
‹‹ለአቅርቦት ችግሩ ጊዜያዊ መፍትሔ በማበጀት እጥረቱን ለመፍታት ተሞክሯል›› – የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን
አዲስ አበባ፡- የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት በኑሯቸው ላይ ጫና መፍጠሩን ገለፁ። ለአቅርቦት ችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ በማበጀት እጥረቱን ለመፍታት መሞከሩን የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ገልጿል።
ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በመኖሩ የእለት ተእለት ኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሯል። ለከፍተኛ ወጪም ዳርጎናል።
በኮዬ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዋ ነፍሰጡርና የአንድ ልጅ እናት የሆኑት ወይዘሮ ፋጡማ አሕመድ በውሃ አቅርቦት ችግር ምክንያት ለንፅሕናም ሆነ ለምግብ ማብሰያ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል። መንግሥት ከሚቀርበው የታንከር ውሃ በመቅዳት ወደ ጋራ መኖሪያ ቤት ለማጓጓዝ እንደሚቸገሩም ገልጸዋል።
በአካባቢው የውሃ ችግር በመኖሩ ምክንያት ከሌላ ቦታ በጋሪ በመቅዳት እስከ ሰባተኛ ፎቅ ለማጓጓዝ በአንድ የ20 ሊትር በሚይዝ የውሃ መቅጃ ከ25 እስከ 30 ብር በሥራው ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ገልፀዋል።
በኮዬ ሁለት የሚኖሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ የውሃ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ ምክንያት ውሃ የሚያገኙት በፈረቃ መሆኑንና ይህም የእለት ተእለት ኑሯቸውና ሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል። በተለይም በንግድ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ጥጋቡ ባጪሶ ‹‹በውሃ እጥረት ምክንያት ለመሥራት ያሰብነው ሥራ ላይ እንዳንሠማራ ሆነናል›› ብሏል።
ዝግጅት ክፍሉ ባደረገው ቅኝት ችግሩ እንደሚስተዋል አረጋግጧል። በተለይም ኮዬ አንድ ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤት የመጠጥ ውሃ የማይደርስ መሆኑን እና በውሃ ጫኝ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ ለነዋሪው ውሀ እየቀረበ መሆኑን ታዝቧል።
በአንፃሩ በተለምዶ ኮዬ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የውሃ አገልግሎት መኖሩን፣ ነገር ግን ይህ አካባቢም በፈረቃ በየሶስት ቀን ልዩነት እንደሚያገኝ ነዋሪዎችን ባነጋገረበት ወቅት ለመረዳት ተችሏል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ በኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚስተዋለው የንፁሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። በኮዬ አንድ የውሃ አቅርቦት አገልግሎት ባልጀመረባቸው አካባቢዎች በውሃ ጫኝ ተሽከርካሪ በቋሚነት እንዲቀርብላቸው መደረጉን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ እንደገለፁት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከመንገድ፣ ከኤሌክትሪክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ቤቶች ልማት መሥሪያ ቤቶች ጋር የጋራ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱንና የውሃ መሠረተ ልማት ዝርጋታ የመንገድ ሥራ መጠናቀቅን ተከትሎ የሚከናወን ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማቱ እንደተጠናቀቀ የውሃ ዝርጋታና ስርጭት ፕሮጀክቱ የሚከናወን በመሆኑ የውሃ አቅርቦት ያላገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በዚህ ረገድ አገልግሎቱን ወዲያው እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ለኮዬ ፈጬ ነባር ፕሮጀክቶች በቀን በአማካይ 25 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የሚቀርብ በመሆኑ በፈረቃ ለማዳረስ መገደዱን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፤ ፍላጎትን የሚመጥን የውሃ አቅርቦት እስኪጀመር ነዋሪዎች በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን በፈረቃ የማቅረብ ሂደቱ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የመብራት መቆራረጥ፣ የመስመር ብልሽት እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ውሃን ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ የሚገድቡ በመሆኑ በፈረቃ የሚያገኙ አካባቢዎች ላይ በተቀመጠው ፈረቃ ላይ አንድ አንድ ጊዜ ተጨማሪ ተጽእኖ የሚፈጥሩ መሆናቸውን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
ፍቃዱ ዴሬሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም