ብሂላችን ሲብላላ፤
የጽሑፉ ርዕስ የተዋቀረው “እሺ ይበልጣል ከሺህ!” የሚለው ነባሩ ብሂላችን መነሻ ሆኖ ነው። ከታዳጊነት እስከ ሽምግልና በአንደበታችን ታዝሎ የኖረው ይህ ዕድሜ ጠገብ ሸበቶ አባባል አንድም ትዕዛዝ ቀመስ ነው፤ ሁለትም መደለያና ማመስገኛ ይሉት ብጤ ነው፤ ሦስትም የእምቢታ ተቃራኒ ነው። “ከእሺታ” ይገኛሉ የተባሉት የሺህ ምንትስ “ምርቶች” የትኞቹ እንደሆኑ እንኳንስ ተቀባዩ ቀርቶ ምኞቱን የሚገልጸው ሰው ራሱ ስለማወቁ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
እንደ ብዙዎቹ ባህሎቻችንና ሥነ ቃሎቻችን ሁሉ በትርጉሙ ጉዳይ ላይ “ተከድኖ ይብሰል” በማለት ካልተጽናናን በስተቀር፤ ላይ ላዩንም ሆነ ውስጠ ምሥጢሩን ዘልቀን እንመርምር ብንል ትርፉ ድካም ስለሚሆን ሰሙን እንደ ወርቅ ቆጥረን ለጎሽታ እና ለምርቃት መገለጫነት መዋሉን ብቻ በማስታወስ ማለፉ ይበጃል። ያለበለዚያ በአባባሎችና በተረታ ተረቶች “እንዴት? ለምን? ማንስ ተናገረው?” ብለን በፍቺያቸውና በትርጉማቸው ዙሪያ ብንሟገት ገላጋይ ዳኛም ሆነ በቂ ምላሽ ለማግኘት ያዳግታል። ስለሆነም ብሂሉን የጠቀስነው ለማዋዣነት እንጂ ጫን ብለን የምናሰላስላቸው በርካታ ጉዳዮች ስላሉ እነርሱን ወደ መጠቃቀሱ ማዝገሙ ይበጃል።
“ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል” እንዲሉ ምርቃት አይሉት እርግማን “ከጅማት በጠነከረ እምነት”፣ “እሺ ይበልጣል ከሺህ” አባባልን በሕይወታችን ውስጥ በትንሹም በትልቁም ጉዳዮቻችን አዘውትረን ስለምንገለገልበት ለእምቢታና ለእውነት ቆመን ለመሟገት አቅም ማግኘት አልቻልንም። በአኗኗራችን ውስጥ ሥር ሰዶ በተንሰራፋው በዚህ የእምቢታና የመራርነት ተቃራኒ ይትባሃል ዳፋ መንስኤነትም በበርካታ ጉዳዮች አሳራችንን እየበላን እንደኖርን ከታሪክም ሆነ ከተሞክሮ አንዳንድ ማሳያዎችን እየጠቃቀስን ለማየት እንሞክራለን። “መቼም አላለልኝ ከዘሩ ቁይልኝ”፤ አለ ይባላል፤ መከራው ተደራርቦ ተስፋው የተፈተነ የአገሬ አርሶ አደር። እኛም እንደዚህ ምስኪን ገበሬ ጭንቀታችን መላውን አሳጥቶን በብሂሎች መጽናናቱን ስራዬ ብለን ይዘነዋል።
“እሺና ገለባ ባይከብድም” – ለእኛ ግን እንደ መርግ ከብዶናል፤
ሕዝብንና ነባር ባህሎችን ሽቅብ እየተንጠራሩ መሄስ በእጅጉ እንደሚከብድ አይጠፋንም። በአገራዊ ታሪኮቻችን ውስጥ “በእሺታ” የፈሊጥ ማምለጫነት አንገት ደፍተን “ውሻን ምን አገባው ከእርሻ” በሚል ስጋትና ምንግዴነት በርካታ መከራዎችን ስንጋት ኖረናል። የደርግ መንግሥት “ሶሻሊዝም” ይሉትን የተውሶ አይዲዮሎጂ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ አሸክሞ ምድሪቱንና ትውልዱን ቁም ስቅል እያሳየ የደም ዋጋ ሲያስከፍል ጠብመንጃውና ጭካኔው አንገት አስደፍቶን “በእሺታ” ስንዘምርለትና ስናወድሰው ዘመናችን ጨሶና ተቃጥሎ ስንለበለብ ኖረናል።
ደርግን እንቃወማለን የሚሉት ጀብደኞቹ የፖለቲካ ቡድኖችም ሳይቀሩ ወጣቱን በየጎራው አቧድነው ይመንበትም አይመንበትም፤ በአግባቡ አስቦበትና አጢኖበት ርእዮተ ዓለማቸውንና ግባቸውን ሳይመረምርና ሳይፈትን “እሺ በማሰኘት ብቻ” የእሳት እራት ሲያደርጉት ኖረዋል። በአሜንታና በፍርሃት መተብተቡ እንደ ቀኖና ተቆጥሮ “እምቢ!” ብሎ እንዳይቃወም እንኳን “በእሺታ መንፈስ” አእምሮውን ሰልበውት ነበር።
“እሺ ይበልጣል ከሺህ”፣ “ክፉ ቀንንና ቅዝምዝምን የሚያሳልፉት ዝቅ ብለው ነው” ወዘተ. የሚሉትን ብሂሎች እንደ መጽናኛ በመቁጠርም ብዙው ሕዝብ ያንን ክፉ ዘመን የተሻገረው ግራ አጋብተውት ግራ ስለገባው
ነበር። “ባለ ጠብመንጃውን ደርግንም ሆነ ቀስተኞቹን የወቅቱን የፖለቲካ ቡድኖች ጨክነን ብንቃወም ኖሮ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችል ነበር?” የሚለው ጥያቄ አካሄዱ ወዴት እንደሚያደርስ ስለሚገባን እንካ ሰላንትያውን አናደምቅም።
ወያኔ ኢህአዴግም ለሦስት ዐሠርት ዓመታት ያህል በብረት በትሩ እየቀጠቀጠ ሲገዛን ከሚሊዮኖች መካከል ጥቂቶች መገኘታቸውን ባንዘነጋም አብዛኛው ሕዝብ ግን አሜን ብሎ “እየተነካካም ሆነ እየተሸማቀቀ” የኖረው ለሥርዓቱና ለሥርዓቱ “ጌቶች” “እሺ ይበልጣል ከሺህ” በሚል ይትበሃል ተቀፍድዶ የግፋቸው ትርዒት እያስነባው ነበር።
ባለጊዜዎቹ ሹመኞችና የቅርቦቻቸው “ብዙኃን” እንደፈለጉ በአገሪቱ ሥልጣንና ሀብት ሲፋንኑና ሲዘባነኑ መመልከት የአደባባይ ገሃድ እውነታ መሆኑ እየታወቀ አብዛኛው ሕዝብ የትርዒቱን ትራዤዲ ይከታተል የነበረው በእንባው ጅረት እየታጠበ ነበር። የተወሰኑት የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች፣ ሚዲያዎችና ብዙ ስም አይጠሬዎች ሕዝቡን ይሸነግሉ የነበረው “ይደልዎ!” በማሰኘት ጭምር “እሺ” አሰኝተው ነበር።
በእሺታና በአሜንታ ሥር ሰደው ወደ ዛሬው አገራዊ መከራ የተሸጋገሩ አንዳንድ የማሕበራዊ ነቀርሳ ማሳያዎችን እናመላክት። “ሹም እሺ እንጂ እምቢ አይባልም!” እንዲሉ፤ በየመስኩ ብዙ የመንግሥት “አደራ በል ልጆች” እንዳሻቸው በስልጣናቸው ሲጨማለቁና ሕዝብ ሲያስለቅሱ እያየን እንዳላየ የምናልፈው “በእሺታችን” እየተጽናናንና “ምን ማድረግ እችላለሁ?” በሚል ምክንያት እያሳበብን ነው።
ይህ ጸሐፊ ባለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት በአገሩ ጉዳይ አምርሮ መጮኹን የሚያውቁ የቅርብና የሩቅ ወዳጆቹም ሆኑ በጎ የሚመኙለት ሁሉ የተመካከሩ ይመስል “ለመሆኑ የአንተን የቁራ ጩኸት፣ ማሕበራዊ ሂስና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እዬዬ ከቶ ማን ይሰማል? ለመሆኑስ ይህንን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋናዎቹ ያነቡታል? ወዘተ” የሚሉትን ጥያቄዎች ደጋግመው ይጠይቁታል። ያሳሰባቸው የአገሬንና የሕዝቤን አበሳ እያየሁ በእሺታ ያለማሳለፌ እንደሆነ ተረድቻለሁ። “እሺ!” ብዬ ነገሮችን እንደ አመጣጡ ብቀበል ይህንን መሰል ጥያቄ እንደማልጠየቅ ይገባኛል።
የጸሐፊው መልስ አጭርና ግልጽ ነው። “ሁሉን እንዳላዩ መስሎ በማለፍ አንደበትንና ብእርን መዘጋቱ አልጠፋኝም። የእኔ ድርሻ የማሕበረሰቡ ህሊና ሆኖ ገንቢ ሃሳቦችን መዝራት ብቻ ነው። ዘሩ በተወሰኑ ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ሕይወት ውስጥ ውጤት ሊያመጣም ሆነ ላያመጣ ይችል ይሆናል። በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ለእውነት ኖሮ መሞት፣ ህሊናን አድምጦ መታዘዝና ለተከታዩ ትውልድ ጩኸትን አጋብቶ ማለፍ በራሱ ከክብር የበለጠ ክብር ነው። ”
ይበልጥ ሃሳቡን እናግዝፈው ከተባለም የእያንዳንዱ ዜጋ ሥራ በፈጣሪ ፊት የሚመዘነው በተቀበለው መክሊት ልክ ሕዝቡንና አገሩን ሳይታክት ምን ያህል በፍጽምና አገልግሎ እንዳለፈ እንጂ ኢትዮጵያዊ መሆኑ በራሱ እርባና ኖሮት “አበጀህ/ሽ” አያሰኝም። ይህ የማሕበረሰብ ድምጽ የመሆን ብርታትና ትዕግሥት የሚገኘው በግል ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ ፀጋ ጭምር መሆኑን ማስተወሱም ይበጃል።
እየጠዘጠዘ ፋታ ወደነሳን የዛሬው መከራች እናቅና፤
ድህነት የአገሬን ሕዝብ ያህል የተጫወተበት ሌላ ሕዝብ ስለመኖሩ ተገቢ ጥናት ያደረገ ሞጋች በድፍረት ወጥቶ ሃሳባችንን ፉርሽ እስካላደረገ ድረስ መልሱ “አይኖርም!” የሚል ይሆናል። “እምቢዮ!” ለማለት ድፍረትም ሆነ እምነትን አጥተን “በእሺታ” የተኮላሸንባቸውን አንዳንድ “መርገምቶቻችንን” እናስታውስ። ለምሳሌ፡- ተፈጥሮ ምንም ሳትበድለን ቆላና ደጋውን፣ ክረምትና በጋውን፣ የተፈጥሮ ሃብትንና ጸጋዎችን አመቻችታ ብትሰጠንም ዛሬም ድረስ “የልመና አኮፋዳችንን አንጠልጥለን” በጥረታቸው በልጽገው ሕዝባቸውንና አገራቸውን ከድህነት ያላቀቁ መንግሥታትን ከመማጠን ነጻ አልወጣንም። ድህነት ሲያሳክከን፣ ርሃብ ሲያቆራፍደን፣ የፍትሕና የርትዕ ጥማት ሲያንገበግበን፣ በስመ ዲሞክራሲ የፖለቲካኞች ጩኸት ሲያደናግረንና ሲያደናቁረን ቆም ብለን ነገሮችን በሰከነ መልኩ ከመመርመር ይልቅ መልሳችን አሜንታና “እሺታ” ስለሆነ እነሆ እንደ ትናንቱ ዛሬም የእለት ዳቦ እንኳን ብርቅ ሆኖብን ራሳችንን ነጻ ለማውጣት ተስኖናል።
ትንሽ ደፈር እንበል። ፖለቲከኞቻችን በአደባባይ ሲዋሹን፣ አንቂዎች ነን ባዮች ማስተዋላችንን አንቀው የራሳቸው የድብቅ አጀንዳ መፈጸሚያ በማድረግ “በሳጠራ ውስጥ እንደታፈኑ ጫጩቶች” ሲያንጫጩን እየዋሉ “እምቢ!” ብለን ከማምረር ይልቅ መወድስ የምናቀርብላቸው በእሽታችን ማረጋገጫነት ከሆነ ውሎ አድራል። ጫን እንበል ካልንም ምክንያታዊ ከመሆን ይልቅ በስሜት እየተላጋን “ለጠራን ሁሉ አቤት እያሉ እሺታን መግለጽ” ወደ ባህል ደረጃ አድጎ የተዋሃደን ይመስላል።
ድፍረታችንን መረር እናድርገው። የሃይማኖት ቤተ እምነቶች ምዕመናኖቻቸው በሥራ ጠንክረው ከጉስቁል ኑሮ እንዲላቀቁ በአስተምህሮም ሆነ በውግዘት እየገሰጹ ቀኖቻቸው በከንቱ እንዳይባክኑና ፍሬያማ እንዲሆን ከማጀገን ይልቅ በባህልና በበዓለት አፍቃሬነት እንዲልፈሰፈሱ ማድረጋቸው የዘመናት ውርሳችን ሆኖ ዛሬም ድረስ እንደገዛን አለ። ፈጣሪ ይህንን ማመካኛችንን ሲመለከት ምን እንደሚሰማው ከቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት መልሱን ባናገኘውም በሰውኛ ስሜታችን ግን፤ “ስሜንና ክብሬን መመከቻ አድርጋችሁ በስንፍና እየኖራችሁ፤ ስትራቡና ስትጠሙ ወደ እኔ እየጮኻችሁ ታደነቁሩኛላችሁ” እያለ የሚገስጸን ይመስላል። ድርቅ መታወቂያው የሆነ ሕዝብና ርሃብ መዘባበቻ ያደረገው አገር እንዴት እንቅልፍ አግኝቶ ሊያንኮራፋ ይችላል? ቢመርም እውነታውን እንጎንጨው። “እሺ ይበልጣል ከሺህ” ሺህ ቦታ ጠፍንጎ እንደተበተበንም ልብ እንበል።
በመንግሥታዊ ተቋማትና በአገልግሎት ሰጭዎች ዘንድ የደለቡት አውሬ ጉበኞች ጉዳይም ከአሳሳቢነት አልፎ “እንደ ለማዳ እንስሳት” እየታዩና እየተጎበኙ መታለፋቸው ሌላው የኢትዮጵያ የወቅቱ ፈተና ነው። ዱሮ ጉቦና ሌብነት ይፈጸም የነበረው በድብቅና በአቀባባዮች በኩል ስቅቅ ታክሎበት ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን ጉቦና ጉበኝነት “የክብር አክሊል ተደፍቶላቸው” ካስገበሩን ሰነባብቷል። የጉበኞች ኔትወርክ እንደ ቀዳሚ ዘመናቱ በስውር የተዘረጋ ሳይሆን “እወቁን እየተባለና” በፋንፋር እየተደለቀለ ጭምር ነው።
ይህንን ለማረጋገጥ ሰሞኑን በየክፍለ ከተማው ሄዶ ብቻ እውነቱን ማጣራት ይቻላል። “በዘጠና ቀናት ሥሩን ነቅዬ ምላሽ እሰጣለሁ” ያለን ገዢያችን ብልጽግና ፓርቲ፤ የጉቦን ነቀርሳ በዘጠና ቀናት ነቅሎ እንኳን ሊፈውሰን ቀርቶ ደዌው ክፉኛ በርትቶ እንደ ክረምት ችግኝ በመራባት ስለበከለን ሕዝቡ ጫናውን መቋቋም ተስኖት ምርር እያለ በማንባት ላይ ነው። “ጉዳይህ እንዲፈጸምልህ ከፈለግህ ይህንን ያህል ገንዘብ አምጣ?” እየተባለ ሲወሰንበት “እሺ ይበልጣል ከሺህ!” እያለ ከእንባው ጋር ደሙን ቀላቅሎ እየሰጠ መሆኑን ገዢዎቻችን አላወቁ ከሆነ ይወቁት። መዋቅራቸው ውሸት እያመረተ የሃሰት ሪፖርት ይመግባቸው ከሆነም እውነቱን ከእኛ ከግፉዓን ጠይቀው ይረዱ። አልሰማ ካሉም “ምከረው ምከረው፤ እምቢ ያለ እንደሆነ መከራ ይምከረው!” ብለን በብሂላችን “እናሟርትባቸዋለን። ”
በሰሞኑ አሳሳቢ ሃይማኖት ለበስ የጥላቻ ክፉ ድርጊቶች መከሰትም ጥቂት አጥፊዎችን ብቻም ሳይሆን የየሃይማኖቱን እልፍ አእላፍ ምዕመናንንና የሃይማኖቶቹን መሪ አገልጋዮች መሞገቱም ተገቢ ይመስለናል። በቄያቸውና በቤታቸው ውስጥ ሴራው ሲውጠነጠን እውነት አልሰሙም? አላወቁም? ምን እርምጃስ ወስደው ነበር? የልጆቻቸውን ትንፋሽ በቅርበት የሚውቁት እናቶች፣ ተከባሪ አባቶች፣ አንጋፋ ወንድሞችና እህቶች፣ ታናናሽ ተደማጭ የቤት ልጆች አጥፊ ልጆቻቸው ሴራ እያውጠነጠኑ ሲመክሩና ሲመካከሩ አላወቁም ነበር ብሎ መደምደም ይቻላል? አይመስለንም።
ከግዙፎቹም ሆነ ከመለስተኞቹ ታሪክና ወቅት ወለድ ጉዳዮቻችን መካከል እንደወረዱ የጠቃቀስናቸው አገራዊ አበሳዎቻችን እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ብዙ ናቸው – እጅግ ብዙ! ከብዛታቸው የተነሳ ፈጣሪም፣ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ የየግላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጸሎቱን ለፈጣሪ፣ በሕግ አምላክን ለመንግሥት፣ አደራውን ለሕዝብ ሰጥተን ነገን በተስፋ እንጠባበቃለን። “እሺ” መዘዙ ሺህ” ያልነውም ስለዚሁ ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014