ሄፒታይተስ ቢ ጉበትን የሚያጠቃ የቫይረስ ኢንፌክሽን ሲሆን አጣዳፊና ሥር የሰደደ በሽታን ሊያመጣ ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት እኤአ በ2019 በወጣው መረጃ መሰረት 296 ሚሊዮን ሰዎች ሥር በሰደደ የሄፐታይተስ ቢ በሽታ ሲያዙ በየዓመቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን አዳዲስ ኢንፌክሽኖች እንደነበሩ ገልጿል። እኤአ እስከ 2019 ሄፒታይተስ ቢ 820ሺህ ለሚገመቱ ሰዎች ሞት መንስኤ እንደነበር፤ ይህም በአብዛኛው ከ‹‹ሲርሆሲስ›› እና ከ‹‹ሄፓቶሴሉላር ካርስኖማ›› በተሰኘ የጉበት ካንሰር ምክንያት እንደሆነም ጠቁሟል።
የሄፒታይተስ “ቢ” እና “ሲ” ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ብዙ ሰዎች መጀመሪያ ሲያዙ ምንም አይነት የሄፒታይተስ ቢ እና ሲ ምልክት አይታይባቸውም። ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ሰዎች የቆዳ እና የዓይን ቢጫ ቀለም (ጆንዲስ)፣ ጥቁር ሽንት፣ ከፍተኛ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ እና የሆድ ቁርጠትን ጨምሮ ለብዙ ሳምንታት የሚቆዩ አጣዳፊ የሕመም ምልክቶች ይታዩባቸዋል።
መተላለፊያ መንገዶች
የሄፒታይተስ ቢ እና ሲ ዋነኛ ምልክቶች ከእናት ወደ ልጅ በወሊድ እና በእርግዝና ጊዜ፣ በቫይረሱ በተበከለ ደም ወይም ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ጋር በመገናኘት፣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ መርፌ ወይም ለሌሎች ሹል መሳሪያዎች በመጋለጥ ናቸው።
ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ እንዳለ እንዴት ሊታወቅ ይችላል ?
ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ በላብራቶሪ የደም ምርመራ በቀላሉ ሊታወቅ ይችላል።
ህክምናውስ?
እስካሁን ድረስ ለከባድ ወይም አጣዳፊ ሄፒታይተስ ቢ የተለየ ህክምና እንደሌለ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች አስታውቀዋል። ስለዚህ እንክብካቤው ምቾትን እና በቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ ሚዛንን ለመጠበቅ የታለመ ሲሆን ይህም በማስታወክ እና በተቅማጥ የጠፉ ፈሳሾች እና ንጥረ ነገሮችን ለመተካት ያግዛል። አላስፈላጊ መድሃኒቶችን ታካሚው ከመውሰድ መታቀብ አለበት። ይህም እንደ ፓራሲታሞል እና ማስታወክን የሚከላከሉ መድሃኒቶች ናቸው።
ሥር የሰደደ የሄፒታይተስ “ቢ” ኢንፌክሽን በመድሃኒት ሊታከም ይችላል?
ሥር የሰደደ የሄፒታይተስ ቢ ኢንፌክሽን በፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ሊታከም ይችላል። ሕክምናው የሲርሆሲስን እድገት ሊያዘገይ ይችላል፣ የጉበት ካንሰር የመፈጠር እድልን ይቀንሳል፣ በሕይወት የመኖር ጊዜንም ይጨምራል ተብሎ ይታመናል።
ለ”ሄፒታይተስ ቢ” ክትባት ቢኖርም ለ”ሄፒታይተስ ሲ” ግን ምንም አይነት ክትባት የለም። የፀረ-ቫይረስ መድሃኒቶች ከ95 ከመቶ በላይ የሄፒታይተስ ሲ ኢንፌክሽንን ይፈውሳሉ፣ በዚህም በሲሮሲስ እና በጉበት ካንሰር የመሞት እድልን ይቀንሳል። ይህ ሂደት በሚወሳሰብበት ጊዜ የጉበት በሽታ (ሲርሆሲስ)፤ የጉበት ካንሰርን ጨምሮ ሞትን ሊያስከትል ይችላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014