
አዲስ አበባ፡- በረመዳን ወቅት የታዩ የአንድነት፣ የመረዳዳት መልካም ተግባራትን እና ባህሎች በቀሪ ዕድሜ ሙሉ ሊቀጥሉ የሚገባቸው እንጂ የአንድ ቀን ተግባራት ሊሆኑ እንደማይገባ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች በረመዳን መልካም ነገሮችን የምንለማመድበት እና በሕይወታችን ቋሚ አድርገን የምንቀጥልበት ወር ነው ብለዋል።
ሼህ መከተ ሙሄ ያለፈውን የረመዳን ወር ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በረመዳን ወር የመተባበር፤ የመተጋገዝ እና አብሮነትን ያሳየበት ወር እንደነበር አስታውሰዋል።
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለድሆች፣ ለምስኪኖች እና አቅሞች ሲያጋራ ቆይቷል ያሉት ሼህ መከተ፤ መጋራትና መስጠት ዕውነተኛ ደስታ ስለሚሰጥ ሙስሊሙ ማኅበረሰብም ይህን ሲያደርግ በመቆየቱ ረመዳን ወር በዕውነተኛ ደስታ አልፏል ሲሉ ገልፀዋል።
ሆኖም በፆም ወቅት የታዩ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የአንድነት መልካም ባሕርይዎች በቀሪ የሕይወት ዘመን ሁሉ ሊፈፀሙ የሚገባቸው እንጂ የአንድ ወር ብቻ አይደሉም ብለዋል።
አቶ ኢብራሂም ከድር በረመዳን ብዙ መልካምና በጎ ሥራዎች የሚከናወኑበት የፆም ወቅት መሆኑን አመልክተዋል ሙስሊም ማኅበረሰብ ከመጥፎ ተግባራት የሚጠበቅበትና መልካም ነገሮችን ያለምንም ግፊትና አነሳሽነት የሚሠራበት ወር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ወሩ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ አንድነቱን፣ መረዳዳቱንና መተሳሰብን ያሳየበት ወር ነበር፣ የረመዳን ወር ልክ እንደመለማመጃ ከፈጣሪ የተሰጠ ወር ነው። ስለዚህ መረዳዳቱ፣ መተጋገዙ፣ መተዛዘኑና በኅብረት መቆሙ ለአንድ ወር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጊዜያት መከወን ያለበት ነው ብለዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት የተለማመደውንና ሲያደርግ የቆየውን አጠቃላይ ዕድሜውን በዚያ መልኩ እንዲያሳልፍ ይጠበቃል ሲሉም አሳስበዋል።
አቶ መሐመድ ፈረጂ በዘንድሮው ረመዳን ወር በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ የነበረው የመደጋገፍና የመረዳዳት ስሜት የሚደነቅ ነበር ብለዋል።
በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ብዙዎች መጎዳታቸውና በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱ መረዳዳቱን እጅግ ወሳኝ ያደርገው ነበር ያሉት አቶ መሐመድ በረመዳን ወር ውስጥ የኢፍጣር ፕሮግራምች የገጠር ከተሞችን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች መካሄዳቸው ከፍተኛ የአብሮነት የመቀራረብ ስሜት እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
አቶ መሐመድ፤ ያለፈው ረመዳን መረዳዳትና መደጋገፍ በአግባቡ የተተገበረበት ወር ነበር፤ በሃይማኖቱ አስተምህሮት መረዳዳትን፣ መደጋገፍና ይቅር መባባል በየትኛውም ጊዜ የሚደግፍና እንዲከናወን የሚፈለጉ ተግባራት መሆናቸውን አመልክተዋል።
በረመዳን የተሠሩ መልካም ነገሮች ሁሉ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ይፈለጋል። ረመዳን በአንድ ወር ተከናውነው የሚያከትምላቸው መልካም ተግባራትን መተግበሪያ ወር ሳይሆን ከዚሁ ወር በልምምድ መልክ የወሰድናቸውን ሥልጠናዎች በዕድሜያችን ሙሉ የምናስቀጥልበት ብለዋል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም