ከዕለታት በአንድ ቀን በአክሱም ከተማ የቅርብ ቤተሰብ የሚሆኑ አንድ አባታችን ከቤተክርስቲያን ወደ ቤት በመመለስ ላይ እያሉ በድንገት ወድቀው እግራቸውና ወገባቸው ይሰበራል። እኚህ አባትም በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት ለመጸዳዳትና ጽዳታቸውን ለመጠበቅ ይቸገሩ ነበር። እርሳቸውም ሲጸዳዱ ስቃዩ ስለሚበረታባቸውና አስታማሚዎች በምናደርግላቸው እንክብካቤ ተሳቅቀው ምግብ ላለመብላት ወስነው ነበር። እኚህ አባት በወቅቱ ምግብ ላለመብላት ሲወስኑ፤ ምግብ ካልበሉ እንዴት ስብራትዎ ይጠገናል? ከህመምዎስ እንዴት ይፈወሳሉ? ብዬ ጠይቄያቸው ነበር።
እርሳቸው «ልጄ እመገብ ነበር ነገር ግን በልቼ መፀዳዳት ስፈልግ እናንተን ስለማስቸግርና ስቃዩ ስለሚበረታብኝ እራቡንና ጥሙን ብችለው ይሻለኛል ብዬ ነው» ብለው በወቅቱ ምላሽ ሰጡኝ። እኔም ስቃያቸው ልቤን ስለነካው ምን ባደርግላቸው እንደፈለጉ ተመግበው ሳይቸገሩ መጸዳዳትና ንጽህናቸውን መጠበቅ ይችላሉ? ብዬ በማሰብ በተቀመጡበት የማንንም እርዳታ ሳያሻቸው መጸዳዳትና ንጽህናቸውን መጠበቅ የሚያስችላቸው ቀለል ያለ ዊልቸር በአካባቢው በተገኙ ቀላል ቁሳቁሶች አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሰርቼ እንዲገለገሉ ማድረግ ችዬ ነበር።
ዊልቸሩም መጸዳጃ፣ መታጠቢያና ሌሎች መገልገያዎችን ያሟላ ስለነበር እርሳቸውም ሳይሳቀቁ ተመግበው ከጉዳታቸው በቶሎ ሊያገግሙ ችለዋል። ዊልቸሩ እኚህ አባት ለመጸዳዳት ከተቀመጡበትና ከተኙበት በሚነሱበት ወቅት ሲደርስባቸው ከነበረው ህመምና ስቃይ የታደገ ነበር። አስታማሚዎችም እርሳቸውን በቀላሉ ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስና እንዲጸዳዱ በማድረግ በቀላሉ ለማስታመም ችለን ነበር» በማለት የፈጠራ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ዊልቸሩን ለመሥራት ምክንያት የሆናቸውን ታሪክ አጫውተውናል።
አቶ ጌታቸው ይሄንን የገጠማቸውን ችግር ምክንያት በማድረግ የፈጠራ ሥራው ለሌሎች ሰዎችም እንደሚያስፈልግ በተግባር በማየታቸው በ2004ዓ.ም በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ጌታቸውና ይብራለም ፓተንትድ ክሬቲቪቲ ኢንጂነሪንግ የሚል ድርጅት አቋቁመው የተለያዩ አዳዲስ ሀሳቦችን በመጨመርና በማዘመን ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እየሠሩ ይገኛሉ።
በዚህም ስድስት የሚደርሱ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በፈጠራ ባለቤትነት ለማስመዝገብ የበቁ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ የፈጠራ ሥራዎች አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን ለማገዝና ለመደገፍ የሚያስችሉ ናቸው። ከነዚህ መካከል ለአብነት የገላ መታጠቢያና መጸዳጃ የተገጠመለት አልጋ፣ የልብስ ማስጫ፣ የኮንዶሚኒየም ቤት እቃ ማጓጓዣ፣ ውሃ ቆጣቢ መጸዳጃ ቤቶች የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ድርጅቱ አሻሽሎ የሠራቸው ዘጠኝ የሚደርሱ ዊልቸሮች የአካል ጉዳተኞችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ነፍሰጡር እናቶችን እና አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች እንደ ጉዳታቸው አይነትና እንደ ጤና ችግራቸው እንዴት መንከባከብ እንደሚያስችልና ያለው ጠቀሜታ ምን እንደሚመስል ከድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና የፈጠራው ባለቤት ከሆኑት ከአቶ ጌታቸው ገብረህይወት ጋር ቆይታ አድርገናል። እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ዊልቸሮቹ ዘጠኝ አይነት ሲሆኑ፤ ከሌሎች ዊልቸሮች የሚለያቸው የመጸዳጃ፣ ጽዳት መጠበቂያ፣ የመመገቢያ እቃዎች ማስቀመጫ፣ ምቹና የማይዝግ መቀመጫ አሏቸው።
አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች ለመጸዳዳት ወደ መጸዳጃ ቤት በሚሄዱበት ወቅት በመውደቅ ለሌላ አካል ጉዳት ይዳረጋሉ። እንዲሁም ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ የሌላ ሰው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ይህ የፈጠራ ሥራ አካል ጉዳተኞች በተቀመጡበት ያለማንም ሰው እርዳታ በቀላሉ መጸዳዳትና ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ያስችላቸዋል። እንዲሁም ነፍሰጡር እናቶች፣ አቅመ ደካሞችና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ዝቅ ያለ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ይቸገራሉ።
በተጨማሪም አደጋ ደርሶባቸው ስብራት የገጠማቸው ሰዎች ምግብ በልተው እንደ ፈለጉ ለመጸዳዳት ይቸገራሉ። በዚህም የሚጠጣም ሆነ የሚመገቡትን ምግብ ይቀንሳሉ ብሎም ምግብ አለመብላት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። እንዲሁም ለመጸዳዳት ከተቀመጡበት ወይም ከተኙበት ወደ መጸዳጃ ቤት በሚሄዱበት ወቅት ለከፍተኛ እንግልት ይዳረጋሉ፤ የገጠማቸው ጉዳት ስብራት ከሆነ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ስብራታቸው ስለሚናጋ ቶሎ ለማገገምና ከህመማቸው ለመዳን ይቸገራሉ።
በአጠቃላይ ለመጸዳዳትና ንጽህናቸውን ለመጠበቅ የሰዎችን እርዳታ ይሻሉ። ነገር ግን ይህን የፈጠራ ሥራ በመጠቀም አካል ጉዳተኞች እራሳቸውን ችለው ያለማንም እርዳታ መጸዳዳትና ንጽህናቸውን ለመጠበቅ ያስችላቸዋል። አስታማሚ አስቸግራለሁ ብለው ሳይጨነቁ ምግብ በልተውና ጠጥተው በቀላሉ በፈለጉት ሰዓት በተቀመጡበት ለመጸዳዳት ያስችላቸዋል። ስብራታቸው ሳይናጋ መንቀሳቀስ ችለው ከጉዳታቸው ቶሎ ለማገገም የሚረዳ የፈጠራ ሥራ ነው። በተጨማሪም አንዲት እናት ከወሊድ በፊትና ከወሊድ በኋላ ሳትቸገር በቀላሉ በቤት ውስጥም ሆነ በሆስፒታል ለመጸዳዳት ያስችላታል።
በአጠቃላይ ዊልቸሮቹ ለማንቀሳቀስ በጣም ቀላል፣ ከዝገት ነፃ፣ ለዓይን ማራኪ በመሆናቸው ማንኛውም ሰው በፈለገው ቦታ ሊጠቀማቸው ይችላል። የፈጠራ ሥራዎቹ በሰፊው ተሠርተው ለማህበረሰቡ ቢዳረሱ ዘርፈ ብዙ ጥቅምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሲሆኑ፤ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አዛውንቶችንና አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያግዙና የሚደግፉ ስለሆኑ ጥቅማቸው ድርብ ነው ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ዊልቸሩ የፈሳሽ ማጠራቀሚያ ታንከር የተገጠመለትና በቀጥታ በፒቪሲ ከመጸዳጃ ቤት ጋር የተገናኝ በመሆኑ፤ ዊልቸሩ ላይ በሚጸዳዱበትና ንጽህናቸውን በሚጠብቁበት ወቅት ወደ ውጭ የሚፈስስ ፍሳሽ እንዳይኖር ተደርጎ በጥንቃቄ የተሠራ ነው። በመሆኑም በሚጸዳዱበትና ንጽህናቸውን በሚጠብቁበት ወቅት ምንም አይነት ሽታና ፍሳሽ ስለማይኖረው አብሮ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ለጎንዮሽ ችግር አያጋልጥም።
እንዲሁም በሽተኞችንና አካል ጉዳተኞችን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ቀላልና ምቹ ነው። «የፈጠራ ሥራ ሲጀመር ባህሪው ድሀ ነው። ነገር ግን ከነባራዊ ሁኔታው ተነስቶ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እያደገና እየበለጸገ የሚሄድ ነው» ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የፈጠራ ሥራውን በብረትና በጣሳ ነበር የሠሩት። አሁን ግን ዓለም የደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም አሻሽለው ሠርተውታል። የፈጠራ ሥራዎቹ ከፋይበር፣ ከኬሚካሎች፣ ከጎማ፣ ከፕላስቲክና ከፒቪሲ ነው የተሠሩት።
በመሆኑም የፈጠራ ሥራዎቹ ሙሉ ለሙሉ ከፋይበር የተሠሩ ስለሆኑ ከዝገት ነጻ በመሆናቸው ለረጅም ጊዜ ጥንካሬና ውበታቸውን ጠብቀው ግልጋሎት የሚሰጡ መሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት፤ የፈጠራ ሥራውን በሰፊው አምርተው ለማህበረሰቡ ለማድረስ የሚያስችል የመሥሪያ ቦታ መንግሥት አበርክቶላቸዋል። በፈጠራ ሥራቸውም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ30ሺ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ሜዳሊያዎችን፣ ዋንጫዎችን፣ የምስክር ወረቀቶችንና የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ወደ አምስት የሚደርሱ ድርጅቶች የ43ሺ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገውላቸዋል። እንዲሁም የፈጠራ ሥራውን ሲሠሩ የቅርብ ቤተሰቦቻቸው በሀሳብና በገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው አጫውተውናል። «አንዳንድ የሚመለከታቸው አካላት፣ ባለሀብቱና ማህበረሰቡ ለቴክኖሎጂና ለፈጠራ ሥራ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና የፋይናንስ እጥረት የፈጠራ ሥራቸውን ሲሠሩ የገጠማቸው ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑ የጠቆሙት የፈጠራ ባለቤቱ፤ ማህበረሰቡ ጥቁር መፍጠር አይችልም በሚል የሥነ ልቦና ቅኝ ግዛት እየተገዛ ያለ በመሆኑ የፈጠራ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን ከማበረታታት ይልቅ መተቸት ይቀልለዋል።
«ህብረተሰቡም በሀገር ውስጥ የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች አስተማማኝ ነው ብሎ ለመግዛትና ለመጠቀም አይደፍርም። በመሆኑም የፈጠራ ሥራዎች ፍጹም ከሆኑ በኋላ ነው ወደ ገበያ እየገቡ ያሉት። ማህበረሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው እንዴ የተሠራው በማለት የፈጠራ ሥራዎቹን የማጣጣል ባህሪ ያለው በመሆኑ፤ የፈጠራ ሥራውን በሚፈለገው መጠን አምርቶ ወደገበያ ለማውጣት ተግዳሮት ሆኖብኛል። የፈጠራ ሥራዎች ለወደፊት ያድጋል ብሎ የሚያምን አስተሳሰብ በማህበረሰቡና በባለሀብቱ ዘንድ ስለሌለ የፈጠራ ሥራዎች እውን እንዲሆኑ ድጋፍ የሚያደርግ የለም።
ኢትዮጵያ ለኢኖቬሽን ምቹ ያልሆነች ሀገር ናት» ሲሉ የፈጠራ ሥራውን ሲሠሩና ለገበያ ሲያቀርቡ የገጠማቸውን ችግር ገልጸውልናል። ሥራ አስኪያጁም የፈጠራ ሥራዎቹን እንደ ሰው የጉዳት አይነት፣ የመግዛት አቅምና የዊልቸሮቹ አይነት ከሁለት ሺ ብር ጀምሮ እስከ 12ሺ ብር እንደሚሸጡ የጠቆሙ ሲሆን፤ ሀገሪቱ ያላት ፖሊሲ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ምቹ አለመሆን አመራሮችና ባለሙያዎች የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን ለመደገፍ ቢፈልጉም መደገፍ አለመቻላቸውን ያብራራሉ።
የፈጠራ ባለቤትነት ሌላ ዓለም ላይ ገንዘብ ማለት ነው። በመሆኑም ብድር የሚገኝበት መንገድ በጣም ሰፊ ነው ያሉት የፈጠራ ባለቤቱ፤ የሀገሪቱ ፖሊሲ ለፈጠራ ሥራ ምቹ ባለመሆኑ የፈጠራ ሥራዎቹ በሰፊው ተሠርተው ለማህበረሰቡ ለማድረስ ብድር የሚያቀርብ ተቋም ባለመኖሩና ባለሀብቱ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲደግፍ ግንዛቤ ስላልተፈጠረለት የፈጠራ ሥራቸውን በሚፈለገው መጠን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንደተቸሩ ገልጸዋል።
ሥራ አስኪያጁ የፈጠራ ክህሎትና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እንዲወጡ የሚያደርግ የመንግሥት መዋቅርም ሆነ ፖሊሲ አለመኖር እና የመንግሥት አካልም ሆነ የማህበረሰብ ክፍል ከአድናቆት ውጭ የሚሠሩ የፈጠራ ሥራ ወደ መሬት እንዲወርዱ በቁርጠኝነት ድጋፍ የሚያደርግ ባለመኖሩ፤ ያሉኝን የግል ንብረት በመሸጥ የፈጠራ ሥራው ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረግ የፈጠራ ሥራዬን በሰፊውም ባይሆን ለገበያ አቅርቤ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረግሁኝ እገኛለሁ። ነገር ግን ወጣቶች የሀገሪቱን ብሎም የአህጉሪቱን ችግር መፍታት የሚችል ትልልቅ ጽንሰ ሀሳቦችን ይዘው ይመጡና የሚደግፋቸው በማጣታቸው ህልማቸው እውን ሳይሆን ቀርቶ ሥራ አጥ ሆነው የተቀመጡ አሉ ብለዋል።
እንደ ዜጋ ሀገሬ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተላቅቃ ያደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ እፈልጋለሁ ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የፈጠራ ሥራ መነሻ ችግር በመሆኑ፤ ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር ያለባት ብትሆንም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት አመቺ ናት። በተጨማሪም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት የሚችሉ የተማረ ወጣት ኃይል ያላት በመሆኗ፤ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል። ስለዚህ አመለካከት ላይ ምንም ስራ ስላልተሰራ መንግሥት አመለካከት ላይ በሰፊው መሥራት ይጠበቅበታል። የፈጠራ ባለቤትነት መብትና የፈጠራ ጽንሰ ሀሳብ ላለን ጽንሰ ሀሳቡ መሬት ላይ የሚወርድበትና የፈጠራ ሥራው ለማህበረሰቡ ተደራሽ የምናደርግበት ብድርና የተለያዩ ድጋፎች ቢደረጉ ይበልጥ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት ያስችለናል።
በዚህም የተለያዩ ጽንስ ሀሳብ ያላቸው የፈጠራ ሰዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፍ በማድረግ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን በሀገሪቱ ለመፍጠር ያስችላል። ለአብነትም ዓለም ላይ የምናያቸው ወጣት ቢሊየነሮች የስኬታቸው ምስጢር የሀገራቸው ፖሊሲ የኢኖቬሽን ፖሊሲ ስለሆነ ነው። ስለዚህ የፈጠራ ባለቤቱ ችግር ፈች የሆኑ ሥራዎችን ይዞ ብቅ ካለ የፈጠራ ሥራው እንዲስፋፋና ለማህበረሰቡ ተደራሽ ሆኖ ችግር እንዲፈታ የማድረግ ድርሻው የመንግሥት፣ የባለሀብቱና የማህበረሰቡ ሊሆን ይገባል ይላሉ የፈጠራ ባለቤቱ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
ሶሎሞን በየነ