
አዲስ አበባ፡- ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ለማፍራት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ መንገዱን መጥረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ወልድያ ከተማ የሚገኙትን የአገር መከላከያ ሠራዊትን የደቡብ፣ ምሥራቅ፣ 6ኛ እና 8ኛ ዕዞችን ጎብኝተዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለመኮንኖች ባደረጉት ንግግር ዝግጁነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል የማሸነፍ ዕድላቸውን እንዲያሰፉ፣ ድል አድራጊ ሰብዕናን እንዲገነቡ እና የስጋት ተጋላጭነትን እንዲቀንሱ አበረታተዋል።
ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ማፍራት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ መንገዱን መጥረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ክርስትናና እስልምና በፍቅር የኖሩባት አገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ የኩራታችን ምንጭ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሚነገር ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሚለማ መሬት እና የሚያለማ ሕዝብ አላትም ነው ያሉት።
ይህንን የተረዱ ጠላቶቻችን ልማታችንን ለማደናቀፍ እና አንድነታችንን ለማጠልሸት እየሠሩ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያን በጥላቻ ታውሮ ማሸነፍ እንደማይቻል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፍቅር ተነሳስቶ መስዋዕትነት ከፍሎ ኢትዮጵያን ማጽናት ነው የሚቻለው ብለዋል።
ፈታናዎች እና የሚያደናቅፉን ቢበዙም በየቀኑ እየበረታን እንሄዳለን፡፡ የኢትዮጵያ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው ምሰሶ የአገር መከላከያ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በጉብኝቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት እና የአገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ተገኝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም