
አዲስ አበባ፡ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት መሻሻል እንዳለበት ተጠቆመ፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በጤና ሚኒስቴር እና በዓለም ጤና ድርጅት ትብብር የተሰራ ጥናት ይፋ በሆነበት ወቅት ነው ይሄ የተገለጸው፡፡
ጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ሥርዓት ላይ ያሉ ጠንካራ ጎኖችንና መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች በመለየት እና በቀጣይ በትኩረት መሠራት ያለባቸውን ነገሮችን ለመጠቆም እንደሚረዳም ተገልጿል፡፡
የጥናቱ ዓላማ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አገልግሎት በጤና ጣቢያ ፣በጤና ኬላ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ እና በከፊል በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የሚሰጡ ማኅበረሰብን ማዕከል ያደረጉ አገልግሎቶች በፋይናንስ በኩል ያላቸው ድጋፍ ምን እንደሚመስል ፣ በአመራሩ በኩል ያለው ትኩረት ምን ያህል እንደሆነ ፣አፈጻጸሙ ምን እንደሚመስል እንዲሁም የፍትሐዊነትን ጥያቄ በምን ያህል መልኩ እየተመለሰ ነው ለሚሉ ሀሳቦች ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡
ጥናቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ክልሎች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት እና በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎችን የጋራ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ታውቋል፡፡
ጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ሥርዓት ላይ በፋይናንስ፣ በፍትሐዊነት እንዲሁም ከጥራት ጋር ተያይዞ ችግሮች መኖራቸውን አመላክቷል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ሥርዓት በፋይናንስ በኩል በሚፈለገው ደረጃ አጋሮች እገዛ እያደረጉ እንዳልሆነ፣ በፍትሐዊነት ረገድም አርብቶ አደር እና በመልክዓ ምድር ምቹ ያልሆኑ ቦታዎች ላይ ደከም ያለ መሆኑን ያሳየ ሲሆን በጥራት በኩል የዓለም የጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት አንጻር የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ከግማሽ ያልዘለለ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ጥናቱ ያመላከታቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በቀጣይ የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ፣ከክልሎች እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመወያየት የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ሥርዓትን ለማሳደግ አቅዶ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ሥርዓትን ለማሻሻል የአስራ አምስት ዓመት ስትራቴጂ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፤ በየአምስት ዓመቱ ከጠቅላላ ዕቅድ እና ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር በማዛመድ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
አመራሩ ትኩረቱን በሆስፒታሎች እና በከፍተኛ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ብቻ ሳይሆን 80 በመቶ የሚሆኑ በሸታዎችን አስቀድሞ መከላከል ስለሚቻል የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ስርዓትን ማሻሻል ላይም ትኩረት እንዲያደርግ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች እገዛቸዉን ማሻሻል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም