ከእውቀት መስፋፋትና ትውልድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሊታይ የሚገባው እንጂ ለድርጅቱ ብቻ የተሰጠ አስተያየት ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው አይደለም።
ከላይ በገለፅነው የርክክብ ስነስርአት ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተገኝተው ነበር። እሳቸው እንዳሉት ገና ካሁኑ አብርኆት ቤተመጻሕፍትን በየቀኑ ከሶስት እስከ አምስት ሺህ ሰዎች ለንባብ እየጎበኙት ነው። ይህም በአገራችን ያለው የቤተመጻሕፍትና የመጻሕፍት እጥረት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። ሕዝብም የማንበብ ፍላጎቱ ምን ያክል እንደጨመረ ያመላክታል። በመሆኑም ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የንባብ ባህልን ለማዳበር እንደ አብርኆት ያሉ ቤተመጻሕፍትን በየክፍለ ከተማው መገንባት ይጠበቃል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ወር ውስጥ አንድ ሚሊዮን መጻሕፍትን ለማሰባሰብ የተያዘው ዕቅድም የቤተመጻሕፍቱን አቅም በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው፤ አብርኆት ቤተመጻሕፍት አራት ሚሊዮን መጻሕፍት የመያዝ አቅም እንዳለው፤ ቤተመጻሕፍቱ ውስጥ ቢያንስ ሁለት ኮፒ ያላቸው ሁለት ሚሊዮን መጻሕፍት እንደሚያስፈልጉ፤ በዚህ ረገድ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት መጻሕፍት በማሰባሰብ ረገድ እያደረጉ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም አምስት ሺህ መጻሕፍትን መለገሱ በሂደቱ አርዓያ እንደሆነ፤ በአንድ ወር ውስጥ አንድ ሚሊዮን መጽሐፍትን ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት ዜጎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ፕሮፌሰሩ በርክክብ ስነስርአቱ ላይ የተናገሩት። ይህም የኢትዮጵያዊያን የእጅ ልገሳ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን በሚገባ የሚያሳስብ ሆኖ ነው የምናገኘው።
ለዚሁ ቤተመጻሕፍት “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ አንድ ሚሊዮን መጻሕፍትን የማሰባሰብ ዘመቻው ከዚሁ አገራዊና ትውልዳዊ ፋይዳው አኳያ ሲታይ መሆን ያለበት ብቻ ሳይሆንየዘገየ ሁሉ የሚያስብል ነውና ለእጅ ልገሳው አንድ እራሱን የቻለ ገፊ ምክንያ ነው ማለት ነው።
የመጻሕፍት አሰባሳቢ ኮሚቴው ሚያዝያ 21 2014 አ.ም በቤተ መጻሕፍቱ አዳራሽ በሰጠው መግለጫ፤ የመጻሕፍት መሰባሰብ ዓላማው፤ ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት የሚሆኑ መጻሕፍትን በአይነትና በብዛት ማሰባሰብ፤ ለሌሎች ክልሎችና ከተማዎች ለሚገኙ አብያተ መጻሕፍት ለመለገስ፤ እንዲሁም የንባብ ባህልን በማዳበር አንባቢና አሰላሳይ ትውልድ እንዲፈጠር ለማበረታታት እንደሆነ አስታውቋል።
ይህ ለአንድ አገር ህዝብ ከ”የእናት አገር ጥሪ” የሚተናነስ አይደለምና እጅ ልገሳው ሊቀጥል ይገባል።
በዚሁ ስነስርአት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ዕውቀት መር ማህበረሰብ ለመገንባት እውቀት የሚሸጋገርባቸው መንገዶችን ማሳለጥ ያስፈልጋል፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ መጻሕፍት ዋነኞች መሆናቸውን፤ ኢትዮጵያዊያን ፊደል ቀርጸው፣ ብራና ፍቀውና ቀለም በጥብጠው፣ ከድንጋይ ዘመን እስከ ወረቀት ዘመን እውቀትን ለማስተላለፍ የተጉ እንደ ነበሩ፤ ይህም መቀጠል ያለበት ስለ መሆኑ፤ በዚህ የፊደል ቀረጻና የእውቀት ምርት ያላቸውን ቦታ ያህል ከታሪካቸው፣ ከቋንቋና ባህል ብዝኃነታቸው ከህዝብ ቁጥራቸው ጋር የሚመጣጠኑ አብያት መጻሕፍት እንደሌሉ መናገራቸው፤ ይህም እውቀት መር የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማጓተቱትን፤ ይሄንን ችግር ለመፍታት ከዛሬ 75 ዓመታት ጀምሮ ዘመናዊ አብያተ መጻህፍትን ለመገንባት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን፤ ነገር ግን የህዝቡን ቁጥር፣ ብዝኃነትና የሥነ ጽሁፍ ሀብት የሚመጥን አለመሆኑን መግለፃቸው ብዙ የሚለው ነገር አለና በእጅ ልገሳው ተግባር ወደ ኋላ ማለት ይከብዳል።
የአብርኆት ቤተ መጻሕፍት፤ እውቀት መርና አመክንዮአዊ የሆነ ትውልድ ለመገንባት፣ ከግንባታው ጀምሮ በያዛቸው አካላዊና ዲጂታል መጻህፍት ድረስ ወደ ፊት ለሚገነቡ አብያተ መጻሕፍት አርአያ እንዲሆንና ለሌሎች አብያተ መጻሕፍት ማሠራጫ ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል እንደተገነባ ከዚህ በፈሪት በዚሁና ሌሎች የጋዜጣው አምዶች ላይ መግለፃችን የሚታወስ ነው። በመሆኑም፣ ይህን ቤተ መጻሕፍት ለኢትዮጵያውያን በሚጠቅሙ አካላዊና ዲጂታል መጻሕፍት ለማሟላት እየተሰራ ያለውም ሆነ ሊሰረታ የታሰበው ስራ በእጅጉ የሚበረታታ ነውና ሁሉም በእጅ ልገሳው ተግባር እዚህ ልማት ውስጥ እጁን ሊያስገባ ይገባል ስንል ዝም ብለን አይደለም።
ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን መጻሕፍት እንደሚሰበሰቡ፤ ይህም የሚከናወነው በአብርኆት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንደሆነ መነገሩ፤ ለሥራው መሳካት የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ተጠሪ ተቋማት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የህክምና ተቋማት፣ የኮንስትራክሽን ተቋማት፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ተቀማጭነታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ አሳታሚዎችና ማተሚያ ቤቶች፣ የታክሲና የረጅም ርቀት ሹፌሮችና ረዳቶች፣ ሊስትሮዎች፣ የቀን ሠራተኞችና ሌሎችም በልዩ ልዩ የኢትዮጵያና የውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ እንዲሁም ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎችን የሚያስረዱ መጻሕፍትን በመለገሥ አሻራቸውን ለትውልድ እንዲያቆዩ በአስተባባሪዎቹ በኩል ጥሪ መቅረቡ ሌላ ሳይሆን ጉዳዩ የጋራ መሆኑን ከማመላከት ባሻገር የ”ኑ፣ እጅ ለግሱ”፤ ወይም፣ ከላይ እንዳልነው ትውልድን የመታደግና የነቃ ማህበረሰብ (Civil society)ን የመፍጠር “የእናት አገር ጥሪ” ስለ መሆኑ ምንም አይነት የሚያሻማ ነገር የለውም።
በእለቱ አስተባባሪዎቹ ዜጎች ራሳቸውን በእውቀት እንዲያጎለብቱ አብርኆት ቤተ መጻሕፍት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው መግለፃቸው፤ በአሁን ወቅት በመጻህፍት ቤቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሮኒክስ መጻህፍት ክምችት እንዳለ መነገሩ ተስፋ ሰጨ ነው።
በአንድ ወር አንድ ሚሊዮን መጻሕፍት ለመሰብሰብ በተጀመረው ተግባር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተወጣጡ አካላት በኮሚቴ ተዋቅረው እየሰሩ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን፤ ሁሉም፣ አቅሙ የፈቀደለት በሙሉ፣ የኢትዮጵያዊያንን የእጅ ልገሳ እሴት በማስቀጠል አብርኆት ቤተ መጻሕፍትን ምሉእ በኩለሄ ማድረጉ ላይ ሊረባረብ ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ