በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ጋዜጣው በ1963 ዓ.ም ይዟቸው ከወጣ ወንጀልና ፍትህ ነክ ዘገባዎች መካከል ብታነቧቸው ብለን የተወሰኑትን ዘገባዎች መርጠን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
በጆንያ ታፍና የተወሰደችው ልጅ አሰላ ትገኛለች
አሰላ (ኢ-ዜ-አ-) በጆንያ ውስጥ ታፍና ከቤቷ የተወሰደችው ፋጡማ መሐመድ ለሁለት ወር ያህል በማታውቀው ቀበሌ ስትንከራተት ከሰነበተች በኋላ ትናንት አሰላ ከተማ ደርሳ በጠ/ግዛቱ ፖሊስ መምሪያ ተገኘች።
፮ ዓመት ዕድሜ ያላት ፋጡማ መሐመድ አዲስ አበባ ካሳ ገብሬ ሠፈር የምትኖር መሆኗን ለፖሊስ መምሪያ በሰጠችው ቃል ማረጋገጧን ረዳት ዋናው አዛዥ ገልጠዋል።
መልኳ ጠይም፤ ዐይነ ትንንሽና ጥርሰ ፍንጭት የሆነችው ፋጡማ መሐመድን አንድ የማታውቀው ሰው ከመኖሪያ ቤቷ ውስጥ በከረሜላ አባብሎ እንድትወጣ ካደረገ በኋላ አፏን በጨርቅ አፍኖና በጆንያ ከትቶ በጭነት መኪና የወሰዳት መሆኑን የጠ/ግዛቱ ፖሊስ ረዳት አዛዥ ኮሎኔል ኃይሌ ጫኔ ገልጠዋል።
ፋጡማ በዚሁ ሁኔታ ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላው ቀበሌ ከመንገደኞች ጋር ስትዘዋወር አሩሲ ጠ/ግዛት ጭላሉ አውራጃ ዟይ ዱግዳ ከተባለው ከተማ ደረሰች። እዚያም በመንገላታት ላይ እንዳለች አንድ ሰው ይህን መንገድ ይዘሽ ወደ አሰላ ሒጂ ብለው ስለመከሩኝ ወደዚህ መጣሁ ብላ ለፖሊስ ጣቢያ በሰጠችው ቃል ገልጣለች።
የፋጡማ ወላጆች ፋጡማን አሩሲ ጠ/ግዛት ፖሊስ መምሪያ ድረስ መጥተው ሊያገኟት መቻላቸውን ረዳት አዛዡ በተጨማሪ ገልጠዋል።
ይሁንና ፋጡማ በማታውቀው ሰው በመኪና ታፍና ከተወሰደች በኋላ የት ቦታ እንደወረደች ወይም እንደተጣለች አዛዡ አላብራሩም።
( ሚያዝያ 22 ቀን 1963 ዓ.ም)
የ10 እና የ25 ሳ.ባለ አልቤርጎች ተከሰሱ
የባህር ዛፍ አጣና እንደቆጥ እየረበረቡ ፤በላዩ ላይ ጆንያ ደልድለው አሮጌ ባና እየደረቡ በአንድ ክፍል ቤት እስከ ፴፪ ሰዎች እያስተኙ ፤በአንድ ሌሊት ከ፲ እስከ ፳፭ ሳንቲም ለአንድ ሰው የሚያከራዩ ፲፬ ሰዎች ተከሰሱ።
ተከሳሾቹ አልቤርጎዎቹን አዲስ አበባ በአሜሪካ ግቢ ፤በጌሾ ሠፈር፤በራጉኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ያለፈቃድ ለብዙ ዓመቶች ሲያከራዩ ቆይተው ሰሞኑን በምዕራብ ጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ተከታታይነት ተይዘው መጋቢት ፳፫ ቀን ፯ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በሦስቱ ቀበሌዎች እስከ ብዙ የአጠና ርብራብ ቆጦች የሚገኙ መሆናቸው ሲገመት በአንድ ሌሊት ቁጥራቸው የበረከተ ሰዎች ለማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውን የምዕራብ ጤና ጥበቃ ሹም አቶ ተረፈ ኃይሉ ባደረጉት መከታተል የደረሱበት መሆናቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ዜና ገልጠዋል።
አሥራ አራቱ አልቤርጎዎች ውስጥ የሚተኙት ሰዎች መግባት የሚጀምሩት ከሌሊቱ ፬ ሰዓት ሲሆን ፤ወድቅቱን በሙሉ ሲወጡና ሲገቡ ቢያድሩም ቀኑን ተኝተው ቢውሉ ሁሉም ነገር ነፃ ነው። ዜና አቅራቢው ለመጎብኘት በሔደበት ጊዜ አንዳንዶቹ ቤቶች ተዘግተው የተኙትን ሰዎች በጭላንጭል ተመልክቷል።
ለማነጋገር ፈልጎ መልስ የሚሰጥ አልተገኘም። ወዲያው ኩሼ ሆነ። በአቅራቢያው የሚገኙ አንዳንድ ኗሪዎች እንዳመለከቱት፤ በነዚህ አልቤርጎዎች ውስጥ ዘወትር ሌሊቱን ጭፈራና ዘፈን ይሰማል። ሁልጊዜ ደስታ ነው። ጥቂትም ቆይቶ ድብድብና ሁካታ ይስተጋባል። ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ሲሆን ፍጹም ጸጥታ ይሆናል። አብዛኛው ጊዜ በቀን ሲወጣና ሲገባ የሚታይ ሰው የለም በማለት አስረድተዋል።
አቶ ተረፈ እንደገለጡት አልቤርጎዎቹ ከተቋቋሙ አያሌ ዓመታት ሆኖዋቸዋል። በሰው ሕይወት ላይ ጠንቅ የሚያስከትሉና ለሠፈር ጸጥታ የሚያውኩ መሆናቸው የተደረሰባቸው በአሁኑ ዓመት በተደረገው የጽዳት ዘመቻ መንገዶች ስለተከፈቱ አካባቢውን ለመቆጣጠር በምንዘዋወርበት ጊዜ ደርሰንበት ባለ አልቤርጎዎቹን ከሰናቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ባለ አልቤርጎዎቹ ፈቃድ አውጥተው ቤታቸውን አጽድተው በደንበኛ አልጋዎች ካልሠሩ በአሁኑ ይዞታ እንዲቀጥሉ የማይፈቀድ መሆኑን አስረድተዋል።
( መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም)
ቆማ የተገኘችው መኪና አሁንም ባለቤት አላገኘችም
አንዲት ባለቤቷ ያልታወቀ ቁጥሯ 2684 አዲስ አበባ የሆነ ቮልክስዋገን መኪና በናዝሬት ከተማ አቅራቢያ ወደ ወንጂ በሚወስደው መንገድ ላይ ቆማ መገኘቷንና የኔናት ባይ ጠፍቶ አሁንም በናዝሬት ፖሊስ ጣቢያ የምትገኝ መሆኗን የሸዋ ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል ገለጠ።
መኪናዋ በዚሁ ሥፍራ ቆማ የተገኘችው በ20 /7/63 ዓ/ም ነው። እስካሁንም ድረስ ወሳጅ ባለቤት አለመገኘቱ ታውቋል። በዚህም ምክንያት በክፍሉ ፖሊስ አማካይነት ከቆመችበት ቦታ ተነስታ ወደ ናዝሬት ፖሊስ ጣቢያ ተወስዳ በዚያ ትገኛለች። ሁኔታውንም በይበልጥ ለማረጋገጥ እንዲቻል ፖሊስ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ይገኛል።
ነገር ግን የመኪናዋ ባለቤት ከተገኘ ከተጠቀሰው ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ሔዶ ለመውሰድ መቻሉ ተገልጧል። አንዳንድ ጊዜ በአቃቂም ሆነ በደብረ ዘይት መንገድ ባለቤታቸው ያልታወቀ መኪናዎች እየቆሙ እንደሚገኙ ታውቋል። ይህችም መኪና እስካሁን ድረስ ወሳጅ ባለቤት ያጣቸው ምናልባት በስርቆት ተወስዳ ይሆናል ሲል አንድ የማስታወቂያ ክፍል ቃል አቀባይ አስረድቷል።
(ሚያዝያ 1 ቀን 1963 ዓ.ም )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም