
አዲስ አበባ፡-የቅባት እህሎችን በአገር ውስጥ በስፋት በማምረት የዘይት ዋጋን ማረጋጋት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው ከሰሞኑ በኮከብ ቃና የዘይት ፋብሪካ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው፤ የቅባት እህሎችን በሃገር ውስጥ በስፋት ማምረት ለዘይት ምርት የዋጋ መረጋጋት የተሻለ አስተዋፅዖ አለው።
ፋብሪካው የዘይት ምርት ለኅብረተሰቡ በስፋት የማቅረብ አቅም ያለው ቢሆንም፤ ባጋጠመው የግብዓት ዕጥረት ምክንያት በአቅሙ ልክ ማምረት እንዳልቻለ ቋሚ ኮሚቴው ከተደረገለት ገለጻ ተረድቷል።
ፋብሪካው የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ፤ ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት መሥራቱን፣ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ተመልክቷል።
ይሁን እንጂ የዘርፉን ምርታማነት አሁን ካለበት በተሻለ ለማሳደግ ግብዓት ሊያቀርቡ ከሚችሉ ድርጅቶች እና አርሶ አደሮች ጋር በበለጠ ቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁሞ፤ ጥሬ ዕቃዎችን በሃገር ውስጥ ለማምረት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል።
ድርጅቱ በአጠቃላይ በግብይት ሥርዓቱም ሆነ በምርት ጥራት ደረጃው ላይ ቁጥጥር በማድረግ፤ የጀመረውን የገበያ ማረጋጋት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ኮሚቴው በግብረ-መልሱ አሳስቧል።
የኮከብ ቃና የዘይት ፋብሪካ የአስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ካሳ እንዳስረዱት፤ በቀን 165 ቶን ዘይት የሚያጣራው ይህ ፋብሪካ፤ በዓመት አንዴ የሚያገኘው የቅባት እህል፣ ከሦስት ወር በላይ የሚያሠራው ባለመሆኑ፤ መሥራት ካለበት ከሃያ በመቶ በታች እየሠራ ይገኛል።
ድፍድፍ ዘይት ከውጭ በማስገባት እና በስፋት በማምረት፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለሸማች ማኅበራት እንዲሁም ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ምርቱን በማድረስ፤ የተከሰተውን የዘይት ዕጥረት ችግር ለመቅረፍ የተሻለ መሠራቱን ዳይሬክተሩ አያይዘው አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የቅባት እህሎች በሚመረቱባቸው ቦታዎች ያለውን የጸጥታ ችግር በመፍታት፣ መንግሥት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እና የባንኮች ድጋፍም እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም