ጠዋት ማታ መሬት እየጫረ የሚተክዘው ጎልማሳ ነገር ሆዱ ከገባ ሰንብቷል። ሁሌም ቢሆን አይኖቹን አያምንም። በቤታቸው የሚገቡ የሚወጡ ሁሉ አይመቹትም። ወጪ ገቢውን በጥርጣሬ እየቃኘ ጥርሱን ይነክሳል። ባሻገር እያስተዋለ ይተክዛል፣ ይናደዳል። በየቀኑ ምክንያት እየፈለገ የሚብከነከንበት ጉዳይ ሰላም እያሳጣው ነው።
ሁኔታውን የተረዱ ወላጅ እናት ከአጠገቡ ሆነው ይመክሩታል። እሱ ዘወትር የሚጨነቅበት ነገር እሳቸውን አሳስቦ አያውቅም። በየቀኑ ጉዳዩን እያነሳ ሲናደድ በእርጋታ ያዩታል። ባልተገባ ግምት ከሌሎች እዳይጠላ፣ እንዳይጋጭ ሲጥሩ ከርመዋል። ምክራቸውን ቢሰማም ቃላቸውን አያምንም። የሚሉትን ይጠራጠራል፣ የሚናገሩትን ያጣጥላል።
እናቱ መልካም ሴት ናቸው። እሳቸውን የሚያውቁ ሁሉ ከልብ ያከብሯቸዋል፤ እህት ወንድሞቻቸውን ጨምሮ መላው ቤተሰብ ለወይዘሮዋ የተለየ ግምት አላቸው። ታላላቅ ወንድሞቻቸው ስለእሳቸው ሲናገሩ ቃላቸው አንድ ነው።
በታናሽ እህታቸው አመኔታና ፍቅር አላቸው። ልጆቻቸው ለእናታቸው በእጅጉ ይሰስታሉ። ሁሉን በእኩል ዓይን እያዩ አሳድገዋቸዋል። ዛሬን ኖረው ለቁምነገር የበቁት፣ ትዳር መያዝ ጎጆ መቀለስ የቻሉት በደጓ እናታቸው ጥረትና ልፋት ነው።
ወይዘሮዋ ልጆቹ እንዲዋደዱ፣ ተከባብረው እንዲዘልቁ በጎ ምሳሌ ናቸው። የመንደሩ ነዋሪም ቢሆን በእኚህ መልካም ሴት በጎነት ሲጠቀም መኖሩን መስካሪ ነው። እሳቸው የተቸገረን ጠያቂ፣ የተጣላን አስታራቂ ናቸው። ሁሌም የተናገሩት ይሰማል። ያሉት ሁሉ ይፈጸማል።
ጎልማሳው የወይዘሮዋ የበኩር ልጅ መሆኑ ይታወቃል። እሱ ማለት ለእሳቸው የትዳራቸው የመጀመሪያ ፍሬ፣ የህይወታቸው አዲስ ምዕራፍ ነው። መቼም ቢሆን ሀዘን ትካዜውን አይወዱም። መጨነቅ ማዘኑ በገባቸው ጊዜ ጠጋ ብለው ሀሳብ ንግግሩን ያጤናሉ። ከሚለው፣ ከሚናገረው ተነስተው መፍትሄ ያሉትን ያጋራሉ።
ልጃቸው የእናቱን መልካምነት አሳምሮ ያውቃል። አንዳንዴ የሚሉትን ሊሰማ ይሞክራል። ብዙ ጊዜ ግን ቃላቸውን አምኖ ለመቀበል፣ እንደሀሳባቸው አድሮ ለመፈጸም ይቸግረዋል።
እናት የሰሞኑን የልጃቸውን ኩርፊያና ጥያቄ ካወቁት ሰንብተዋል። ከቅያሜ አልፎ ቂም የያዘበትን ጉዳይ መላ ለማለት ሲለፉ ቆይተዋል። እሳቸው እንዳሰቡት ጉዳዩ ባይሳካም ተስፋ አልቆረጡም። የሚናገረውን ክፉ ቃል በደግ እየመለሱ፣ የሚያስበውን አጉል ጉዳይ እያስታመሙ፣ ሊያሳምኑት ሞክረዋል።
እናት በእሳቸውና በእህት ወንድሞቹ ላይ ያሳደረው ጥርጣሬ ሲያሰጋቸው ቆይቷል። ሀብትና ንብረትን ሰበብ አድርጎ የሚያስበውን አጉል ጉዳይ መቀበል አይሹም። ከሚላቸው ተነስተው ለማሳመን ያደረጉት ጥረት ፍሬ አልያዘም። ያም ሆኖ ዛሬም ዝም አላሉም። በተቻላቸው ሁሉ የልጃቸውን ክፉ ስሜት በበጎ መንፈስ ሊተኩ ጥረታቸውን ይዘዋል።
የቂም መነሻ …
ጎልማሳው ራህማቶ ከድር በሚኖርበት የገጠር ቀበሌ ከአያቱ የተቸረውን አራት ጥማድ መሬት ሲያርስበት ቆይቷል። መሬቱ ከዓመት እስከ ዓመት ያሰበውን ያሳፍሰዋል። ለም መሬቱን በርትቶ ባረሰ ጊዜ የልቡን መሻት አያጣም። በምርቱ በረከት እንዳሻው ሲጠቀም የኖረው ጎልማሳ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ስጋት ገብቶት ትካዜ አብዝቷል።
ራህማቶ ታናናሽ እህት ወንድሞቹን በጥላቻ ማስተዋል ጀምሯል፤ ሰብሰብ ብለው ካያቸው ውስጡን ደስ አይለውም። መገናኘት ማውጋታቸውን በበጎ አይተረጉመውም። የእነሱ በአንድ መሆን ለአንዳች ምክር እየመሰለው ይጠራጠራል።
ራህማቶ ከአያቱ ያገኘውን መሬት ሌሎች እንዲያዩበት አይሻም። እስከዛሬ ማናቸውም የጥቅም ተካፋይ እንዳይሆኑ ሲሞግት፣ ሲያከላክል ቆይቷል። እናቱ ከእህት ወንድሞቹ እንዲስማማና፣ ጥላቻና ቂምን እንዲተው እየመከሩ፣ እየዘከሩ ነው። እሱ ግን ይህ አይነቱን ቃል ፈጽሞ መስማት አይፈልግም። ማንም በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ለማሳወቅ ጥላቻውን አሳይቷል።
ወላጅ እናቱ ሰሞኑን ከልጃቸው አንደበት ያረጋገጡት እውነታ በእጅጉ እየረበሻቸው ነው። ራህማቶ ከእሱና ከእሳቸው በቀር በቤቱ ማናቸውንም ማየት እንደማይሻ መናገር ጀምሯል። እህት ወንድሞቹ የሀብት ንብረቱ ስጋት መሆናቸውን ከመናገር አልፎ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይዟል።
እናት ልጃቸው ራህማቶ እህት ወንድሞቹ በግቢው ‹‹አይድረሱብኝ›› ማለቱን አልወደዱትም። ቤቱ የጋራቸው በመሆኑ ሀሳቡን መቀበል እንደማይችሉ ነግረውታል። በየአጋጣሚው ጥላቻውን የሚያሳየው ጎልማሳ በእናቱ ውሳኔ ተበሳጭቶ ጉዳዩን በሌላ ተርጉሞታል።
አሁን ራህማቶ በወላጅ እናቱ ተናዶ ውስጡ እያቄመ ነው። ለንብረቱ ስጋት ከሆኑ እህት ወንድሞቹ ‹‹ተስማማ›› የመባሉ እውነት አልተመቸውም። በግቢው ‹‹አይድረሱብኝ›› የማለቱ ሀሳብ በእናቱ ዕውቅና ያለማግኘቱ እያበገነው ያተክነው ይዟል። እናት ደጋግመው ‹እነሱ እንዳይመጡ መከልከል አልችልም›› ብለውታል። እንዲህ የማለታቸውን ጉዳይ በበጎ ያላየው ጎልማሳ የእሳቸውን ሀሳብ ከእነሱ አዛምዶ በአንድ ደምሯቸዋል።
ጎልማሳው ራህማቶ እናቱን ማድመጥ ትቶ የጎሪጥ ማየት ከጀመረ ሰንብቷል። እሳቸው ‹‹የራሴ›› የሚለውን ንብረት ለእህት ወንድሞቹ ሊያካፍሉ መሆኑን ጭምር እያስወራ ነው። እናት ሌሎች ልጆቻቸው ከቤት እንዲርቁ አይሹም። ሁሉም ተሰባስበው ማየት ፍላጎታቸው ነውና ‹‹ተው፣ እረፍ›› ማለቱን ቀጥለዋል። የራህማቶን ስጋት የሚያስወግዱበት ጥረት ባይሳካም በየቀኑ ሊያሳምኑት፣ ሊያግባቡት ይተጋሉ።
ራህማቶ እያደር ጠባዩ መቀየር ይዟል። ‹‹የግሌ ነው›› በሚለው መሬት መነሻ በእህት ወንድሞቹ ያሳደረው ቂምና ጥላቻ በርትቷል። ጥቂት ቆይቶ ያስከተለው አዲስ ወሬ ደግሞ ቤተዘመዱን እያነጋገረ ነው። ጎልማሳው እናቱ ለእህት ወንድሞቻቸው ጭምር መሬቱን ሊሠጡበት መሆኑን ላገኛቸው ሁሉ ማውራት፣ ማስወራቱን ቀጥሏል።
ይህ ወሬ በስፋት መዛመቱን ተከትሎ የእናት ስጋት መጨመሩ አልቀረም። ልጃቸው ከእህት ወንድሞቹ አልፎ ወደ አክስት አጎቶቹ ማለፉ አሳስቧቸዋል። አሁን ጉዳዩን ለመፍታት ሌላ አማራጭ ያሻቸዋል። ራህማቶ ከጀመረው አጉል ጥርጣሬና ጥላቻ መውጣት አለበት። ይህን ዕውን ለማድረግ ወይዘሮዋ ሽማግሌዎችን ሰበሰቡ። ቤተዘመድ ጠርተው ትልልቅ ሰዎች ይዘው ልጃቸውን ጠየቁ፣ አስጠየቁ።
ራህማቶ በሸምግልናው ቀን ውስጡ ያለውን ስጋት ደጋግሞ ተናገረ። እህት ወንድሞቹን ጨምሮ አክስትና አጎቶቹ የራሱን መሬት ሊቀራመቱ ማሰባቸውን በስጋት አወጋ። ለዚህ ችግር ሰበብ ሆናለች ያላቸውን እናቱን እየወቀሰ፣ ተጠያቂ አደረገ። እናት አሁንም የሚለው ሁሉ ከእውነት የራቀ መላ ምት መሆኑን ገለጹ። የሚሉትን እንዲሰማና፣ እንዲቀበል አሳሰቡ። ጎልማሳው ልጃቸው ቃላቸውን አላመነም።
ሽማግሌዎቹ ሀሳቡን ሰምተው የሚለው ሁሉ ሀሰትና የተሳሳተ መሆኑን አሳወቁት፤ ራህማቶ ለጊዜው ጉዳዩን በግማሽ ልቡ ተቀበለ። ይህን ያዩት እናት እፎይ ብለው ሰነበቱ፤ እስካሁን የተነሳው የመሬት ጉዳይ ከእንግዲህ ርዕስ ሆኖ ጠብ እንደማይዘራ አሰቡ።
ውሎ አድሮ በራህማቶ ውስጥ የከረመው ጥርጣሬ ዳግመኛ አገረሸ። በየቀኑ በሚያነሳው ተቃውሞና ወቀሳም እናቱን ተጠያቂ ያደርግ ያዘ። እናት አሁንም ልጃቸውን እየለመኑ የሚያስበው ሁሉ ከእውነት የራቀ ጥርጣሬ መሆኑን ሊያስረዱት ሞከሩ። ራህማቶ ከሚያርሰው ለም መሬት በየአመቱ ከበቂ በላይ ገንዘብ ያገኛል።
ይህ ገቢ ለጎልማሳው ርካታ ሆኖ አያውቅም። ሁሌም ከወገኖቹ እየተጣላ በርካቶችን እየተቀየመና እያስከፋ ነገውን በአጉል ተስፋ ያልማል። ተስፋው አልያዝ፣ አልጨበጥ ባለው ጊዜም ጥላቻው እያየለ፣ ውስጡ እየጎሸ አርቆ ያስባል። ሁሌም የሀሳቡ መጨረሻ በበጎ ተደምድሞ አያውቅም። በዚህ ስሜት እንደተያዘ ሰአታት ይነጉዳሉ፣ ቀናት ያልፋሉ።
በሽማግሌዎች እርቅ በእፎይታ የከረመው ቤተሰብ ሰላሙ መናጋት ሲጀምር ጎልማሳው ወንድም ታናናሾቹ ከቤት እንዲወጥሉት ጠየቀ። ይህ መሆን ካልቻለም ነገሮች በዚህ እንደማይቀጥሉ አሳሰበ። ጉዳዩን በመፍትሄ የቋጩት ሽማግሌዎች በሌሎች ላይ ፈርደው የእሱን ሀሳብ አጸደቁ፡፤ ልጆቹ ከቤት ወጥተው ሌላ ቦታ ካለው የአባታቸው ቤት እንዲቆዩ ወሰኑ።
እንደሀሳቡ የሆነለት ራህማቶ አሁንም ለጥቂት ቀናት ሰላማዊ መስሎ ሰነበተ። ሁኔታውን ያስተዋሉም እፎይታ አግኝተው ከረሙ። ጎልማሳው ዛሬም የውስጡን የረሳ አይመስልም። ነግቶ በመሸ ቁጥር የክፉ አይኖቹ ምልከታ እንደቀድሞው ቀጠለ። ጥላቻና ጥርጣሬው ብሶም በወላጅ እናቱ ማቄም መቀየሙ ታወቀ።
እናት አሁንም ከአጠገቡ አልራቁም። በውስጡ ያደረውን ጥላቻ አርቀው በፍቅር ሊያቀርቡት ሞከሩ። ራህማቶ እጅ አልሰጣቸውም፤ ልቡ አልሳቀላቸውም። እናቱን ከእህት ወንድሞቹ ፈርጆ፣ የሀብት ንብረቱ ጠንቅ፣ የማንነቱ ዕንቅፋት አድርጎ ሳላቸው።
ራህማቶ በእጁ ያለው ለም መሬት፣ በውርስ ያገኘው ሀብት ለሌሎች ማለፉን አምኖ በጥላቻ ይብከነከናል። ማንም በዚህ ጉዳይ ሊመክርና ሊያሳምነው ቢሞክር ሊሰማና ሊቀበል አይፈልግም። ጠዋት ማታ የሚጨነቅበት የውርስ ጉዳይ ሰላም ነስቶ ጥርስ አስነክሶታል። ለዚህ ተጠያቂ የሚያደረጋቸውን እናቱን ባየ ቁጥር ውስጡ ይጋያል፣ ጥላቻው ይጨምራል።
አሁን ጎልማሳው ራህማቶ በእናቱና በእህት ወንድሞቹ ላይ ያሳደረው ጥላቻ በርትቷል። ባገኛቸው ቁጥር አጠገቡ እንዳይቀርቡ፣ ወደግቢያቸው እንዳይዘልቁ የማይሆነው የለም። በየጊዜው ለዕርቅ ጣልቃ የሚገቡ ሽማግሌዎች የዕለት ድርጊቱን እንደልማድ ቆጥረው ትተውታል። ምክርና ተግሳጽ የማይገባው ሰው ዛሬም በማንአለብኝነት መራመዱን፣ በትዕቢት መታበዩን ቀጥሏል።
ወንድሞቹ መኖሪያቸውን ለቀው ከወጡ በኋላ ውስጡ ያልረካው ራህማቶ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቂምና ጥላቻውን ሊያሳይ ይሞክራል። ሰበብ የሚያደርጋቸው እናቱን ሲያገኝም በወቀሳ ሲያሸማቅቃቸው ይውላል። እናት የሚያውቁትን እየነገሩ ልጃቸውን ይመክራሉ መስማትና ማመን የማይሻው ራህማቶ ልቡ በጥላቻ እንደተሞላ ፊቱን ያዞርባቸዋል።
ሚያዚያ 20 ቀን 2006 ዓ.ም
ይህ ዕለት ከሌሎች ቀናት የተለየ አልነበረም። የሚያዚያ ሙቀት ያረፈበት ውሎ በወበቁ እንደታጀበ አመሻሹ ደርሷል። የራህማቶ እናት ወይዘሮ ጠጂቱ ከእራት በኋላ በስራ የደከመ አካላቸውን ሊያሳርፉ ጋደም ይላሉ። የልጃቸው ራህማቶን ኩርፊያና ግልምጫ ለምደውታል። በማደጎ የሚያሳድሯት ትንሽ ልጅ ገና በጊዜ ዕንቅልፍ እያዳፋት ነው።
እሳቸውም ቢሆኑ ተቀምጠው መቆየትን አይሹም። በድካም ዝለዋል። በዕንቅልፍ አምሮት የጠበቡ አይኖቻቸው፣ ወደመኝታ እየመሯቸው ነው። ጠጂቱ ደጋግመው እያዛጉ ከትንሽዋ ልጅ አጠገብ ደረሱ። ከባድ ዕንቅልፍ ጥሏታል። ጥቅልል ብላ ከተኛችው ታዳጊ ትከሻ ብርድልብሱን ገልጠው ከጎኗ ጋደም አሉ። አፍታ አልቆዩም። ራሳቸውን ለዕንቅልፍ አሳልፈው ሰጡ።
አሁን እኩለ ሌሊቱ ተጋምሶ የንጋቱ መንገድ ጀምሯል። እስካሁን በአይኑ ዕንቅልፍ ያልዞረው ራህማቶ ዓይምሮው ነገር እንዳመላለሰ አስር ሰአት ደርሷል። ገና በጊዜ ዕንቅልፍ የጣላቸው እናቱ በዓይኑ ውል አለቡት። ለእሱ ዕንቅልፍ ማጣት ሰበብ ሆነዋል። ሀብት ንብረቱን ለእህት ወንድሞቹ፣ ለአክስት ለአጎቶቹ መስጠታቸው አይቀርም። ይህን ቆሞ ከሚያይ ሞት ይሻለዋል።
ራህማቶ በዚህ ጉዳይ ሌሊቱን ሲያስብበት አድሯል። ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ከእናቱ ሌላ ተጠያቂ አላገኘም። ሰአቱን ደጋግሞ አስተዋለው። ከለሊቱ አስር ሰአት እያለፈ ነው። ንዴት እንደዋጠው ወደ እናቱ መኝታ ቤት ተንደረደረ። እናቱ ትንሽዋን ልጅ በክንዳቸው እንዳቀፉ በእንቅልፍ ወድቀዋል።
እናቱን ሲያያቸው ሰውነቱ ጋለ፣ የተለየ ብሽቀት ብልጭ አለበት። በመጣበት ፍጥነት ጎናቸው ደርሶ ልጅቷን ከእጃቸው ፈልቅቆ አነሳት። ዕንቅልፍ የረታቸው ወይዘሮ ፈጽሞ አልሰሙትም። ህጻኗን ሌላ ክፍል አስተኝቶ ያዘጋጀውን ወፍራም ቆመጥ ይዞ ወደ እናቱ ተመለሰ።
አሁንም ወይዘሮዋ በዕንቅልፍ እንደተሸነፉ ነው። ራህማቶ የእናቱ ሁኔታ አላሳዘነውም። ያመጣውን ዱላ እንዳጠበቀ ወደ አናታቸው ሰነዘረ። ዱላው ዒላማውን አልሳተም። አይምሮው ያሰበውን አልዘነጋም። ቆመጡን የያዙ እጆቹ ድርጊቱን ደግመው፣ ደጋግመው ፈጸሙት።
ራህማቶ በደግ እናቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት ያስደነገጠው አይመስልም። በእልህ እንደተሞላ ጠጋ ብሎ አስተዋላቸው። እናት ከዕንቅልፋቸው ሳይነቁ በደም ተነክረው አሸልበዋል። ልጃቸው መሞታቸውን ሲረዳ ጊዜ አልፈጀም። በሩን የኋሊት ጠርቅሞባቸው በጥድፊያ ከመንደሩ ተሰወረ።
ሲነጋ…
ያለልምዱ ተከርችሞ ያረፈደው የእማወራዋ በር የብዙዎችን ዓይን ስቧል። ለወትሮው ወይዘሮዋ በዚህ ሰአት በስራ ሲጣደፉ ማየት የተለመደ ነበር። ባተሌዋ እናት ሁሌ ማለዳ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የሚያውቋቸው ጎረቤቶች በድምጻቸው መጥፋት ተጨንቀዋል። አንገታቸውን በአጥሩ አስግገው፣ ድምጻቸውን ዘለግ አድርገው በስማቸው ተጣሩ። ምላሽ አላገኙም። ግቢው ዝምታ እንደዋጠው ባወቁ ጊዜ ስጋት ገባቸው።
ሰዎቹ ግቢውን አልፈው የተዘጋውን በር ከፍተው ገቡ። ያዩትን ማመን አልቻሉም። ቅን አሳቢዋ ወይዘሮ በዱላ ተቀጥቅጠው ህይወታቸው አልፏል። ጉዳዩን ፈጥነው ለፖሊስ አመለከቱ። ፖሊስ በአስፈላጊው ጥንቃቄ አስከሬኑን እንዳነሳ በእማኞቹ ምስክርነትና ጥርጣሬ ተፈላጊውን ማሰስ ጀመረ። ብዙ አልቆየም። ራህማቶ ርቆ ሳይሄድ እጁን ለዱራሜ ፖሊስ መስጠቱን አረጋገጠ።
የፖሊስ ምርመራ…
የከምባታና ጠንባሮ ዞን ፖሊስ ተጠርጣሪውን አቅርቦ ስለወንጀሉ ድርጊት ጠየቀ። ራህማቶ ወላጅ እናቱን ስለመግደሉ አልካደም። የፈጸመውን ድርጊት አንድ በአንድ በማስረዳት አመነ። በበቂ መረጃዎች ማስረጃዎችን የሰነደው ፖሊስ ጉዳዩን ለዓቃቤ ህግ አሳልፎ ክስ እንዲመሰረት መዝገቡን አቀረበ። ዓቃቢ ህግ ከፖሊስ የቀረበለትን ዶሴ በጥልቀት መርምሮ በተጠርጣሪው ላይ ክስ መሰረተ።
ውሳኔ…
ጳጉሜ 5 ቀን 2006 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የከምባታ ጠንባሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ራህማቶ ሀጂ በወላጅ እናቱ ላይ በፈጸመው አሰቃቂ፣ ከባድና የነውረኝነት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራትን በመወሰን መዝገቡን ዘግቷል።
መልካምሥራአፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014