ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዞን 4.4 የግል የበላይነት የቼስ ቻምፒዮናን እያስተናገደች ትገኛለች። ቻምፒዮናው ካለፈው እሁድ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ማግኖሊያ ሆቴልና ኮንፈረንስ ማእከል እየተካሄደ ሲሆን ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።
ቻምፒዮናውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የ2022 የአፍሪካ “የዞን 4.4 የግል የበላይነት የቼስ ቻምፒዮናን ‘’ በስኬት ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ገልጿል። “አንድ ቤተሰብ ነን( We are one family)” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው ቻምፒዮና ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ጠንካራ ፉክክር እያስተናገደም ይገኛል
በዚህ የዞን 4.4 የግል የበላይነት የቼስ ቻምፒዮና ላይ ከአሥራ ሶስት የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የቼስ ተጫዋቾች እየተሳተፉ ይገኛሉ። የቻምፒዮናው ዋና አላማ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለንን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር በማጎልበት ወዳጅነታችንን ከማጠናከር ባለፈ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ለሌሎች የዓለም አገራት መልካም ገፅታዎችን ለማሳየት እንደሚጠቅም የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ ገልፀዋል ።
በቻምፒዮናው ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ተሳታፊ ከሆኑ አገራት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ይህ ውድድር በኢትዮጵያ መካሄዱ የቼስ ስፖርትን የበለጠ ለማስፋፋት የራሱ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል። በዚህ ውድድር እያንዳንዱ ሀገር አምስት ወንድና አምስት ሴት ስፖርተኞችን የሚያሳትፍ ይሆናል። ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ሌሎች ከሚያሳትፉት በእጥፍ ስፖርተኞችን ታሳትፋለች። በተጨማሪም አሥር ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች በአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን በቀጥታ ተወክለው በግል ይወዳደራሉ።
ኢትዮጵያ የ2022 ዓ.ም የዞን 4.4 የግል የበላይነት የቼስ ቻምፒዮና አዘጋጅ አገር በመሆኗ በውድድሩ ከሚፈቅደው ተሳታፊ ቁጥር በላይ ተጨማሪ ቡድን በአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን ቀጥታ ፈቃደኝነት መጨመር እንደተቻለ ታውቋል። በዚህም በአጠቃላይ ከመደበኛው ቡድን ውጪ ከዘጠኝ በላይ የግል ተወዳዳሪዎችን ማሳተፍ የተቻለበት ዕድል እንደተፈጠረ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።
በቻምፒዮናው ላይ ከአምስት ሺ አምስት መቶ የአሜሪካን ዶላር በላይ የማግኘት ዕድል ሰፊ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ከሁለቱም ፆታ ቻምፒዮን ለሚሆኑ ሁለት ተጫዋቾች ሙሉ ወጪ ተሸፍኖ በአረብ ኢምሬት የ2022 ሻርጃሀ ማስተር ቼስ ቻምፒዮና ላይም የመሳተፍ ዕድል ሊኖር እንደሚችል አቶ ሰይፈ ተናግረዋል።
በቻምፒዮናው የመወዳደሪያ ፔሪንግ ሲስተም ከአንድ አገር የተሰለፉ ተጫዋቾችን እርስ በርስ የሚገናኙበት እና የሚሸናነፉበት የውድድር አይነት እንደሚኖር የተጠቆመ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን (ACC) እና የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን (ECF) በጋራ በመሆን ውድድሩን እንዳዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል።
ከቻምፒዮናው ጎን ለጎን የተለያዩ መርሐግብሮች የተካተቱ ሲሆን ለአብነት ያህል የኢንተርናሽናል የዳኝነት ስልጠና ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የሙዚየም ጉብኝት ፣የባህል ትውውቅ እና የእራት ግብዣ እና የሽልማት እና የስጦታ መርሐግብሮች እንደሚኖሩ ተብራርቷል ።
በዚህ ቻምፒዮና ላይ በአጠቃላይ በሁለቱ ፆታ ከስልሳ በላይ የቼስ ተጫዋቾች ከተለያዩ አሥራ ሶስት የአፍሪካ አገራት ተሳታፊ ናቸው። በዚህም ከታዳጊ ወጣቶች ጀምሮ እስከ አዋቂዎች ድረስ ከስድስት የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ሃያ የቼስ ተጫዋቾች ተመርጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተወዳዳሪ ሆነዋል። ስፖርተኞቹ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ቀደም ብለው በቂ ዝግጅት እንዳደረጉም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም