ኢትዮጵያ ካላት በርካታ መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህሎች መካከል የአገር ባህል አልባሳቶቿ አንዱ ነው። በተለይም አሁን አሁን በተለምዶ የሀበሻ ልብስ ተብሎ የሚታወቀውና በብዛት በባህላት ወቅት የሚለበሰው የአገር ባህል አልባሳት መልክና ዲዛይኑን እየቀያየረ በአዘቦትም ፋሽን ሆኖ እየተለበሰ ይገኛል። ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ አገር እንደመሆኗም እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ የየባህሉን አልባሳት በመልበስ አካባቢውን ያስተዋውቃል፡፡
ማህበረሰቡ በአገር ባህል አልባሳት ከመዋብና ከመድመቅ ባለፈ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ፣ የተለያዩ ባህላዊና መንፈሳዊ ባህሎች ባለቤት፤ ስለመሆኗም ለውጭው ዓለም እያስተዋወቀበት ይገኛል። ብዙዎች የሚያጌጡበትና የሚዋቡበት የአገር ባህል አልባሳት በተለይም በሰርግና በባእላት ወቅት በብዛት ተዘውትሮ ይለበስ እንጂ በዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት ከሰርግና ከባዕላት ወቅት ባለፈም መለበስ እንዲችል በተለያዩ ዲዛይኖች እያመረቱት ይገኛሉ።
አሁን አሁን ታዲያ ሸማኔው የተጠበበት የጥበብ ሥራ በቀላሉ ማህበረሰቡ ጋር ለመድረስ የዋጋው ሁኔታ እጅጉን ፈታኝ ያደረገው ስለመሆኑ ይነገራል። እርግጥ ነው ከምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ ቀጥሎ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየታየበት ያለው አልባሳት ነው። በተለይም በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አልባሳትና የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየታየባቸው ያሉ ቢሆንም የአገር ባህል አልባሳትም በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል። በዛሬው የንግድና ግብይት ገጻችንም የሽሮ ሜዳ አገር ባህል ገበያው ምን እንደሚመስል በመቃኘት ሸማችና ነጋዴውን በማነጋገር እንደሚከተለው አቅርበናል።
የሸማኔው የእጅ ሥራዎች በስፋት ከሚስተዋሉበትና የጥበብ ባህር ከሚመስለው ሽሮ ሜዳ የአገር ባህል አልባሳት ለመግዛት ወዲህ ወዲያ ሲሉ ያገኘናቸው ሸማች ወቅቱ የፋሲካ በዓልና የሰርግ ጊዜ እንደመሆኑ አልባሳቱ በእጅጉ ይፈለጋል፤ ሆኖም ግን ዋጋው የሚቀመስ አልሆነም በማለት ሀሳባቸውን ያካፈሉን ወይዘሮ አልማዝ በቀለ ናቸው። እንደሳቸው ገለጻ የአገር ባህል አልባሳት በተለይም በባዕላት እና በሰርግ ወቅት በእጅጉ የሚፈለግ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ዋጋው እጅጉን መወደዱን ይገልጻሉ፡፡
የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በዓል የሆነው የፋሲካ በዓልን ተከትሎ የተለያዩ ፕሮግራሞችና ሰርጎች ይከናወናሉ። ለዚህም በአብዛኛው የአገር ባህል አልባሳት ይፈለጋል የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ እርሳቸውም ሰርግ ኖሮባቸው ለመግዛት እንደፈለጉ ጠቁመው፤ ነገር ግን ዋጋው የሚቻል እንዳልሆነ ነው ያጫወቱን። የአገር ባህል በአገር ውስጥ የሚመረት ሆኖ ይህን ያህል መወደዱ ሰዎች በአገራቸው ምርት እንዳይኮሩና እንዳይለብሱ ያደርጋቸዋልም ብለዋል፡፡
ዋጋው እጅጉን ውድ ይሁን እንጂ ሸማኔው የሚሰራቸው የእጅ ሥራ ጥበቦች ግን ተወዳዳሪ የሌላቸውና እጅጉን ውብና ድንቅ ስለመሆናቸው ያነሳሉ ወይዘሮ አልማዝ። በየጊዜው እጅጉን የተዋቡና የሚደነቁ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎች የሚታዩ ስለመሆናቸው በመጥቀስ የሸማኔውን የጥበብ ሥራ አድንቀዋል። ታድያ እንዲህ ያማረና የተዋበውን ጥበብ ማንኛውም ማህበረሰብ ገዝቶ መልበስ ቢፈልግም ዋጋው ግን የማህበረሰቡን የመግዛት አቅም እጅጉን እየተፈታተነው ይገኛል። ወደፊትም ዋጋው በዚሁ ከቀጠለ የአገር ባህል ገዝቶ መልበስ የሚቻል አይሆንም ብለዋል፡፡
ሰዎች በአሁን ወቅት የአገር ባህል አልባሳቱን የመግዛት አቅም የሌላቸው በመሆኑ ከቻይና አገር በገፍ ወደሚገባው የሽፎን አልባሳት እየሄደ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በተለይም ቻይናውያን የኢትዮጵያን የአገር ባህል አስመስለው በሽፎን ጨርቅ ላይ ጥበቡን አትመው የሚያመርቱትን ልብስ በብዛት ይጠቀማሉ። ይህ ልብስም በአሁን ወቅት በብዛት እየተለመደ የመጣ በመሆኑ የአገር ባህል አልባሳቱን እየተካ እንዳይሄድ ያላቸውን ስጋት ጠቁመዋል። ይህም የሽመና ባለሙያውን እንዲሁም ነጋዴውን ስራ እንዳያጣ ያሰጋል ሲሉም ይጠቅሳሉ።
የአገር ባህል ልብስ ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን በማስታወስ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ መጠን የጨመረ መሆኑን ወይዘሮ አልማዝ አንስተው እርሳቸው አንድ የአገር ባህል ቀሚስ ዘጠኝ ሺ ብር እንደገዙ ተናግረዋል። ከሴት ልጃቸው ጋር 18 ሺ ብር አውጥተው ሁለት የአገር ባህል ቀሚስ የገዙት ወይዘሮዋ፤ ከሌሎች የገበያ ቦታዎች (ከቦሌና አራት ኪሎ የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቆች) ደግሞ ሽሮ ሜዳ የተሻለ እንደሆነም ጠቁመዋል። በሌሎች አካባቢዎች ብዙም ውበት ለሌላቸው አልባሳት እንኳን እስከ 10 ሺ ብር ይጠየቃል። በሽሮ ሜዳ ገበያ የሚታየው ዋጋ ከሌሎች አካባቢዎች በመጠኑ የተሻለ ከመሆኑም ባለፈ ጥራት ያላቸውና ውብ የሆኑ የጥበብ ሥራዎች ይታያሉ።
ትንሹና በቡና ማፍላት ፕሮግራም ላይ የሚለበሰው ቀለል ያለው የአገር ባህል አልባሳት በሽሮ ሜዳ ገበያ እስከ ሶስት ሺ ብር የሚሸጥ እንደሆነና እንደየደረጃቸው ስምንት ሺ አስር ሺና ከዛም በላይ በሆነ ዋጋ የሚሸጥ እንደሆነም አጫውተውናል። እኛም ተዘዋውረን እንደተመለከትነው እጅጉን ያማረና ባለሙያዎች የተጠበቡበት አይን የሚይዙ የአገር ባህል አልባሳት መኖራቸውን እና ከፍተኛ ዋጋ የሚጠራባቸው መሆናቸውን ታዝበናል።
ሌላኛዋ ሸማች ወጣት ሜላት ተሾመ ዘንድሮ የአገር ባህል አልባሳት መወደዱን ገልጻልኛለች። የዋጋው መወደድ ሰዎች ባህላዊ አልባሳቱን መጠቀም እንዳይችሉ እያደረጋቸው ነው ትላለች። በአሁን ወቅት ለበዓላት፣ ለሰርግ፣ ለግብዣና ለሌሎችም ዝግጅቶች የአገር ባህል አልባሳትን መልበስ በስፋት ይወደዳል። ነገር ግን ዋጋው በዚህ ከቀጠለ አልባሳቱን የሚጠቀም አይኖርም በማለት ሀሳቧን ገልጻለች።
የአገር ባህል አልባሳቱ በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ ለመምጣቱ ነጋዴው የግብዓት መወደድን በምክንያትነት ቢያነሳም አሁን እየታየ ባለው ዋጋ መጠን ልክ የግብዓት እጥረትና ውድነት አጋጥሟል ማለት የማይቻል ነው። ያም ቢሆን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ከሚያመርተው ሸማኔ ጋር ሲወዳደር ነጋዴው የሚያገኘው ጥቅም የሚበልጥ እንደሆነና ሸማኔው የልፋቱን ያህል እንደማያገኝ አስተያየት ሰጪዋ ትናገራለች፡፡
የግብዓት እጥረትም ሆነ የዋጋ መናር የሚገጥመው ሸማኔ ለአገር ባህል አልባሳቱ ትልቅ ዋጋ ከፍሎና ችሎታና ጥበቡን ተጠቅሞ ያመርታል። ከሸማኔው ገዝቶ በተከራየው ሱቅ የሚሸጠው ነጋዴ ግን የሸማኔውን ያህል ሳይለፋና ሳይደክም ትልቅ ዋጋ በመጠየቅ የአገር ባህል አልባሳት ዋጋን ያስወድዳል፤ ይህም ማለት አንድ ሸማኔ ለጥበብ ሥራው ካወጣው ወጪ፣ ጉልበትና የወሰደበት ጊዜ ተደምሮ ያለው ወጪና ነጋዴው ምንም እሴት ሳይጨምር ከሸማኔው ተቀብሎ በሚሸጠው ልብስ ላይ የሚያገኘው ትርፍ ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
ለአገር ባህል አልባሳቱም ሆነ ለሌሎች ምርቶች ዋጋ መናር ነጋዴው አንደኛ ምክንያት እንደሆነ በማንሳትም ነጋዴው ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በተለይም በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ግብዓቶችን በማይጠይቁ ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማስታረቅ የሚመለከተው አካል ቢመለከተው መልካም ነው በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
የአገር ባህል አልባሳት በአይነት በአይነቱ ተሰድሮ የሸማቹን አይንና ቀልብ ከሚስበው ሱቆች መካካል በአንደኛው ሱቅ ያገኘናት የአገር ባህል አልባሳት ነጋዴ ወይዘሮ ማህሌት በቀለ ትባላለች። በዘርፉ ከተሰማራች ቆየት ያለች መሆኑን ገልጻ እርሷም እንደሌሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገር ባህል አልባሳት ከነጠላ ጀምሮ በከፍተኛ መጠን እየተወደደ የመጣ መሆኑን ትገልጻለች፡፡
አጠቃላይ የገበያው እንቅስቃሴ እንዴት ነው ፍላጎቱና የዋጋው ነገርስ የሸማቹን አቅም ያገናዘበ ነው ወይ ስንል ላነሳንላት ጥያቄ ስትመልስ፤ ገበያው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የተሟሟቀ እንደሆነና በየጊዜው የአገር ባህል አልባሳት በእጅጉ እየተፈለገ መምጣቱን አንስታለች። ይሁንና አሁን ያለንበት ወቅትና የአገር ባህል አልባሳቱ ዋጋ ሊገናኝ አልቻለም። አሁን ላይ አልባሳቱ በጣም እየተወደደ የመጣ በመሆኑ ሰዎች አልባሳቱን ከመግዛት ይልቅ ወደ መከራየት እያዘነበሉ እንደሆነ ትናገራለች፡፡
በርካታ ተጠቃሚ ያለው የአገር ባህል አልባሳት በተለይም በአሁን ወቅት ፍላጎቱ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን ዋጋውም በዛው ልክ እየጨመረ በመሆኑ ሰዎች ለሚፈልጉት ጊዜ ብቻ በኪራይ እንዲለብሱ ተገደዋል። ለዋጋው መወደድ ዋናው ምክንያትም የግብዓት መወደድ መሆኑን ያነሳችው ማህሌት፤ በአሁን ወቅት ከመደበኛ ክር አንስቶ ማንኛውም የሽመና ግብዓት ጨምሯል። ግብዓቶቹ በመወደዳቸው ምክንያትም የአገር ባህል አልባሳቱ መወደዱን ለተጠቃሚ ለማስረዳት አስቸጋሪ እንደሆነባትም ትናገራለች፡፡
እጅግ የሚያማምሩና የተዋቡ የሸማኔው የጥበብ ሥራዎች የሆኑ አልባሳት በየጊዜው የሚሰሩ እንደሆነ ያነሳችው ወይዘሮ ማህሌት፤ ዋጋው ግን የሸማቹን የመግዛት አቅም የሚፈታተንና በእጅጉ የሚያስደነግጥ እንደሆነ አልሸሸገችም። ታድያ ሰዎች የመግዛት አቅማቸውን ያማከለ እንዲሆን በግብዓቱ ላይ የሚታየው የዋጋ ንረቱ መረጋጋት አለበት። ነጋዴውም ቢሆን ምክንያታዊ የሆነ ዋጋው ሲኖር ነው በብዛት ሸጦ ማትረፍና ተጠቃሚ መሆን የሚችለው ካልሆነ ግን ሸማቹ መግዛት አይችልም፤ ሸማቹ መግዛት ካልቻለ ደግሞ ነጋዴው ከሸማኔ ገዝቶ መሸጥ ካልቻለ ትርፉ ኪሳራ እንደሚሆን ታስረዳለች፡፡
በበዓላት ወቅት እና በሰርግ ጊዜ በብዛት የሚፈለገው የአገር ባህል አልባሳት በአሁን ወቅትም በስፋት የሚፈለግ ቢሆንም ካለፉት ሁለትና ሶስት ወራት ወዲህ እንኳን የአልባሳቱ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። ያለፉት ሁለት በዓላት ገናና ጥምቀት በከፍተኛ መጠን የአገር ባህል አልባሳት የተሸጠበት ዋጋውም ጥሩ የሚባል እንደነበር በማስታወስ በአሁን ወቅት ግን ዋጋው በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ትናገራለች። ለዚህም ምክንያቱ በዋናነት መነን የተባለው ምርት መወደዱ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ የጥለት መወደድ መሆኑን ትገልጻለች።፡
ለአገር ባህል አልባሳት በዋናነት አስፈላጊ የሆነው ጥሬ ዕቃ መነን እንደመሆኑ በአሁን ወቅት ደግሞ ሸማኔው የመነን እጥረት አጋጥሞታል ። በዚህ ምክንያት የባህል አልባሳት ተወዷል። 20 እና 30 ሺ ብር የሚሸጥ የአገር ባህል አልባሳት እንዳለ ሁሉ ትንሹ ዋጋ የሚባለው ስምንት እና አስር ሺ ብር እንደሆነ በመግለጽ፤ በተለይም ፋሽን ተብሎ የሚመጡ የተለዩ ጥለቶች እስከ 50 ሺ ብር ድረስ እንደሚሸጡም ታስረዳለች፡፡
ሸማኔው የተጠበበትን የአገር ባህል በመግዛት ለገበያ የምታቀርበው ወይዘሮ ማህሌት ደንበኞቿም ይዘውት የሚመጡት ዲዛይን ካለም በሸማኔው አሰርታ እንደምትሸጥ ትገልፃለች። በብዛት ግን ሸማኔው በራሱ ዲዛይን ሰርቶ የሚያቀርብ እንደሆነና በወቅቱ የገበያ ዋጋ ገዝተው አትርፈው የሚሸጡ መሆኑንም ታስረዳለች። ሸማኔው ከሚያመጣው በተጨማሪም አብዛኛው ደንበኛ በፎቶግራፍ የተለያዩ ዲዛይኖችን ይዘው ይመጣሉ። ይሄንኑ ሸማኔውም ሰርቶ እስኪያመጣ ሰፊ ጊዜ የሚወስድበት በመሆኑ በቀጠሮ ርዝማኔ በብዛት ደንበኞች የሚሸሹበት አጋጣሚ መኖሩንም አንስታሳለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሸማኔው በራሱ ዲዛይን ከሚሰራው ጥለት በላይ በፎቶግራፍ በትዕዛዝ እንዲሰራ በሚሰጠው ሥራ ላይ የሚሰጠው ዋጋ በእጅጉ ከፍ ያለ በመሆኑ ለዋጋው መወደድ አንድ ምክንያት ነው። ከዋጋው መወደድ ባለፈም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በትዕዛዝ የሚሰሩ አልባሳት ላይ ዋጋው ይበልጥ ይወደዳል። ለአብነትም መደበኛ የሆነ ነጠላ የዛሬ ዓመት ከ300 እስከ 400 ሲሸጥ የነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት እስከ ሰባት እና ስምንት መቶ ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን አስረድታለች።
ዘንድሮ 50 ሺ ብር ድረስ የሚሸጡ የአገር ባህል አልባሳት ማለትም ቀሚስ የዛሬ ዓመት 30 እና 35 ሺ ብር ድረስ ሲሸጡ የነበሩ ናቸው።፤ 10 እና 15 ሺ ሲሸጡ የነበሩት ደግሞ 20 እና 30 ሺ ብር እየተሸጠ ነው። በተለይም ባለፈው በጥምቀትና በገና በዓላት የነበረው ገበያ ጥሩ የነበረ መሆኑን በማንሳት በአሁን ወቅት ከፋሲካ ጾም ጀምሮ ያለው ዋጋ ግን በፍጹም የማይሞከር ነው ትላለች። ለዚህም ዋናው ምክንያት ከ37 እስከ 40 ብር ሲሸጥ የነበረው የአንድ ሜትር መነን በሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ዋጋው በእጥፍ ጨምሮ በአሁን ወቅት እስከ 80 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ይህ ለአገር ባህል አልባሳቱ መወደድ ዋናው ምክንያት እንደሆነ በማንሳት ሀሳቧን ቋጭታለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014