
አዳማ፡- በተለያዩ መንገዶች ከውጭ ሃገራት የሚገቡ መጤ አረሞች ሳይስፋፉ እርምጃ ስለማይወሰድባቸው ሥርዓተ ምህዳሩን እየጎዱ እንደሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ።
በኢንስቲትዩቱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን አስተባባሪ ዶክተር ሳሙኤል ቱፋ እንደተናገሩት፤ ከውጭ ሃገር የሚገቡ አረሞች ሳይስፋፉ እርምጃ ስለማይወሰድባቸው ሥርዓተ ምሕዳሩን እየጎዱ ነው።
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለፃ፤ በተለያዩ መንገዶች ከውጪ ሃገራት የሚገቡት የአረም ዝርያዎችን ሳይስፋፉ እና አካባቢን ሳይጎዱ መቆጣጠር ቢቻልም እርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት በክልሉ አደገኛ መጤ አረሞች በሰብል እና በግጦሽ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያስከተሉ ይገኛሉ።
የተከሰተውን መጤ አረም በፀረ-ተባይ ኬሚካሎች መከላከል እንደሚቻል የጠቆሙት ዶክተር ሳሙኤል፤ አደገኛ አረሞቹ ግን መሬት ውስጥ ለረጅም ጊዜያት ተደብቀው በመቆየት በድጋሚ የመራባት አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አረሞቹ ብዛት ያለው ዘር የሚያፈሩና ባላቸው በአጭር ጊዜ አካባቢን የመውረር ባሕሪ ምክንያት እነሱ ባሉበት አካባቢዎች ሌሎች እፅዋት የማይበቅሉ በመሆናቸው በግብርናው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ እንደሆነም ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።
ከሌሎች እፅዋቶች ጋር አብሮ የመኖር ባህሪ የሌላቸው አረሞቹ የአካባቢውን የእፅዋት መብቀያ ስፍራዎችን በመውረር፣ የአፈሩንም ባሕሪያት በመቀየርና አካባቢውን ለተክሎች ምቹ እንዳይሆን በማድረግ የውኃ አካላትን እንደሚያደርቁም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።
የአረም አይነቶቹ ከተለያዩ ሃገራት ከዕርዳታ እህል፣ ከውጭ በሚገቡ የማሽነሪ ዕቃዎች ጋር እና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የጠቆሙት ዶክተር ሳሙኤል፤ እነዚህ አረሞች በመንገድ ዳር፣ በማሳ ውስጥ እንደሚበቅሉም ተናግረዋል።
ቅድሚያ ተሰጥቶ አረሞቹ በትክክል እያደረሱ የሚገኙትን የጉዳት መጠን በተለይም በእፅዋት ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ፣ ምን ያህል ሄክታር መሬት በአረሞቹ እንደተወረረ እንዲሁም የአረሞቹን አይነት ብዛት ለማወቅ ደረጃውን የጠበቀ ጥናት መካሄድ እንደሚገባውም ዶክተር ሳሙኤል አሳስበዋል።
ዶክተር ሳሙኤል፤ በሕንድና አሜሪካ በመሳሰሉ የውጭ ሃገራት የትኛውም አይነት አስቸጋሪ አረም በተገኘበት ወቅት በፓርላማዎቻቸው ሁሉ ሳይቀር ምሕረት እንዳይደረግላቸው በማወጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚያስወግዱበት አግባብ እንዳለ ጠቁመው፤ በኢትዮጵያም መሰል አሠራሮች ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም