እኛ ኢትዮጵያውያን “ውብ ድብልቅ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቅርስ፣ ታሪክ እንዲሁም ማንነት ያለን ህዝቦች ነን” ስንል እንዲያው ዝም ብለን አይደለም። ይልቁኑ በዓይን የሚታዩ፣ በእጅ የሚዳሰሱ፣ ያለምንም ችግር በህሊና ፍርድ የሚሰጣቸውና ምስክር የማያሻቸው በመሆናቸው ጭምር እንጂ። ለዚህ ነው የኛ ያልሆነውን ሁሉ አግበስብሰንና ህሊናችንን አውረን ለመታበይ የማንፈልገው። በዓለም መድረክ ላይ ረብጣ ገንዘቦችን አውጥተን የማስተዋወቅ እድሉን ባናገኝ እንኳን ዓለም ደጃፋችን ድረስ መጥቶ እውነታውን ቆፍሮ እንዲያገኝ እሴቶቻችን በራሳቸው አፍ አውጥተው የሚናገሩ ናቸው።
ከእነዚህ ውብ እሴቶች መካከል ለዛሬው ወደ ምስራቅ ተጉዘን በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የረመዳን ፆም እንዳበቃ የሚጀመረውን የሸዋል ኢድ እናስተዋውቃችኋለን። በተለይ በሃረሪ ክልል ይህ ሃይማኖታዊ ስርዓት ሌሎች የማህበረሰቡን እሴቶች ጨምሮ ባህላዊ ስነ ስርዓትን አካትቶ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። ይህን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ስነ ስርዓት በተመለከተ የሃረሪ ክልላዊ መንግስት ባህል ቅርስ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ አብደሸ “የሃረሪ ብሔረሰብ የማይዳሰሱ ቅርሶች ክንዋኔዎችና ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ስነ ስርዓቶች” ጥናትን መነሻ አድርገው እንደሚከተለው አብራርተውልናል።
ሹዋልኢድ
የሹዋሊድ ክብረ በዓል በእስልምና ሃይማኖት ያሉ አጽዋማትን (የጾም ወቅትን) ማንኛውም ለአቅም አዳምና ሄዋን የደረሰ የእምነቱ ተከታይ መጾም ሃይማኖታዊ ግዴታው ነው። ከእነዚህም መካከል ዋናው የጾም ወቅት የረመዳን ወር ጾም ነው። የሹዋል ፆም በእስልምና እምነት የረመዳን ወር ጾም እንደተጠናቀቀ የሚጀመር ነው። በሹዋል ወር የመጀመሪያው ቀን የዒድ አልፈጥር በዓል ይከበራል። ከሹዋል ሁለተኛው ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ስድስት ቀናት ደግሞ የሹዋል ጾም ይጾማል። ይህ ጾም በሹዋል ወር የሚጾም በመሆኑ ስያሜውን ከወሩ አግኝቷል። የሹዋል ጾምን ነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት ዘመናቸው ሲጾሙት የነበረ ጾምና በሹዋል ወር ስድስት ቀናትን የጾመ ዓመቱን በሙሉ እንደጾመ ይቆጠራል የሚል አስተምህሮት ያላቸው በመሆኑ የሹዋል ጾም በዚሁ መነሻነት በሐረሪዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ መጾም እንደተጀመረ ይነገራል። የሹዋል ጾም በፍላጎት የሚጾም የሱና ጾም ነው። ሱና ስንል የነብዩ መሐመድ ወይም የረሱልን አስተምህሮ የተከተለ፣ አጅር ወይም ምንዳ የሚገኝበት፣ በረመዳን ጾም በምክንያት የተፈታን ጾም ለማሟላትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮትን መተግበርን ሁሉ የሚያካትት ነው።
በሃይማኖቱ የሹዋልን ጾም በተከታታይም ሆነ ነጣጥሎ መጾም ይቻላል። ሁለቱም የአጿጿም ስልት ደረጃቸው እኩል ነው። ይሁንና ከዒድ አልፈጥር በኋላ ያሉትን ስድስት ቀናት በተከታታይ መጾም ግን የበለጠ ዋጋ አለው። እንደሚታወቀው ሴቶች በተፈጥሮ አስገዳጅነት ምክንያት በረመዳን የጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ለማቋረጥ መገደዳቸው አይቀሬ ነው። ይህን ያቋረጡትን ወይም ያጓደሉትን የጾም ቀናትም በሹዋል ጾም ማካካስ ይጠበቅባቸዋል። 138 ምንም እንኳ በሃይማኖቱ በወሩ በማንኛውም ጊዜ ማካካስ እንደሚቻል ቢጠቀስም በሐረሪዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በተከታታይ መጾሙ እንደ ባህል ተይዞ የመጣ ነው። ለዚህም መነሻቸው የሴቶችን ጫና ከመቀነስ አንፃር፣ ሴቶች ለብቻቸው ከሚጾሙ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በጋራ መጾሙ አብሮነትን፣ መተሳሰብንና መደጋገፍን ያጎለብታል በሚል አስተሳሰብ ነው። ከዚያም ባለፈ በመጾማችን ከአላህ ወይም ፈጣሪ የምናገኘው አጅሪ ወይንም ምንዳ ከፍተኛ ነው በማለት ያምናሉ። በዚህም መሠረት ጾሙን ከስራ ባህላቸው ጋር እንዲስማማ አድርገው ባህልና ወጋቸውን በጠበቀ መልኩ ስድስቱን ቀናት በተከታታይ በመጾም የሹዋሊድን በዓል ያለምንም የጾታ፣ ዕድሜና ማኅበራዊ ደረጃ ገደብ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ በደመቀ ሁኔታና ባህላዊ እሴቶቻቸውን በሚያንጸባርቅ መልኩ እየተከበረ ይገኛል።
ይህም ባህላዊ ቅርሱን የብሔረሰቡ ህያው ሀብትና የማንነታቸው መገለጫ አድርጎታል። ሹዋሊድን በሐረር የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ሐረሪዎች ጭምር የበዓሉን ቀን ጠብቀው ከያሉበት በመሰባሰብ ያከብሩታል። ክብረ በዓሉ በድሬዳዋ፣ በጉርሱም በተለይ ካለፉት ሁለት አስርተ አመታት ወዲህ በአዲስ አበባም በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ እየተከበረ የሚገኝ የሐረሪ ብሔረሰብ ትልቅ የማንነት መገለጫ እሴት ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምንም እንኳን የሹዋል ጾምን የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች የሚጾሙት ቢሆንም የሹዋሊድን በዓል እንደሐረሪዎች የሚያከብሩት አለመሆኑ ነው።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 2 ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበር፣ የማሳደግና በዘላቂነት የመንከባከብ መብት መረጋገጡ ይታወቃል። 139 የሐረሪ ሕዝብ ክልል ህገ መንግስትም የሐረሪ ብሔረሰብ ታሪኩንና ባህሉን የማልማትና የማበልፀግ እንዲሁም በቋንቋው የመጠቀምና የማሳደግ ህጋዊ መብት የተጎናጸፈ መሆኑ ተደንግጓል። በዚህም መሠረት በአዋጅ ቁጥር 61/1999 የሹዋሊድ በዓል የሚከበርበት ዕለት በክልሉ የበዓል ቀን ሆኖ እንዲከበር በአዋጅ ተደንግጓል። ይህም በዕለቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው በዓሉ በየዓመቱ በድምቀት እንዲከበር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ክብረ በዓሉም በብሔረሰቡ አባላትና በሌሎችም አካባቢ ማኅበረሰቦች ዘንድም እንዲታወቅ ምክንያት ሆኗል፡፡በዚህም መነሻነት ቅርሱ የተለያዩ የዓለም ሕዝቦች የመነጋገሪያ እና የመወያያ ርዕስ እንዲሆንና ከሹዋሊድ በዓል እሴቶች ሌሎች ሕዝቦችም ልምድ መቅሰም እንዲችሉ ቅርሱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገብ አስፈልጓል።
የሹዋሊድ በዓል አከባበር ሂደት
የሹዋሊድ በዓል በሐረሪ የሚከበረው ለሶስት ተከታታይ ቀናት ነው። ሐረሪዎች በዓሉ የማንነታቸው መገለጫ ባህላቸው መሆኑን ለመግለጽ ዚኢኛ ኢድ (የኛ በዓል)፣ አዳ ኢድ (የባህል በዓል ወይም ባህላዊ ይዘት ያለው በዓል)፣ ሹዋል ኢዴ በማለት ይጠሩታል። በሹዋሊድ የበዓል አከባበር ወቅት በሚዜሙ ዜማዎች ውስጥ ዚኢኛ ኢድ፣ ሹዋል ኢዴ የሚሉትን ሐረጋት ይደጋግሙታል። በሌላ በኩል አዳ ኢድ (የኛ የሐረሪዎች በዓል) እያሉም ያዜሙበታል። ሹዋሊድ መሠረቱ ሃይማኖት ቢሆንም እንደ ሐረሪ በዓሉ በባህላዊ ክንዋኔዎችና ሥነ-ሥርዓቶች ታጅቦ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ነው (ዙሄር)። ሹዋሊድን ከሐረሪዎች በተጨማሪ ሌሎች በሐረርና በአካባቢዋ የሚኖሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ወደ ከተማዋ በመምጣትና በበዓሉ ላይ በመሳተፍ በጋራ የሚተገብሩትየ ማይዳሰስ ቅርስ ነው።
አንዳንዶች አብሮ በመኖርና የአካባቢውን ባህል ከመልመድ የተነሳ የበዓል ሥነ-ሥርዓቱን ከመሳተፍ ባለፈ በአንዳንድ ሥርዓተ ክዋኔ ላይ በትግበራ የሚሳተፉበት ሁኔታም አለ። ለምሳሌ ዝክሪ በማውጣትና ከበሮ በመምታት በመሳሰሉት ተሳትፎ ያደርጋሉ። የሹዋሊድ በዓል የአካባበር ሥነ-ሥርዓት የሚጀምረው ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ማለትም ከሹዋል ወር ስድስተኛው ቀን ምሽት ላይ እስከ የሹዋሊድ ዕለት ከሚውልበት ስምንተኛው ቀን ድረስ ይቀጥላል። በስድስተኛው ቀን ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ አባቶችና እናቶች ዝክሪ በማድረግ ማለትም ፈጣሪያቸውን አላህን፣ ነብዩ መሐመድንና በማስታወስና በማወደስ በዓሉን ያከብራሉ። በሚቀጥለውም ምሽት ይኸው ሥነ-ሥርዓት ይቀጥላል። ዋናው የበዓሉ ሥነ-ሥርዓት የሚጀምረው በዋዜማው ምሽት እና በሹዋሊድ በዓል ዕለት ነው (ዲኒ ረመዳን)። በዓሉ በዋነኝነት በሁለቱ የጁገል መግቢያ በሮች በሚገኙ አዋቾች ይከበራል። ይኸውም በሐረር ከተማ በስተምስራቅ የሚገኘው አርጎ በሪ (ኤረር በር) አጠገብ በሚገኘው አው ሹሉም አህመድ አዋች ላይ እና በሐረር በስተሰሜን በኩል አስሱም በሪ (ፈላና በር) አቅራቢያ በሚገኘው አውዋቅበራ አዋች ላይ በጋራ ይከበራል።
በእነዚህ ምሽቶች የሹዋሊድ በዓል የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት በአዋቹ ግቢ ይከናወናል። በመጨረሻው የዋዜማ ቀን ሁሉም የሚሳተፍበት በመሆኑ ሰፊ የበዓል ማክበሪያ መድረክ ይዘጋጃል። የሥርዓቱ መሪዎች ወይም ሙሪዶች፣ አባቶችና እናቶች በመድረኩ ላይ ሆነው በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ። ሌሎች ተሳታፊዎች ደግሞ ዙሪያቸውን በመሰባሰብ ሥርዓቱን መከታተል በሚችሉበት ሁኔታ ቆመው አለያም ተቀምጠው ይከታተላሉ፡፡
በእነዚህ የዋዜማ ቀናት የአካባቢው ታዳጊ ህፃናት ለዋዜማው ሥነ-ሥርዓት ማድመቂያ የሚገለገሉበት ትንሽና ትልቅ ከረቡ (ከበሮ) የተፈለገውን ድምጽ እንዲያወጣ በእሳት መሞቅ ስላለበት በየቤቱ እየዞሩ እንጨት ያሰባስባሉ። በዚህም ጊዜ የሚከተለውን ዜማ ያዜማሉ።
በሐረሪኛ ፡- ወዚዞው በሐሬይ
አው አባድርሌ ኢስሓት አሐድ ኢንጪ
ዳኢም አመትዞም ያቦርደኹ…በማለት ያዜማሉ፡፡
በአማርኛ ሲመለስ፡-
በሠፊው መጥተናል
ለአው አባድር አንድ አንድ እንጨት
ዓመት ዓመት ያድርሳችሁ እንደማለት ነው፡፡
በዚህ መልኩ ታዳጊዎቹ የተፈለገውን እንጨት ከአሰባሰቡ በኋላ ወደ አዋቹ ይገባል። ከዚያም የተዘጋጁትን ከበሮዎች በእሳት የማሞቅ ሥራ ይከናወናል።
ከዚህ በኋላ የበዓሉ እድምተኞች ወደ አዋቹ ገብተው በተዘጋጀላቸው ቦታ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ከበሮውንም የሚመቱት የዓመታት ዕውቀት ልምድና ክህሎት ያካበቱ አዛውንቶች እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን ዕውቀት የቀሰሙ ወጣቶች ናቸው። ከበሮ መቺዎቹ መጀመሪያ ድምጹን በመቃኘት የተስተካከለ መሆኑን ያረጋግጡና ለበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ዝግጁ ያደርጋሉ።
ዕለተ በዓሉ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የተጀመረው የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት የሚጠናቀቅበት በመሆኑ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ውዳሴዎችና ባህላዊ ጭፈራዎች ታጅቦ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። በዚህ በዓል ላይ ለሥነ-ሥርዓቱ ማድመቂያ የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ። ከእነዚህም መካከል ትንሽና ትልቅ ከረቡ ወይም ከበሮ አንዱና ዋናው ሲሆን ከቁርጥራጭ ጣውላ ከእንጨት የተሰራ በብሔረሰቡ አጠራር ‹‹ከበል›› በመባል የሚታወቀው የእጅ ማጨብጨቢያ እና የከበሮ መምቻ ዱላ ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እንደውዳሴው የዜማ ይዘትና የጭፈራ ዓይነት የተለያዩ የዓመታት ስልቶችን በመከተል የተለያዩ ድምጾችን ለማውጣት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሲሆን ለበዓሉ አከባበርም ልዩ ድምቀት ይሰጣሉ። የምሽቱ የበዓል ሥነ-ሥርዓት የሚጀመረው በአባቶች ምርቃት ነው። ከዚያም ዝክሪ ወይም የምስጋና ዜማ ይቀጥላል። ዝክሪው ‹አዋዮው ሰላም አዋዮው ሰላም ሰላም› በሚል የዜማ ስልት ያለው ነው። በዚህ ሂደት የሴቶች ሚና ዝክሪውን መቀበል፣ በጭብጨባ እና በእልልታ ሥነ-ሥርዓቱን ማድመቅ ይሆናል። ወንዶቹ ደግሞ በተቀመጡበት ከግራ ወደቀኝ አንገታቸውን በማንቀሳቀስ ከፍ ዝቅ የሚለውን የዜማ ስልት እየተከተሉ በመቀበል እየደገሙ ማዜም ነው። የዜማ ስልቱም ‹አዋዮው አዋዮው ሰላም › የሚል ሲሆን፣ ይህም መሀመድ እንዴት ነህ! ሰላም ባንተ ይውረድ እንደማለት ነው። በዚህ ሂደት የበዓሉ ተሳታፊዎች ከአንዱ አዋች ወደሌላኛው አዋች የበዓል ሥነ-ሥርዓቱ ወደደመቀበት እየተመላለሱ ያከብራሉ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝ 30 ቀን 2014 ዓ.ም