በመዲናችን አዲስ አበባ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት አምራቾችን አቅም የማሳደጊያ የምክክርና ንቅናቄ መድረክ ተካሂዶ ነበር። መድረኩ የከተማችንን አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅም ለማጎልበት ያቀደ ብሎም ያሉባቸውን ችግሮች አዳምጦ ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ እንደነበር የዝግጅት ክፍላችን በቦታው ተገኝቶ ለመታዘብ ችሏል። በእለቱ የነበረውን ሁነትም ከዚህ እንደሚከተለው በመዳሰስ ለእናንተ አንባቢዎቻችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
በእለቱ ማልዶ በቦታው የተገኘው ታዳሚ ውጤታማ የተባሉትን መካካለኛ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝቷል። በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኝ ደረጃውን የጠበቀ፤ ከውጭ የሚገባውን መተካት የሚችል ሶፋ የሚያመርት ኢንዱስትሪን ፣ በመቀጠል በርካታ የሰው ሀይል በውስጡ ይዞ የሚያሰራ አንድ ጋርመንት ተጎብኝቶ ወደ አዳራሽ ነበር የተገባው።
ንቅናቄው ለምን አስፈለገ?
በዋናው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዣንጥራር አባይ፤ በከተማዋ ከተያዘው እቅድ አንዱ “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ንቅናቄ መሆኑን አንስተው በዚህም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል። በተጨማሪም ንቅናቄው አሁን ካሉት 10 ሺህ 504 አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና ቁጥር ወደ 26 ሺህ 260 ለማሳደግም እንደሚረዳ ነው ያነሱት። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅማቸውን ከ42 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 85 በመቶ እንዲደርስ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንም አመላክተዋል። ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ አንዱ የስትራቴጂክ እቅድ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዣንጥራር ተኪ ምርት አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሰፉ በማድረግ ከነበሩበት 418 ወደ 1 ሺህ 226 ለማሳደግ ታቅዷል። ወደ ውጭ የሚላከው የኢንዱስትሪ ምርት ከነበረበት 133 ወደ 381 በማድረስ፤ የውጭ ምንዛሪ ከነበረበት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የማስገኘት እቅድ መኖሩንም አብራርተዋል።
“ያለ ኢንዱስትሪ ልማት ያደገ አገር የለም” የሚሉት አቶ ዣንጥራር እንደ አገር ለመበልፀግ የተለያዩ ፖሊሲዎችን አሻሽሎ ከኢንዱስትሪያሊስቶች ጋር ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የሚሰሩ እጆችን ከስራ ጋር በማገናኘት ከተለመደው መንፏቀቅ ለመውጣት የተለየ ንቅናቄ ማስፈለጉንም አብራርተዋል። በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት ኢንዱስትሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ከሚጠበቅባቸው አቅም 50 በመቶ ብቻ እያመረቱ እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች የተጠቀሱ ሲሆን በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ በየአመቱ መሻሻል እየተደረገ 85 በመቶ የምርት መጠን ላይ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከሁለት ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች ከቦታ፣ ከመብራት ከብድር እና ሌሎች ችግሮቻቸው እንዲፈታላቸው መደረጉን የተናገሩት አቶ ዣንጥራር ከ3 ሺህ በላይ ኢንዱስትሪዎች አሁንም የመብራት፣ የውሀ፣ የብድር፣ የውጭ ምንዛሬና ሊፈቱላቸው የሚገቡ በርካታ ተግዳሮች እንዳሉባቸው ያስረዳሉ። ቀደም ሲል የተቋቋሙ ለአመታትም ወደ ምንም ዘርፍ ሳይለወጡ ባሉበት ሲሰሩ የቆዩ ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው ከፍ ባለ ደረጃ እንዲለወጡ የሚሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዣንጥራር መፈታት ያለባቸው ችግሮች ተፈተው በአገሪቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት አምራች እንዲሆኑ ብሎም የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኙ ለማድረግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የከንቲባዋ መልእክት
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው “አብዛኛው የአገራችን ዜጎች አምራች እድሜ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ተባብረን ሰርተን በአጭር ጊዜ የብልፅግና ማማ ላይ እንደርሳለን” ብለዋል። የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና የከተሞችን የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ተቀርፀው ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።
የከፍታ ማማ ላይ ወጥተው የምናያቸው አገራት መነሻቸው ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ በሰጡት ትኩረት ነው የሚሉት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ እድገት ያለ ጥረትና ድካም ከቶውንም አይታሰብም፤ ራዕይን ማጥራት፣ ለሥራ ያለንን ፍቅርና ትጋት ማሳደግ፣ ጊዜያችንንና ሀብታችንን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ይገልፃሉ። በከተሞች ለስራ ፈላጊዎች የተለያዩ አማራጮችን ለማመቻቸት የስራ እድል ማጠናከርና የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ድጋፍን ማከናወን ዋና አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም ያነሳሉ። የስራ መዳረሻ አላማው የስራ ክቡርነትን ባህል በማድረግ፤ የማምረትና አገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባሻገር በዓለም ገበያ ውስጥ በብቃት መግባትን መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
“በስራ ለውጥን ለማግኘት የሚተጉትን ለማግኘት፤ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል” የሚል መልእክት ያስተላለፉት ከንቲባዋ፤ ስራን የመናቅ አስተሳሰብን ከውስጥ በማውጣት ለለውጥ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ፈተናዎች
በንቅናቄው ተሳታፊ በነበሩ አምራቾች በመድረኩ የተለያዩ ሀሳቦች ቢነሱም በዋነኛነት የፋይናንስ እጥረት ስራቸውን አስፋፍተው እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸው፤ ለብድሮች መያዣ ተብለው የሚጠየቁት ንብረት ከአቅም በላይ የሆነ የተለያዩ የቢሮክራሲ መስመሮች ስራውን በተቃና መልክ እንዳይሄድ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል። የባልትና ውጤቶችን ለውጭ ገበያ እያቀረብን ገበሬዎች እና ነጋዴዎች ሚዛን እንዲያነሳላቸው የደረቀው በርበሬ ዛላ ላይ ውሀ ያርከፈክፉበታል። ይሄም ሻጋታ ‹‹አፍላ ቶክሲን›› ያጋልጣል። በመሆኑም ስለአፍላ ቶክሲን በቂ ግንዛቤ ስለማይኖራቸው ይህን ለመከላከል ከቻይና በርበሬ እያስመጣን እስከመጠቀም ደርሰናል ነው ያሉት። ጥራት ያለው ግብአት አቅራቢ ቢመቻችልን የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር። የሀይል አቅርቦት ችግር፤ ሰፊ የማምረቻ ቦታ ማጣት፤ ስልጠናዎችን የሚፈልጉ አምራቾች የክህሎት ስልጠና አለማግኘታቸው፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሌሎችም ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የባለድርሻ አካላት ሚና
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቶ መላኩ አለበል በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ እንደ አገር የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀሩ ተኪ ምርት አምራቾች በብዛት ስለሚያስፈልጉ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። አምራቾች ከአስፈፃሚ አካላት ጋር በቅርበት መገናኘታቸው ችግሩን በጥልቀት ታይቶ እንዲፈታ ለማድረግ ትልቅ መንገድ እንደሚከፍት ተናግረው፤ እያንዳንዱ ችግሮ በሙያተኞች እየተለዩ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
“አምራች ኢንዱስትሪዎች በሀይል አቅርቦት ምክንያት ስራቸው እንዳይስተጓጎል እየሰራን ነው” ያሉት በእለቱ የተገኙት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ በበኩላቸው የሀይል አቅርቦት ጥያቄ ለሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ የሚሰጥበት አግባብ መኖሩን አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም ለነበሩት ክፍተቶች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሰብስቴሽኖች አቅም መሙላት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎቹ የሚያቀርቡት የኃይል ፍላጎትና አጠቃቀም አለመመጣጠን፣ የተሰጣቸውን የኃይል መጠን በአግባቡ አለመጠቀም እና የነባር አምራች ኢንዱስትሪዎች አመሰራረት በኢንዱስትሪ ዞን የተጠቃለለ አለመሆን በኤሌክትሪክ መሰረት ልማት ግንባታ እና ማሻሻያ ላይ ተግዳሮት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ከልማት ባንክ የመጡት ተወካይ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፤ ለማሽን ማስገቢያ ተብሎ የተዘጋጁ ብድሮች ከግንዛቤ እጥረት ይሁን ከሌላ ብዙም ተጠቃሚ እንደሌላቸው ጠቅሰዋል። አምራቾች በርቀት ይህ ገጥሞናል ከማለት ባሻገር በቅርበት በመገናኘት የገንዘብ ማግኛ አመራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እንደ አገር የተከሰተ ሲሆን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊው ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በማይክሮ ፋይናንስ በኩል የሚጠየቁ መያዣዎች አስፈላጊነት የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች የቢሮክራሲ ጉዳዮችን የማጥራት ስራ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመፍትሄ ሃሳቦች
ማጠቃለያውን የሰጡት አቶ ጃንጥራር የአቅርቦት ችግር ኖሮብን ከቻይና በርበሬ እያስመጣን ነው ለተባለው ሀሳብ በቀጥታ ከገበሬዎች ህብረት ስራ ጋር በመገናኘት ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ የሚደረግ የአሰራር ስርዓት የሚዘረጋ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይ በአገር ውስጥ ግብአት መሸፈን የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ መባከናቸው አግባብነት እንደሌለው አብራርተዋል። የቦታ ጥያቄ የሁሉም ኢንዱስትሪዎች ጥያቄ መሆኑን በማስረዳትም አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ቦታን እንደ ሀብት መያዝ የመፈለግ አዝማሚያ እንዳላቸው ገልፀዋል። ይህ አካሄድ ግን ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል። ቦታን እንደማምረቻ፤ እንደሀብት ማግኛ አድርጎ ማሰብ ውጤታማነት ላይ እንዲያተኩሩ የሚረዳቸው መሆኑን ጠቅሰው ከተማዋ ካለባት የቦታ እጥረት አንፃር በአንድ አካባቢ በሚገነቡ ማምረቻዎች ይሄንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
“የተነሱ ችግሮች በሙሉ ባለቤት ያላቸው በመሆናቸው በቀላሉ ተፈተው ወደ ምርታማነት እንደምንሸጋገር ተስፋ አለኝ” ያሉት አቶ ጃንጥራር፤ ስልጠናዎች የአቅም ማጎልበቻ መድረኮች በየጊዜው እየተዘጋጁ አምራቾችን ወደ ውጤት የማምጣት ስራ ትኩረት የሚያገኝ ትልቅ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ። ኢንዱስትሪዎች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ፤ ብሎም ወደ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ ኣካል ስራውን አውቆ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል። አምራቾችም እንቅፋትን ሳይፈሩ ወደ ፊት የሚያሻግራቸውን መንገድ በሙሉ መሞከር እንደሚገባቸው አብራርተዋል።
እንደ መውጫ
በመርሀ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይ ለኢንዱስትሪዎች የምስጋናና የእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርአት ተካሂዷል። በእለቱም ለሁለት ጥቃቅንና ለሶሰት አነስተኛ ኢነተርፕራይዞች፤ ለስድስት መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፤ ለአምስት ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ዋንጫ በእለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቷል።
አገር እንድታድግ፤ ያለአግባብ የሚወጣ የውጭ ምንዛሪ በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በሚመረት ተኪ ምርት መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል። ብሎም ወደ ውጭ አገር በመላክ የውጭ ምንዛሪ አቅማችንን ከፍ ለማድረግ አምራቾች ሊበረታቱ ይገባል። ዓለም በተለያየ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በምትናጥበት የውስጥ አቅምን በአገር ልጆች እውቀት ከመገንባት የሚበልጥም አማራጭ የለምና ይህ ተግባር ተጠናከሮ መቀጠል ይኖርበታል። በቀጣይም በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን የሚሰበስቡ ኢንዱስትሪዎች በማበራከት የኢትዮጵያን እድገት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማፅናት ይጠበቅብናል በሚለው የመርሀ ግብሩን ማጠቃላያ ሀሳብ አበቃን።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27 /2014