
አዲስ አበባ፡- የኢድ-አልፈጥር በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ አስታወቀ። የጋራ ግብረ ኃይሉ የኢድ-አልፈጥር በዓል የመልካም ምኞት መግለጫ አውጥቷል።
በየትኛውም እምነት ውስጥ ተደብቀው እምነቱ ከሚፈቅደው ውጪ የተለያዩ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ሕዝቡ ከውስጡ አውጥቶ በማጋለጥ ለፀጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት የተለመደውን ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልና አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ሳምንት ተከብሮ ያለፈው የፋሲካ በዓል እና ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀው ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሃ ግብር በሰላማዊ መንገድ መካሄዱን አስታውሷል መግለጫው።
በመሆኑም ከጥምር የፀጥታ አካላት የተሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ላደረጉ የሁሉም ሃይማኖት አባቶች፣ በዓሉን በኮሚቴነት ላስተባበሩና ለመሩ አካላት፣ ምዕመናኑን በማስተናገድ ከፍተኛ ድርሻ ለተወጡ ወጣቶችና ሰላም ወዳዱ የአገራችን ሕዝብ እንዲሁም በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ የራሳችሁን ድርሻ ላበረከታችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና ደህንነት ኃይሎች በሙሉ የፌዴራል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ምስጋና አቅርቧል፡፡
ልክ እንደ ፋሲካ በዓል እና የኢፍጣር መርሃ ግብር ሁሉ የኢድ-አልፈጥር በዓልም በተመሳሳይ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ተልዕኮውን በአዲስ አበባና በሌሎች የአገራችን አካባቢዎች በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል ሲልም ጠቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት ለበዓላቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሕዝቡን ለማሳሳትና የእምነቶቹ ወግና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ምዕመናኑን ወደ ግጭት ለማስገባት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዳሉ የጋራ ግብረ ኃይሉ እንደደረሰበት አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ግጭት የተቀሰቀሰ ቢሆንም ግጭቱን በሃይማኖት ሽፋን ለማባባስ የሚደረገው ጥረት እኩይ ዓላማ ላላቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች ዕድል ስለሚፈጥር ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ይህንን ተገንዝባችሁ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ ያለውን ተግባር ማገዝ ይጠበቅባችኋል ብሏል በመግለጫው።
በተመሳሳይ በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ ግጭቱን ለማባባስ በተናበበ በሚመስል አኳኋን በቤተ እምነት ላይ የደረሰው ቃጠሎ እና በክቡር የሰው ልጅ ሕይወት ላይ የደረሰው ሞት የክርስትናንም ሆነ የእስልምናን እምነቶች የማይወክል ተግባር እንደሆነም አንስቷል።
በጎንደርና በወራቤ ከተሞች በጠፋው ክቡር የሰው ልጅ ሕይወት እና በእምነት ተቋማቱ ላይ በደረሰው ውድመት የጋራ ግብረ ኃይሉ የተሰማውን ኀዘንም ገልጿል፡፡
ከዚሁ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ከሁለቱም ወገን በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ እንዲሁም ከጀርባ ሆነው ግጭቱ እንዲባባስና ወደ ሌሎች የአገራችን አካባቢዎች እንዲዛመት ሲቀሰቅሱና ሲያነሳሱ የነበሩትን ፀረ-ሰላም ኃይሎችን የጋራ ግብረ ኃይሉ እያደነ ለሕግ ማቅረቡን እንደቀጠለም በመግለጫው ላይ ተነስቷል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም