በጣሊያኗ የሚላን ከተማ አቅራቢያ 51 ተማሪዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ አንድ አውቶቡስ ትናንት ተጠልፏል።
በጣሊያኗ የሚላን ከተማ አቅራቢያ የሁለት ክፍል ተማሪዎችና የተወሰኑ መምህራኖች የያዘ አውቶብስን የጣሊያን ዜግነት ያለው ትውልደ ሴኔጋላዊ የ47ዓመቱ አሽከርካሪ ተሳፋሪዎቹን ጠልፏል፡፡
ፖሊስ ባደረገው ክትትል የተጠለፈው መኪና ላይ መድረስ የቻለ ሲሆን፤ ጠለፋውን ያካሄደው ትውልደ ሴኔጋላዊ (በዜግነት ጣሊያናዊ) ኦውሰይኑ ሳይ 51 ተማሪዎችን በውስጡ አሳፍሮ ሲጓዝ በነበረው አውቶብስ ላይ እሳት ለኩሶበታል። ነገር ግን ፖሊሶች መኪናው ከመጋየቱ በፊት መስኮቱን በመስበር ተማሪዎቹን በመስኮት በማውጣት የተማሪዎቹን ህይወት ታድገዋል። ተማሪዎቹ የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው የተረፉ ሲሆን፤ 14 ተማሪዎች ግን በተፈጠረው ከፍተኛ ጭስ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እገታውን የፈጸመው አሽከርካሪ ጣሊያን በስደተኞች ላይ ያወጣቸውን ህግ ለመቃወም እንደሆነ ለፖሊስ ተናግሯል።
ከተማሪዎቹ ጋር በአውቶብሱ ተሳፍረው የነበሩት መምህራኖች ተጠርጣሪው ስሙ ኦውሰይኑ ሳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ከመያዙ በፊት “ማንም አይተርፍም፤ የጅምላ ግድያ ከመፈጸም ማንም አያግደኝም” በማለት ይዝት ነበር ብለዋል። የፖሊስ ቃል አቀባዩ ማርኮ ፓልሜሪ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪው “የባህር ላይ ሞት ይቅር” እያለ ይጮህ ነበር። አሁን ላይ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን፤ በሽብር ድርጊት እንዲከሰስ ክሱ የሚከብድበትን የህግ አግባብ የአቃቢ ህግ ኃላፊዎች እየፈለጉ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የሚላን አቃቢ ህግ ኃላፊ ፍራንሲስኮ ግሪኮ በበኩላቸው፤ ትውልደ ሴኔጋላዊው ካሁን በፊትም ጥቃት በማድረስና ጠጥቶ በማሽከርከር ወንጀል ክስ ተከሶ እንደነበር ማስረጃዎች ተገኝተዋል ብለዋል።
ባለፈው ሰኔ በጣሊያን የቀኝ ክንፍ ሊግ ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በስደተኞች ላይ ጠንካራ አቋም እየወሰደ ይገኛል። በሜዲትራኒያን በኩል ጣሊያን ያላትን ወደብ ለጀልባ አገልግሎት ዝግ እንዲሆን እስከማድረስም ታቅዷል። ባሳለፍነው ሳምንት ሃሙስ እለት 50 ስደተኞች በዚሁ የጣሊያን የባህር ዳርቻ በበጎ አድራጊዎች እርዳታ ከተረፉ በኋላ ወደ ወደብ ከተማዋ ላምፔዱሳ ተወስደው ነበር። ነገር ግን የጣሊያን መንግሥት እነዚህን ስደተኞች ወደ ጣሊያን መግባት እንዲችሉ ማን እንደረዳቸው ምርመራ አደርጋለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
ሶሎሞን በየነ