![](https://press.et/wp-content/uploads/2022/05/9.png)
አዲስ አበባ፡- የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የግጭቶችን ባህሪና ምንነት በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋል ሲሉ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት የአገረ መንግሥት ግንባታ ተመራማሪ አቶ ወንድወሰን ንጉሴ ገለጹ::
አቶ ወንድወሰን ንጉሴ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአገርን ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ የግጭቶችን ባህሪ መለይ ብሎም እንደየባህሪያቸው ዘላቂ መፍትሄን ማበጀት ይጠይቃል።
ግጭት በተለያየ አጋጣሚ ይከሰታል ያሉት አቶ ወንድወሰን፤ ትልቁ ችግር የግጭት አፈታት ሂደቱ ነው:: የግጭት አፈታት ሂደቱንም በኃይል ሳይሆን በመግባባት ላይ የተመሰረተ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞከረው ደም አፋሳሽ በሆነ ጦርነት በመሆኑ ከባድ የሆነ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ ውድመት ያስከትላል ሲሉ ተናግረዋል።
መንግሥት የግጭቶችን ምንነት በመለየት እንደየ ችግሮቹ ባህሪያት ለይቶ የጸጥታ ኃይሉንና በየደረጃው ያሉ አካላትን በማስተባበር እልባት መስጠት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።
ሕዝቡን በማሳተፍ በአጥፊዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ ስለማይወሰድ ሌሎች ግጭት ቀስቃሾች የሚበረታቱበት ሁኔታ እየታየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን፤ ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላም በአጥፊዎች ላይ ግልጽና ተጨባጭ እርምጃ ባለመወሰዱ አጥፊዎች አድማሳቸውን ሲያሰፉ ይስተዋላል ብለዋል።
ግጭት ፈጣሪዎች የሚታረሙበትና የተጎዱ የሚካሱበት አሰራር መኖር መቻል አለበት ያሉት ተመራማሪው፤ በቀጣይ አጥፊዎችን ወደ ሕግ በማቅረብ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ይገባል። በአጠቃላይም የሕግ የበላይነትን ማስከበር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል::
ከዚህ ባለፈ ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ በቂ ሆነ የተግባቦት ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን፤ ችግር በፈጠሩ አካላት ላይ ምን አይነት ርምጃ ተወሰደባቸው፣ የግጭቱ መንስኤና ጠንሳሽስ ማን ነበር በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የተግባቦት ስርዓት መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
አስፈላጊ ሲሆን በተለይም ፖለቲካዊ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸው ቸግሮች ላይም የሚመለከታቸውን የፖለቲካ ምሁራንና ፓርቲዎች በማሳተፍ መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ግጭት እንዲሁ የሚመጣ ሳይሆን ዑደቱን ጠብቆ የሚከሰት በመሆኑ መንግሥት በየደረጃው ያሉ የደህንነትና የፍትህን ተቋማት በማጠናከር ችግሮች ከመከሰታቸው በፊትና ከተከሰቱ በኋላ ደም አፋስሽ ግጭት እንዳይፈጠር መከላከል ይገባል ብለዋል።
እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ፤ ግጭት ሲባል በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በአገራት መካከል የሚደረግ ሊሆን ይችላል። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በዋናነት ነፍጥ ያነሱ አካላት ብሔርን፣ የሥልጠን ፍላጎትን፣ ሃይማኖትን፣ የአደባባይ በዓላትን መሰረት አድርገው በሚቀሰቅሱት ችግር የተፈጠረ ነው።
በመሆኑም መንግሥት የጸጥታ ስጋቶችን በአግባቡ ለሕዝቡ በማስገንዘብ ችግሮች እንዳይስፋፉ ማረቅ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አገር ከዚህ በፊት የነበረው ሰላም በአፈና ውስጥ በነበረ ዝምታ የመጣ ነው ያሉት የአገረ መንግሥት ተመራማሪው፤ ሁሉም ፍላጎቶች በኃይል ተገድበው እንዳይወጡ ተደርገው የነበረ ሰላም እንጂ በዴሞክራሲ የሰፈነ ሰላም እንዳልሆነ ማሳያ ነው ብለዋል::
ይህ አይነቱ ሰላም ደግሞ አንድ ቀን አፈናው ሲላላ የሚላላና ዘላቂነት የሌላው እንደነበር ጠቁመዋል።
መንግሥት አፈናን ሳይሆን ዴሞክራሲዊ ሂደትን መከተል ስለመረጠ ታፍነው የነበሩ ሀሳቦች አደባባይ በመውጣታቸው ግጭቶች እንዲከሰቱ አንዱ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህም የግጭቶቹን መንስኤ የለየ ጥልቅ ውይይት ማድረግ ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ያግዛል ብለዋል።
በአሮሚያ ክልል በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያስከተለው ጥቃት፤ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺና መተከል ያሉ ግጭቶች እንደአብነት አንስተው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩን መንስኤ፣ የየአካባቢውን መፍትሄ መፈለግ፣ ሕዝቡን ያሳተፈ ውይይት ማድረግና ተመሳሳይ እርምጃዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም