
አዲስ አበባ፡- የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ የፍቼ ጨምበላላ በዓል የቱሪስት መስህብ ከመሆኑ ባለፈ የፍቅርና የይቅርታ በዓል ነው ሲሉ መምህርና ደራሲው አለሙ ኪርባ ገለጹ።
መምህሩ የዘመን መለወጫ በዓሉን ትውፊትና ዕሴቱን በጠበቀ መንገድ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።
መምህርና ደራሲ አለሙ ኪርባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ፍቼ ጨምበላላ ብዙዎች ሊታደሙበት የሚመኙት የፍቅር፣ የሰላም፣ የመረዳዳትና የይቅርታ በዓል ነው።
በዓሉ የአንድነትና የመተሳሰብ በመሆኑ ፍቼ ጨምበላላን የሚያከብር ሁሉ የበዓሉን ዕሴት በጠበቀ መልኩ ችግረኞችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባውም መምህር አለሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፍቼ ጨምበላላ ስለ ሃገር ሰላም፣ ስለ አዝመራው ደህንነት እንዲሁም ስለእንስሳቱ ጤንነት እንዲሁም ስለ መላው ሃገር ወደ ፈጣሪ የሚለመንበት ክብረ በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ኢትዮጵያውያን ሰላማቸውን፣ ፍቅር አንድነትና ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክሩበት ነው ያሉት መምህሩ፤ በመሆኑም በዓሉን ስናከብር በመዋደድና ሰላምን በመፈለግ መንፈስ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የፍቼ ጨምበላላ በዓል የሲዳማ ብሔር የማንነቱ መገለጫ ነው። ይሁንና በተለያዩ ጊዜያት የብሔሩ መገለጫ የሆነው ፍቼ ጨምበላላ እንዳይከበር በርካታ ፈተናዎች ይጋረጡ ነበር። እነዚያን ተግዳሮቶች ታልፈው አሁን ላይ በነጻነት እንዲከበር መደረጉ አስደሳች ነው ብለዋል።
አባት ቅድመ አያቶች እስከዛሬ ያደረሱትን የፍቼ ጨምበላላ በዓል ትውፊት በሥነሥርዓት ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የፍቼ ጨምበላላ በዓል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።
የሲዳማ ሕዝብ የጨረቃና ከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት አዲስ ዓመት ያከብራል። በዓሉም ፍቼ ጨምበላላ ይባላል። በዓሉ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ሲከበር የቆየ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአደባባይ ሳይከበር ማለፉ ይታወሳል።
የ2014 ፍቼ ጫምበላላ በዓል በዓሉ እሴቱን በተጠበቀ መልኩ ሚያዚያ 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚከበር በ”ጉዱማሌ” ወይም በባህላዊ አደባባይ፣ በቄጣላና በተለያዩ ውብ ባህላዊ ክንዋኔዎች እንደሚከበር የሲዳማ ክልል አስታውቋል።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለመላው የሲዳማ ሕዝብ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014