ወርሃ መስከረም ውስጥ ነው፤ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምዝገባ የሚያደርጉበት ወቅት። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት በትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተገኘ የበጎፈቃድ ሰራተኛ ወጣት በአርሶአደሮች አካባቢ ባለ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ወላጆቻቸው ሊያስመዘግቧቸው የቀረቡትን ተማሪዎችን እየመዘገበ ነው። የሚመዘግባቸው ተማሪዎችን ስም፣ እድሜ፣ የቀደመ የክፍል ደረጃ፣ ወዘተ እየጠየቀ ይመዘግባል። አንዱ ተመዝግቦ ሲያልቅ ሌላኛው እየተከተለ ምዝገባው እየተከናወነ ነው። አስመዝጋቢው ቤተሰብ ማስረጃውን አቅርቦ ልጁን በስሙ ከማስመዝገብ ባለፈ፤ ለምን ልጃችሁን እከሌ አላችሁት የሚል ጥያቄ የለም። የወላጆች መብት ነውና ወላጆች ይዘውት የቀረቡትን ስም መመዝገብ የመዝጋቢው ግዴታ ስለሆነ።
ጥያቄው ግን በመዝጋቢው በጎፈቃደኛ ወጣት አእምሮ ውስጥ ግን ይመላለሳል። አንዳንዱን ስም ሲሰማ “ለምን ወላጆች ልጃቸውን እከሌ አሉት?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል። እያንዳንዱን ወላጅ እየጠየቀ እንዳይረዳ ሰዓቱ አይፈቅድለትም፤ በጥድፊያ እየተከናወነ የሚገኝ ምዝገባ ነውና። አንዳንዱ ስም ሆን ተብሎ ከአባት ጋር እንዲስማማ ሆኖ የወጣ ይመስላል፣ አንዳንድ ስም ደግሞ የአንድን ወቅት አገራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የወጣ፣ አንዳንዱ ደግሞ የሆነን የጭንቅ ወቅት አመላካች ይመስላል ሌላው ደግሞ ዛሬን አሻግሮ ነገን በተስፋ መመልከትን። ብዙ ስም፣ ብዙ ተስፋ፣ ብዙ መልእክት።
ስንቶቹ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስለስማቸው ጠይቀው መረዳት ያላቸው መሆኑን እርግጠኛ መሆን ባንችልም በልማድ እንደምናውቀው ብዙ ሰው ቤተሰቡ ያወጡለትን ስም ትርጉም ጠይቆ የመረዳትና ለሌሎች ሰዎችም የማስረዳት ልማድ አለን። በስም ትርጉሙ ደስተኛ መሆኑን የሚገልጽ እንዲሁም ሚያዝንሰው ሊገጥመን መቻሉም አያጠያይቅም። በስማቸው ደስተኛ ያልሆኑ ስማቸውን እስከማስቀየርም ድረስ የደረሰ ስራን ሊሰሩ እንደሚችሉም እንረዳለን፤ በተጨባጭ የሚገጥመንም ስለሆነ።
የተማሪዎቹ ምዝገባ እንደቀጠለ አንድ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ከእናቱ ጋር ሊመዘገበ የበጎፈቃድ መዝጋቢው ፊት ወረፋው ደርሶት ቀረበ። እናቱ የልጁን ስም ተናገረች፤ ታዳጊውም በመነጫነጭ “እማ በዚህ ስም መጠራት አልፈልግም ብዬሽ የለም እንዴ፤ አዲስ አመት መጥቶ ትምህርት ቤት ስትመዘገብ እንቀይረዋለን ብለሽኝ ነበር እኮ?” አለ። እናትም ደጋግመው በማስረዳት የደከመ በሚመስል ድምጸት “ልጄ ልክ ነህ፤ ግን ከበደኝ። ደጋግሜ እኮ አስረዳሁህ፤ ለምን አትረዳኝም። እኔ ስምህን መቀየር አልፈልግም፤ በጠራሁህ ጊዜ ትርጉም የምሰጥህ በዚሁ ስምህ ስጠራህ ነው። የእኔ የእናትህን ሃሳብ መቀበል ካልቻልክ በቃ እኔ ስሞት ራስህ ታስቀይረዋለህ” ብለው ተናገሩና ከአይናቸው እምባ ዱብ አለ። ልጅም ደነገጠ፤ በአቆሙ ጸንቶ “እንግዲያውስ በዚህ ስም የምታስመዘግቢኝ ከሆነ ትምህርት አልማርም እንድታውቂው” ለማለት አስቦ የእናቱን እምባ ሲያይ አፉ ላይ አድርሶ መለሰው። መዝጋቢው እናት ፊት ላይ ያየው የስሜት መረበሽ ተጋባበትና ተረበሸ። መዝጋቢውም ስሙን ጠየቀ። ስሙ በህይወቱ ውስጥ ስላለው ስሜት። ከመደበኛ ስሙ በተጨማሪ በህይወት ጉዞው ስለወጡለት አያሌ የግብር ስሞች ሁሉ አሰበ።
በዚህ የምናብ ታሪካችን ውስጥ ያገኘናቸው እናትና ልጅ በስም ጉዳይ የጀመሩት ክርክር መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ለራሳችን አስበን እንለፈው። ዋናው ፍሬ ነገሩ በዚህ ደረጃ የስም ጉዳይ የቤተሰብ መነጋገሪያም እስከመሆን ሊደርስ እንደሚችል እንድናስብ፤ በስም ውስጥ አልፎ የሚፈጠረው የስሜት ቁርኝት ቀላል አለመሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ግን እንረዳ። አንድ እውነተኛ ታሪክ አንስተን እንቀጥል። ሰላም የሚባል ስም የምትጠራ ነገርግን በስሟ ደስተኛ ያልሆነች ሴት አስታውሳለሁ። በእናትና አባት መካከል በነበረው ከፍተኛ ያለመግባባት ወቅት የተወለደች በመሆኑ በቤተሰቡ ውስጥ ያለው ሰላም ማጣት በእርሷ መምጣት ይፈታል ተብሎ በመታመኑ የወጣላት ስም ነው። ነገርግን እናትና አባት በልጅቱ ዘመንም ሰላም ኖሯቸው አልተመለከተችምና ሰላም በሌለበት ሰላም መባሏ፤ ሰላም ታመጣለች ተብላ ታምኖባት ባለመሆኑ አዝና ስሟን ጠላችው። አንባቢው ስሜ ማን ነው? ብሎ ራሱን እየጠየቀ በስምና በመሆን መካከል ያለውን እርቀት ስለማጥበብ እያሰበ አንድ ሁለት እንላለን። በቅድሚያ …
የተቀበልከው እና የሰራኸው
በህይወት ጉዞ ውስጥ እንዲሁ የተቀበልናቸው እና እና በተግባር እራሳችን የሰራናቸው ወይንም ዘርተናቸው በቅለው ከእጃችን የሚገኙ ነገሮች አሉ። አንድ ልጅ አባቱንና እናቱን መርጦ አልተወለደም፤ እንዲሁ የተቀበለው እንጂ። አገር መርጦም የተወለደ የለም፤ እንዲሁ ሆኖበት ያገኘው እንጂ። የደም አይነቱን የመረጠ የለም፤ ከሆነ በኋላ አወቀው እንጂ።
የተቀበልከው እና የሰራኸው መካከል ስላለው ነገር የሚኖር የምልከታ ልዩነት ስማችንን ተሻግሮ የሚመጣ ጓዝ በአግባቡ ሰድረን ለማስቀመጥ ይረዳል። ልንቀይረው የማንችለው እንዲሁ የተቀበልነው ነገር ላይ የሚኖር መኮፈስ ሆነ መሸማቀቅ ትርጉም የለሽ ነው። በንጉሣዊ ስርዓት ወቅት የነበረው ማህበረሰባዊ መስተጋብር በተቻለው መጠን ከንጉሳዊ ስርዓቱ ጋር በደም ለመገናኘት መሞከር የተለመደ ነበር። የዘር ሃረግን ጠምዝዞም ቢሆን እንደምንም ከንጉሳዊ ስርዓት ውስጥ ራስን ለመጨመር መሞከር የሚስተዋልበት ልፋት። ወደ መሪነት መምጣት የሚፈልጉ ደግሞ የሚሄዱበት እርቀት ሩቅ የሆነ።
“ስምህ እንዴት ባህሪህ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል” በሚል ርእስ በbbc.com/future ላይ በሜይ 26፣ 2021 ላይ የወጣ ጽሁፍ ላይ እንዲሁ በነጻ ከወላጆች ልጆች የሚቀበሉት ስም ያለውን የሥነልቦና ተጽእኖ ባለሙያዎችን ዋቢ በማድረግ ያትታል። የሰዎች የራሳቸው ጥረት ነገራቸውን መወሰኑ እንዳለ ሆኖ ስምን ተከትሎ የሚመጣው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትም ይሞግታል። የሰዎች ስም አንዳንዴም ብሔርን እንዲሁም እምነትን አመላካች ስለሚሆን በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ጫና መፍጠሩ አይቀርም። በዚሁ ጽሁፍ ውስጥ የአሜሪካ መንትያ ህንጻዎችን ያወደመው የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የአረብ ስም ያላቸው ሰዎችን ከስማቸው ተነስቶ የማግለል ወይንም የመፍራት አካሄዶች እንደተስተዋለ ይጠቅሳል።
በተፈጥሮ በተቀበልነው ነገር ላይ የቱንም ያህል ወጥተን ብንገባ ልንቀይረው እንደማንችል ተገንዝቦ መቀበል የተሰኘን ፖሊሲ ማስተናገድ አማራጭ የሌለው ነው። ልንቀይረው ከምንችለው ባሻገር ያለ በተግባር ስራችን ቀይረነው ልናይ በምንችለው አቅጣጫ ላይ ማተኮር ግን ተገቢነት ያለው። ሰርተን ከእጃችን ያደረግነው የላባችን ፍሬ ምን ሊሆን እንደሚችል መረዳት። ከቤተሰብ በተቀበልነው ማናቸውም ነገር ላይ የሚኖረን መመጻደቅ ሆነ እፍረት የዛሬ ኑሯችንን እንዳይጎዳ ማድረግ።
ስማችን የቱንም ያህል አስደሳችና ምርጥ ስም ቢሆን ግብራችን እንደስማችን ካልሄደ የፊደሎች ጋጋታ ከመሆን ያለፈ ሊሆን አይችልም። እንዲሁ ከተቀበልነው ከስማችን ባሻገር ትርጉም ያለው ነገር በተግባር ማከናወን የቻልነው የተግባር ህይወታችን ማሳያ እርሱ ነውና። የተግባር ህይወታችን ድምር ውጤት የህይወት ዘመናችን መከናወንም ነውና። አንባቢው በህይወት ዘመኑ በክንውን ዘመኑን መጨረስ ይፈልጋል፤ ጸሐፊውም እንዲሁ። አንባቢው አንዳች አቅም ሰው በመሆኑ ውስጥ ብቻ አለው፤ ሌላውም ሰው እንዳለው። አቅሙ ወደ ፍሬ ሊቀየር የሚችለው ስሙን ጠይቆ በስሙ ውስጥ ያለውን የትኛውንም መልእክት ቀንና ማታ ማሰብ ሳይሆን ዛሬ ላይ ወደ ውጤት የሚያደርስ ነገር መዝራት ሲችል ነው።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወደ ኋላ መቶ አመታትን በመሄድ በተሰራው ስራ እከሌ እኮ ከእኔ ወገን ነው የሚል አጉል ሽለላ፤ በሌላው አንጻር ደግሞ ከመቶ አመታት በፊት የተፈጸመን ጥፋት የሆነ ወገን አድርጎ እከሌ ላይ ድንጋይ ማንሳት ይስተዋላል። ይህ ስምን ጠይቆ በራስ ስም ትርጉም ላይ መደሰትና ማዘን ብቻ ያልሆነ ለዛሬው ተጨባጭ ህይወት አንዳች ፋይዳ የሌለው ነው። በተቀበልነው እና በሰራነው ላይ የሚኖር የተሳሳተ ትርጉም የሚፈጥረው ለራስ ስም አወጣጥ።
ያወጡልህና ያወጣህላቸው
ማርከስ አውሪሊስ የተባለ ሰው፤ “ማንኛውም የምንሰማው ነገር አስተያየት እንጂ ተጨባጭ መረጃ ሊሆን አይችልም፤ ማንኛውም የምናየው ነገር እይታ እንጂ ተጨባጭ እውነት ሊሆን አይችልም” በማለቱ ይጠቀሳል። ይህ አባባል የምንሰማውና የምናየውን ሁሉ ተቀብለን የምንወስደው እርምጃ ወደተሳሳተ ድምዳሜ ሊያደርሰን እንደሚችል የሚያሳይ ነው። በህይወት ጉዞ ውስጥ አስተውለነውም ይሁን ሳናስተውል ከምናደርጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ ለሌሎች ስም ማውጣት ነው። የመዝገብ ስም ኖሯቸው ነገርግን የግብር ስም እናወጣላቸዋለን። ከመጠሪያ ስሙ ላይ የምንጨምረው የፍርደኝነት ስም። ገንዘብ በማባከን ካየነው “አባካኙ” ብለን ስም አውጥተን ባወጣነው ስም በውስጣችን እየጠራነው በአፋችን መደበኛ ስሙን አቆላምጠን እንጠራዋለን። በጾታዊ ግንኙነቱ አንዳች ክፍተት ካየንበት እድሜ ልኩን በዚያው መንገድ እየሄደ እየማገጠ እንደሚኖር ቆጥረን ስም እናወጣለታለን። በንግግሩ ውስጥ አንዳች ነገር መደነቃቀፍን ከፈጠረ የተፈጠረችውን መደነቃቀፍ አጉልተን በመሳል መጠሪያው እናደርጋለን።
የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ስም የወጣላቸውን አያሌ ሰዎች አስተዋውቆናል። በአንዳች ነገር ጎድለው የተገኙ ሰዎች ከሆኑ መጠሪያቸው ያጎደሉት ነገር ሆኖ ሲሽከረከር ይውላል። “ምንም ኃጢአት የሌለበት ሰው የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውር”ተብሎ ቢጠየቅ ሰው ሁሉ ወደራሱ ቢመለስ የማያደርገው የሚመስል፤ ነገርግን ቅጽበታዊ በሆነ ወሬን ከአንድ ጫፍ ወደሌላ ጫፍ የማጋባት ልማድ ይህን እያደረገ እናገኛለን። የአንድ ግለሰብ የግል ጉዳይና ሌሎች ነገሮችን መለየት እስካይቻል ድረስ የማህበራዊ ሚዲያ መወያያ ሆኖ እናስተውላለን። በህይወት መንገዳችን ላይ ፍጹም የሆነን እርምጃ ለመራመድ አስበን የምናደርገው ጉዞ ያለውን ፋይዳ እረዳለሁ፤ የጥንቁቅ ሰውነት ህይወት። እንደ ኃይማኖት አስተማሪ ሰው ሁሉ ለመልካም ነገር ሁሉ ራሱን እያዘጋጀ እንዲኖር አስተምራለሁ። ነገርግን የሰው ልጅ ፍጹም የሆነ እንከን አልባ የሆነን ኑሮ መኖር የሚችልበት አቅም ላይ አለመሆኑንም እረዳለሁ። የኃጢያት ስርየት ወይንም ኃጢያተኛ ነኝ ብሎ የቀረበን ሰው ይቅር ማለት ያስፈለገበት ምክንያቱም፤ ስለ ስርየትም መስዋእት ይሆን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር እንደመጣ የምናስተምረው ሰው በራሱ ወደ ፍጹምነት መድረስ ባለመቻሉ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታን ከጠየቀ ከፈጣሪው ይቅርታን ሊያገኝ ስለተገባው ነው።
የማህበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ ያለውን ምልልስ ስንመለከት ሁሌ ራሳችን እንከን አልባ ሌላኛውን ወገን ደግሞ በእንከን ውስጥ ውሎ የሚያድር አድርገን እናቀርባለን። እውነታው ግን ሰው ሁሉ ደካማም መሆኑ ነው፤ በሁላችንም ውስጥ ስህተት የሚገኝ መሆኑ ነው።
በመሆኑም ሰዎች ባወጡልን ስም ተደናግጠን ከጉዞ የምንገታ ከሆነ እኛም ጥፋተኞች እንሆናለን። ሰዎች ስለራሳቸው ጥፋት ሳይሆን ስለሌላው መመልከት የሚቀናቸው ሆነው በተገኙ ቁጥር ራሳችንን ጎድተን፤ ጊዜያችንን በማይገባ ሁኔታ ውስጥ ስናሳልፍ እናያለን።
ዛሬ ስሜ ማንነው ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ ቤተሰቦቻችን ካወጡልን ስም ባሻገር ሰዎች ከሆነው ተነስቶ ያወጡልንን ስም እንመልከት? በዚያስ ምን ያህል አእምሮችን ተይዞ ከጉዞችን ተስተጓጎልን። መስተጓጎል አስቀምጦን ከሆነ እንድናነሳ፤ ዝለን ከሆነ እንድንበረታ፤ ተስፋ ቆርጠን ከሆነ ተስፋችንን እንድናድስ፤ ተደብቀን ከሆነ እንድንወጣ ይገባል።
መሻሪያው ላይ ማተኮር
በሰዎች ዘንድ ስላለው ስም አብዝቶ ከመጨነቅ ስለመሻሪያው ማሰብ የተሻለ ነው፤ እርሱም መልካሙን ስራ ማድረግ። ሰዎች ያወጡልን የቱንም ስም ቢኖር በክርክርና በሌሎች መንገዶች ለማጥፋት ከመሄድ በተግባር ስራ ማሸነፍ የተሻለው ነው። ሰዎች በሌብነት ስም ያወጡለት ሰው ሌባ አለመሆኑን ለማስረዳት ከሚደክመው ድካም ሌባ ሆኖ የተገኘ ከሆነ ከድርጊቱ መመለስ እንዲሁም በንጽህና መኖር ትክክለኛው መንገድ ነው። ሁልጊዜ በቅድሚያ ለራሳችን ታማኝ መሆኑ አስፈላጊ ነው። በጾታዊ ግንኙነት ችግር ውስጥ የገባ ሰው ሰዎች ስለ እርሱ ከሚሉት ነገር ይልቅ ትክክል መሆን አለመሆኑን ራሱ መበየን፤ ትክክል አይደለሁም በሚልበት አግባብ ላይ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ነው። ከትዳሩ ውጪ የሚሄድ ስህተቱን ተመልክቶ በፍጥነት የሚያደርገው መመለስ የተሻለ ነው የተበላሸ ስሙን ለማደስ በውሸት ጋጋታ ውስጥ ከመዋኘት። ስህተትን መቀበል ይዞት የሚመጣው አደጋ ቢኖርም ቢያንስ በራስ ደረጃ ስህተትን ተቀብሎ ለመፍትሔው መስራት የተሻለው ነው።
የህይወት ጉዞ አስደሳች የሚሆነው በሆነው እንጂ በተናገርነው ልክ አይደለም። ልንሆን የተገባውን ማወቅ፤ ልንሆን የተገባውን መሆን፤ ልንሆን የተገባውን እንዳንሆን የሚያደርጉ አንገትን ለሚያስደፉ ድምጾች አንገትን በመድፋት ምላሽ ከመስጠት ቀና ብሎ መመላለስ። ይህ ማለት ጥፋትን እያጠፉ እፍረት የለሽ መሆን ማለት ሳይሆን ያለፈውን አስተካክሎ ወደፊት በንጽህና የመራመድ ቀና ማለት ትርጉም ነው።
ወደ ማጠቃለያ ሃሳባችን ስንመጣ ደግመን ደጋግመን ስማችንን እንጠይቅ። ስሜ ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ቤተሰብ የሰጠንን ስም ትርጉም መነሻ አድርገን በስሙና በእኛ ወቅታዊ ሁኔታ መካከል ያለውን ልዩነት ተመልክተን ልዩነቱን የሚያጠብ የተግባር ሰውነትን ስናስቀድም ትጋት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ በሌላው ጫማ ውስጥ ራስን መጨመር፣ ስኬት ማለት አንድ ነገር ብቻ አለመሆኑን፣ ከሰው ጋር በሰላም መኖር ያለውን ቦታ፣ ወዘተ እንረዳለን። የተሰጠን ስም ትልቅን ተስፋ አመላካች ቢሆን ወደታየው ተስፋ ለመድረስ የሚገባውን ዛሬ ላይ ማድረግ ከተቀበልነው ስም በላይ ለውጤት አቅም ይሆነናል።
በትላንት ጉዟችን ላይ ተመርኩዘው ሰዎች ያወጡልን ስም ዛሬ ላይ ወደፊት ከመራመድ አቁሞን እንደሆነ ሰው ሁሉ ስህተት እየሰራ የሚኖር፣ የፍጽምና አቅም የሌለው መሆኑን ተረድተን፣ ፈጣሪ የምንሻውን መልካም የመሆንን አቅም እንዲያበዛልን እየለመንን ወደፊት ለመራመድ ስለመነሳት ተመለከትን። ሰዎች ምንም ቢደረግ የሚሉት አያጡምና በሰዎች አስተያየት ላይ የተመሰረተን የህይወት አቅጣጫን ከመምረጥ መታገስ እንዳለብን ይህን አልን።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014