
አዲስ አበባ፡- ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው መከራ እንዲያበቃ የትግራይ ልሂቃን ድምጻቸውን እንዲያሰሙ የትግራይ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ጠየቀ።
የትግራይ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሕወሓት በ1977 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለትግራይ ሕዝብ የተላከን እርዳታ ለመሳሪያ መግዢያ ሲያደርግ የነበረ የትግራይ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው።
አሁንም ከስልጣን ተገፍቶ በመሄድ የትግራይን ሕዝብ እንደምሽግ በመጠቀም በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ግፍ እየፈጸመ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ከመንግሥትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚላከውን የሰብዓዊ እርዳታ የሽብር ቡድኑ ለራሱ ጥቅም እያዋለው ነው።
እንደ አቶ ሙሉብርሃን ገለጻ፤ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግደውንና በሕዝቡ ላይ እየፈጸመ ያለውን ሁለንተናዊ ግፍ ለትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ልሂቃንና ዲያስፖራዎች እውነቱን በመረዳት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያስረዱ ይገባል። አሸባሪ ቡድኑ የሚላከውን የሰብዓዊ እርዳታ ለሕዝቡ መስጠቱ ቀርቶ ሕዝቡ ካለው እንዲያወጣ እያስገደደ ነው። የምናዋጣው የለንም የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለእስራት፣ ለድብደባና እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ሕወሓት እየተከተለው ያለው አካሄድ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እንዳይኖርና እንዲጠፋ ነው ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ልሂቃኑና ዲያስፖራው ሕወሓት እየተከተለ ያለውን አደገኛ አካሄድ በመገንዘብ ድምጽ ለተነፈገው ሕዝብ ድምጽ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
የትግራይ ልሂቃንና የትግራይ ተወላጅ የዲያስፖራ አባላት አሸባሪ ቡድኑ በሕዝቡ ላይ እያስከተለ ያለው ሁለንተናዊ ግፍ ገብቷቸው ሕዝቡን ለማዳን ድምጻቸውን ሊያሰሙ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በመንግሥትም ሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች አማካኝነት ወደ ትግራይ የሚላከው የሰብዓዊ እርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እየደረሰ እንዳልሆነ ትዴፓ እንዳረጋገጠ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ለትግራይ ሕዝብ እናስባለን የሚሉ የትግራይ ልሂቃንና ዲያስፖራዎች ድምጻቸውን እያሰሙ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ እየጠፋ በዝምታ መመልከታቸው ታሪካዊ ስህተት እየፈጸሙ መሆኑን ሊያውቁ ይገባል። ሕወሓትን ለማዳን ሲባል የትግራይ ሕዝብ መጥፋት እንደሌለበትም ገልጸዋል።
የትግራይን ሕዝብ ራሳቸው እየመቱ መቺ እየፈጠሩ በተዛባ መረጃ እንዲደናገር በማድረግ ወደ ጦርነት እያሰለፉት ነው። የትግራይ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ከዚህ በላይ ሊሸከማቸው አይገባውም፣ በቃህ ሊላቸው እንደሚገባ አቶ ሙሉብርሃን አሳስበዋል።
አንድ አሸባሪ ሽፍታ ቡድንን ለማዳን ሲባል የትግራይ ሕዝብ መጥፋት የለበትም ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ በተለያዩ መስኮች የተሠማሩ የትግራይ ተወላጆች እየሆነ ያለውን በመገንዘብ ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው ብለዋል።
ለትግራይ ሕዝብ እናስባለን የሚሉ ልሂቃን ድምጻቸውን ለሕዝቡ እያሰሙ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉብርሃን፤ በትግራይ ሕዝብ መድኃኒትና የተለያዩ የምግብ እርዳታ እየገባ ቢሆንም በትክክል ለሕዝቡ ባለመድረሱ በተለያዩ በሽታዎችና ረሃብ እንዲጋለጥ ሆኗል ብለዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም