በዛሬው አዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን ጋዜጣው በ1960ዎቹ ከቀረቡ ዘገባዎች ጥቂቶቹን ይዞ ቀርቧል፡፡ በጋዜጣው ከተዘገቡ ሥራዎች መካከልም የኑሮ ውድነትን የተመለከው ይገኝበታል፡፡ የኑሮ ውድነትን የዚያን ዘመንም ፈተና እንደነበር ከዘገባው እንረዳለን፡፡
ችግሩን ለመፍታት የአዲስ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ ያደርግ የነበረውን በጽሑፉ እንቃኛለን፡፡ ዛሬም በትኩረት የሚከናወኑ የኮንትሮባንድ እርድን ለመቆጣጠር ይወሰድ ስለነበረው እርምጃ እና በዘይት ፋብሪካ ልማት ይሠሩ ከነበሩ ተግባሮች መካከል ፋብሪካ መገንባት አንዱ መሆኑን የሚያመለክቱ ዘገባዎችንም ይዘናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መማክርት ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ (ኢ-ዜ-አ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ መማክርት ትናንት በክቡር ዶ/ር ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሊቀመንበርነት ስብሰባ አድርገው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።
መማክርቱ ከተወያዩባቸውም ልዩ ልዩ ጉዳዮች ውስጥ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የደረሰው የእህል ዋጋ መወደድ ሁኔታ ይገኝበታል። ይህንኑ አሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡትና የገለጡት በምክር ቤቱ የገፈርሣ ወረዳ ግዛት ሕዝብ አማካሪ የሆኑት የተከበሩ አቶ ጌታሁን ሞገሴ ሲሆኑ በዚሁ ጉዳይ ላይ መማክርቱ የአሳብ መለዋወጥ ባደረጉ ጊዜ የከተማው ሕዝብ በልዩ ልዩ መንገድ በተፈጠረው የኑሮ ውድነት ምክንያት
የደረሰበትን ችግር በመዘርዘር ሰፋ ያለ አስተያየት ሰጥተዋል ሲል የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ማስፋፊያና ማስተዋወቂያ ክፍል በሰጠው ዜና ላይ ገልጧል።
የማስታወቂያ ክፍሉ እንደገለጠው፤ መማክርቱ በተለይ የእህል ዋጋ ይህን ያህል በሚያድግበት ጊዜ የእህል ቦርድ የገበያውን ሚዛን መጠበቅ ይገባዋል፤ የሚል አስተያየት ሠንዝረዋል። እንደዚሁም በፋሲካ በዓል ሰሞን ይህን ያህል እህል ዋጋ ውድ መሆንና ከሚገባው በላይ ወጥቶ መገኘት ያስገረማቸው መሆኑን ገልጠዋል። ከዚህም በቀር ገበያው መልክ ሲያጣ የዋጋ ቁጥጥር መደረግ ይገባዋል በማለት ሠፊ አስተያየት ሰንዝረዋል።
ከዚህም ሌላ እህል ጠፍቶ ነው ወይስ ነጋዴዎቹ ዘግተውበት ነው ? የሚል ጥያቄ አዘል አሳብ ቀርቦ መማክርቱ ሰፊ ውይይት ያደረጉበት መሆኑንና በመጨረሻውም፤ ክቡር ከንቲባው ጉዳዩ ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን ከገለጡ በኋላ፤ ይህንን ጉዳይ በሠፊው ለመረዳት እንዲቻል የንግድ ሚኒስቴር፤ የእህል ቦርድና የነጋዴዎች ወኪሎች ባሉበት ብንወያይበት ይሻላል በማለት ያቀረቡትን አሳብ መማክርቱ በአንድ ዓይነት ድምጽ የተቀበሉት መሆናቸውን የማስታወቂያ ክፍሉ አረጋግጧል።
ሚያዝያ 13 ቀን 1963 አ.ም
5000 ኪሎ ስጋ ተቃጠለ
በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በምእራብ ማዘጋጃ ቤት ክልል ውስጥ ያለ ፈቃድ ሳይመረመሩ የታረዱ ከብቶች 5 ሺ ኪሎ ስጋ ተቃጠለ።
ያለፈቃድ ንጽህናቸው ባልተጠበቀ ስፍራዎች ከብቶች አርደው ሲሸጡ ከተገኙት መካከል አብዛኞቹ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ሲቀጡ፣ ሌሎቹም ያራዷቸው ከብቶች ስጋ ተይዞ መቃጠሉን ከምእራብ ጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ተገለጠ።
ከብቶቹ ያለፈቃድ ከቄራ ወጥተው በብዛት የታረዱባቸው ስፍራዎች በአዲሱ ሰፈር አካባቢ፣ በደጃዝማች ገነሜ ሰፈር፣ በኮልፌ፣ በአዲሱ ፯ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት አጠገብ፣ ቃጫ ፋብሪካ፣ አለም ጤና ከተባለው መሆኑ በዜናው ተገልጧል።
በአዲሱ ከተማ አካባቢ አንዳንድ የስጋ ነጋዴዎች በየጊዜው የኮንትሮባንድ ስጋ እያረዱ ለህዝብ ስለሚያቀርቡ መስሪያ ቤቱ በቅርብ በመከታተል ከ40 በላይ ጥፋተኞችን ለፍርድ አቅርቧል።
ለህዝብ ጤና ተስማሚ ያልሆነውን ከቄራ ውጪ የሚታረድ ስጋ ማቃጠል በህግ የተፈቀደ ነው በማለት የምእራብ ማዘጋጃ ቤት የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት ሹም አቶ ተረፈ ሀይሉ በሰጡት ዜና አስረዱ።
በጤናው ክፍል ሠራተኞች ተቆጣጣሪነት በየጊዜው ከሚያዙት ያለፈቃድ የታረዱ ከብቶች ስጋ ጋር የበሬ፣ የመሲና፣ የበግና የፍየል ቆዳዎች ተይዘው አብረው መቃጠላቸውም በዜና ተገልጧል።
ጥር 1 ቀን 1963 አ.ም
በጥጥ ፍሬ ቅቤ ለመስራት ታቅዷል
በንፋስ ስልክ አካባቢ በመሰራት ላይ ያለው የጥጥ ፍሬ ዘይት ፋብሪካ ከዘይት ሌላ ማርጋሪን የተባለ ለዳቦ መብያና ለወጥ ማጣፈጫ የሚሆኑ የቅቤ አይነቶችን በተጨማሪ ለመስራት እቅድ እንዳለው የተባበሩት ዘይት ፋብሪካዎች ዳይሬክተር ሚስተር ኒኮላ ጀርጋአስ ገለጡ።
ፋብሪካው ስራውን የሚያካሂደው በአቶማቲክ መሳሪያ ሲሆን እስከአሁን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለፋብሪካው የሚያስፈልገው መሳሪያ መቅረቡንና ቀሪውም በቅርብ እንደሚመጣ ስራ አስኪያጅ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ፋብሪካው ከጥጥ ፍሬ የመብል ዘይት ይሰራል፤ ወደፊት የሀገር ውስጥ ፍላጎት ካረካ በኋላ ወደ አንዳንድ የጎረቤት ሀገሮችም ለመላክ ሀሳብ አለው። በየቀኑ እስከ 120 ቶን ጥጥ ፍሬ ለመጭመቅ ኃይል የሚኖረው ይህ ፋብሪካ ከሁለት ወር በኋላ ሥራ ይጀምራል። በዚህም ደረጃ ሥራውን ካካሄደ በቀን እስከ 13 ቶን ዘይት ሰርቶ ለማውጣት ይችላል ሲሉ ሚስተር ጆርጋአስ አስረዱ።
የዘይት ፋብሪካው አንዱ ዋና አላማ ይላሉ ሚስተር ጆርጋአስ ፤ እስከ አሁን በቂ አገልግሎት ላይ ሳይውል የቀረውን የጥጥ ፍሬ በሚጠቅም ተግባር ለማዋል ነው። ዘይቱ ከወጣ በኋላ የሚቀረውን አስር ለከብት መኖ ወደ አውሮፓ በመላክ ለኢትዮጵያ አንድ የገበያ ምንጭ እንደሚሆን ይታመናል፤ የጥጥ ፍሬ ቁም ነገር ላይ መዋል የጥጥ ገበሬዎችን በይበልጥ ሊያበረታታቸው ይችላል።
በግማሽ ሚሊዮን ብር የሚሰራው ይህ ፋብሪካ ተፈጽሞ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የተባበሩት የዘይት ፋብሪካዎች ሠራተኞችን ቁጥር በአንድ መቶ ከፍ ያደርገዋል በማለት ሠራ አስኪያጁ ገልጠዋል።
ጥር 8 ቀን 1963 አ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014