ንብ ማነብ ከሰብል ልማትና ከሌሎች የግብርና ሥራዎች መካከል አንዱና የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ አካባቢያዊና አገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ለማር ልማት ምቹ የሆኑና ዕምቅ ሀብቱ የሚገኝባቸው ሰፊ ቦታዎች መኖራቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ በትኩረት ባለመሰራቱና የንብ ማነብ ሥራውም ባለመዘመኑ ከማር ልማት እዚህ ግባ የሚባል ኢኮኖሚ ማመንጨት ሳይቻል መቆየቱ ቁጭት ያሳድራል። ሰሞኑን ለማር ልማት ምቹና ዕምቅ የሆነ ሀብት ካለባቸው የኢትዮጵያ ክፍል አንዱ በሆነው ኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን ተገኝተን እንቅስቃሴውን ለመቃኘት ዕድሉን አግኝተናል።
በማር ልማቱ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች ቡኖ በደሌ፣ኢሉ አባቦራ፣ እና ጅማ ዞኖች ከፍተኛ ድርሻውን እንደሚይዙም በቆይታችን ለመገንዘብ ችለናል። በነዚህ አካባቢዎች የማር ልማቱን ለማሳደግና አመራረቱንም ለማዘመን ይበል የሚባል ጥረት እየተደረገ ይገኛል። አካባቢው ከሰብል ልማት በተጨማሪ በቡና ልማትም የሚታወቅ በመሆኑ ከቡና፣ ከግራዋና ከተለያዩ ዕጽዋቶች ነው የማር ልማቱ የሚከናወነው።እንዲህ በአካባቢ የሚገኝ ፀጋን ጨምሮ በተለያዩ የፅዋት ዝርያዎች በአካባቢው በንብ ማነብ የማር ልማት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች በዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ተጠቅመው ከተለያየ ዕጽዋት ያመረቱትን ማር ለሁለት ቀናት በተካሄደ የማር ፌስቲቫልና ባዛር ላይ አቅርበው በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር ለመፍጠር አመቻችተዋል። ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንዲሉ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ልማቱን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስሩን በማስፋት እንዲህ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እየተቻለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው ላይ እሴት የተጨመረበት ምርትም ማቅረብ መቻሉ አንድ እርምጃ እንደሆነም በቆይታችን ለመረዳት ችለናል።
በቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ከተማ በተካሄደው የማር ፌስቲቫል ባዛርና ኤግዚቢሽን ላይ የማር ምርታቸውን ይዘው የቀረቡት በዘርፉ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በማስተርካርድ ፋውንዴሽን የሚታገዘው ዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት ምርምር ማዕከል ሞይሽ ፕሮግራም የተለያየ ድጋፍ ተደርጎላቸው በዘመናዊ የማር አመራረት ዘዴ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶችና በግል ጥረታቸው ተምሳሌት (ሞዴል) የሆኑ አርሶአደሮች ናቸው። በንብ ማነብ ተደራጅተው ለውጤት የበቁት እነዚህ ወጣቶች ሞይሽ ላለፉት ሁለት አመታት በንብም ማነብ ላይ የክህሎት ሥልጠና፣ የንብ ዝርያ ማባዛት፣ የማር ቀፎ፣ ማር ሲቆርጡ በንብ እንዳይነደፉ የሚከላከሉበት አልባሳት፣ ማሩን ከሰፈፉ የሚለዩበት መጭመቂያና ማጣሪያ መሳሪያ፣ያጣሩትን ማር አሽገውና የምርት ማስተዋወቂያ ለጥፈው የሚያቀርቡበት ዕቃ በማቅረብ እንዲሁም ማር የሚያቀነባብሩበትን ቤት በመገንባትና የተለያየ ድጋፍ ያደረገላቸው ሲሆን፣ ዞኑ ደግሞ ንቦች የሚቀስሙትን ዕፅዋት ለሚያለሙበት መሬትና ማሩን የሚያቀነባብሩበት ቦታ አመቻችቶላቸዋል። በሞይሽና በዞኑ የጋራ ድጋፍ በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።ባህላዊው ንብ ማነብ ቀፎ በዛፍ ላይ በመስቀል የሚከናወን በመሆኑ ለሴቶች ምቹ አይደለም።በመሆኑም ሴቶች ከንብ ማነብ ሥራ የራቁ ነበሩ። አሁን ላይ ያለው ዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራ የልማቱ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚም አድርጓቸዋል።
ስድስት ሴቶችና አራት ወንዶች ሆነው በማህበር ተደራጅተው በልማቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ፎዚያ አብዱርቃድር አንዷ ናት። ‹‹ልማቱ ገቢ ያስገኛል። ሥራውም አይከብድም። ቀደም ባለው ጊዜ ሴቶችን አሳታፊ ባለመሆኑ ሳንጠቀም ቆይተናል። አሁን ግን ሞይሽ ለሴቶች ቅድሚያ በመስጠት በስልጠና ከማብቃት ጀምሮ ላለፉት ሁለት አመታት ድጋፍ አድርጎልን ተጠቃሚ መሆን ችለናል። ድጋፉ ቀጣይነት ስላለው የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገን ተስፋ እናደርጋለን። ››በማለት ያገኘችውን ጥቅም አስረድታለች። ከማር ልማቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ሞይሽ በስልጠና በማብቃት የሙያ ባለቤት እንዳደረጋትም ገልጻለች። እርስዋ እንዳለችው እርስዋን ጨምሮ የማህበሩ አባላት አብዛኞቹ ቤተሰብ በባህላዊ መንገድ ማር ሲቆርጥ እንጂ በንብ ማነብ ላይ ግንዛቤው አልነበራቸውም።በተለይ ደግሞ እሴት ጨምሮ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ክህሎት ያገኙት በሞይሽ ፕሮግራም በተደረገላቸው ድጋፍ ነው። የማር ልማቱ በሁለት መንገድ ይጠቅማቸዋል። አንዱ የተጠራውን ማር አሽገው ለገበያ በማቅረብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጣርቶ የቀረውን ሰፈፍ በመሸጥ ይጠቀማሉ። ወጣት ፎዚያ ዘመናዊ የማር ልማት ሥራ በአካባቢው ላይ መጀመሩን ትልቅ ለውጥ እንደሆነ አድርጋ ትወስዳለች። የማር ልማቱ ለማር ቀፎ ለሚያዘጋጅ፣ በማርቆረጣ ወቅት የሚለበስ ልብስ ሰፍቶ ለሚያቀርብ፣ ለተጠራ ማር ማሸጊያም ዕቃ ለሚያቀርብ የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ የአካባቢው ወጣቶች በተለያየ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ ዕድል እንደሚሰጥ ታምናለች። በዚህ መልኩ ተጠናክሮ ከቀጠለ ከአካባቢያቸው አልፈው አገራዊ ኢኮኖሚን በማሳደግ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ወጣት ፎዚያ ተስፋ አላት። ምርት አምርተው ገበያ መውጣት ከጀመሩ ገና አጭር ጊዜ እንደሆነና የገበያ ትስስሩ እንዲፈጠርላቸው በዞኑ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቃለች።
የማር ልማትን ከሰብልና ከሌላ የግብርና ሥራ ጎን ለጎን በማከናወን ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በግላቸው ከኢሉ አባቦራ መቱ ዞን ያዩ ወረዳ በማር ፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፉት አርሶአደር ታሪኩ ቶለሳ አንዱ ማሳያ ናቸው። ከቡና አበባ ማር ምርታቸውን ይዘው ነው የቀረቡት። ምርታቸው በዋጋም ውድ ነበር። በግላቸው አምርተው በማቅረባቸውና ማሩም የቡና በመሆኑ እንደሆነ ምክንያት አቅርበዋል። አርሶአደር ታሪኩ እንደገለጹልን የማር ልማቱን የሚያከናውኑት በባህላዊ፣ በዘመናዊና የሽግግር ቀፎዎች በመጠቀም ሲሆን፣ በሁሉም አይነት 205 ቀፎዎች አሏቸው። ከቡና አበባ፣ ከግራዋና ከአደይ አበባ ዕፅዋት የሚያመርቱትን ማር ከአካባቢያቸው አልፈው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ገበያ ያቀርባሉ። በአንድ ባዛር ላይ ያገኟቸው የጀርመን ዜጎችም ደንበኛ በማድረግ ገበያ መፍጠር ችለዋል። ጀርመናዊያውያኑ በየአመቱ ኢትዮጵያ ሲመጡ የአርሶአደር ታሪኩን የማር ምርት ይገዛሉ።በስፋት አምርተው ማቅረብ ከቻሉና ሌሎችም አርሶአደሮች ተጨምረው በአገራቸው ጀርመን ገበያ እንደሚያፈላልጉላቸውም ቃል ገብተውላቸዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የማር ፌስቲቫልና ባዛር ሲዘጋጅ ምርታቸውን ይዘው በመቅረባቸው ነው ገበያቸውን በማስፋት የገበያ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ የቻሉት።
አርሶአደር ታሪኩ በአመት ሶስት ጊዜ ያመርታሉ።ከዘመናዊ ቀፎ እስከ 250 ኪሎ ግራም፣ ከሽግግር ቀፎ 150 ኪሎ ግራም፣ ከባህላዊ ቀፎም በተመሳሳይ ያመርታሉ። ማር ብቻ ሳይሆን ሰፈፍም በመሸጥ ይጠቀማሉ። የማር ማቀነባበሪያ ማሽንም ገዝተው በማጣራት ነው ለገበያ የሚያቀርቡት። በሚኖሩበት ገጠር ውስጥ መብራት ባለመኖሩ ጀነሬተር በማስገባት የተሻለ ኑሮ ለመኖር ችለዋል። ከተማ ውስጥም ዘመናዊ ቤት ገንብተው ልጆቻቸው እየኖሩበት እንዲማሩ በማድረግ መለወጥ ችለዋል። ኑሮአቸውን በገጠር ያደረጉት የማር ልማቱን ጨምሮ የግብርና ሥራቸውን ለማከናወን እንዲረዳቸው ነው።
አርሶአደር ታሪኩ ለሌሎች ተምሳሌት ሊሆኑ እንደሚችሉ ከሥራቸው ለመረዳት ችለናል።የማር ልማቱን የሚያከናውኑት የቀኑን የግብርና ሥራ ከጨረሱ በኋላ ነው። እርሳቸው እንዳሉት ማር ለማልማት ሌላው የግብርና ሥራ እንቅፋት አይሆንም። የማር ልማቱ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ በመሆኑ ምሽት ላይ አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋሉ። ‹‹የማር ልማቱ የእርሻ ሥራ እንዳልሰራ አላደረገኝም››ይላሉ። ይህ ጥረታቸው አርሶ አደር ታሪኩን ሞዴል ተሸላሚ አድርጓቸዋል። በክልል፣ በሀገር አቀፍና በዞናቸው በተለያየ ጊዜ የማበረታቻ የሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል።
እንደአለመታደል ሆኖ እንደ አርሶ አደር ታሪኩ የአካባቢያቸውን ፀጋ ተጠቅመው ሁለገብ ልማት በማከናወን ጠንካራ ገበሬዎች ጥቂት ናቸው። አርሶአደር ታሪኩ እንደነገሩን ያዩ ወረዳ በደን ልማት ትታወቃለች። ለንብ ማነብ የሚሆኑ የተፈጥሮ ዕፅዋቶች አሉ። ሰው የሚጠበቅበት ቀፎና ቦታ ማዘጋጀት ብቻ ነው። ‹‹የአካባቢያችንን ሀብት አልተጠቀምንበትም።ቀን መሥራት እንጂ 24 ሰአት መስራት የሚል ባህል አላዳበርንም›› ሲሉም ይገልጻሉ። እርሳቸው ልማቱን በማሳደግ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩና ሌሎችንም ለማነሳሳት ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።
በንብ ማነብ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ወጣቶች በቅርበት የሚያግዙት በዓለም አቀፍ የሥነ ነፍሳት ምርምር ማዕከል (icipe) የሞይሽ ፕሮግራም የኦሮሚያ ተጠሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ኩመላ እንደገለጹት፤ ድርጅታቸው አካባቢው ላይ ሙያዊና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ወጣቶቹን ተጠቃሚ ለማድረግና ብሎም የማር ልማቱ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማስቻል ከሁለት አመት በፊት እንቅስቃሴ የጀመረው የአካቢውን እምቅ ሀብትና ለንብ ማነብ ሥራ ምቹነቱን በመለየት ነው። ፕሮግራሙ ለአምስት አመት የሚቆይ ሲሆን፣ በቀሪው ሶስት አመታትም አጠናክሮ ይቀጥላል። ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል በአራት ዞኖች በስምንት ወረዳዎች ውስጥ በስፋት በማር ልማት ላይ ድጋፍ በማድረግ ልማቱ እንዲከናወን የሚያደርግ ቢሆንም። ሞይሽ በተጨማሪ ምሥራቅ ሸዋ ላይ በሀር ልማት ላይም በተመሳሳይ የክህሎትና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን በማብቃት የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። በፕሮግራሙ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ወደ 14ሺ200 ወጣቶችን ተደራሽ ማድረግ ችሏል። የተደረገላቸውን ድጋፍ ተጠቅመው ወደ 188ሺ ኪሎ ግራም ማር አምርተው ለገበያ አቅርበዋል። ፕሮግራሙ በአምስት አመት ቆታው በንብ ማነብና በሀር ልማት አንድ መቶ ሺ ወጣቶችን ለመድረስ ወይንም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነው እየሰራ የሚገኘው።
የዓለምአቀፍ የሥነ ነፍሳት ምርምር ማዕከል (icipe) የሞየሽ ፕሮግራም የኦሮሚያ ተጠሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ኩመላ እንደገለፁት፣ በክልሉ አራት ዞኖች ሰምንት ወረዳዎች ውስጥ ያለውን ሀብት ማዕከል በማድረግ ፕሮግራሙ ከሁለት አመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ አምስት አመት የሚቆይ ፕሮግራም ነው። እስካሁን በተከናወነው ሥራ 14ሺ200 ወጣቶች ስልጠና አግኝተው ወደ ልማት ገብተዋል። ከነዚህ ውስጥ 60በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በተደረገላቸው የቁሳቁስ ድጋፍና ባገኙት ስልጠና በሁለት አመት 188ሺ ኪሎግራም ማር አምርተው ተጠቃሚ ሆነዋል። ንብ በማባዛትም ክህሎት አግኝተዋል። በአጠቃላይ የተጣራና የታሸገ ማር በጥራት በማምረት በአካባቢው ላይ ማሳየት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ከአንድ አመት በፊት የኦሮሚያን ምዕራብ ክፍል በማር እናጥለቀልቃለን በሚል ጅማ ከተማ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት በተገኙበት የይፋ ሥነሥርአት ተካሂዶ እንደነበር ያስታወሱት የቡኖበደሌ ዞን ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ጅፋር፤ ከይፋ ሥነሥርአቱ በኋላ ዞናቸው የቤት ሥራ በመውሰድ ባደረገው እንቅስቃሴ ወደ29ሺ የንብ ቀፎዎችን በማምረት ለገበሬው በክላስተር በማዳረስ ወደ አራት ሺ ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የዞኑን እንቅስቃሴ የሚያግዙ እንደ ዓለምአቀፍ የሥነ ነፍሳት የምርምር ማዕከል ሞይሽ (ፕሮግራሙ) ያሉ ተቋማት የተለያየ እገዛ በማድረግ ላይ መሆናቸውንና ሞየሽ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ወጣቶች ይዞ እያደረገ ያለው እገዛ ግን ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። (ፕሮግራሙ) እገዛ ጥራት ያለው ማር እንዲመረት በማድረግ ጭምር በመሆኑ ውጤታማ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ የግብርና ሥራው ሁለገብ እንዲሆንም የማር ልማቱ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። የገጠሩ ማህበረሰብ መለወጥ የሚችለው በአካባቢው ያለውን ሀብት አሟጦ መጠቀም ሲችል ነው። የዞኑ ግብርና ቢሮውም ይህንኑ በማስገንዘብና አስፈላጊውን ድጋፍም በማድረግ ያለሥራ የባከነውን ጊዜ በማካካስ የአካባቢውን ማህበረሰብም ሆነ ብሎም አገርን ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሀብቱ በሚገኝበት አካባቢዎች በክልሉ፣ በሞየሽና በግለሰብ አርሶአደሮች ጭምር እየተከናወነ ያለው የንብ ማነብ የማር ልማት የግብርናው ክፍለኢኮኖሚ አንዱ አካል መሆኑንም ያስመሰከረ እንቅስቃሴ በመሆኑ ይበል መልእክታችን ነው።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014