን ጊዜ እንግሊዞች የጣሊያን ጠላት ሆነው ኢትዮጵያን መደገፍ ጀመሩ።
ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥተው፤ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ረዷቸው፡፡ በጄኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬንያ ተነስቶ በደቡብ አቅጣጫ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ሲገሰግስ፤ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ከሱዳን ተነስቶ ወደ አሥመራ ፤ ከዚያም በሰሜን አቅጣጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡
በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የሚመራውና የአርበኞችና የእንግሊዝ አማካሪዎች የሚገኙበት ‹‹ጌዲዮን›› ተብሎ የተሰየመው ጦር ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጐጃም በኩል ወደ መሐል አገር ገሠገሠ።
በመካከለኛው ኢትዮጵያ አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃታቸውን አፋፋሙ፡፡ ጣሊያኖች ክፉኛ ተሸነፉ። በየቦታው ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ። ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ሳይሞላው ፤ ጣሊያኖች አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡
መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ እንግሊዞች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ስላልፈለጉ ቀዳማዊ አጼ ኃይል ሥላሴን በደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ አደረጓቸው። ይሁንና በአዲስ አበባ በአርበኞች ተፅዕኖና ቅሬታ የተነሳ አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቀዱ። አፄ ኃይለ ሥላሴም ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱ። ንጉሰ ነገስቱም አዲስ አበባ በታላቁ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ።
አዲስ አበባ ገብተው ‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው። አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልን አገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ጀምሮ ስለሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን እይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነው። እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ እርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግስታቱ ማህበር ወደ ወዳጆቻችን መንግስታቶች መጣን፤ እዚህ ስንነጋገር በቆየንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ አላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሳሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋር የባሕርይ የሆነውን ጀግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በጀግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸው አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት አመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዕዋታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ፡፡
የአገሬ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ዛሬ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት ደስታዋንም ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባድ የመከራ ቀንበርና ከዘለዓለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት አመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በዓል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚወዷት ላገራቸው ነፃነት ለንጉሰ ነገስታቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብር ካባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስዎስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሰሱትን አጥንታቸውን የከሰከሱትን ጀግኖቻችንን እናስታውሳለን። ለዚህም ለጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።
ባለፈው አምስት አመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያልቁ ያገኘናቸው መከራና ስቃይ ትምህርት ሆነውን ሰራተኛነት አንድነት ህብረትና ፍቅር በልባችሁ ተጽፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምህርት የሚሰጣችሁ ነው። ባዲሷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክልና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን። አገር የሚለማበትን ሕዝብ የሚበለጽግበትን እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርትና ጥበብ የሚሰፋበትን የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን የአገር አስተዳደርም ባዲሱ ስልጣኔ ተለውጦ ፍጹም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ስራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
ይሄ የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት የሆነው የአርበኞች ቀን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ምላጭ ስቦ ጥይት ከተኮሰው አርበኛ በተጨማሪ በየቤቱ ሆኖ የተባበረውም ቀላል አልነበረም።
ሰራዊቱ ‹‹ደረቅ ጦር›› እና ‹‹መደዴ ጦር›› ተብሎ ለሁለት ተከፍሎም ነበር። ደረቅ ጦር የተባለው ሙሉ በሙሉ ውጊያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ‹‹መደዴ ጦር›› የተባለው ደግሞ እንደሁኔታው የእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል። ነገሩ ሲከፋ ግን አርበኞች ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠልና የዱር አውሬ ሁሉ እየበሉ ተዋግተዋል። እናቶች ከሰራዊቱ ጋር አብሮ በመዝመት ምግብና ውሃ ከማቀበል በተጨማሪ ባህላዊ ህክምና እየሰጡ ሰራዊቱን ታድገዋል። የወደቀውን በማንሳት የቆሰለውን በመጠገን ተሳትፈዋል።
ይህ የአርበኞች ቀን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ድል ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ይህንና ኢትዮጵያውያን በወራሪዎችና ተላላኪዎቻቸው ላይ በየጊዜው የተቀዳጇቸውን ድሎች ሁሌም ያስቧቸዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30 /2014