በኢጋድ የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ-መንግስታት ከአውሮፓ ህብረት የኮቪድ-19 ምላሽ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ የህክምና ግብአቶችን ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመገኘት አበርክቷል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ኮቪድን ለመከላከል የሚያስችል የሶስትዬሽ ስምምነት ተፈራርሟል።
ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተበረከተው ድጋፍ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚሰጠውን ምላሽ የሚደግፉ ሶስት አምቡላንሶች፣ አንድ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ እና ለህክምና ግብአት የሚሆኑ የእጅ ጓንቶች መሆናቸውም ታውቋል። በአውሮፓ ህብረት-ኢጋድ የኮቪድ-19 ምላሽ ፕሮግራም አማካኝነት የተገኙት ደረጃቸውን የጠበቁ ሁለት አምቡላንሶች እና አንድ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠው አምቡላንስ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭ የሆኑ የድንበር ተሻጋሪ ማህበረሰቦችን ለመደገፍ እንደሚረዱም ተጠቁሟል።
በድጋፍ የተበረከቱት አምቡላንሶቹ የጤና እንክብካቤ ምላሽን ለማሻሻል በኢትዮጵያ ድንበር ዘለል አካባቢ ወደሚገኙት ጋላፊ፣ መተማ እና ሞያሌ እንደሚላኩም ተነግሯል። ድጋፉ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ እያደረሰ ያለውን የጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ለመቅረፍ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑም ተገልጿል።
ከዚሁ የህክምና ግብአቶች ድጋፍ ጎን ለጎን በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር፣ በጂቡቲ ጤና ሚኒስቴርና በኢጋድ መካከል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶች ፊርማ ስነስርአት ተካሂዷል። የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የኮቪድ-19 የክትባት ተደራሽነትን ማሻሻል ላይ ያተኮረ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ስምምነቱ በጅቡቲ-አዲስ አበባ የንግድ ኮሪደር ላይ የሚመላለሱ 10ሺ 500 የንግድ መኪና አሽከርካሪዎችን እና ከእነዚህ ጋር ግንኙነት የሚኖራቸውን ሰዎች ለመከተብ የሚያስችል እንቅስቃሴን እንደሚያመቻችም ተገልጿል።
ከዚህ የሶስትዬሽ ስምምነት በተጨማሪ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እና ኢጋድ በድንበር ተሻጋሪ አካባቢዎች ያለውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት የሚከታተል የማህበረሰብ ተሳትፎ (RCCE) ጥናት ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ይህ የጥናት ፕሮጀክት በኢጋድ የምርምር ክፍል እንደሚደገፍም ታውቋል።
የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደሚናገሩት በጤና መስከ የተደረጉ ስምምነቶች በኢጋድ አባል አገራት ውስጥ የሚገኙ ህዝቦችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከልና የበሽታውን ስርጭት በመግታት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው። ኢጋድ ለጤና ሚኒስቴር በድጋፍ መልክ ያቀረበው የኮቪድ-19 መከላከያ ግብአትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
በቀጣይም፣ ኢጋድ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚረዱ ወሳኝ የህክምና ግብአቶችን ከአውሮፓ ህብረት የኮቪድ-19 ምላሽ ፕሮግራም ማስተባበር ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል። አገራቱ ከኮቪድ-19 ለማገገም የሚያደርጉትን ጥረትም ይደግፋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤና፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሮ ቆይቷል። ከዚህ አኳያ ወረርሽኙ ያሳደረውን ተፅእኖ ለመቅረፍና ተፅእኖውንም ለመቀነስ በአገራት መካከል ጠንካራ ትብብርና በጋራ መስራት ወሳኝ መሆኑ ታይቷል።
በኢጋድ በኩል የተደረገው ለኮቪድ-19 መከላከያ የሚውል የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ወቅታዊና የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። የላብራቶሪ ተደራሽነት በኮቪድ-19 ወርሽኝ ወቅት ቁልፍ ችግር የነበረ በመሆኑ ይህ ድጋፍ ይህን ችግር በመቅረፍና ድምበር ተሻግሮ የወርሽኙን ሰርጭት በመዋጋትና ሌሎች በሽታዎችንም በመከላከል ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። በተጨማሪም በዚህ ቀጣና ለሚገኙ ነዋሪዎች የኮቪድ ምርመራና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች ተደራሽነትን ለመጨመር የሚደረገውን ጥረትም ይደግፋል።
በኢትዮጵያና በጅቡቲ ጤና ሚኒስቴርና በኢጋድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በወሳኝ ወቅት የተደረገና በጅቡቲ-አዲስ አበባ የንግድ ኮሪደር ላይ የሚመላለሱ የመኪና አሽከርካሪዎችንና ከእነዚህ አካላት ጋር ግንኙነት የሚኖራቸውን ሰዎች ለመከተብ የሚያስችል ይሆናል።
የአውሮፓ ህብረት-ኢጋድ ኮቪድ-19 ምላሽ ፕሮጀክት ከአውሮፓ ህብረት የሚደረግለት የ60ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ በUNOPS እየተዳደረ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን፣ በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM)፣ በTrade Mark East Africa (TMEA) እና በተባበሩት መንግስታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) አማካኝነት ለጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ አገራት ለተቀናጀ የኮቪድ-19 ምላሽ ትግበራ እንደሚውል ይታወቃል።
መርሃ ግብሩ በምስራቅ አፍሪካ ወሳኝ በሆኑ የድንበር አቋራጭ አካባቢዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን የኢጋድን የማስተባበር አቅም ማሳደግ፣ የጤና እና የውሃ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የጤና እና ንፅህና አጠባበቅ አገልግሎትን ማሳደግ፣ ሥርዓተ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መዋጋት፣ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ድንበሮች ለንግድ አስተማማኝ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑበትም ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም በጀርመን መንግስት የሚደገፈው ዲጂታል የጤና መፍትሄዎች አካል በGIZ ራሱን ችሎ የሚተዳደር እና የሚተገበር ሲሆን በአጠቃላይ መርሃ ግብሩ በሰባት አገራት 45 ጣቢያዎችን በማቋቋም 8ሚሊዮን 196ሺህ 321 የግል የኮሮና መከላከያ መሳሪያዎች እና 208ሺህ 977 የኮቪድ-19 መመርመሪያ መሳሪያዎችን ለኢጋድ አባል አገራት አቅርቧል።
እስካሁን የአውሮፓ ህብረት-ኢጋድ ኮቪድ-19 ምላሽ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ 1ሚሊዮን 074ሺህ 762 የግል የኮሮና መከላከያ መሳሪያዎችን ማበርከቱ የሚታወስ ሲሆን እነዚህ የህክምና መገልገያዎችም ለኮሮና ቫይረስ የሚጋለጡ፣ በድንበር አካባቢ ያሉ ሰራተኞችን፣ ድንበር ተሻጋሪ ማህበረሰቦችን እና ተጋላጭ ህዝቦችን ከኮቪድ-19 ለመከላከል አግዘዋል።
ይህ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ በስፋት ባከናወናቸው ተግባራት 864ሺህ 974 ሰዎችን ተደራሽ በማድረግ 731 ሰዎችን ከኮቪድ-19 መከላከል እና ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለደረሰባቸው ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ያስቻለ ሲሆን፤ 10ሺህ 240 የንጽህና መጠበቂያ ዕቃዎችንም ለተጠቃሚዎች አቅርቧል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014