አቶ ጌታቸው ነጋሽ የሚኖሩት በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ሁለት አካባቢ ነው። ዕድሜያቸው ስልሳ ሰባት ነው። ከዛሬ ስድስት አመታት በፊት በእጃቸው ላይ የመንቀጥቀጥ ስሜት ይታይ ጀመር። መጀመሪያ ይህን ስሜት ሲመለከቱ አልኮል የሚጠጡ ሰዎች አልኮሉን ሲያጡ የሚያሳዩት ምልክት መስሏቸው ነበር። እርሳቸው ግን በጊዜው አልኮል ጠጪ አልነበሩምና ከሰው ጋር ሲገናኙ የሚንቀጠቀጠው እጃቸው እንዳይታይ ተሸማቀው ይደብቁ ጀመር። አንዳንድ የጎረቤት ሰዎችም «ይህ ሰውዬ መጠጥ ይጠጣ ነበር እንዴ?» እያሉ ይጠቋቆሙባቸው ነበር። ቀስ በቀስም የእጃቸው መንቀጥቀጥ እየተባባሰ ሄደ።
እንዲያውም አንድ ጊዜ ቤተሰባቸውን ለመጠየቅ ወደ ደብረ ዘይት ሲያቀኑ በፍተሻ ወቅት እጃቸው ሲንቀጠቀጥ የተመለከቷቸው ፖሊሶች እርሳቸውን ከሌሎች መንገደኞች ነጥለው ይመረምሯቸው ጀመር። ተቀምጠውበት የነበረውን አካባቢም ፈተሹ። ለምን እንደሚንቀጠቀጡ በፖሊስ ሲጠየቁም በሽታ እንደሆነ ያስረዳሉ። ነገር ግን ሊታመኑ አልቻሉም። በመጨረሻ ግን የሚወስዱትን የፓርኪንሰን መድኃኒትና አንዳንድ ስለበሽታው የሚያስረዱ ወረቀቶችን በማሳየት ተለቅቀዋል።
አቶ ጌታቸው ያጋጠማቸው የመንቀጥቀጥ ሕመም እየተባባሰ ሲሄድ ሆስፒታል ሄዱ። የነርቭ ችግር መሆኑም በሀኪሞች ተነገራቸው። ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ እንደ ልብ መንቀሳቀስ እየተቸገሩ መጡ። ችግራቸውን ለሐኪሞች ካስረዱ በኋላ በምርመራ የፓርኪንሰን ሕመም እንዳለባቸው አረጋገጡላቸው።
የፓርኪንሰን ታማሚ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ወዲያውኑ ሕክምናውን መከታተል ጀመሩ። መድኃኒቱንም መውሰድ ቀጠሉ። አሁንም ከበሽታው ጋር እየኖሩ በሽታው ወደ ቀኝ የሰውነት ክፍላቸው እንዳይሸጋገር ለማስቆም እየታገሉ ይገኛሉ።
ወደ «የፓርኪንሰን ፔሼንትስ ሳፖርት ኦርጋናይዜሽን – ኢትዮጵያ» ከመጡም በኋላ ስልጠናዎችንና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ይወስዳሉ። የአይን ሕክምናና ምርኩዝም ያገኛሉ። በዚህም በራስ መተማመናቸውን ማዳበር ችለዋል።
የፓርኪንሰን ታማሚዎች ትልቁ ችግር የመድኃኒት እጥረት ነው የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ እርሳቸው የፓርኪንሰን ፔሼንትስ ሳፖርት ኦርጋናይዜሽን – ኢትዮጵያ አባል በመሆናቸውና ከዚሁ ድርጅት መድኃኒት ስለሚያገኙ ችግሩ እንዳልነካቸው ይናገራሉ።
ይሁንና ሌሎች በርካቶች በመድኃኒት እጥረት ምክንያት በሕመሙ የሚሰቃዩ በመኖራቸው መንግሥት የዚህን ድርጅት አርአያ በመከተል የፓርኪንሰን ታማሚዎች ሁለገብ መርጃ ማዕከል ቢከፍት ችግሩን ማቃለል ይቻላል ይላሉ። ነገር ግን መንግሥት ችግሩ እንዳለ እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ መሄዱ እጅግ እንደሚያሳዝናቸውም ይጠቁማሉ።
በርግጥ ድርጅቱ አቅም ለሌላቸው ሰዎች መድኃኒት ከከነማ የመድኃኒት መደብር በነፃ እንዲወስዱ አድርጓል። ይህም በተለይ አቅም ለሌላቸው ትልቅ እገዛ ነው። ነገር ግን ይህን ዕድል ያላገኙ ሌሎች አሉና መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ሊደርሱላቸው ይገባል።
የፓርኪንሰን ፔሼንተስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን – ኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ታለሞስ ዳታ እንደሚናገሩት፣ መንግሥት ለአንድ በሽታ መድኃኒት ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው የበሽታውን ሥርጭት በማየት ነው። የፓርኪንሰን ሕመም በኢትዮጵያ መኖሩ የማይታወቅ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም የሽታውን ስርጭት በተመለከተ ጥናት አልተካሄደም። ከዚህ አንፃር በርከት ያለ መድኃኒት ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ልምድ ከመንግሥት በኩል የለም። ስርጭቱ ባለመጠናቱም በቂ የፓርኪንሰን መድኃኒት አቅርቦት የለም። ይህ ነገር እንዲቀየር ታዲያ ስለሕመሙ ግንዛቤ ከመፍጠር በመነሳት በጤና ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከል ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችንና ዳይሬክተሮችን በማነጋገር የስርጭት መጠኑ እንዲጠና በድርጅቱ በኩል በርካታ ግፊት ሲደረግ ቆይቷል፤ አሁንም ግፊት እየተደረገ ይገኛል።
መንግሥት ካሉበት የተለያዩ ጫናዎች የተነሳ ይህን ማድረግ ባይችልም መድኃኒቱን የማምጣት ሃሳብ አለው። እንደ ማህበርም የመድኃኒት ስርጭት ጥናቱ እንዲደረግ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ገንዘብ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና መድኃኒት አስመጪዎች በማሰባሰብ መድኃኒቱን የመግዛት አቅም የሌላቸው ታማሚዎች መድኃኒቱ ያለበት ቦታ ሄደው እንዲወስዱ የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነው።
ከጤና ሚኒስቴር፣ ከከነማ መድኃኒት መደብሮችና ከመድኃኒት አቀራቢዎች ጋር በመነጋገር ከ419 በላይ የፓርኪንሰን ሕሙማን መድኃኒቱን በነፃ እንዲያያገኙ ተደርጓል። ከዚያም በላይ ቁጥር ያላቸውን መድኃኒቶችን መውሰድ ደረጃ ላይ የደረሱ የፓርኪንሰን ታማሚዎች ካሉም መጥተው እንዲወስዱ ተደርጓል። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ከመድኃኒቱ ውድነትና እንደ ልብ አለመገኘት ጋር በተያያዘ ችግሩን ለመቅረፍ ሕሙማን መድኃኒቱን በነፃ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች ተሠርተዋል።
እንደ ዶክተር ታለሞስ ገለፃ ድርጅቱን ከሚለግሰው ተቋም ጋር በመሆንና ለዚሁ ተቋም ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ በማቅረብ የፓርኪንሰን ሕሙማን መርጃ ማዕከል ለመግዛት በሂደት ላይ ነው ያለው። ይሁንና ሂደቱ በኮቪድ-19 እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት ሊዘገይ ችሏል። ሆኖም ረጂ ድርጅቱ በቅርቡ በጎ ምላሽ ሰጥቶ ንግግር እየተካሄደ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የቤቶች ኪራይ ድርጅት ካሉት ቤቶች ለሕሙማን መንከባከቢያ እንዲሰጥ በድርጅቱ በኩል የማነጋገር ሥራ ተሠርቷል። ንግግሩ ለጊዜው የተሰካ ባይሆንም እንደገና የመቀጠልና የማሳመን ሥራ ይሠራል። ይህ ካልሆነም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፓርኪንሰን ሕሙማን መርጃ ማዕከል የሚሆን ቤት ወይም ቤት መገንቢያ መሬት እንዲያቀርብ ጥያቄ ቀርቧል፤ ግፊትም እየተደረገ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የክሊኒካል ሰርቪስ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር ዶክተር አባስ ሀሰን በበኩላቸው እንደሚሉት፣ የፓርኪንሰን ሕመም ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያሉ። በሽታው በኢትዮጵያም በተለይ ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ በስፋት እየታየ መጥቷል። እንደ አገር ብዙም ትኩረት ካልተሰጣቸው በሽታዎች ውስጥም አንዱ ነው።
ከዚህ አንፃር በሁሉም ደረጃዎች ለኅብረተሰቡም ሆነ ለመንግሥት ተቋማት፣ ለግል ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በሽታውን በተመከተ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል።
ከዚህ አንፃር ጤና ሚኒስቴር የፓርኪንሰን ታማሚዎች ወደ ጤና ተቋማት ሲሄዱ የሕክምና አገልግሎቱን እንዲያገኙና ባሉበት ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። አገልግሎት የሚጀምረው ከመከላከልና ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ እንደ መሆኑ መጠን ሁሉም የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል።
በጤና ተቋማት ላይ ታማሚዎች ተደራሽና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች ጋር አቀናጅቶ መሥራት ይፈልጋል። አገልግሎቱ ሕመሙን መለየት፣ ማከምና ለታማሚዎቹ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ድጋፎችን፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የተሃድሶ ሕክምናን ማሟላት ይገባል። እንደ አገርም የተሀድሶ ሕክምና ላይ የሚሠራ ትልቅ ተቋም ለማቋቋምም ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከመድኃኒት ጋር በተያያዘም የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ሥራ እየተሠራ ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014